Saturday, 27 June 2015 09:36

ወፈፌው

Written by  በደረጀ ይመር
Rate this item
(11 votes)

አንገቱ ላይ የተንጠለጠለውን ገመድ የሙጥኝ እንዳለ ነው፡፡ ቁርጠኛ ውሳኔውን ለማጨናገፍ የሚንከወከው ድንገቴ ቢመጣ  ሳይቀድመው እንደሚቀድመው ተማምኗል፡፡ አንዲት እራፊ ጨርቅ ብቻ ነች ኃፍረተ - ሥጋውን የሸፈነችው፡፡ ገመዷ ከቦታዋ መኖር አለመኖሯን እያሰለሰ ይሰልላታል፡፡
ጠደፍ ጠደፍ እያለ ሠፊውን ጎዳና በሰጎን ቅልጥሞቹ እየመተረ ማቋረጥ ጀመረ፡፡ ግራ ቀኙን አልተመለከተም፡፡ ሲከንፉ የመጡ አውቶሞቢሎች የወፈፌው በጎዳናው ላይ ድንገት መደንጎር ቢያጥበረብራቸው እንደ ወታደራዊ ዘብ ቀጥ ብለው ቆሙ፡፡ ጎማቸው ከጎዳና ጋር ክፉኛ ተሳሳመ፤ አካባቢውን ለጆሮ በሚቀፍ ድምጽ አወኩት፡፡
“ይሄ ጋኔል የሰረረው…ደርሶ…ሰበብ..ሊሆን ነው..እንጂ“ ከወዲያ ማዶ ያሉት የባንክ ቤቱ ጥበቃ አንቧረቀ፡፡
ወፈፌው ሁኔታውን ከመጤፍ አልቆጠረውም። ወደ ግራ የሚታጠፈውን የአስፓልት ጎዳና ያዘ፡፡ ሕዝበ አዳም የዕለት ጉርሱን ሊያበስል በየአቅጣጫው ይተማል፡፡ ይህ ጭንቀት ከወፈፌው ጫንቃ ላይ ከወረደ ሰነባበተ፡፡ ስለ ዕለት ጉርስ፣ ስለ ጎን ማረፊያ የሚያውጠነጥነው ናላው ታውኳል፡፡
ፍጥነቱን ከቅድሙ የባሰ ጨመረ፡፡ አላፊ አግዳሚው በሁኔታው ተደናግጦ ጥጉ ጥጉን እየያዘ እያሳለፈው ነው፡፡
የወፈፌው ጥድፊያ እንደው በዋዛ አይደለም። ነፍሱን በእጅ ይዞ የሚካለበው ከሚያሳድደው መንፈስ ለማምለጥ ነው፡፡ ከደቂቃዎች በፊት ሠፊ ሆድ ካለው ጨለማ ዋሻ ውስጥ ቁምስቅሉን ሲያይ  ነበር፡፡ ምርኮው ያደረገው ጋኔን የእሳት ጅራፉን ከገላው ላይ ማሳረፍ ከሰለሰ ገና ጥቂት ሰዓታት ነው የነጎዱት፡፡ አንገቱ ላይ የሸመቀቃት ገመድ ልክ እንደጨቅላነቱ ክታብ ከሳጥናኤል ጡቻ የሚመክትባት ጋሻው ሆናለታለች፡፡ ገመዷን ጠበቅ አደረጋትና ፍጥነቱን ጨመረ፡፡
ትንሽ እልፍ እንዳለ ትከሻዋን እየሰበቀች፣ ዳሌዋን እያማታች የምትውረገረግ መልከመልካም ሴት ከአላፊው አግዳሚው ልቃ ከአይኑ ገባች፡፡ ይህቺን ሴት በእዛ በከርሳም ዋሻ ውስጥ በደንብ ያውቃታል። ከሰዓታት በፊት የሳጥናኤል ቀኝ እጅ፣ የእርሱ ጣውንት ነበረች፡፡ አለንጋ ጣቶቿ የዋሻውን እሳት ለማንተርከክ ነው የሰለጠኑት፡፡ በረገጠበት ቦታ ሁሉ እንደጥላው የምትከተለውን ባላንጣውን አንድ ነገር ማድረግ እንዳለበት አሰበ……ደመነፍሱ ፈጥኖ እርምጃ እንዲወስድ ወተወተው፡፡
“እዚህ ደግሞ ምንድን ነው የሚያልከሰክሳት፣ይህቺ ጆሮ ጠቢ፣ የሳጥናኤል መልእክተኛ፤ ሳትቀድመኝ ልቅደማት?” በውስጡ አጉተመተመና ወደ ልጅቷ ተንደረደረ፡፡
