Saturday, 27 June 2015 09:36

የሠፈር ስደተኛ (የልጅነት ወግ)

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(0 votes)

መሀል ከተማ ዘይኔ ሻይ ቤት ቁጭ ብዬ ማዶውን የጓደኛዬን የእነ መላኩን የቃጫ መጋዘን ሣይ አብሬ ብዙ ነገር አያለሁ፡፡ የጫት ገበያተኞች ወከባ፣ የሊስትሮዎች ሣቅና ተረብ፣ የመንገደኞች ወዲያ ወዲህ ማለት፡፡ ልቤ ግን አሁንም ተመልሶ መላኩ ጋ ነው፡፡ ዛሬ መላኩ ካገኘኝ አይላቀቀኝም፡፡ በዚህ ሰዓት ደግሞ የትም አይሄድም፡፡ ጠዋት ትምህርት ቤት በሩቅ አይቼው ነበር፡፡ ለምን እንደተጣደፈ ባላውቅም ተደብቆ ሲፎርፍ አይቼዋለሁ፡፡ ለነገሩ ፎርፌ ሕይወቱ ነው፡፡
እኔም ትምህርት ቤት የምሄደው የእርሻ አስተማሪዬ ያዘዙኝን ለመፈፀም ነው፡፡ መምህራችን ያከፋፈሉንን መደብ በደንብ ካልቆፈርንና ለዘር ካላመቻቸን ማርካችን ይቆረጣል፡፡ ያንን ፈርቼ ነው፡፡ ያለፈው ሴሚስተር ውጤቴ ጥሩ ስላልነበረ ማስተካከል አለብኝ፡፡ የክፍል ደረጃዬ ሲቀንስ ደግሞ እቤት ውስጥ መከራ ይጠብቀኛል፡፡ ከዚያ መከራ ለማምለጥ ነው አሁን ከመላኩ ጋር መከራ የገባሁት። አሁን ካገኘኝ ይጣላኛል፡፡ ሳያየኝ በአንዳች ዘዴ ነው መጋዘናቸውን ማለፍ ያለብኝ፡፡
መላኩ ደግሞ አባቱ ወንበር ላይ ተቀምጠው በሚዛን ቃጫ እየመዘኑ ከሚገቡበት ቦታ አይጠፋም። ርስቱ ነው፡፡ አንዳንዴ ቢጠፋም ለተንኮል ነው። ሰው ጓሮ ሄዶ ኮክና ዘይቱን ለመስረቅ ወይም ሸንኮራ ለመስበር ነው፡፡ ለትምህርቱ ግድ የለውም። ከጓደኞቹ እየኮረጀ ነው አራተኛ ክፍል የደረሰው፡፡ አባቱም እንደእርሳቸው እንዲነግድ ይሆን ባላውቅም አይቆጡትም! እንደ ልቡ ነው፡፡
መጋዘኑ ወደ ትምህርት ቤት ማለፊያ መንገድ ላይ መሆኑ ደግሞ ከፋ፡፡ ፉርኖ የምትባል ያክስቱን ልጅ ስመሀታል ብሎ ነው ለመደባደብ ዘራፍ የሚለው፡፡ ሠፈሩ ስለሆነ እንጂ እኔም በሠፈሬ ለርሱ አላንስም፡፡
