Saturday, 27 June 2015 09:37

‹‹እንዲያው ለጨዋታ››

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(0 votes)

--ያ ግሪካዊ መንፈስ፤ ከዚያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ሞቶ እንደ ተቀበረ ቀርቷል፡፡ ‹‹በነገርህ ሁሉ ምጥን ሁን›› የሚል ወርቃማ ህጓን የተወችው ግሪክ፤ ብድር አብዝታ ወስዳ በማጣጣር ላይ ትገኛለች፡፡ ከእነ አቴና ወይም ስፓርታ ጋር ስትነፃፀር ትልቅ ግዛት ያላት ቢሆንም፤ ትንሽ ሐገር ነች፡፡---

‹‹ዘመናዊው የዓለማችን ሰው በጠቅላላ፤ ‹ትልቁ› የሚል ቃል ይወዳል›› የሚለው ዊል ሔልም ሄንድሪክ ቫንሉን የሚሉት ድንቅ የታሪክ ፀሐፊ፤ ‹‹እኛ ዘመናውያን፣ የዓለም ‹ትልቁ› ሐገር ዜጋ በመሆናችን፣ ትልቅ የቲማቲም ወይም የድንች ፍሬ አምራች በመሆናችን እንኮራለን፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሚኖሩበት ከተማ ነዋሪ መሆን እንወዳለን፡፡ ደግሞም ከሐገሪቱ ውስጥ ተወዳዳሪ በሌለው ትልቅ የመቃብር ስፍራ ብንቀበር ምርጫችን ነው›› ሲል ይተቻል፡፡
በተቃራኒው፤ ‹‹የጥንታዊት ግሪክ ዜጋ የሆነ ሰው እንዲህ ስንል ቢሰማን፤ ግራ ሊጋባ ይችላል›› የሚለው ቫንሉን፤ የጥንታዊት ግሪክ ሰዎች የህይወታቸው ግብ እና የምኞታቸው ወደብ በሁሉም ነገር የተመጠነ ነገር ሆኖ መገኘትን ነው፡፡ ግባቸው ‹‹ልከኛው›› ወይም ‹‹መካከለኛው›› ነው -‹‹Moderation in all things››
ስለዚህ፤ በክብደት ወይም በስፋት ትልቅ መሆን ትርጉም አይሰጣቸውም፡፡ ‹‹ሳይረዝም - ሳያጥር፣ ሳይበዛ - ሳያንስ፣ ሳይቀላ- ሳይጠቁር›› ወዘተ ተብሎ ሊገለፅ የሚችለውን ነገር ይወዳሉ፡፡
አንድ ግሪካዊ፤ ‹‹እኛ ግሪካውያን ‹ምጥን› ነገር እንወዳለን›› ሲል፤ በሸንጎ ወግ ለማሳመር ወይም በግብዝነት መንፈስ ለመመፃደቅ አይደለም፡፡ አንድ ግሪካዊ ‹‹በነገርህ ሁሉ ምጥን ሁን›› ሲል ለላንቲካ አይደለም፡፡ ‹‹በነገርህ ሁሉ ምጥን ሁን›› የሚለው ሐሳብ ወይም መርህ፤ የአንድን ግሪካዊ ህይወት ከልደት እስከ ሞት የሚዘልቅ ጉዞ የሚገዛ እና በሁሉም የህይወት እንቅስቃሴዎች ገዢ የሚሆን የህይወት መመሪያ ነው፡፡
የሥነ- ፅሑፍ እና የኪነ - ጥበብ ሥራቸውን የሚገዛ ህግ ነው፡፡ ስለዚህ፤ ግሪካዊ ቤተ እምነቱን ሲሰራ፤ እንከን የለሽ እና ምጥን አድርጎ ነው፡፡ ወንዱ በሚለብሰው ልብስ፤ ሴቲቱ በምታደርገው የጆሮ ጌጥ ወይም የእጅ አምባር ይህ ህግ ይገለፃል። ወደ አምፊ ቴአትር ሲሄድ ተከትሎት ይሄዳል። እንደ ብረት የፀናን የ‹‹መልካም ሀሳብ›› ወይም የ‹‹መልካም ለዛ›› ህግን፤ (the Iron law of good taste and good sense) የሻረ ፀሐፌ ተውኔት ሲገጥማቸው፤ ከመድረክ ጎትተው እንዲያወርዱት የሚያስገድዳቸው ቀጭን ህግ ነው፡፡
