Saturday, 04 July 2015 10:36

ምጽአተ-ኢትዮጵያ መቼ ነው?

Written by  አብነት ስሜ
Rate this item
(15 votes)

ኢትዮጵያ ውስጥ መኪና፣ አውሮፕላን፣ ሮኬት፣ የኒኩለር ማበልፀጊያ አይሠራም አትበሉ። ዓለም እኮ
ብዙ አልቀደመችንም። ቢበዛ የሀምሳ ወይም የመቶ ዓመት እርምጃ ነው ከፊታችን ያለችው። ----

   ይህን አጭር መጣጥፍ ለመጻፍ ያነሳሳኝ ባለፈው እሁድ በኢቢሲ የመዝናኛ ፕሮግራም የተመለከትኩት በአንድ ኢትዮጵያዊ የተደረገ የመለስተኛ አውሮፕላን ሥራ ሙከራ ነው።
በብዙ የፈጠራ ሙከራዎች በተለይ ደግሞ በአውሮፕላን፣ በሮኬት እና በኒኩለር ማበልፀጊያ ሥራዎች የበርካታ ኢትዮጵያዊያን አመለካከት አይቻልም የሚል ነው። በዚህ ጐራ ውስጥ የሚመደቡት የተማሩ የሚባሉ ኢትዮጵያዊያን ጭምር መሆናቸው ደግሞ ሁሌም የሚያስገርመኝ ነገር ሆኖ ቆይቷል። ዘመን ይጥላል፤ ዘመን ያነሳል። ባንድ ወቅት ኢትዮጵያ ከሦስቱ የዓለም ኃያላን መንግሥታት አንዷ ነበረች። በአንድ ወቅትም ግብጽ ኃያል ነበረች። ፐርሺያም፣ ግሪክም፣ ሮማም በዘመናቸው ኃያል ነበሩ። እንግሊዝ፣ ፖርቱጋል እና ስፔን ኃያል ነበሩ። የአሜሪካ ኃያልነት አሁንም ለጥቂት ጊዜ ይቀጥላል። ከአሜሪካ ጐን ለጐን ጃፓን ወደ ታላቅነት ተሸጋግራለች። አሁን ደግሞ ቻይና ወደ አንደኛነት እየተንደረደረች ነው። የቻይና ታላቅነት ከአንድ መቶ ዓመታት ጀምሮ ሲተነበይ የቆየ ነው። የያኔ ነቢያት ራእይ እንደ ቅዠት ተወስዶ ነበር። አሁን ግን እውን ሆኗል። በቻይና የትልቅነት ትንቢት የተሳለቁ አሁን አፍረዋል።
የእሥራኤል ምጽአት እና ትልቅነት በየባህሉ ሲተነበይ ቆይቷል። በዓለም ካርታ ላይ እንኳ ምልክት ያልነበራት እሥራኤል አሁን አንቱ የተባለች አገር ሆናለች። አስትሮሎጂ ጥንታዊ እና ድንቅ የሆነ ጥበብ ነው። አንዳንዶች የሳይንስ ሁሉ አባት ነው ይሉታል። ይኸ የከዋክብት ሳይንስ የበርካታ ሀገራትን ውድቀትና እድገት ተንብዮአል።
የዛሬ አሥራ ሁለት ሺህ ዓመት (በአስር ሺህ ዓመተ ዓለም) ሊዮ ሀገሮች ተነስተዋል። እነ አትላንቲስን የመሰሉ አኳሪየስ ሀገሮች ጠፍተዋል። የዓለም ዐቢይ ሥልጣኔ የሚጀምረውና የሚያበቃው በአኳሪየስ ኮከብ ነው። በዓለም ላይ አኳሪየስ የሆኑ አገሮች ጥቂት ሲሆኑ በቁጥር ስድስት ናቸው። እነዚህም ራሺያ፣ ስዊድን፣ ፖላንድ፣ እሥራኤል፣ ፐርሺያ (ኢራን) እና ኢትዮጵያ ናቸው።