“እኔ ፉርኖን ቁመቴ የት ደርሶ ነው የሣምኳት?” ስለው “በረንዳችሁ ላይ ቆመህ ነው ሰምቻለሁ!” አለኝ፡፡ ይህን ያቃጠረው ማን እንደሆነ አውቃለሁ። አንድ ቦቅቧቃ ጓደኛችን አለ፡፡ ለርሱ ዋጋውን እሰጠዋለሁ፡- ፊቱን በጥፊ ሳጮለው ቀይ ፊቱ ሣንባ ይመስላል፡፡ ከዚያ እንባው ይፈስሳል፡፡ ቁመት ብቻ ነው እሱ ደሞ! ሴት መልክ! ትዝ ሲለኝ ብሽቅ አልኩ።
መጋዘኑ ደጅ መላኩ የለም፡፡ ግን አንደኛው ወንድሙ አለ፡፡ ሁሉም ተሣዳቢ ናቸው፡፡ ባይመቻቸው እንኳ ምላስ ያወጣሉ፡፡ ካልሆነም በወንጭፍ ጠጠር ይሰድዳሉ፡፡ በትምህርት ቤት የጓሮ መግቢያ መሽሎኪያ ቀዳዳ አለ፡፡ ግን ዘበኞቹ ካገኙኝ አበሳ ያስቆጥሩኛል፡፡ በተለይ ጋሽ ጦቢያ ጆሮ ይተለትላል፡፡ በዚያ ቁመቱ ጢሙን ጠቅልሎ ሲያስፈራ! ጠመንጃማ ከእጁ አይለይም፡፡ እድሜው ረጅም ነው፤ ጋሽ ጦቢያ ሸሚዝ ለብሶ፣ የወታደር ጫማውን ተጫምቶ፣ እግሩን ብድግ ብድግ እያደረገ በዋናው መንገድ ሲያልፍ አየሁት፡፡ ነፍስ እንደያዘው ሰው ሮጬ “ጋሽ ጦቢያ” አልኩት፡፡
“ምን ሆነሃል?” አለኝ፡፡ የተቆጣ መስሎኝ ነበር፣ ፈገግ አለ፡፡ ጥርሶቹ እንዲህ ያምራሉ እንዴ?
“አይ ወደ ትምህርት ቤት ልሄድ ነው፡፡”
“ና - ታዲያ” አለና አንድ እጁን ዘረጋልኝ፡፡
እጄን ይዞኝ “ከልጆች ተጣልተሃል እንዴ?” አለና ሳቀ፡፡ እኔ አሁንም መላኩን እያሰብኩ ነው፡፡ በደግ ቀን ይጋብዘኛል፡፡ ስንጣላ ደሞ ሰይጣን ነው መላኩ። ፀጉሩ ቁርንድድ፣ አፍንጫው ድፍጥጥ ያለ ነው፡፡
ቀስስ ብዬ ከጋሽ ጦቢያ ጋር ሳልፍ ታናሽ ወንድሙ በአይኑ ፈልፍሎ አየኝ፡፡ ጋሽ ጦቢያ እያለ እንደማይነካኝ አውቃለሁ፡፡ ግን አጥር ዘልሎም ቢሆን ሊመጣብኝ ይችላል፡፡ ሲለው ያቺን ተፈሪ ኬላን ዳር እስከ ዳር ያምሣታል፡፡ ቢገረፍም ግድ የለው፡፡
ትምህርት ቤት ግቢ ስገባ ጨፈቃ ነገር ልቆርጥ አስቤ ነበር፡፡ ግን አልተመቸኝም፡፡ በዚህ ሃሳብ ውስጥ ሆኜ ወደ እርሻ መደቤ እየሄድኩ እያለ የጋሽ ጦቢያ ድምጽ አቋረጠኝ፡፡
“ምን ልታደርግ ነው የመጣኸው?”
