Saturday, 27 June 2015 08:14

“የዳኛቸዉ ሐሳቦች” መፅሐፍ እና እዉነታዉ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

   ሰሞኑን ‹‹የዳኛቸው ሐሳቦች›› በሚል ርዕስ ያሳተምኩትን መጽሀፍ ተከትሎ በየቦታው አቧራ ተነስቶ ከርሟል፡፡ በርካቶችም የአቧራውን ጭስ ብቻ በመከተል ተቧድነዋል፡፡ እኔም እውነታው ብዙ ነገር ስለሚያናጋ ይህንን ጽሁፍ እስከምጽፍበት ጊዜ ድረስ አተካራ ውስጥ ላለመግባት ሞክሬያለሁ። በሌላ በኩል ከእውነታውና ከምጠብቀው ፍጹም የተቃረነ ነገር ስለገጠመኝ መደናገጤን መሸሸግ አይቻለኝም። ለዶክተር ዳኛቸው የነበረኝ አክብሮት፣ ያልተፈተሸ ፍቅር ብሎም አሁን ያሉበት ሁኔታም መልስ ከመስጠት እንድቆጠብ ካደረጉኝ ምክንያቶች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡ ይሁን እንጂ ዝምታዬ አንዳንድ ሰዎችን ወደ ገደል ሲመራም አስተውያለሁ፡፡ ከዶክተር ዳኛቸው ጋርም አሁን ባለበት ሁኔታ በንግግር መግባባት አልቻልንም፡፡ በመሆኑም ነገሩ የህልውና ጉዳይ እየሆነና በሚያስደነግጥ ሁኔታ መልኩን እየቀየረ ስለመጣ በአቧራው ጭስ የተሸፈነውን እውነት
ለመገላለጥና ለተሰነዘሩብኝ እጅግ ሰቅጣጭ ውንጀላዎች መልስ ለመስጠት እግረ መንገዴንም በአንባቢዎቼ ላይ የተጋረዱትን ብዥታዎች ለማጥራት ስል ይህን ጽሁፍ ለማዘጋጀት ተገድጃለሁ፡፡ዛሬ ላይ ለውዝግብ የተዳረገው መጽሀፌን አስመልክቶ በግልጽ ከተናገርኩኝ አንድ ዓመት ከስድስት ወር አለፈው፡፡ ረቡዕ ታህሳስ 16 ቀን 2006 ዓ.ም በወጣችው “ኢትዮ-ምህዳር” ጋዜጣ ላይ ‹‹በዳኛቸው ላይ የተሰነዘረ መርህ አልባ ትችት›› በሚለው ጽሁፌ ውስጥ በሚከተለው መልኩ ነበር የስራዬን መጠናቀቅ የገለጽኩት፡- ‹‹... ዶ/ር ዳኛቸው ተነቦ የማያልቅ መጽሀፍ ነው፣ በሀሳቦቹ ውስጥም የኢትዮጵያን ችግሮች ማየትና መመርመር ይቻላል፣ ታሪክንም ሆነ ፍልስፍናን ጠንቅቆ ያውቃል፣... በግል ተነሳሽነት ሀሳቦቹን መርምሬ በመጽሀፍ መልክ እያዘጋጀኋቸው እገኛለሁ፡፡ ሌላው ወገን ደግሞ ከፈለገ ተቃራኒውን ሀሳብ አንስቶ በምክንያት መሞገት ይችላል፡፡... ›› ከላይ