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት ሦስቱ ሰብአሰገሎች (አስትሮሎጀርስ) የፖላንድ፣ የፐርሺያ እና የኢትዮጵያ ጠቢባን እንደሆኑ ይታመናል። ከስድስቱ አኳሪየሳዊ ሀገራት ውስጥ ሙሉ በሙሉ አኳሪየስ የሆኑት ፖላንድ እና ኢትዮጵያ ናቸው። ራሺያ ስኮርፒዮነት፣ እሥራኤል ስኮርፒዮነት እና ቶረስነት፣ ፐርሺያ ቶረስነት፣ ስዊድን ሳጁታሪየስነት የተጫናቸው ስለሆኑ መቶ በመቶ አኳሪየስ የሆኑ አገሮች አይደሉም። ፖላንድ እና ኢትዮጵያ የሚበላለጡት በአሁኑ ታላቅ የአኳሪየስ ዘመን ዋናው ተራ ወይም ጽዋ የኢትዮጵያ መሆኑ ብቻ ነው። በሚቀጥሉት መቶ ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ በዋናነት፣ ፖላንድ ደግሞ በተከታይነት የዓለም ቁንጮ እንደሚሆኑ ይጠበቃል። አሁን ኢትዮጵያ ላይ እናትኩር።
የኢትዮጵያ ኮከብ አኳሪየስ ነው። ይኸ እኔ እንኳን እስከማውቀው የዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት በፒቶሎሚ ቴትራቦሊስ የተመዘገበ ነው። በየጊዜውም የተነሱ ሰብአሰገሎች መዝግበውታል። በእኛ ዘንድ በጥቂቱ  ከዛሬ አስራ አራት ሺህ ዓመት በፊት ይታወቃል። በሀገራችን ዐውደነገሥትም ነገሩ ስለመታወቁ ፍንጮች አይቻለሁ።
ዘመንፈስ ቅዱስ አብርሃ ባጠናቀሩት ሐተታ መናፍስት ወዓውደነገሥት በመጨረሻው አስራ ሁለት ገፆች የአስራ ሁለት ሀገራት ኮከብ ተዘርዝሯል። ሮም ሐመል (ኤሪስ)፣ ቱርክ ሠውር (ቶረስ)፣ ምስር (ግብጽ) ገውዝ (ጄሚናይ)፣ ዠንዲ ሸርጣን (ካንሰር)፣ ካቤል አሰድ (ሊዮ)፣ ኤለለንጅ ሰንቡላ (ቪርጐ)፣ አልኸዠሬ ሚዛን (ሊብራ)፣ ህንድ ዓቅራብ (ስኮርፒዮ)፣ ሰገድ ቀውስ (ሳጁታሪየስ)፣ አልቡም ጀዲ (ካፕሪኮርን)፣ ሐቢሽ (ኢትዮጵያ) ደለዊ (አኳሪየስ)፣ እንግልጣር (እንግሊዝ) ደግሞ ፓይሰስ ተብላለች። እዚህ ላይ በተለይ ኢትዮጵያ በደለዊነት ወይም በአኳሪየስነት መጠቀሷን ልብ ይሏል።
አኳሪየስ የፈጠራ እና የፍጥረት መነሻ ነው። የሳይንስ ንፋስ ወዴትም ይንፈስ ወዴት ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መጀመሪያ የተፈጠረባት፣ የሥልጣኔ መሠረቶች ሁሉ የተጣሉባት አገር እንደሆነች አሁን ብዙም ጥርጥር ያለው ነገር አይደለም።
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የሴማዊ ቋንቋዎች ምንጭ መካከለኛው ምስራቅ ተደርጐ ሲወሰድ ቆይቷል። የሀገራችን መምህራንም ከፈረንጅ የሰሙትን እያስተጋቡ የኢትዮፒክ (ሳባ) ፊደል ከወደየመን እንደመጣ ሲናገሩና ሲጽፉ ቆይተዋል። የቅርብ ጊዜ ምርመራዎች ግን የፊደላቱም ሆነ የቋንቋው ምንጭ ኢትዮጵያ እንደሆነች በግልጽ አመላክተዋል።
