Saturday, 11 July 2015 12:19

አዲሱ የተጨዋቾች የዝውውር መመርያ ያለስምምነት ተግባራዊ መሆን ጀምሯል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

    አዲሱ የተጨዋቾች ደረጃና የዝውውር መመሪያ ባለድርሻ አካላትን ሳያስማማ ተግባራዊ መሆን ጀምሯል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አፅድቄዋለሁ የሚለውን ይህ መመርያ ከሐምሌ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ሕጋዊ ሰነድ ሆኖ እንደሚቀጥል ገልፆ እየሰራበት ነው።  ከመመርያው ተግባራዊነት በፊት ተጨማሪ ውይይት እንደሚያስፈልግ የተጨዋቾች ተወካዮች  በደብዳቤ ቢጠይቁም ምላሽ አልተሰጣቸውም፡፡ ለፕሪሚዬር ሊግ  ክለቦችም የመመርያው አፈፃፀም በቀጣዩ የውድድር ዘመን በሚኖራቸው ዝግጅት  ላይ እንቅፋት እየሆነባቸውም ይገኛል፡፡
መመርያው ተግባራዊ ከመሆኑ 1  ሳምንት ቀደም ብሎ በክለቦች መካከል የተፈጠሩ ውዝግቦች ነበሩ፡፡ ይህን ተከትሎ የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በመመርያው ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ላይ ለመነጋገር ስብሰባ ቢቀመጡም ሳይስማሙ እንደተለያዩ ተነግሯል፡፡
መመርያው ተጨዋቾችንና ቀጣሪዎቻችንን በዋናነት ይመለከታል በማለት የተጨዋቾች ማህበር ተወካዮች ያቀረቡት  ግልፅ ደብዳቤ ትኩረት ስለተነፈገው  ቅር ተሰኝተዋል፡፡  ተጨዋቾቹ በመመርያው የሚመክሩበት ጊዜ እንዲሰጣቸው ፣ በአገሪቱ የአሠሪና ሠራተኛ ውል መሠረት በሁለት ባለጉዳዮች መካከል በሚደረገው ስምምነት ሦስተኛ ወገን እንደማያስፈልግ፣ የክፍያውን መጠንና የአከፋፈሉ ሒደትን በተመለከተም በሁለቱ ባለጉዳዮች ስምምነት የሚወሰን እንጂ በሦስተኛ ወገን ወይም ፌዴሬሽን ሊሆን እንደማይገባ በመጠቃቀስ መስተካከል ስላለባቸው አንቀፆች እንነጋገር ብለው ነበር።   በተለይ ሰኔ 30 ከሆነ በኋላ በሁሉም የፕሪሚዬር ሊግ ተወዳዳሪ ክለቦች    ብዙ ተጨዋቾች ኮንትራታቸው ስለተጠናቀቀ ክፍት በሆነው የዝውውር ገበያ ውላቸውን ለማደስም ሆነ ክለብ ለመቀየር  በፊርማ ክፍያ በተፈጠሩ አለመግባባቶች እየተስተጓጎለ ይገኛል፡
በተለይ በመመርያው እያንዳንዱ ክለብ በስብስቡ ሊኖረው የሚገባን የውጭ ተጫዋቾችን በተመለከተ ቁጥሩ ከአምስት ወደ ሦስት ዝቅ እንዲል መባሉ እና የፊርማ ክፍያ የሚለው አሰራር ተቀይሮ ተጨዋቾች በደሞዝ አገልግሎት እንዲሰጡ በመመርያው መደንገጉ በቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብና በተጨዋቾች ማህበር ተቀባይነት አልነበራቸውም፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ የውጭ ተጨዋቾችን ለመገደብ ደንብ ያስፈለገው ለአገር ውስጥ እግር ኳስ ተጫዋቾች የተሻለ ትኩረት መስጠት ያስችላል ብሏል፡፡  የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ሃላፊዎች በበኩላቸው የውጪ አገር ተጫዋቾች ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ያሉትን ጠቀሜታዎች በመዘርዘር ለማስረዳት ሙከራ አድርገዋል፡፡ የውጭ አገር ተጨዋቾች በክለብ ስብስብ መካተታቸው የአገር ውስጥ ተጨዋቾችን በተፎካካሪነት ጎልተው እንዲወጡ እንደሚያደርግና የፕሮፌሽናልነት ዕድል እንዲፈጠርላቸው ያደርጋል የሚሉ ማስረጃዎችንም ገልፀዋል፡፡ ባለፈው የውድድር ዘመን በኢትዮጵያ ለመጫወት ከአፍሪካ 6 አገራት የተውጣጡ ከ26 በላይ ተጨዋቾች በ7 ክለቦች በመቀጠር ህጋዊ እውቅና በማግኘት ለመጫወት ችለው ነበር፡፡ የውድድር ዘመኑ ከመጀመሩ በፊት የእግር ኳስ ፌደሬሽን ይፋ አድርጎት በነበረው ዝርዝር መሰረት በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ሲጫወቱ የነበሩት 26 የሌላ አገር ተጨዋቾች 8 ከካሜሮን፤ 7 ከናይጄርያ፤ 6 ከጋና፤ 3 ከኡጋንዳ እንዲሁም ከኬንያ እና ከደቡብ አፍሪካ የመጡ ናቸው፡፡ ከ26ቱ የሌላ አገር ተጨዋቾች ጊዮርጊስ 7፤ ኤልፓ እና ሀረር ቢራ እያንዳንዳቸው 5፤ ደደቢት 4፤ ኢትዮጵያ ቡና እና ድሬዳዋ ከነማ እያንዳንዳቸው 2 እንዲሁም ኒያላ ለ1 ተጨዋች ቅጥር ፈፅመው በፌደሬሽኑ የእውቅና ማረጋገጫ የውድድር ዘመኑን አሳልፈዋል፡፡