የጠቀስኩት ጽሁፍ ለህትመት በበቃበት ቀን የዕለቱ ጽሁፌን ዶ/ር ዳኛቸውን ጨምሮ በዙሪያው የነበሩ ፕሮፌሰሮችና ወዳጆቹ በጣም እንደወደዱትና ከመጽሀፌ ጋር በተያያዘ ይፋ ያደረግሁት ነገርም እንዳስደሰታቸው ዳኛቸው እራሱ በደስታ ስሜት ውስጥ እንዳለ ነበር ደውሎ የነገረኝ፡፡ በወቅቱ እኔ ከአዲስ አበባ ውጪ ስለነበርኩ በተደጋጋሚ የተገናኘነው በስልክ ነበር፡፡ ጽሁፉንም በኢሜል እንድልክለት ጠይቆኝ ልኬለታለሁ፡፡ በቅርቡም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከተባረረ በኋላ ለኢሳት ሰጥቶት የነበረውን ቃለ መጠይቅ እንዳስደምጠው በጠየቀኝ መሰረት፤ ይዤለት እቤቱ ሄድኩና ተገናኘን፡፡ ፕሮግራሙንም ይዤለት የሄድኩት በኮምፒውተሬ ነበር። ሰምቶ እንደጨረሰም እዛው በተቀመጥንበት ከኮምፒውተሩ ላይ ለህትመት ዝግጁ የሆነውን ስራ በጋራ እያሳለፍንና እያወራንበት አየነው፡፡ አይቶ እንደጨረሰም ካልተሳሳትኩኝ የአምቦ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆነ ወዳጁ ጋር ይደውልና እጅግ በተገረመ ስሜት ውስጥ ሆኖ ‹‹ስማ እንጂ... ያ ጉደኛ ልጅ አንዴት አድርጎ መሰለህ መጽሀፉን የሰራው! ... የሚገርም ነው መቼም እልሀለው፤ ስንገናኝ አወራሀለሁ....›› ነበር ያለው፡፡ እነዚህን ሁለት ማሳያዎች ዳኛቸው ከመጽሀፌ መውጣት ጋር ተያይዞ ከሰጠው ሀሳብ ጋር አነጻጽሩት፡፡ እነዚህን ነጥቦች የማነሳቸው ዳኛቸው ለሰጠው አስተያየትም ሆነ አብዛኞቻችሁ ለምታነሱት ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጥልኝ እንጂ እኔ በግሌ የዳኛቸው ሀሳቦች ላይ ትንታኔም ሆነ ትችት ለመስራት የግዴታ እሱ ማየትና መፍቀድ አለበት ብዬ አላምንም፡፡ ምክንያቱም ብዙዎች መጽሀፉን ሳያነቡ ከድምዳሜ
ላይ እንደደረሱት መጽሀፉ የእሱ ሃሳቦች ስብስብ ሳይሆን በዳኛቸው ሀሳቦች ላይ ትንታኔ የሚያቀርብ
ነው፡፡ ይህንንም ዘግየት ብዬ በአስረጂ ማሳያ እመለስበታለሁ፡፡መጽሀፉ ገበያ ላይ ሊውል አንድ ቀን እስኪቀረው ድረስም አንድም ተቃውሞ ከዶክተሩ ተቀብዬ አላውቅም፡፡ መጽሀፉ ሊወጣ አንድ ቀን ሲቀረው ዳኛቸው ጋ ሁኔታውን ልነግረው ስደውል ደሴ መሆኑን ነገረኝ፡፡ እኔም የመጽሀፉ ህትመት መጠናቀቁን ላበስረው እንደደወልኩኝ ስገልጽለት፤ ‹‹ልጅ መሐመድ ባለፈው ሳምንት የቀጠርኩህ እኮ በጉዳዩ ላይ እንድናወራ ነበር፤... ፐብሊሸሬ ኮንሰርን አለው፤ ብናወራ ጥሩ ነበር፤...