ይህ ህግ፤ ሌላው ቀርቶ በፖለቲከኞቻቸው እና ባለዝና በሆኑ ጠንካራ አትሌቶቻቸው ባህርይ እንዲንፀባረቅ ይፈልጋሉ፡፡ እንደ አቦ ሸማኔ ሊታሰብ የሚችል አንድ ሯጭ፤ ስፓርታ ሄዶ፤ ‹‹በምድረ ግሪክ የሚኖር፤ ከኔ በበለጠ ረጅም ሰዓት በአንድ እግሩ ሊቆም የሚችል አንድ ሰው አይገኝም›› እያለ ጉራ ቢነዛ፤ ከከተማቸው ያባርሩታል፡፡ አንዲት ተራ ዳክዬ (goose) ልታስከነዳው በምትችልበት ጉዳይ ራሱን አኩራርቷልና ‹‹ውጣልን›› ብለው ያሳድዱታል፡፡
ይህን ስነግራችሁ፤ ምናልባት ‹‹ይገርማል›› ትሉ ይሆናል፡፡ ግን ጥያቄ መያዛችሁ አይቀርም፡፡ ‹‹እንከን የለሽ ሥራ ለመስራት እና ለምጥን ህይወት (Moderation) ይህን ያህል መጠንቀቅ ትልቅ ምግባር ነው፡፡ ግን በጥንታዊው ዘመን፤ እንዲህ ያለ የባህርይ ፅዳት ይዘው የሚገኙት ግሪካውያን ብቻ መሆናቸው ለምን ነው?›› ብላችሁ ብትጠይቁ፤ መልሱ ‹‹ሂዱ የግሪካውያን የኑሮ ሁኔታ ተመልከቱ›› የሚል ነው፡፡
የጥንታዊ ግብፅ ወይም የመሰጰጦምያ ህዝቦች፤ አንድ ቀን እንኳን በአይናቸው አይተውት በማያውቁት እና ከእነሱ ስንት ሺህ ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ ጨለማ በወረሰው ቤተ መንግስት ውስጥ በሚኖር እና ከስንት አንዴ አደባባይ ወጥቶ ለህዝብ በሚታይ፤ ማንነቱን በደንብ በማያውቁት ፍፁም ፈላጭ ቆራጭ በሆነ ንጉስ የሚገዙ ህዝቦች ናቸው፡፡
በተቃራኒው ግሪኮች፤ ፈላጭ ቆራጭ መንግስት ያልተጫነባቸው፤ መቶ በሚደርሱ ትናንሽ የከተማ መንግስታት የሚኖሩ ‹‹ነፃ ዜጎች›› (free citizens) ናቸው፡፡ በግሪክ ‹‹ትልቅ›› ሊባል የሚችለው ከተማ፤ በአሁኑ ዘመን ካሉ ትላልቅ ከተሞች አንድ ክፍለ - ከተማ ወይም መንደር ያነሰ የነዋሪዎች ቁጥር ያለው ነው፡፡
አንድ በኡር የሚኖር ገበሬ፤ ‹‹እኔ ባቢሎናዊ ነኝ›› ሲል፤ በጊዜው ምዕራባዊ የእስያ ክፍልን ጠቅልሎ ይገዛ ለነበረ አንድ ንጉስ፣ ግብር ከሚከፍሉ በሚሊዮኖች ከሚቆጠሩ ተገዢዎች አንዱ መሆኑን እየተናገረ ነው፡፡ ነገር ግን አንድ ግሪካዊ፤ ኮራ ብሎ፤ ‹‹እኔ አቴናዊ ነኝ›› ወይም ቴቢያዊ (Theban) ነኝ›› ሲል፤ ስለ አንዲት ከተማ እያወራ ነው፡፡ ይህች ከተማ፤ በአንድ ጊዜ የመኖሪያ አድራሻው እና ሐገሩ ናት፡፡ ለአንድ ግሪካዊ፤ በገበያ ሥፍራ ተሰብስቦ ውሳኔ ከሚያሳልፈው የከተማው (የሐገሩ) ህዝብ ፈቃድ ሌላ፤ የሚገዛለት ጌታ የለውም፡፡