በኢትዮጵያ እግር ኳስ የተጨዋቾች ዝውውር ገበያ እየተሟሟቀ የመጣው በተለይ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ነው፡፡ በተለይ የፊርማ ክፍያ ከተባለው አሰራር ጋር ተጨዋቾች ከፍተኛ ጥቅም እያገኙ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ የዝውውር ገበያ ካለፈው 4 ዓመት ወዲህ በ50ሺ ብር የፊርማ ክፍያ ተጀምሮ፤ ወደ 100ሺ ብር ከዚያም ወደ 200ሺ ብር፤ 300ሺብር በአማካይ ወደ 500 ሺ ብር ደርሷል፡፡
የተጨዋቾች ደረጃና የዝውውር መመርያ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ባቀረበው ጥያቄ በተለይም የመመርያው ዋና ተዋንያን ተብለው በሚጠቀሱት ተጨዋቾች ባቀረቡት ግልፅ ደብዳቤ ሳይፀድቅ ለውይይት በድጋሚ ይቀርባል የሚለው ተስፋ ባለመሳካቱ  ሁኔታዎች የተድበሰበሱ መስሏል፡፡   የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ይፋ ባደረገው መግለጫ ከሐምሌ 1 ቀን 2007 ዓ.ም የመመሪያው ተግባራዊነት እንደሚጀመር አረጋግጦ፤ መመሪያው እንደተሻሻለ ወይም ተግባራዊ እንደማይሆን ከአንዳንድ ወገኖች እየተሠነዘረ የሚገኘው አስተያየት መሠረተ ቢስ ብሎታል፡፡ በመመርያው  የአፈጻጸም ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን መሰረት በማድረግ በየጊዜው በሚደረግ ፍተሻ የማሻሻያ እርምጃዎች እንደሚወሰድ የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አቋም መሆኑን ያመለከተው የፌደሬሽኑ መግለጫ፤  በቀጣይነትም መመሪያውን በተመለከተ ከተለያዩ አካላት የሚቀርቡትን ገንቢ አስተያየቶች ፌዴሬሽኑ እየተቀበለና እያጤነ በማሻሻል አስፈላጊውን መግለጫ የሚሰጥ መሆኑ እንዲታወቅ መመሪያውን በተመለከተ የተለወጠ ወይም የተሻሻለ ሁኔታ ባለመኖሩ ተግባራዊነቱ የሚቀጥል መሆኑን አሳስቧል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን  በአገሪቱ የሚፈፀመው የእግር ኳስ ተጨዋቾች ደረጃና ዝውውር በሕግና በሥርዓት እንዲመራ ባለው ፍላጎት መፅናቱን አረጋግጧል፡፡ መመርያው በፊፋ ዝቅተኛውን የተጨዋቾች ደረጃና ዝውውር መስፈርት ያሟላ እንዲሆን፣ በተጨማሪም አሠራሩ በሕጋዊ ወኪል እንዲመራና ሒደቱም ተጨዋቾችን፣ ክለቦችንና መንግሥትን ተጠቃሚ በማድረግ ለአገሪቱ የእግር ኳስ ዕድገት መፋጠን የራሱን አወንታዊ ሚና እንዲጫወት ይፈለጋልም ተብሏል፡፡
በኢትዮጵያ ከተጨዋቾች ዝውውር ጋር ተያይዞ እየተሠራበት የነበረው አሠራር ለአገሪቱ እግር ኳስም ሆነ ለክለቦች፣ ተጨዋቾችና መንግሥት ምንም ዓይነት ጥቅም እንዳላስገኘ የሚገልፀው ፌደሬሽኑ፤ የዝውውር ሂደቱ የክለቦችን የፋይናንስ አቅም ማዳከሙን፤ ለተጨዋቾችም እንደተከፈለ የሚነገረው ገንዘብ ሙሉ በሙሉ እንደማይደርሳቸው፤ ህገወጥ የዝውውር ደላሎች እንደበዙበት፤  በፕሮፌሽናል ስም የሚመጡት ብዙዎቹ ተጨዋቾች የችሎታቸው ጉዳይ ጥያቄ እንደሚያስነሳ፤ ተጨዋቾች ከደመወዝ ይልቅ ትኩረት ሰጥተው የሚከራከሩት ለፊርማ ተብሎ ስለሚሰጣቸው ገንዘብ መሆኑ፣ ገንዘቡን ከወሰዱ በኋላ ለክለባቸው ተገቢውን አገልግሎት እንደማይሰጡ፣  ክለቦች ታዳጊዎችን አሳድገው ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም በማሳጣቱ፣ አዲሱ ደንብ ተግባራዊ መሆኑ ይህን እነዚህን ችግሮች ለማስተካከል መፍትሄ እንደሚያመጣ በዝርዝር አብራርቷል፡፡

Read 1470 times