በግልጽም ሆነ በስውር በተጻፉ መዛግብት ደግሞ የአስትሮሎጂ ሳይንስ ራሱ ከኢትዮጵያ እንደሆነ ተነግሯል። የሮኬት፣ የኒኩለር፣ የበረራ እና መሰል ዕውቀቶችም ምንጫቸው ኢትዮጵያ ነች። ይኸ መቼም ከንቱ ግብዝነት ነው የሚመስለው። እስከ አለፉት አስር ዓመታትም ድረስ የኔ አመለካከት እንደዚያ ነበር።
የመጽሐፍ ቅዱሱን ሙሴ ከኢትዮጵያ ጋር ማቆራኘት አጉል ጀብደኝነት አይደለም። ሙሴ የሀይማኖት መሪ ብቻ አልነበረም። ሙሴ የታላቅ ጥበብ ባለቤት የነበረ ኢትዮጵያዊ ነው። ከቃል ኪዳኑ ታቦት ጋር ተጣምሮ መላቅጡ ጠፋብን እንጂ ሙሴ ከኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን ከሌላ ዓለማት ጋር የሚነጋገርበት ቴክኖሎጂ (ራዲዮ) ሠርቷል። ይህ ራዲዮ የሳባ ንግሥት የተባለችው ኢትዮጵያዊት ወደ ኢትዮጵያ ይዛው ተመልሳለች። ይህ ልዩ ራዲዮ ከቃል ኪዳኑ ታቦት ጋር አንድ አይደለም። የቃል ኪዳኑ ታቦት የመጣው በሳባ ልጅ ነው። ቀዳማዊ ምኒልክ የሰለሞን ልጅ ነው የሚባለው መነሻው ልክ ቢሆንም መድረሻው ግን ተረት ነው። የሱ ታሪክ ሌላ ነው። [በመጪዎቹ ሠላሳ ዓመታት ውስጥ ይህ ምስጢር ይገለጣል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።] ሁሉ ነገር ከውጪ ካልመጣ ለምን ትልቅ እንደማይመስለን አይገባኝም። አሁን እንደሚመስለኝ ኢምፖርት የማናደርገው ፓትርያርክ ብቻ ሳይሆን አይቀርም።
የዓለም ጊዜ በአስራ ሁለት ታላላቅ ዘመናት (Great Ages) ይከፈላል። አንዱ ዙር በአማካይ ሀያ ስድስት ሺህ ዘመን ይወስዳል (ቀጥታ ቁጥሩን ለጊዜው እንተወው)። በዚህ ስሌት የአኳሪየስ ዘመን በ26ሺህ ዘመን ይከሰታል። በዚህ መሐል የአኳሪየስ ዋልታዊ ኮከብ የሆነው ሊዮ በ13ኛው ሺህ ይወጣል።
አኳሪየስ ታላቅ፣ ሊዮ ታናሽ ነው። በአኳሪየስ ዘመን የሚታይ ትንቢት በሊዮ ዘመን ከፊሉ ይወጣል። የዛሬ 12 ሺህ ዘመን ገደማ (10,000 ዓመተ ዓለም) በምድራችን ታይቶ የነበረው ታላቅ የሳይንስና ቴክኖሎጂ እመርታ በሊዮ ዘመን የሆነ ነው። በዚህ ጊዜ አሁን እንደ ተረት የምትጠቀሰው የአትላንቲስ አህጉር ከነሥልጣኔዋ ጠፍታለች። ከዚህችም አህጉር እየተቀነጨቡ የደረሱንን ጥበባት የቃረሙ ሊቃውንቶቻችንን እንደ ጠንቋይ እና አስማተኞች ስናይ ቆይተናል። በአሁኑ ዘመን እየታዩ ያሉ የሳይንስ እመርታዎች ሁሉ የአትላንቲስ ዘመን የሁለት በመቶ ያህል ብቻ ቅጂዎች ናቸው። ኢትዮጵያ እና አትላንቲስን ምን አገናኛቸው? ይህን በሌላ ጽሑፍ እመለስበታለሁ።
ዩራነስ የተባለው ፕላኔት የአኳሪየስ ኮከብ መሪ ሲሆን በሥርዓተ ፀሐይ ውስጥ ሰባተኛው የፀሐይ ጭፍራ ነው። ፕላኔቱ ለምዕራባዊያኑ ጠበብት መኖሩ የታወቀው እ.ኤ.አ በ 1781 ቢሆንም በኢትዮጵያውያን ዘንድ ግን ከዚያ ቀድሞ የሚታወቅ ነበር።