›› ካለኝ በኋላ በነጋታው እንደሚመለስ ገለጸልኝ፡፡ እኔም መጽሀፉን እቤት ይዤለት እንደምመጣ ከተነጋገርን በኋላ በሰላም ተለያየን፡፡ በነጋታውም ዶክተር ደወለና ‹‹ ፐብሊሸሬ ኮንሰርን አለው፤ ደጋግሞ እየደወለልኝ ነው ›› ሲል ከሌላው ጊዜ ጠንከር ባለ ድምጸት አወራኝ፡፡ እኔም በዚህ ስራ ላይ የሱ አሳታሚን የሚያሳስበው ነገር እንደሌለ ስገልጽለት፣ ‹‹እንዴት
ነው የማይመለከተው፤ የኔን ስብስብ እኮ ላሳትመው ነው›› ሲለኝ ‹‹እና ምን ችግር አለው? የኔ ስብስብ ስራ አይደል፤ አንተ አታውቀውም እንዴ?›› አልኩት፡፡ ‹‹ነው እንዴ! ስብስብ ነው ብለውኝ እኮ ነው›› ብሎ ሲለኝ እንደዛ በማሰቡና ሌሎችን በማመኑ ቅሬታዬን ገልጬለት ስልኩ ተዘጋ፡፡ ልብ አድርጉ! እንግዲህ እዚህ ሀገር ጠልፎ የሚጥለው ብዛቱ! መጽሀፉ ገና እኔ እጅ እንኳን ሳይገባ ስብስብ ስራ ነው እያሉ የሚያወሩ ነበሩ፡፡ መጽሀፉ እንደወጣም እቤቱ ሄጄ አስቀምጬለት ወጣሁ፡፡ መጽሀፉን ወደቤት ተመልሶ ገና ሳያገኘው አሁን የምንሰማውን ቅሬታ በዛኑ ዕለት ማታ መሰማት ጀመረ፡፡ ስለብቃቴ፣ መጽሀፌ መዉጣት፣... ያወደሱ አንደበቶች ወደዘለፋ ለመቀየር ጊዜና ማስተዋል አላስፈለጋቸውም፡፡ መጽሀፉን ሳያነቡ ወቀሳውን የሚያስተጋቡት ሌሎችም ነበሩ፡፡ ከዓመት በፊት የታወጀን እውነታ ካለማንበብ የተነሳ አለማወቅ አንድ ነገር ሆኖ ሳለ አሁንም መጽሀፉን ሳያነቡ በቲፎዞነት የተሰለፉ በርካቶች ነበሩ፡፡ በዚሁ አጋጣሚ በማስተዋል ውስጥ ሆናችሁ እኔንም ሆነ ሌሎችን ለማረጋጋት አስተውሎቱ የነበራችሁ ጥቂት የፌስቡክ መንደር ታዳሚዎች የምር ክብር ይገባችኋል፡፡ በቲፎዞነት ዓለም ውስጥ ለዋተታችሁ አብዛኞች ደግሞ ማስተዋልና ልቦናን ከክብር ጋር
ተመኘሁ!የጠሉትን መውረስ!ዳኛቸው አጥብቆ የሚነቅፋቸውን የስርዓቱ ተግባራት ለመፈጸም ጊዜ አልፈጀበትም። በኔው ስራ እኔኑ ከመጠየቅ ይልቅ ምርጫው ያደረገው ጀርባዬን ማጥናት ነበር፡፡ የጠላቸውንና የጠረጠራቸውን ሁሉ ከኔ ጋር ያጣብቃቸዋል፡፡ በውል እንኳን ከነመፈጠራቸው የማላውቃቸውን ሰዎች ስም እየጠራ ከጀርባህ እነከሌ ስላሉ እውነቱን አውጣ ማለቱን ተያያዘው፡፡ ከመጽሀፌ ጋር በተያያዘ ለተፈጠረው