“የእርሻ ቲቸሬ የእርሻ መደቤን ኮትኩት ብለውኝ ነው፡፡”
“ታዲያ መኮትኮቻ የታል? በጥፍርህ ልትኮተኩት ነው፡፡”
“በል ና መኮትኮቻ ውሰድ!” ብሎ ይዞኝ ሄደ። እንደ ፌንጣ ወደሰማይ ብዘልል ደስታዬ ነው፡፡ አሁን መላኩ ቢመጣ እንኳ ግድ የለኝም፡፡ ዋጋው እሰጠዋለሁ፡፡ ደረቴን ነፋሁ፡፡ ከብዙ መቆፈሪያዎች አስመርጦኝ ባለ ሁለት ምላስዋን መኮትኮቻ ተቀበልኩ፡፡
“እንደ ጨረስክ መልስ ታዲያ…”
“እሺ ጋሼ!” ብዬ በረርኩ፡፡
በአንድ በኩል የእርሻ መምህራችንን ሃሳብ በመፈፀሜ፣ በሌላ በኩል ከመላኩ ስጋት በመዳኔ እየተደሰትኩ ሄጄ ኩትኳቶ ጀመርኩ፡፡ መደቤን ቆንጆ አድርጌ አሣመርኩና የመምህሬን ፈገግታ አሰብኩት። ከጥቁር ፊታቸው ታች እሸት በቆሎ የሚመስሉ ጥርሶቻቸውን አሰብኩ፡፡ በአለንጋ አይነኩኝም፤ ወይም ልምጭ ቆርጠህ አምጣ አይሉም፡፡ ፈገግ ብለው ትከሻዬን ቸብ ቸብ ያደርጉኛል፡፡
የመላኩ ነገር ግን በዛሬ ብቻ የሚያበቃ አይደለም፤ አንላቀቅም አውቃለሁ፡፡ ችግሩ ግን ትምህርት ቤት የምሄደው በእነርሱ መጋዘን በር አልፌ ነው፡፡ መቸም ለምን ነገረኛ እንደሆነ ባላውቅም በጉልበት ግን አላንሰውም፡፡ የርሱ ክፋት ዱላ፣ ብረት፣ ድንጋይ መያዙ ነው፡፡ ሰሞኑን ለፉርኖ ጠበቃ ሆኖ እኔን ጓደኛውን ማወኩ አልገባኝም። ፉርኖ ያክስቱ ልጅ ብትሆንና እኔ ብስማት ምን አገባው? ያንዱን ጓደኛ እህት የሚያገባት ሌላ ሰው መሆኑን እንኳ አያውቅም፡፡
ሰማዩ እንደመጨለም፣ እንደማጉረምረም አለ። ከከተማው ግራና ቀኝ የተንጠራሩት ተራሮች ፊታቸውን ማጥቆር ጀመሩ፡፡ እኔም ኩትኳቶዬን ጨርሼ መኮትኮቻውን አሥረክቤ ለመውጣት ወደ ጋሽ ጦቢያ ፈጠንኩ፡፡
ጋሽ ጦቢያ ካፖርቱን ግጥም አድርጐ ለብሶ፣ ፊቱን በፎጣ ነገር ጠቅልሏል፡፡ በዚያ ላይ ጠመንጃውን እንዳነገተ ነው፡፡ ጠመንጃውን ለምን እንደማይለቅ ግራ ይገባኛል፡፡ ፈሪ ሣይሆን አይቀርም፡፡
“አመሠግናለሁ ጋሽ ጦቢያ” አልኩና ሰጠሁት። ዞር ቢልልኝ በጓሮ አጥር በኩል ሾልኬ መላኩ ሳያገኘኝ ላመልጥ ፈልጌ ነበር፡፡ ግን አልለቀቀኝም እስከዋናው በር ተከተለኝ፡፡
ከግቢ ከወጣሁ በኋላ ትንሽ ቆሜ አመነታሁ፡፡ እንዴት አድርጌ የእነመላኩን መጋዘን ልለፍ? በዓይኔ ከወደ በንቆቃ በኩል የሚመጣ ሰው ፈለግሁ፡፡ በንቆቃ ወንዝ በዲላ መስመር ነው፡፡ አንዳንዴ ከዚያ በኩል የሚመጡ ተማሪ ጓደኞች አሉኝ፡፡ እነርሱን ጠበቅሁ፡፡ ማንም አልመጣም። ለክፉም ለደጉም አልኩና አንድ ረዘም ያለ ሹል ድንጋይ በኪሴ ያዝኩ፡፡
ቀጥዬ ማዶውን በሰዎች በረንዳ እየታከክሁ ሄድኩ፡፡ ከቤታቸው ፊት ለፊት አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ አለ፡፡ እዚያ ደረስኩና ቆምኩ፡፡ ፖሊሱ ምትኩ ቆሟል፡፡ እሱም ፊቱን አስቀርቶ ጭንቅላቱን በጃኬት ቆብ ጠቅልሏል፡፡ ቀስ ብሎ አየኝ፡፡
“ምን ታረጋለህ አንተ ልጅ?”