ድንገት አቅጣጫ ለውጦ ጎዳናውን ለመሻገር እግሩን ሲሰነዝር ሲከንፍ ከመጣ መኪና ጋር ተሳሳመ፡፡ አየር ላይ ተንሳፍፎ በአርበ ሰፊው ጎዳና ላይ እንዳይሆኑ ሆኖ ተነጠፈ፡፡ በደም የተለወሰውን በድን አላፊ አግዳሚው እንደ ንብ ሠራዊት ከበበው፡፡
*   *   *
ወፈፌውን ዓለም ከተፋችው ሰንብታለች። አሁን ሲበር የመጣው ከአማኑኤል ሆስፒታል ሾልኮ ነው፡፡ የሆስፒታሉ ታካሚ መሆን ከጀመረ መንፈቅ አልሞላውም፡፡ ፊት ወሰድ መለስ ነበር የሚያደርገው፡፡ ኋላ ላይ ወሰድ መለሱ ወደ ለየለት እብደት ተለወጠ፡፡
የወፈፌነቱ አባዜ ገና ኮሌጅ እንደበጠሰ ነው የተጠናወተው፡፡ ግብሩ ሁሉ ከዕድሜ እኩዮቹ ጋር አይገጥምም ነበር፡፡ ቢጤዎቹን፣ የእድሜ አቻዎቹን መምሰል ተሳነው፡፡ እንደ ኮብል ድንጋይ ተጠፍጥፎ ላለመበጃጀት እባጭ ሆኖ ተውተረተረ፡፡
የቀለም መምህሩ ልክ እንደፈሪሳዊያን በቃላት የሚታበይ ነው፡፡ ከአአምሮው በመሰገው መናኛ እውቀት ክፉኛ ይደለላል፡፡ ከእዚህ ድብታ መሓል ለአመል ዘለግ ብሎ የሚገዳደረው ወፈፌው ነበር። መምህሩ በአራት ነጥብ ያሰረውን ፍሬ ሐሳቡን ወፈፌው በጥያቄ ምልክት ይፈተዋል፡፡
“ይህ ትውልድ ለመቀበል እንጂ ለመጠየቅ አልታደለም…..“ይላል ፈሪሳዊው መምህር ገና ክፍል እንደገባ፤ ከወፈፌው ሊቃጣ የሚችልን ፈታኝ ጥያቄ ለመመከት፡፡
ቀናት በገፉ ቁጥር የወፈፌውና የፈሪሳዊው መምህር መቃቃር እየከፋ ሄደ፡፡ እሰጣ ገባው ወፈፌው ላይ ሌላ መዘዝ ይዞ ብቅ አለ፡፡ በአምስት አመት የሚገባደድን ትምህርት እስከ ሰባት ዓመት አስዘለቀው፡፡ ኮሌጅ በረገጠ በሰባት ዓመቱ ቆብ ለመድፋት በቃ፡፡
ቆብ በደፋ ማግስት ከአንድ አገልግሎት ሰጪ መ/ቤት ተቀጠረ፡፡ ሳይውል ሳያድር ወንበር ማሞቁ አጥወለወለው፡፡ መምህር በስንት ጣዕም ብሎ ከአንድ ኮሌጅ እጅግም በማያወላዳ ደሞወዝ ቀለም ማስቆጠርን ሥራዬ ብሎ ተያያዘ፡፡ ከእዚህ ቀደም ሲቀናቀነው በነበረው መምህሩ እግር ተተክቶ ትውልድ የመቅረጽ ድርሻውን እየተወጣ ሰኔ ግም እስኪል ጠበቀ፡፡ የጠናወተው ልክፍት ግን ከዚህ በላይ ሊያዘልቅው አልቻለም፡፡
የወሰድ መለሱን ስብዕናውን ቀስ በቀስ እያጣ እንደሆነ ሲገባው ጥቂት አወጣ አወረደ፤ እና የቀለም ተማሪዎቹን ተሞክሮ በማይታወቅ ሃዲድ ላይ ሊያነጉዳቸው ወሰነ፡፡
ክፍለ ጊዜውን ባልተመለደ ሁኔታ በሁለት እኩሌታ ከፈለው፡፡ በመጀመሪያ ክፍለ-ጊዜ ለፈተና በደንብ የሚያዘጋጅ ፍሬ-ሐሳብን ከላይ እስከታች ይተረትራል፡፡ በተቀረው ክፍለ ጊዜ ደግሞ ንቃትን በሚያበረታ ፍሬ ሐሳብ ላይ ይጠበባል፡፡ በሰላሳ ደቂቃ ያስተማረውን ፍሬ ሐሳብ በተቀረው ሰላሳ ደቂቃ ያፈራርሰዋል፡፡