ስለዚህ፤ አንድ ግሪካዊ ‹‹አባት ሀገሬ›› ብሎ የሚጠራት፤ እትብቱ የተቀበረባትን፣ አፈር ፈጭቶ - ጭቃ አብኩቶ፣ ድብብቆሽ እና እቴሜቴን ተጫውቶ ያደገባትን አጥቢያ ነው፡፡ በአክሮፖሊስ ቋጥኞች እንደ ዝንጀሮ እየዘለለ፤ በሽህ ከሚቆጠሩ አብሮ አደግ ሴቶች እና ወንዶች ልጆች ጋር እየተላፋ፤ ጉርምስናን ዘሎ ጉልምስናን የተቀዳጀበትን ቦታ ነው፡፡ በቅጽል ስማቸው ልትጠሯቸው እንደምትችሏቸው የክፍል ጓደኞቻችሁ፤ የድፍን የሐገሩን ሰዎች በቅጽል ስም ሊጠራቸው ይችላል፡፡ ግሪካዊ ‹‹አባት ሐገሬ›› ሲል፤ የእናቱ እና የአባቱ አጽም ያረፈባትን የተቀደሰች ምድር እየጠቀሰ ነው፡፡ ልጆቹ እና ምሽቱ በደህንነት ተጠብቀው የሚኖሩበትን እና ከፍ ባለ የግንብ አጥር የተከበበች ትንሽ መኖሪያ ቤቱ የምትገኝን ምድር እየጠቀሰ ነው፡፡
አንድ ግሪካዊ ‹‹አባት ሀገሬ›› ብሎ በፍቅር የሚጠራት፤ ምናልባት ከሦስት እና ከአራት ጋሻ የማይበልጥ ስፋት ያላትን እና በራሷ ምሉ የሆነችን ዓለታማ ምድር ነው፡፡ ታዲያ እንዲህ ያለ የመኖሪያ አካባቢ (ዓለም) በአንድ ሰው ግብር፣ ንግግር እና በሐሳብ ላይ እንዴት ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ማሰብ አስቸጋሪ አይሆንም፡፡
የባቢሎን፣ የአሲሪያ እና የግብጽ ህዝብ፤ ቢሄዱ - ቢሄዱ የማያልቅ የአንድ ትልቅ ግዛት ቁራጭ አካል በሆነ ክልል የሚኖሩ ናቸው፡፡ ስለዚህ፤ ማንነታቸው ለቁጥር በሚያታክት ብዛት ተውጦ፤ ከባህር እንደ ወደቀ ጨው ሟሙቶ ይጠፋል፡፡
ባቢሎናዊያን፤ የዲማው በዛብህ፤ አዲስ አበባ ሲገባ እንደ ገጠመው፤ ‹‹አባከና›› የመባል ፀጋን የሚያሳጣ ‹‹ስፋት እና ብዛት›› ባለው ግዛት የሚኖሩ ህዝቦች ናቸው። በተቃራኒው፤ አንድ ግሪካዊ የሚኖረው በልዩ ልዩ ትዝታ የተገመደ ትስስር ካለው የሀገሩ ሰው ጋር ነው፡፡ ከሚያውቃቸው እና ከሚያውቁት ጋር ይኖራል፡፡ እሱ፤ ሁሉም ሰው፤ ሁሉንም ሊያውቅ የሚችልበት ትንሽ ከተማ ዜጋ ነው፡፡ ስለዚህ፤ ሁሌም የሰላ አዕምሮ ባላቸው ጎረቤቶቹ እይታ ሥር ነው፡፡ ይህን ያውቃል፡፡ ምንም ነገር ቢሰራ ይታያል፡፡ ተውኔት ቢፅፍ ወይም የዕብነ - በረድ ሐውልት ቢያንፅ፤ ግጥም ቢገጥም፤ አለያም ዜማ ቢደርስ፤ ስለ ጥበብ ሥራዎች ባህርይ አብጠርጥረው በሚያውቁ የትውልድ ከተማው ወይም ‹‹የአባት ሐገሩ›› ነፃ ዜጎች፤ ሥራው ሁሉ በጥንቁቅ ዳኝነት እንደሚመዘን አሳምሮ ያውቃል፡፡ ይህ ዕውቀቱ ‹‹እንከን የለሽ›› ከሚባል ደረጃ የሚቀመጥ ሥራ እንዲሰራ ያተጋዋል፡፡ ከህፃንነቱ ጀምሮ እንደ ተማረው፤ ‹‹እንከን የለሽነት›› ያለ ‹‹ምጥንነት›› (moderation) ሊገኝ እንደማይችል በደንብ ይገነዘባል፡፡
እናም ወለም - ዘለም ማለትን በማይፈቅድ በዚህ ዓይነት የህይወት ጎዳና የሚያልፉት ግሪካውያን፤ በሁሉም መስክ የላቀ ሥራ ሰርቶ መገኘትን ተማሩ፡፡ አዲስ የመንግስት አስተዳደር ስርዓት ፈጥረው አፀኑ፤ አዲስ የሥነ- ፅሑፍ ቅርጽ ፈለስፉ፤ የሰው ልጅ በልቀት ተሻግሮ ሊያልፈው ያልቻለ አዲስ የሥነ- ጽሑፍ እሳቤ (Ideals) አበጁ፡፡ በዘመናዊ ከተሞች አራት ወይም አምስት ሪጋ (Blocks) ሊያሳርፍ ከሚችል ቦታ ያነሰ የቆዳ ስፋት ባላቸው ትናንሽ መንደሮች ውስጥ እየኖሩ ይህን ተዓምር ፈጠሩ፡፡
ታዲያ ወደ ኋላ ምን ሆነ?
