Saturday, 11 July 2015 11:59

ልማታዊ መንግስታችን መፍታት ይልመድበት!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(13 votes)
  • ስንት ወላጅ፣ስንት ቤተሰብ፣ስንት ጓደኛ፣ስንቱ --- ተደሰተ!?
  •  በዚህ ሳምንት ብቻ 15 ወጣት ታሳሪዎች ከእስር ነጻ ወጥተዋል

    በዘንድሮ ምርጫ የሚዲያ ቅስቀሳ ላይ ኢዴፓ በEBC “ሳንሱር ተደርጐ” (በአዋጅ ከቀረ እኮ ዘመናት አልፈዋል!) ሳይተላለፍ ቀረብኝ ያለው አንድ የቅስቀሳ መልዕክት ባስታወስኩት ቁጥር ግርም ይለኛል። ለምን ይገርመኛል? ባለመተላለፉ! ብቻ ግን አይደለም፤ ምክንያቱ ባለመታወቁም ጭምር ነው። ይታያችሁ…ኢዴፓ መንግስት ሆኜ ከተመረጥኩ አለ በ if clause… “መንግሥት ሆኜ ከተመረጥኩ --- የፖለቲካ እስረኞችን በሙሉ እፈታለሁ”  ጉዳዩ የሚመለከታቸው የEBC ሃላፊዎች (ኢህአዴግም መንግስትም አያደርጉትም ባይ ነኝ!) ይሄ በሚዲያ መተላለፍ አይችልም ብለው ተፈጠሙ፡፡ (የደርግ “ሳንሱር” ያገረሸበት ኃላፊ እንደሚኖር ጠርጥሩ!) መፍትሔው ምን ቢሆን ጥሩ ነው? “ተስተካክሎ ይምጣ!” እግዜር ያሳያችሁ…ምኞት እንዴት ሆኖ ይስተካከላል! (የሆኖ ሆኖ የኢዴፓ ምኞት ሳንሱር ተደረገበት!)
እውነቱን ልንገራችሁ አይደል… መልዕክቱ ሊስተካከል የሚችለው እኮ፤ “ኢዴፓ መንግስት ሆኖ ከተመረጠ የፖለቲካ እስረኞችን በሙሉ ከእስር አይፈታም” በሚል ተቃራኒ ሃሳብ ብቻ ነው፡፡ (ሌላ መላ የለውማ!) እናላችሁ---ነገርዬው ግራ የሚያጋባ ነበር (እንኳን ለባለቤቱ ለ “ኢዴፓ” ለእኛም ጭምር!) ደግነቱ ግን የማያልፍ የለም---- ሁሉም አለፈ፡፡ (“እንዳያልፉት የለም ያ ሁሉ ታለፈ” አለ ብአዴን!) የምርጫ ቅስቀሳውም… የቦርዱ ማስፈራሪያም…የፓርቲዎች መዘላለፍም… የሰፊው ህዝብ  ፍርሃትም… የምርጫ ውጤቱም… ሁሉም ነገር ከሞላ ጐደል በሰላም ተጠናቋል - በምርጫ ቦርድ መግለጫ መሰረት፡፡
ወዳጆቼ፤ ይሄን ያለፈ የምርጫ ውዝግብ ያነሳሁት ጐዶሎአችንን ለማጉላትና ባለፈ ስህተት የEBCን ሃላፊዎች ለመውቀስ አስቤና አልሜ እንዳይመስላችሁ (ለነገሩማ ሥራዬ ተብሎ ሊወቀሱ ይገባቸው ነበር!) እኔ ጉዳዩን ለማንሳት ሰበብ የሆነኝ ግን ሰሞኑን የዞን 9 ሁለት ጦማሪያንና 3 ጋዜጠኞች (ከ1 ዓመት ከ 4 ወር እስር በኋላ መሆኑ ነው) ክሳቸው ተነስቶ ከእስር የመፈታታቸው ዜና ነው (ዜና ብቻ ያንስበታል ልበል!?) እስቲ አስቡት---በእኒህ ወጣቶች መፈታት ስንት ወላጆች ---- (በተለይ እናቶች!) በተስፋ ተሞልተው በደስታ እንደሚያነቡ? (እያነቡ እስክስታ አለ ቴዲ አፍሮ!!)
