Saturday, 13 June 2015 15:45

በመዲናዋ ዓለምአቀፍ የፊልም ፌስቲቫል እየተካሄደ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 60 ዘጋቢ ፊልሞች ለተመልካች ይቀርባሉ
  ፌስቲቫሉ በክልል ከተሞችም ይቀጥላል
      በመላው ዓለም ከተሰሩ ምርጥ ዘጋቢ ፊልሞች የተመረጡ 60ዎቹ ለዕይታ የሚቀርቡበት “9ኛው አዲስ ኢንተርናሽናል ዘጋቢ ፊልም ፌስቲቫል” ትላንት በብሄራዊ ሙዚየም የቅርስ ጥናት እና ጥበቃ ባለስልጣን አዳራሽ ተከፈተ፡፡ ፌስቲቫሉ ለአምስት ቀናት እንደሚካሄድ የገለፁት የ“ኢንሺዬቲቭ አፍሪካ” ዋና ዲያሬክተር አቶ ክቡር ገና፤ በቀጣይ ዓመታት ፌስቲቫሉ የራሱን ውድድር አድርጎ ፊልሞችና ፊልም ሰሪዎችን ለመሸለም እንዲሁም ኢትዮጵያዊያን ፊልም ሰሪዎች በዘጋቢ ፊልሞች ስራ የተሻለ ተሳትፎ እንዲኖራቸው እንተጋለን ብለዋል፡፡ ፌስቲቫሉ የተከፈተው በሩት ኢሼል ዳይሬክተርነት በተሰራው “Shoulder Dancing” የተሰኘ ዘጋቢ ፊልም ነው፡፡ እስከ ሰኔ 9 በሚዘልቀው ፌስቲቫል፤ 60 የሚደርሱ ዘጋቢ ፊልሞች ለዕይታ የሚቀርቡ ሲሆን በአዲስ አበባ  በቅርስ ጥናትና ምርምር ማዕከል፤ በሀገር ፍቅር ትንሽዋ አዳራሽ፤ በብሪትሽ ካውንስል እና በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሲዝ ለተመልካቾች ይታያሉ፡፡ የፊልም ፌስቲቫሉ ሰኔ 19 እና 20 ደግሞ በአዳማ፤ ባህርዳር፤ ሃዋሳ እና መቀሌ  ከተሞች እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡
በዘንድሮው ፌስቲቫል በዓለማችን አበይት የመነጋገሪያ አጀንዳዎች ላይ ተመርኩዘው የተሰሩ ዘጋቢ ፊልሞች ተመርጠው መቅረባቸውን በጋዜጣዊ መግለጫው የተናገሩት አቶ ክቡር ገና፤ ከ10 በላይ የፊልም ዳይሬክተሮችን ከተለያዩ አገራት በመጋበዝ በፊልሞቹ ዙሪያ ከተመልካች ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጡበት መድረክ መመቻቸቱንም ገልፀዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ከ10ሺ በላይ ታዳሚ የነበረው አዲስ ኢንተርናሽናል ዘጋቢ ፊልም ፌስቲቫል፤ ዘንድሮ ደግሞ በፊልሞቹ ብዛት፤ በሚቀርቡት ዘጋቢ ፊልም ሰሪዎች የብቃት ደረጃና አይነት እንዲሁም በሚያገኘው ተመልካች ብዛት በአፍሪካ ግዙፉ ፌስቲቫል ይሆናል ተብሎ ይገመታል፡፡ በፌስቲቫሉ ላይ ለመሳተፍከመላው ዓለም 500 ፊልሞች አመልክተው እንደነበር የገለፁት አዘጋጆቹ፤ ከግምገማ በኋላ 60 ዘጋቢ ፊልሞች ለዕይታ መመረጣቸውን ጠቁመው “አዲስ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫልን” በአፍሪካ ትልቁ መድረክ ለማድረግ በአበረታች አቅጣጫ ላይ ነን ብለዋል፡፡
ከዘጋቢ ፊልሞቹ ለዕይታ መቅረብ ባሻገር ከመላው ዓለም ከመጡ የፊልም ባለሙያዎች ጋር የጥያቄ እና መልስ እንዲሁም የውይይት መድረኮች ይካሄዳሉ ተብሏል፡፡
ኢትዮጵያውያን ፊልም ሰሪዎች በፌስቲቫሉ ላይ ያላቸው ተሳትፎ አነስተኛ መሆኑን ጠቁመው ዋናው ምክንያትም ዘርፉ ብዙም ንግድ የማይሰራበት በመሆኑ ስለማያበረታታቸው ነው ብለዋል፡፡
በፌስቲቫሉ ከሚቀርቡ ዘጋቢ ፊልሞች መካከል በኢትዮጵያዊያኑ ዳይሬክተሮች ትርሲት አግዝ እና ኃይሉ ከበደ የተሰሩት “የበሬው ውለታ” እና “ትስስር” የሚገኙበት ሲሆን “35 OWS AND A KALASHINIKOV”, “5 MINUTES Of FREEDOM”, “9999”, “At 60 Km/h” የሚሉና ሌሎችም ይታያሉ ተብሏል፡፡

Read 1237 times