“ዕውቀት እና ሽልማት ለየቅል ናቸው፡፡ ሽልማት ካላችሁ ቀዳሚውን …. እውቀት ካሰኛችሁ ደግሞ የኋልኛውን መምረጥ የእናንተ ፋንታ ነው” የየዕለቱን ማብራሪያ ከመጀመሩ በፊት ከአንደበቱ የሚፈልቅ አባባል ነው፡፡
የወፈፌው የመማር፣ማስተማር ስልትን በበጎ የሚተረጉም ወገን ግን ጠፋ፡፡ ይብስ ብሎ የኮሌጁ ቀለም ቆጣሪ በአንድነት አብሮ የትምህርት ገበታውን አራቆተው፡፡ ሳይውል ሳያድር የኮሌጁ አስተዳዳሪዎች ትውልድ እየገደልክ ነው ብለው ወፈፌውን መምህር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አሰናበቱት፡፡ በፈሪሳዊው መምህር ግብር ተመዝኖ ትውልድ ገዳይነቱ ታወጀ፡፡
ሥራ አጥ ሆኖ ወዲህ ወዲያ መንከላወስ የአዘቦት ግብሩ መሆን ከጀመረ ቀናት አለፉ፡፡ ሲያገኝ ይበላል፣ ሲያጣ ድፍት ብሎ ያድራል፡፡
ቀኑ ዕለት ሰንበት ነው፡፡ ደርሶ  ጠጣ ጠጣ የሚል ስሜት  ሽው አለበት፡፡ አንድ ሁለት ለማለት ወደ አንዲት ባለጉልላታም ጠጅ ቤት ጎራ አለ። ቤቷ ብርድን እና ድብርትን በሸሹ እድምተኞች ተጨናንቃለች፡፡ ገና ከመቀመጡ ጠጅ ቀጂው በሆድ ዕቃዋ ጥም ቆራጭ ያቆረች ከርሳም ብርሌን ኳ….ኳ አድርጎ ከፊቱ ጎለተለት፡፡ ዓይነ ግቡዋን ብርሌ ወደ አፉ አስጠጋት፡፡ በሆድ ዕቃዋ ያዘለችውን ጥም መቁረጪያ ወደ ጉሮሮው ላከው፡፡ የእርካታ ስሜት መላ ሰውነቱን ሲወረው ተሰማው፡፡
የነተበ የወታደር ዩኒፎርም የለበሰ ጎስቋላ ሰው፣ በጠጅ ቤቱ ሁካታ ላይ የራሱን ነጠላ ጩኸት እያከለ ነው
“ቢንጎ ቢንጎ፤ ቢንጎ ለባለዕድል” ድምጹን ከሁካታው መሃል ዘለግ ለማድረግ ይታገላል፡፡
ጥርስ አልባ ድዳቸው እንዳይታይ በተከናነቡት ነጠላ ጠርዝ የሚመሸጉ ጠና ያሉ ሴት ከቢንጎ አጫዎቹ ላይ በርከት ያሉ ዕጣዎቹን ለመሸመት ቅድሚያውን ወሰዱ። ከሴትየዋ ጋር እልህ የተጋቡ የሚመስሉ ሌሎች አቻ ጠጪዎች ቀሪዎቹ እጣዎች ላይ ተረባረቡ። አጫዋቹ እጁ ላይ የቀሩትን ጥቂት እጣዎች ለባለዕድለኞች ለመሰዋት ግራ ቀኙን እያማተረ ድምጹን ያለ ስስት ማውጣቱን ቀጠለ፤
“ቢንጎ  ቢንጎ ለባለ ዕድል” ይላል
ወፈፌው አገጩ ላይ ዘርዘር ብሎ ከበቀለው ጺሙ መካከል መለሎ የሆኑትን መርጦ በጣቶቹ መሀል  እየፈተለ ለቀሪዎቹ ዕጣዎች እጁን ዘረጋ። ቢንጎ አጫዋቹ የተቀበላቸውን ጥንድ ሽልንጎች ከሌሎች  የሽልንግ ቤተሰብ ጋር እየደመረ ፊቱን ፈንዲሻ አደረገለት።