የሚገርመው ደግሞ ከወላጅም በላይ ብዙ ኢትዮጵያውያን በደስታ ጮቤ ረግጠዋል፡፡ (የልማታዊ መንግስታችን ግብም እኮ ለእኛ ሁለንተናዊ ደስታ ማጎናጸፍ ነው!) እናላችሁ --የመዲናዋ ድባብ ሁሉ ተቀይሮ ነው የሰነበተው፡፡ እኔ በበኩሌ---ከአንዳንድ ጭፍን የኢህአዴግ ካድሬዎች በቀር ለምን ተፈቱ በሚል ያጉረመረመ እንኳን አልገጠመኝም (ሰው ከእስር ሲፈታ ማጉረምረምማ ሰብዓዊነትም አይደለም!) እናላችሁ----መንግስት መፍታቱን እንዲለምድበት ጅምሩን እናድንቅለት፡፡ በነካ እጁ ታዲያ ቀሪዎቹንም ቢፈታቸው --- በቀጣዩ ምርጫ ድምጼን አሽረው ነበር፡፡ (ለነገሩ እኮ እንደ ኢህአዴግ ዕድሉን ላገኘ ያሰሩትን መፍታት ቢጠቅም እንጂ አይጎዳም!!)
በነገራችን ላይ በእነዚህ ወጣቶች መፈታት ያጉረመረሙ አንዳንድ “ፍሬሽ ካድሬዎች”ና ጭፍን ደጋፊዎችም ቀስ እያሉ መደሰታቸው አይቀርም። (እያፌዝኩ ከመሰላችሁ---በዚህ ፌዝ የለም!) ይሄውላችሁ----ልማታዊ መንግስታችን ልጆቹን በመፍታቱ አንድ ከባድ ዕዳ ከላዩ ላይ እንዳቃለለ ነው የምቆጥረው፡፡ (ማን ነበር “ሰነፍ መሪ ጭንቅላቱ ላይ ሸክም ያበዛል” ያለው?) እንዴት አትሉኝም? ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማትና ከጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ድርጅቶች የዘወትር ወቀሳ መጠነኛ እፎይታን ያገኛል፡፡ (ኢህአዴግ እፎይ ሲል ደግሞ አባላትና ደጋፊዎችም እፎይ ማለታቸው አይቀርም!)
እግረመንገዴን ግን ለኢህአዴግ በወዳጅነት የምለግሰው አንድ ምክር አለኝ፡፡ በፌስ ቡክ ላይ ፓርቲውን ደግፈው የሚጽፉ (የሚጽፉ የሚመስላቸው ቢባሉ ይሻላል!) “ፌስቡከሮች” ኢህአዴግ የመለመላቸው ከሆኑ ዳግም ምልመላውን መፈተሽ ሳይኖርበት አይቀርም፡፡ (ወይም መልማዮቹ መገምገም አለባቸው!) እንዴ----አብዛኞቹ እኮ እንኳንስ ሃሳብን በሃሳብ ሊመክቱ ቀርቶ ከማንበብና መፃፍ ደረጃ የዘለሉ አይመስሉም፡፡ ከምሬ እኮ ነው…የአስተሳሰብ ብስለትና ምጥቀት በሉት…የማሳመን ክህሎትና የአፃፃፍ ችሎታ--- ሲያልፍም አይነካቸው። ብቸኛ ሃብታቸው ጭፍን ድጋፍ ብቻ ነው፡፡ (ከ7 ሚሊዮን በላይ ደጋፊ አለኝ የሚል ፓርቲ እንዴት ጥሩ አውጠንጣኝ መመልመል ያቅተዋል!)
ወደ ዋና አጀንዳችን ስንመለስ…ፋና ሬዲዮ “ራሳቸውን ጦማሪያን የሚሉት…” በሚል የገለጻቸውን ወጣቶች መንግስት መፍታቱ (ማንም ምንም ይበለው!) እኔ ከልማታዊ መንግስት የሚጠበቅ ሰናይ ተግባር ነው ባይ ነኝ፡፡
አንዳንድ “ፍሬሽ ካድሬዎች”ም ነገርዬውን ከአገር ገጽ ግንባታ አንፃር ቢያዩት ነው የሚበጃቸው። (የአገር ገጽ በወሬ አይገነባም!) ዳያስፖራው የኦባማን የኢትዮጵያ ጉብኝት የሚቃወመው ለምንድነው? እነ ዋሺንግተን ፖስት ጉብኝቱን ያብጠለጠሉት በምን ሰበብ ነው? ፖለቲከኞች---ብሎገሮችና ጋዜጠኞች ያለአግባብ ታስረዋል----ገዢው ፓርቲ ምርጫውን በ100 ፐርሰንት ጠቅሎ ወሰደው--(ይሄ እንኳን ከአቅም በላይ ነው!) ወዘተ እያሉ አይደለም እንዴ? እናም መንግስት ልብ ገዝቶ የታሰሩትን ሲፈታ ማበረታታት እንጂ ማጉረምረም አይበጅም፡፡ ይልቅስ የቀሩትንም እንዲፈታ መገፋፋት ነው የሚገባው። (ለነገሩ ጥቅሙን እያየው ሲመጣ ማንም ሳይለው መፍታቱ አይቀርም!) ጥቅሙን ስላችሁ ደግሞ ሌላ ማለቴ እንዳይመስላችሁ፡፡ የህዝቡ መንፈስ ሲቀየር… የዓለምአቀፍ ሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ወቀሳና ጩኸት ሲቀንስ… በጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች እስርና ወከባ ዙሪያ የሚሰነዘረው ክስና ስሞታ ሲበርድ እንዲሁም በምትኩ ምስጋናና ውዳሴ ሲዘንብለት… ኢህአዴግ ራሱ በዓመት ሁለት ሦስቴ እስረኞችን መፍታት እንደሚጀምር እገምታለሁ፡፡ (መገመት መብት ነው!)
