Saturday, 04 July 2015 11:27

ኢትዮጵያ ሴካፋን ታዘጋጃለችቻንንም የማዘጋጀት እድል ይኖራታል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ኢትዮጵያ በ2015 መካሄድ ያለበትን 38ኛው ሴካፋ ሲኒዬር ቻሌንጅ ካፕን እንደምታስተናግድ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አስታወቀ፡፡  ፕሬዝደንቱ ጁነዲ ባሻ በግል የትዊተር ገፃቸው ባሰፈሩት ማስታወሻ ፌደሬሽኑ የሴካፋ ዋንጫን በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የክልል ከተሞች ለማዘጋጀት ማቀዱን አመልክተዋል። ለብሄራዊቡድኑ የአፍሪካ እና የቻን ማጣርያዎች ምቹ የሆነው ባህርዳር ስታድዬም ለሴካፋ ውድድር ማስተናገጃነት ቅድሚያ ከሚያገኙት ስታድዬሞች አንዱ መሆኑ በመነገር ላይ ነው፡፡ የ38ኛው ሴካፋ ሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ መስተንግዶ ከተሳካ  ኢትዮጵያ ለአራተኛ ግዜ ማዘጋጀቷ ይሆናል፡፡  በ1987 እኤአ ፣ በ2004 እና በ2006 እኤአ ኢትዮጵያ የሴካፋ ዋንጫን በተሳካ ሁኔታ እንዳዘጋጀች ይታወቃል፡፡ በሌላ በኩል የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት በ2020 እኤአ 5ኛውን የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ (ቻን) ውድድር ለማዘጋጀት እድል እንዳላትም ገልፀዋል፡፡ ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት መካሄድ የነበረበትን የ2014 ሴካፋ ሲኒዬር ቻሌንጅ ካፕ ለማዘጋጀት ተመርጣ የነበረ ቢሆንም ከኢቦላ ወረረሽኝ፤ በአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ውድድሮች መደራራብ እና በሌሎች ተያያዥ ችግሮች መስተንግዶውን እንደተወች የሚታወስ ነበር፡፡ የዘንድሮውን ሻምፒዮና ደግሞ ሩዋንዳ ለማዘጋጀት ከተመረጠች በኋላ በ2016 እኤአ ከምታካሂደው 4ኛው የቻን ውድድር ጋር በተያያዘ መስተንግዶውን ለማከናወን ያዳግተኛል በማለቷ ኢትዮጵያ በምትክነት ውድድሩን ለማስተናገድ እንደወሰነላት ታውቋል፡፡ ሴካፋ ሲነዬርስ ቻሌንጅ ካፕ ባለፈው የውድድር ዘመን ኢትዮጵያ ከመስተንግዶ ራሷን በማግለሏ ሳይካሄድ የቀረ ሲሆን ከሁለት ዓመት በፊት ሻምፒዮናው ለ37ኛ ጊዜ በኬንያ አስተናጋጅነት በተካሄደበት ወቅት ኬንያ 2ለ0 በሆነ ውጤት ሱዳንን በማሸነፍ ሻምፒዮን ሆናለች፡፡
የሴካፋ ምክር ቤት 12 አባል አገራት ያሉት ሲሆን እነሱም ብሩንዲ፤ ጅቡቲ፤ ኤርትራ፤ ኢትዮጵያ፤ ኬንያ፤ ሩዋንዳ፤ ሶማሊያ፤ ደቡብ ሱዳን፤ሱዳን፤ ታንዛኒያ ኡጋንዳ እና ዛንዚባር ናቸው፡፡  ምክር ቤቱ በየውድድር ዘመኑ 5 ውድድሮች የሚያካሂድ ሲሆን እነሱም ሴካፋ ሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ፤ ሴካፋ ካጋሜ ካፕ፤ ሴካፋ ናይልቤዚን ካፕ፤ እንዲሁም የሴካፋ ሀ17 እና ሀ 20 ውድድሮችን ናቸው፡፡
በሴካፋ ሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ የወቅቱ ሻምፒዮን በ2013 እኤአ ላይ ያዘጋጀችውን ዋንጫ ያሸነፈችው እና በአጠቃላይ 6 ጊዜ ያሸነፈችው ኬንያ ናት፡፡ ኡጋንዳ ለ13 ጊዜያት የዞኑ ሻምፒዮን በመሆን ከፍተኛውን ውጤት ይዛለች፡፡ ኢትዮጵያ በ18 ሴካፋ ሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ  የተሳትፎ ታሪኳ 4 ጊዜ ሻምፒዮን፤ 1 ጊዜ 3ኛ ደረጃ እንዲሁም 2 ጊዜ አራተኛ ደረጃ በማግኘት ከኡጋንዳ እና ኬንያ በመቀጠል በክፈተኛ ውጤት ሶስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡

Read 1272 times