የዩራነስ የግኝት ዘመን ከአኳሪየስ ዘመን መቃረብ ጋር የተሰናሰለ ነበር። የርሱን መገኘት ተከትሎ የሳይንስ ዘመን (ኤጅ ኦቭ ሪዝን) ተበስሯል። ዓለም በብዙ ዓይነት አብዮታዊ (ድንገታዊ) ለውጦች ተጥለቅልቃለች።  የፈረንሳይ አብዮትና የሊዮው የናፖሊዮን ጦርነት የዚህ አካል ነበር። በዚህ ጊዜ የመጀመሪያው የኤሌክትሪክ ሳይንስ ሙከራ ተደረገ። የባሪያ ንግድ በህግ ተከለከለ። በዚህ ጉዳይ ዋናው ተዋናይ አኳሪየሱ አብርሃም ሊንከን ነበር። ከዚሁ የዩራነስ ግኝትና ግንነት በኋላ መሀውሮች (ሎኮሞቲቭስ) ተፈጠሩ። አውሮፕላን፣ ቴሌቪዥንና መሰል ፈጠራዎችም ተግተለተሉ። ከዩራነስ ግኝት  እና ግንነት በኋላ በኢትዮጵያ ምን ተስተዋለ? ወዲያው የተፈጠረው ነገር ውዥንብር ነበር። ይኸውም ዘመነ መሳፍንት  እየተባለ የሚታወቀው ጊዜ ነው። ይህ ዘመን ዩራነስ የፈጠረው ድንጋጤና ድንጋሬ ነው።  ሁሉም እየተነሳ እኔ ልንገስ አለ። ነገሩ አስፈላጊ ነበር። በዚሁ ዘመን ኢትዮጵያዊያን ከፍተኛ የሆነ ወደ ኋላ የመቅረት ቁጭት አድሮባቸዋል። ቁጭቱ የዕውቀት ጥማትን ፈጥሯል። በዘመኑ ከነበሩ ነገሥታት ውስጥ የዕውቀት ያለህ እያሉ የጮኹ አስተዋዮች ነበሩበት። ዘመነ መሳፍንት  በዐፄ ቴዎድሮስ መንገሥ ተጠቃለለ። ዐፄ ቴዎድሮስ በጥር ወር መጀመሪያ እንደተወለዱ ስለሚገለፅ ካፕሪኮርን እንበላቸው እንጂ በብዙ ነገረ-ሥራቸው ወደ አኳሪየስነት የተጠጉ መሪ ነበሩ። የሀገር ኮከብ በሦስት መንገድ ይሰየማል። አንዱ ባህሪን በማየት ነው። በዚህ አካሔድ ኢትዮጵያ አኳሪየስ እንደሆነች የፍካሬ ከዋክብት ጠቢባን እየመላለሱ ተናግረዋል። ሁለተኛው መልክዐምድራዊ ነው። በዚህ ልኬት ከነፒቶሎሚ ጀምሮ የኢትዮጵያ አኳሪየሳዊነት የታወቀ ነው። ሦስተኛው የምስረታ ጊዜ ነው። የኢትዮጵያን ቀዳሚ የልደት ቀን አሁን ለጊዜው ማስላቱ አስቸጋሪ ነው። ሌላ ተቀራራቢ ሥነ ዘዴ ግን አለ። ይኸውም የዳግም ልደት ይባላል። በዳግም ልደትም የኢትዮጵያ ኮከብ አኳሪየስ ነው።
የኢትዮጵያ የዳግም ልደት ቀን ዐፄ ቴዎድሮስ  የነገሡበት ዓመት፣ ወር፣ ቀን እና ሰዓት ነው። ይኸውም በአውሮፓውያን አቆጣጠር በ11 ፌብሯሪ 1955 ከጠዋቱ በ3 ሰዓት ከ20 ደቂቃ ላይ (9፡20 AM) በደብረታቦር (11 N 51 38 E 01) ነው። የዚህ ዝርዝር ለሌላ ጊዜ ይቆየን።