ውዝግብ ዋነኛ ማጠንጠኛውም ይሄው ነጥብ ይመስለኛል፡፡ አንዳንዶችም ለክብራቸው በማይመጥን መልኩ መሰሉን የመሸታ ቤት ሀሜት ሰምተው፣ በአደባባይ የግለሰቦችን ክብር የሚነካና በወንጀልም ጭምር ሊያስጠይቃቸው የሚችል ጽሁፍ ጽፈዋል፡፡ የዚህ ከጀርባዬ የሌለን ሰው የመፈለጉ ሽኩቻ በግላዊ ፀብ፣ በፖለቲካዊ ጥንስስ፣ በማፊያዎቹ ኣሳታሚዎች ፍላጎት፣... ወዘተ ሊሆን ይችላል፡፡ እርግጠኛ ስላልሆንኩኝ ከጀርባ ስላለው ነገር አላወራም። የምፈልገው እከሌን እንጂ አንተን አይደለም፣ እናም መስክር፣ ... አይነት የፍረጃ ተግባሮች ሲተቹ የኖሩትን ስርዓት መንገድ መከተል ይመስላል፡፡ አስራት አብርሀምን እንኳን ካወቅሁት አንድ ወር አይሞላኝም፤ ግንኙነታችንም እሱ በሚካፈልበት ኤግቢሽን ላይ መጽሀፎቼን ለአንባቢም ሆነ ለነጋዴዎች እንዲሸጥልኝ ከማድረግ የዘለለ አይደለም፡፡ ሌላው ከነመፈጠራቸው የማላውቃቸው ሰዎች ስም እየተጠራልኝ ‹‹ከኋላህ አሉ!.. እራስህን ነጻ አውጣ... ሞኝ አትሁን...›› ዓይነት ማስፈራሪያ አዘል ንግግሮችም በጣም አስገራሚ ነበሩ። ከዚህም በላይ ለመጥቀስ የማይመቹ ዝርዝር ጉዳዮች እየተነሱ በማላውቀውና በማልጠብቀው አሳዛኝ ጉዳይ ውስጥም ተዘፍቄ ነው የከረምኩት፡፡ አስራትም ሆነ የሚጠሩልኝ ሰዎች የዶክተሩ እንጂ የኔ ወዳጆች አይደሉም፡፡ ከላይ ካነሳሁት ተግባር ጋር የሚመሳሰለው ዶክተሩ በዚሁ ጋዜጣ ላይ ‹‹መሐመድ ይቅርታ ጠይቆኛል...›› በሚል ያነሱት ነጥብ ነው፡፡ ዶክተሩን ወደ አደባባይ ያወጣቸውና ተቀባይነትም ያስገኘላቸው ከብርቱካን እስር ጋር ተያይዞ ይህንን የይቅርታ ጠይቆኛል አባዜ፣ በከፍተኛ ሁኔታ
ማውገዛቸውና ጠንካራ አስተያየትም ማቅረባቸው ነበር፡፡ ከሰሞኑ ግን ዶክተሩ ይህንኑ ተግባር እንደልጄ አይሀለው በሚሉኝ እኔ ላይ በከፍተኛ ጭካኔ ተግባራዊ አድርገውታል፡፡ መመስገንና መሸለም ሲገባኝ በከፍተኛ ሁኔታ የሞራል ኪሳራ የሚያደርሱ ጽሁፎችና ወሬዎች ሲያናፍሱ ከቆዩና በኋላም ክስ መስርተው ሲያበቁ በወጉ እንኳን ባልተስማማንበት የአንድ ቀን ግንኙነት ይቅርታ ጠይቆኛል አሉ፡፡ እኔ ዶክተሩን አስቀይሜ ይቅርታ ብጠይቃቸው እንኳን ካለን ቀረቤታ አንጻር እሳቸውን ደረት አስነፍቶ በአደባባይ የሚያስፎክር፣ የኔንም አንገት የሚያስደፋ አይደለም። የነበረውን ሁኔታ በግልጽ ላስቀምጠው፡፡ እኔና ዳኛቸው ከውዝግቡ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በአካል የተገናኘነው ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ስድስት ኪሎ አካባቢ ካለ አንድ ግሮሰሪ ውስጥ ነበር፡፡