“ምንም!”
“ዝናም ሳይመጣ ወደቤትህ አትሄድም!”
“አይ መላኩ የሚባል ነገረኛ ልጅ አለ እዚያ!”
“ፈርተህ ነው? በልና” ብሎ እጄን ያዘና አሳለፈኝ፡፡
እኛ ሠፈር መጥቶ እትዬ አበባየሁ ጠጅ ቤት ይጠጣል። ለነገሩ እዚያች ትንሽ ከተማ ውስጥ የማይተዋወቅ የለም። ባለሱቁ፣ ባለዳቦ ቤቱ፣ ባለቡና ቤቱ፣ ልብስ ሰፊዊና አናጢው ሁሉም ይተዋወቃል፡፡
የነመላኩን መጋዘን እንዳለፍኩ ወደ ቤት በረርኩ። ይሁን እንጂ ቤት ሄጄም ልቤ አላረፈም፡፡ ከመላኩ ቁጣ የማመልጥበትን ዘዴ አሰላሁ፡፡ ወደ ማዕድ ቤት ገባሁና ትልቅ ምሥማር ፈለግሁ፡፡ ለክፉ ቀን የማስቀምጣቸው ብረቶች አሉኝ፡፡ አሰስኩ፡፡ እናቴ ሳትመጣ ሁሉን ለማጠናቀቅ ተፍ ተፍ አልኩ። ያገኘሁት ምስማር ተስማሚ ነበር፡፡ ጫፉን እንደ ሴንጢ ጠፍጥፌዋለሁ፡፡ በቃ ይቺ ለመላኩ ልክ ማስገቢያ ናት፡፡
ወደ ኪሴ ከተትኳት፡፡
ዝናቡ ዶፉን አወረደው፡፡ ፊት ለፊቴ በረንዳ ላይ ቆሜ ማዶውን ወዳሉት ተራሮች አየሁ፡፡ ጨልመዋል፡፡ ጓደኞቼም በየቤታቸው ተከትተዋል። በየበረንዳው ፍዝዝ ብሎ ዝናቡን ከሚያየው ሰው በቀር መንገዱ ባዶ ነው፡፡
ዝናሙ ሳያባራ ቀጠለ፡፡ ማምሻ ላይ ብቻ ጨለምለም ሲል ቀስ እያለ አባራ፡፡ ሰውም ከትምህርት ቤት እንደተለቀቀ ተማሪ በየአቅጣጫው ተመመ፡፡
እኔም ምሥማሬን በኪሴ ይዤ ተንቀሳቀስኩ፡፡
ነጐድጓዱ ሰማይ እየቧጠጠ፣ ሆድ እያባባ ሲቀጥል፣ እናቴ ሻማ ግዛ ብላ ወደ ሱቅ ላከችኝ፡፡ የልጅ ባርኔጣዬን አናቴ ላይ አድርጌ ዶፍ ከመዝነቡ በፊት በረርኩ፡፡ ቢሆንም አልዘነጋሁም፡፡ የተሣለ ምስማሬን በግራ እጄ ጨብጫለሁ፡፡ አሁንም ልቤ ጥርጣሬውን አልተወም፡፡
ሱቅ ገብቼ ስወጣ ሰማዩ የተንጓጓ፣ መብረቅ እላዬ ላይ የወደቀ መሠለኝ፡፡ ጆሮ ግንዴ ጮኸ፡፡ መሬት ላይ ተዘረርኩ፡፡ በእጄ የያዝኩት ሻማና ምሥማር ወደቀ፡፡ በጆሮዬ ድምጽ እንደ ሕልም ይሰማኛል። ሁለተኛ እንኳን ከንፈሬን እግሬን አትስማትም፡፡ የፉርኖ መሆን አለበት፡፡ በመሸነፌ አፍራ ይሆን?

Read 1414 times