በእርግጥ ኢዴፓ በምርጫ ቅስቀሳው ላይ እንዳለው፤ የፖለቲካ እስረኞችን በሙሉ በአንዴ አይፈታ ይሆናል (አገር መምራትና የምርጫ ቅስቀሳ ለየቅል ናቸው!) ግን አንዳንዶች እንደሚሉት…እኚህ ባራክ ኦባማ መለስ ቀለስ ካሉ፣ ቀስ እያለ መፍታቱ አይቀርም (ፈርቶ እኮ አይደለም!) ኦባማ የዲሞክራሲ እናት የምትባለው የአገረ አሜሪካ ፕሬዚዳንት በመሆናቸው ለክብራቸው ሲል ብቻ ያደርገዋል፡፡  በሌላ አነጋገር ለዲሞክራሲ ካለው ጥልቅ ክብር የተነሳ “የፖለቲካ እስረኞች”ን በሙሉ አንድ ቀን ፈትቶ፣ ወህኒ ቤቶቹን ኦና ባያደርገው ምን አለ በሉኝ፡፡ እንዴ…ኢህአዴግ ዕድሜ ዘመኑን የታገለው ሰዎች በፖለቲካ አመለካከታቸው የተነሳ እስር፣ ወከባ፣ ስደት፣ መገለል እንዳይደርስባቸውና በነፃነት ያሻቸውን የፖለቲካ ሃሳብ እንዲያንሸራሽሩ፣መብታቸውም ሙሉ በሙሉ እንዲከበርላቸው እኮ ነው፡፡ ግን ምን ያድርግ? ሥልጣን ላይ ሆኖ ሲያየው ጉዳዩ ሌላ ሆነበት፡፡ እንጂማ የኦባማ መምጣትም ባላስፈለገው ነበር፡፡ (የሆኖ ሆኖ ግን ኦባማ እግራቸው እርጥብ ነው!) አንዴ ሳይሆን ሺ ጊዜ ይምጡልን!!
እናላችሁ… አንዳንዶች መንግስት ብሎገሮቹንና ጋዜጠኞቹን የፈታው ኦባማ ስለሚመጡ ነው (“The Obama Effect?” የሚል ስያሜ ሁሉ አውጥተውለታል!) ብለው ሲመፃደቁ ሰምቼ ተገርሜአለሁ፡፡ (ኦባማ ባይሆኑ ኖሮ፣ ነጭ አምላኪዎች ልላቸው ከጅሎኝ ነበር!)
እኔ ግን ኦባማ ሰበብ ሆኑ እንጂ ዋናው የልማታዊ መንግስታችን ልበ -ቀናነት ነው ባይ ነኝ። የለም ኦባማ ናቸው ያስፈቱት ብሎ የሚፈጠም ካለ ግን ይሁንለት፤ደስ ይበለው! (መቻቻል እኮ ሌላ አይደለም!)
በነገራችን ላይ ከአገር ውስጥ ተቃዋሚዎች ያስደሰቱኝ----ኦባማ እንዲያነጋግረን እንፈልጋለን ብለው ለአሜሪካ ኤምባሲ በደብዳቤ የጠየቁት ናቸው (ፕራግማቲክ ይሏችኋል እንዲህ ነው!) እንዴ…! ምንስ ቢሆን እንደነ ዋሺንግተን ፖስት ኦባማን ወደ ጦቢያ ድርሽ እንዳይሉ ማብጠልጠል ከኢትዮጵያዊ ይጠበቃል እንዴ? ይልቁንስ በአካል መጥተው ልማቱንም --ባቡሩንም--ቤተመንግስቱንም---ወህኒቤቱንም-----ተቃዋሚውንም---የመንግስት ባለስልጣናቱንም--ሚዲያውንም---- ጐብኘት ጐብኘት አድርገው ቢመክሩን አይሻልም?  በነገራችን ላይ ኦባማ  በተቃውሞ ሰልፍና በጋዜጣ ነቀፋ የሚመሩ ቢሆን ኖሮ እግራቸውን ከዋይት ሃውስ አያነሱም ነበር፡፡ (ማን ነበር “ከኢያሪኮ ውጭ በጩኸት የፈረሰች ከተማ አናውቅም” ያለው?)

Read 4876 times