ግንኙነታችንም ከሳቸው በተነሳ ጥያቄ መሰረት ሚስጥራዊ እንዲሆን ብንስማማም በወቅቱ ያነሳናቸውን ጉዳዮች በተዛባ መንገድ እያነሱ ዛሬም ድረስ በስልክ የሚረብሹኝ ሰዎች አሉ፡፡ በወቅቱ ስንገናኝ የነበረው ሁኔታ ሚዲያው ላይ በሚራገበው መጠን ብዙም ውጥረት የበዛበት አልነበረም፡፡ በሂደት ሁለታችንም በሚያግባባን አንድ ነጥብ ላይ ማውራት ስላልቻልን ስሜቴ መረበሹ አልቀረም፡፡ ሆኖም ግን የምናወራው እንደ አባትና ልጅ ነበር፡፡ በኋላም በደረሰብኝ ነገር ሁሉ ስሜቴ ክፉኛ እንደተጎዳ፣ አስካሁን ከደረሰብኝ ጉዳት የባሰ ነገር በክሱም ቢሆን እንደማይገጥመኝ፣ ስራውንም ለገንዘብ ብዬ እንዳልሰራሁት፣ ወዘተ ካስረዳሁ በኋላ በዶክተሩ ፍላጎት እንዲወሰኑ ሁለት አማራጮችን አቀረብኩኝ። የመጀመሪያው አማራጭ እስካሁን የተበተነው መጽሀፍ የተበደርኩትንና መጽሀፉን ያሳተምኩበትን ወጪ ብቻ ከሸፈነ ቀሪዎቹን መጽሀፎች እንዲሰበሰቡ የሚል ሲሆን፤
ሁለተኛው አማራጭ መጽሀፉን ደግሞ የማሳተም ፍላጎት እንደሌለኝና አሁን የታተመው ግን ከኛ ቁጥጥርም ጭምር ዉጪ በመሆኑ ተሸጦ እንዳለቀ ለኔ የሚደርሰኝን ገንዘብ አምጥቼ ለዶክተር ልሰጥና፣ እሳቸውም በገንዘቡ ላይ የፈለጉትን ውሳኔ እንዲያሳልፉ የሚል ነበር፡፡ ይህንን በልመና ጭምር የታገዘውን አማራጭ ሳቀርብ አሁን የተፈጠረው አተካራ ማናችንንም እንደማይጠቅመን በማስረዳት ጭምር ነበር፡፡ በዚህ ላይ ለመወሰንም ለአርብ ጠዋት ቀጠሮ ይዘን ተሰነባበትን፡፡ የነበረው ነገር ይህ ነው፡፡ ገና ባልተቋጨ ጉዳይ ላይ ነው እንግዲህ “ይቅርታ ጠየቀኝ” በሚል መግለጫ የሰጡት። ታዲያ የቀጠሯችን ቀን አርብ ሲመጣ ከሳቸው በስልክ የደረሰኝ ውሳኔ ሳይሆን ቀደም ብዬ ከላይ ያነሳሁት የተጠናከረ ፍረጃ ነበር፡፡ ሌላውን ለማጥቃት እኔን መግደልም እንዴት
ምክንያታዊ እንደሚሆን አልገባኝም። እውነታውን በማስረጃ ለሚዲያው ፍጆታም ሆነ ሽያጭ ከኔ ይልቅ የዳኛቸው ፊት ገጽ ላይ መውጣት ሚዛን እንደሚደፋ እርግጥ ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል ከሰንደቅ ውጪ የትኛውም ሚዲያ ዘገባውን ሲሰራ ወደኔ በመደወል እውነታውን ለማጣራት ያልሞከረው፡፡ ባለፈው ሳምንት በወጣው የአዲስ አድማስ ዜና ላይም ዶክተር ዳኛቸው የመጽሀፉ 95 ከመቶ የሚሆነው ሀሳብ ከሳቸው እንደተወሰደ ተናግረዋል፡፡ የሆነው