ዐፄ ቴዎድሮስ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ጉዳይ ምን ያህል ይቆረቁራቸው እንደነበር ሁላችንም የምናውቀው ነው። ቴዎድሮስ ያለጊዜያቸው የተነሱ መሪ ነበሩ እየተባለ ተደጋግሞ ይነገራል። እርግጥ የተነሱት በመነሻው ዘመን ነው። ችግሩ እሳቸው ተነስተው ህዝቡ ግን አልተነሳም ነበር። ህዝቡ ጋርዶበት ነበር። ይኸ ችግር አሁን ሳይብስበት አልቀረም [አሁንም የጋረደብን ነገር አለ]። ቴዎድሮስ የባርያን ንግድ ተቃውመዋል። ይኸ እንግዲህ ከአብርሃም ሊንከንም የቀደመ ነው። ቴዎድሮስ ሴባስቶፖል የተባለን መድፍም አሠርተው ነበር። ግን አልቀጠልንበትም። አሁን የያዝነው ፈሊጥ አይቻልም ነው። አሁን ስንት ሴባስቶፖል ሠርተን መደነቅ በነበረብን ጊዜ የድሮውን ሴባስቶፖል ብቻ እያመለክን እንገኛለን። ተክለሐዋርያት ከሞስኮብ እንደተመለሱ ዐፄ ምኒልክ ጋ ቀርበው መድፈኝነት እንደተማሩ ነገሯቸው። የንጉሡ ቀዳሚ ጥያቄ “አሁን መድፍን ኢትዮጵያ ውስጥ መስራት እንችላለን?” የሚል ነበር። ከዚያ በኋላ ግን የተጠናወተን አባዜ የመግዛትና በዚያም የመፎከር ነው። ከምንበላው ገምሰን፣ ከሥጋችን ቆርሰን እየሸጥን  አውሮፕላን፣ መኪና፣ ቴሌቪዥን፣ ራዲዮ፣ እርሳስ፣ ወረቀት፣ ኮምፒውተር፣ ሞባይል፣ ወዘተርፈ እንገዛለን።
ቴዎድሮስ ካለጊዜያቸው አልነበረም የተነሱት። በጊዜያቸው ነው። እኛ ግን አልነቃንም። የዓድዋ ድል አኳሪየሳዊት ኢትዮጵያ አይበገሬነቷን ያሳየችበት የአኳሪየስ ዘመን የንጋት ላይ ብስራት ነበር። እኔ የምፈራው ብኩርናችንን በምስር ወጥ እየሸጥን እንዳይሆን ነው። አሁንም ሌላ የዕድል በር እያንኳኳ ነው። የፕሉቶ ፕላኔት ከ2013 ጀምሮ ወደ አኳሪየስ ክምችት ይገባል። ይኸ ሌላው የመነሻ ጊዜ ነው።
ለሚቀጥሉት 30 ዓመታት ከፍ ያለ እመርታ እናስመዘግባለን። ለመጪዎቹ አንድ መቶ ዓመታትም ከዓለም ቁንጮ ሀገራት ቀዳሚ የመሆን ዕድላችን የተጻፈ ነው። እኔ እምፈራው ግን እሱንም ደግሞ ለመሰረዝ ትልቅ ላጲስ እንዳናዘጋጅ ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ መኪና፣ አውሮፕላን፣ ሮኬት፣ የኒኩለር ማበልፀጊያ አይሠራም አትበሉ። ዓለም እኮ ብዙ አልቀደመችንም። ቢበዛ የሀምሳ ወይም የመቶ ዓመት እርምጃ ነው ከፊታችን ያለችው። እድገቷም የጥቂት ግኝቶች ድግግም ነው።
ማጠቃለያ
በእሁድ መዝናኛ ፕሮግራም የታየው የአውሮፕላን ሥራ ሙከራ አስደስቶኛል። ያላሰብኩትን ያናገረኝ እሱ ነው። እመኑኝ እነዚህ ነገሮች ሀሉ ቀላል ናቸው። አይቻልም አትበሉ፤ ይቻላል። እሱማ ሌላስ ጋ ተችሎ የለም እንዴ ? አሁን ማምረቱ ነው እንጂ ይቻላል አይቻልም ማለቱ ሌላ ቁልቁለት መውረድ ይሆናል። ብታምኑም ባታምኑም፣ በሚቀጥሉት 30 ዓመታት ውስጥ ብዙ ትንግርት ያልሆነ ነገር ግን ትንግርት የሚመስል ነገር ይከሰታል። ዕድሜ ከሰጠን እናያለን። የቸኮልኩትም ለዚያ ነው እንጂ መሆኑማ የት ይቀራል!

Read 8213 times