Saturday, 27 June 2015 09:28

ወተትና የወተትተዋጽኦ በጥራትምበብዛትም

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

ዝቅተኛ መሆን አሳሳቢ ሆኗል


የ5ኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ ኢትዮጵያ በ53 ሚሊዮን የቀንድ ከብቶች ብዛት ከአፍሪካ 1ኛ፣ ከዓለም 10ኛ መሆኗን ተምሬአለሁ፡፡ ዛሬ በሥራ ዓለም ከ20 ዓመት በላይ ቆይቼ ቁጥሩ ያው ከመሆኑም በላይ የወተትና የወተት ተዋጽኦ በጥራትም ሆነ በብዛት ዝቅተኛ መሆኑ ሰሞኑን ተገለፀ፡፡
ኢትዮጵያ ካላት 53 ሚሊዮን የቀንድ ከብቶች 10 ሚሊዮን ያህሉ የወተት ላሞች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ላሞች ውስጥ 98 በመቶ ያህሉ አገር በቀል ዝርያ ያላቸው ናቸው፡፡ አንድ የምትታለብ ላም በቀን በአማካይ የምትሰጠው ወተት ከ 1 ሊትር ተኩል እስከ 1 ሊትር ነው፡፡ የተዳቀሉት ላሞች በቀን በአማካይ 8 ሊትር ወተት ይሰጣሉ፡፡ በአገሪቷ ካሉ የወተት ላሞች በዓመት የሚገኘው ወተት 4 ቢሊዮን ሊትር እንደሆነ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 95 ሚሊዮን ይሆናል ብለን ብንገምት አንድ ኢትዮጵያዊ በዓመት በአማካይ የሚያገኘው የወተት መጠን 19 ሊትር ብቻ ሲሆን፣ የአንድ አፍሪካዊ የወተት ፍጆታ 27 ሊትር ተኩል ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የጤና ድርጅት አንድ ሰው በዓመት መጠጣት አለበት ብሎ የወሰነው 75 ሊትር ወተት እንደሆነ ከትናንት በስቲያ በወተትና ወተት ውጤቶች ጥራትና ደህንነት ላይ ለመምከር በሀርመኒ ሆቴል በተዘጋጀው ወርክ ሾፕ ላይ ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ ያለባትን የወተት ክፍተት የምትሸፍነው ከውጭ አገር የወተት ውጤቶችን በማስገባት ሲሆን ለዚህም በዓመት 10 ሚሊዮን ዶላር ያህል ውጪ እንደምታደርግ ታውቋል፡፡
በዓመት የሚመረተው የወተት መጠን ማነስ ብቻ አይደለም ችግሩ፤ የጥራቱም ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ በመላ አገሪቱ በዘመናዊ ዘዴ የሚመረተው ወተት ከመቶ 10ሩ ብቻ ነው። 90 በመቶው የሚመረተው በኋላቀሩ ባህላዊ የአመራረት ዘዴ በመሆኑ ጥራቱ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ወተት የሚታለብበት ዕቃ፣ ማስቀመጫው፣ ለማቀነባበር ወደ ፋብሪካ ሲወሰድ በየደረጃው ጥራቱ እየተጓደለ ነው፡፡
የወተት ጥራት የሚጓደለው በዚህ ብቻ አይደለም፡፡ ወተት ዱቄት ይጨመርበታል፣ የምትታለበው ላም ጤነኛ መሆኗ በየዓመቱ ምርመራ ስለማይደረግላት ቲቢ ከያዛት ከብት የታለበ ሊሆን ስለሚችል ለጤና ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል፡፡ ወተት 87 በመቶ ውሃ ነው፡፡
አሁን ከእጥረቱ የተነሳ ለገበያ የሚቀርበው ወተት ብዙ ውሃ ተደባልቆበት ስለሆነ የፕሮቲን እጥረት ይከሰታል፡፡ በፕሮቲን እጥረት የተነሳ በአገሪቷ ከሚወለዱ ሕፃናት 64 በመቶ ያህሉ በዕድገታቸው ቀጫጫ እንደሚሆኑ የሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ም/ዳይሬክተር አቶ ታደሰ ጉታ አመልክተዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ጥራቱና ደህንነቱ ያልተጠበቀ ወተት ተጠቃሚዎች ለሞት ለሚዳርግ በሽታ ሊጋለጡ እንደሚችሉ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡

Read 3288 times