ሆኖ አንባቢ በእውነታው መካከል ያለውን ልዩነት አይቶ፣ የራሱን ፍርድ ይስጥ፤ እኔ ግን እውነታውን በቁጥር አስደግፌ ላስፈር፡፡ መጽሀፌ 236 ገጾች አሉት፡፡ በነዚህ ገጾች ውስጥ የዶክተሩ ሀሳቦች አስፈላጊ በሆኑበት ቦታ ላይ በሩብ፣ በግማሽ እና በሙሉ ገጽ ላይ እንደወረዱ የሰፈሩባቸው ቦታዎች አሉ፡፡ እነዚህ እንደወረዱ የተጠቀምኳቸው የዶክተሩ ሀሳቦች ተደማምረው ወደ 76 ያህል ገጽ ናቸው፡፡ ልብ አድርጉ 236 ገጽ ካለው መጽሀፍ ውስጥ 76 ገጽ ምን ያህል ፐርሰንት እንደሚሆን አስቡት፤ ወደ 32 ከመቶ ገደማ ነው፡፡ ከዚህ በቀጥታ የዶክተሩን ሀሳብ እንደወረደ ካሰፈርኩበት 76 ገጽ ውስጥ ደግሞ ወደ 30 ያህል ገጽ የሚሆነው ከኔው ጋር የቃለምልልስ ቆይታ በነበራቸው ወቅት የሰጡኝ ሀሳብ ነው፡፡ በተቀረው ገጽ ላይ የሰፈሩት ሀሳቦች የኔው ትንታኔዎች፣ ማብራሪያዎች እና አቶ ጌታቸውን ጨምሮ የሌሎች ሰዎች አጋዥ ስራዎች ናቸው፡፡ ይህንን ቁጥር እሳቸው ካሉት 95 ከመቶ ጋር ማነጻጸር ነው እንግዲህ፡፡ ይህንኑ እውነታ በሌላ ተጨባጭ ማስረጃ ለማስቀመጥ ያህል ሌላ ማሳያ ላምጣ፡፡ በመጽሀፉ እስከ 27ኛው ገጽ ድረስ የሳቸውን ሀሳብ እንደወረደ የተጠቀምኩት ሁለት ቦታ ላይ ከራሴው ጋር ካደረጉት ቆይታ ውስጥ ነው፡፡ ሽፋኑም ተደምሮ በገጽ ሲገመት አንድ ገጽ ከግማሽ ነው፡፡ ... ከገጽ 30 እስከ 35 ድረስ አንድ ቦታ ላይ ሩብ ገጽ ያህል ከ “ኢትዮጵያን ማን ይታደጋት” ላይ በቀጥታ ተወስዶ የሰፈረ ሀሳብ አለ፡፡... እንዲህ አድርገን ስንደምረውና በተለይም ከብርቱካን ጋር በተያያዘ የጻፉት ጽሁፍ፣ ለሰራሁት ትንታኔ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ አብዛኛው ክፍል በመግባቱም ጭምር ነው ከላይ የጠቀስኩትን ያህል ቁጥር የመጣው፡፡ በመጨረሻም ከአንደኛው ገጽ ያልዘለለ ንባብና በስማ በለው በቲፎዞነት መሰለፍ ውጤቱን አደገኛ ያደርገዋል፡፡ መጽሀፉን ማንበብ ብቻ ወደትክክለኛው መንገድ ደርሰናል፡፡ አንብቦ ስራው አይረባም ማለት ይቻላል፡፡ ድምዳሜውን ለአንባቢያኑ መተው ይሻላል፡: በተረፈ ግን በቀሪ አተካራዎች ላይ ገብቶ መዋጀቱ ትንሹ እድሜዬ ሳይሆን በልበሙሉነት
የምናገርለት የሞራል ልዕልናዬ አይፈቅድልኝም፡፡ እውነቱ ይህ ነው! ትዕግስትም፣ ዝምታም፣
አክብሮትም ልክ አለው!!

Read 2976 times