ኮርነር ላይ የመሸገው ጠጅ አንቆርቋሪ ከጠጪው በተለየ ትኩረት የመስረቅ ኃይል አለው፡፡ ሁካታውን እንደ ጥዑም ዜማ እየጣጣመ መጽሓፍ ይገልጣል፡፡ ብርሌ የጨበጡ እጆቹ የመጽሓፍ ገላን ለመደባበስ አልሰነፉም። ከገለጠው መጽሐፍ ትንሽ ገጽ ያነበንብና መልሶ ይከድናዋል፡፡ የመጽሐፉ ልባስ ግማሽ አካሉ የለም፡፡ ጣቱ ያረፈበት ገጽና የሽፋኑ ስዕል ሳይገጥምበት አልቀርም፡፡ ወደ ልባሱ አይኑን ወርወር ያደርግና መልሶ ጭንቅላቱን  ግራና ቀኝ  ያማታል፡፡
 “የሃቅ..መግቢያ ልክ እንደ የቀበሮ ጉድጓድ ጠባብ ናት …” አለ በስሜት ተውጦ ከሆነ ገጽ ላይ ሲደርስ። ሰሚ ያገኘ አይመስልም፡፡ ብርሌውን እንደመፈክር ወደ ላይ ከፍ አደረገና በፍቅር ከብርሌዋ ጋር ከንፈር ለከንፈር ተሳሳመ፡፡ ጠረጴዛውን በኃይል ደቃና አባባሉን ደገመው፤
“የሃቅ መግቢያ ልክ እንደ የቀበሮ ጉድጓድ ናት” የአሁኑ ድምጹ ግን አለቅጥ ዘለግ ብሏል፡፡
ከእርሱ ገጥ ለገጥ ወደ ተሰየመ ጎልማሳ ሰው እየጠቆመ፤
“ለእንደ አንተ…አይነቱ ሴት አውል…ግን...መግቢያው የመርፌ ቀዳዳ  ይሆናል” አለ  የድምፁን ጉልበት ሳይቀንስ።
ጎልማሳው ቃል አልተነፈሰም፡፡ ፊቱን ወደ ወለሉ ዘመም አድርጎ በውስጡ አጉተመተመ፡፡
‘ባለጠጋ መንግሥተ ሰማያትን ከሚወርስ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀላል…..አትልም…… አንድ ፊቱን” ወፈፌው አከታትሎ በጨለጠው ጠጅ ተበራትቶ አንደበቱን አፍታታ፤
“በቀዳዳው ለመሹለክ …..ከእዚህ ሴት አውል..ይልቅ… እኔ ከሲታ ነኝ….አሃሃሃሃሃሃሃ”
ጠጪው አብሮ አውካካ፡፡ የጎልማሳው ገጽታ ከመቅጽበት ከሰለ፡፡ የቀረበለትን ጠጅ በአንድ ትንፋሽ ጨለጠና ፊቱን ጨፍግጐ መሬት መሬቱን እያየ ትካዜ ውስጥ ገባ፡፡ ድንገት ብርሌውን አንስቶ ወደ ሰውዬው ግምባር ተኮሰው፡፡ የተተኮሰው ብርሌ ግን የሰውየውን ግምባር ሸሽቶ ከወፈፌው መስቀለኛ ላይ ውኃ ሆነ። ከእዚህ በኋላ ወፈፌው ራሱን ያገኘው አማኑኤል ሆስፒታል ውስጥ ነው፡፡ የብርሌዋ ገላ የወፈፌውን የአዕምሮ ድር ለመበጣጠስ ጊዜ አልወሰደባትም፡፡ በቋፍ የነበረው ማንነቱ ከእነአካቴው ወደ ለየለት እብደት ተለወጠ፡፡ የለየለት እብድ ሆነ፡፡
*  *  *
ይሄኛው የመኪና አደጋ የትኛውን ድር ይበጣጥስ ይሆን… ወይስ ከእነካቴው የሕይወቱን ድር ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ በጣጥሶ ይገላግለዋል?
በምናብ የፈጠረውን ሴጣን ሲሸሽ በአካል እየከነፈ የመጣው ሴጣን ገላፊቻ አለው፡፡ በአካል የመጣን ሴጣን አማትበው አይርቁት ነገር!

Read 4420 times