ከክርስቶስ ልደት በፊት በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን፤ የመቄዶንያው ታላቁ እስክንድር፤ አያት - የቅድመ አያቱ ያኖሩለትን ወግ ሽሮ ዘመቻ ጀመረ፡፡ ዓለምንም ተቆጣጠረ፡፡ ጦርነቱን ብሎት ብሎት ሲሰለቸው፤ ኢዩር የግሪክ ሊቃውንት የሰጡትን የዕውቀት ፀጋ፤ ለጠቅላላው የሰው ዘር ማዳረስ አለብኝ አለ፡፡
ያን ድንቅ የዕውቀት አዝመራ፤ ከትናንሾቹ የግሪክ ከተሞች እና መንደሮች እየሸመጠጠ ወስዶ፤ አዲስ ባቀናው ግዛተ - አጼ (Empire) በሚገኙ የነገስታት መኖሪያዎች እየዘራ፤ ዘሩን ለማፅደቅ ታገለ፡፡
ታዲያ የለመዱትን ቤተ እምነታቸውን ለማየት ከማይችሉበት ሩቅ ስፍራ የሄዱት፤ አሳምረው የሚያውቁትን እና ጆሯቸው የለመደውን ድምጽ ከሚሰሙበት የሐገራቸው ጎዳና በጣም ርቀው የሄዱት ግሪኮች፤ ያን ልብ የሚፈነቅል ደስታቸውን አጡ፡፡ ጥንታዊ የከተማ መንግስቶቻቸውን ከሁሉ የላቀ ሆኖ እንዲታይ ለማድረግ ደፋ ቀና ሲሉ፤ የዕደ ጥበባቸው እና የአዕምሯቸው ውጤት የሆኑ ድንቅ ሥራዎቻቸውን ሲሰሩ ንቁ መንፈስ እንዲይዙ ያደረጋቸውን ነባር አስተሳሰብ በአንድ ጊዜ ጣሉት፡፡ ሲያልቅ አያምር እንዲሉ፤ ለትልቅነት ያበቃቸውን ያን አስተሳሰብ ሲተው፤ ግሪካውያን ቅራሬ በሆነ ሥራ (second- rate work) የሚረኩ፤ ውርዴ ዕደ ጥበባውያን (cheap artisans) ሆነው ቀሩ፡፡
የጥንታዊ ሔለናውያን ትናንሽ የከተማ መንግስታት ነፃነት ሲፈርስና፤ የአንድ ትልቅ ሐገር ቁራጭ አካል ክፍል እንዲሆኑ በተደረገ ማግስት፤ ጥንታዊው የግሪካውያን መንፈስ ሞተ፡፡ ያ ግሪካዊ መንፈስ፤ ከዚያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ሞቶ እንደ ተቀበረ ቀርቷል፡፡ ‹‹በነገርህ ሁሉ ምጥን ሁን›› የሚል ወርቃማ ህጓን የተወችው ግሪክ፤ ብድር አብዝታ ወስዳ በማጣጣር ላይ ትገኛለች፡፡ ከእነ አቴና ወይም ስፓርታ ጋር ስትነፃፀር ትልቅ ግዛት ያላት ቢሆንም፤ ትንሽ ሐገር ነች፡፡
ይህን የግሪክ ታሪክ ያወሳሁት፤ ‹‹እንዲያው ለጨዋታ›› ብዬ አይደለም፡፡ እንዲያውም ‹‹አስተምራለሁ›› ብዬ ነው። ‹‹ሁሉም ነገር በልክ›› ከማለት የበለጠ ምን ትምህርት ይኖራል፡፡

Read 1212 times