Saturday, 18 July 2015 10:44

“የዳኛቸው ሀሳቦች” እንደ ምክንያት

Written by  አስራት አብርሃም
Rate this item
(3 votes)

ዛፍ አይቆርጥም አሉ!፤ እግዚሄር ሲቆጣ፤
“Selfless” ያልነው ሰው፥ ሰልፍ… ይዞ መጣ።

ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ እድሜውንና የእውቀት ደረጃውን በማይመጥን ሁኔታ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ፣ በቁም ነገር መፅሔት፣ እና በመሳሰሉት ሚዲያዎች ላይ ተገቢ ባልሆነ መንገድ ጥላሸት ሊቀባኝ ሞክሯል፤ እንግዲህ እርሱ እንደፈለገ እንዲናገር ሌላው ደግሞ ዝም እንዲል የሚፈቅድ ዓለማዊ ይሁን ኃይማኖታዊ፤ ሞራላዊ ይሁን ህጋዊ ማቀፍ የለምና፤  ተገቢ በሆነ ሁኔታ የጉዳዩን ትክክለኛ ገፅታ በማሳየት እውነቱን አስረዳለሁ።ከሁሉም በላይ የሚገርመው ነገር ደግሞ በዚህ መሰረተ ቢስ ውንጀላው ላይ “አስራትና ጓደኞቹ፣
አስራትና ሌሎች ተማሪዎቼ” እያለ የሌሎቹን በድፍኑ ሲያልፈው፣ የእኔን ስም ግን ከሃያ ጊዜ በላይ ማንሳቱ ነው። እሱ እንደሚለው ከዚህ መፅሐፍ ጀርባ ሊኖሩ ይችላሉ ብሎ ያሰባቸው ሌሎች ሰዎች በስማቸው ያልጠቀሰበት የራሱ የሆነ ምክንያት ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ አንድም እኔ ላይ የሚለውን ያህል የሌሎች ስም ቢጠቅስ የሚመለስለትን የአፀፋ መልስ ስለሚያውቅ ሊሆን ይችላል፤ አንድም ደግሞ እኔ በሚዲያው አካባቢ አዲስ ሰው ስላልሆንኩ፣ የእኔን ስም ደጋግሞ ሲያነሳ እኔን የጎዳ መስሎት ሊሆን ይችላል፤ ወይም የእሱን ስም ባጠፋ ማንም ምንም አይለኝም፤ የሚቆረቆርለት ወገን የሌለው፤ ከመንግስትም የተጣላ፤ ብቻውን የሆነ ሰው ነው ብሎ አስቦ ሊሆን ይችላል፤ ለእኔ ከፍትሀዊነትና ከሰብዕና መውደቅ ማለት ይሄ ነው።
ለመሆኑ ከመሀመድ ሀሰን ጀርባ አሉ የሚላቸው ሰዎች ስንት ናቸው?! ለምሳሌ “አስራት ጓደኞቹ ወይም አስራትና ሌሎች ተማሪዎቼ” ሲል ከተማሪዎቹ ስንቶቹን ነው በዚህ ስራ ላይ እየወነጀላቸው ያለው?! ለእኔ በጣም የሚገርም ነገር ነው። “በዙሪያዬ ያለው ሰው ሁሉ ከጀርባ ያሴርብኛል” ዓይነት አስተሳሰብ የሆነ ህመም ምልክት ነው የሚመስለኝ ለመሆኑ ይሄ የመሀመድ ሀሰን መፅሀፍ ምን ተአምር ስለያዘ ነው ይሄ ሁሉ ሰው ከጀርባ ሊሰፍለት የሚችለው?! ለእኔ እንቆቅልሽ የሆነብኝ ነገር ይሄ ነው። እሱ እንግዲህ ከገንዘብ ማጋበስ ጋር ነው ሊያያይዘው የሚሞክረው፤ ነገር ግን እሱ እንደሚለው ብዙ ሰዎች ከዚህ ጀርባ ካሉ ነገሩ ገንዘብ ፍለጋ ብቻ ይሆናል የሚያስብል አይደለም፤ ለምሳሌ ከዚህ መፅሐፍ ምን ያህል ጥቅም ነው ሊገኝ የሚችለው?! የሚለውን ማየት ይቻላል፤ ዶ/ር ዳኛቸው ከመፅሐፍ ሽያጭ ገንዘብ ማጋበስ የሚቻል ከመሰለው ምናልባት እስካሁን መፅሐፍ አሳትሞ ስለማያውቅ ሊሆን ይችላል፤ ቢያንስ ግን ከወረቀት መወደድ ጋር ተያይዞ የማተሚያ ቤት ወጪው በአጠቃላይ ከመፅሐፍ ህትመት የሚገኘው ጥቅም ያን ያህል የማዩጓጓ አለመሆኑን መረዳት መቻል ነበረበት! ለምሳሌ እኔ አራት መፅሐፍ አሳትሜያለሁ፤ አንዳንዶቹ እስከ አምስት ጊዜ ታትመዋል፡፡ ለምሳሌ “ከሀገር በስተጀርባ” አምስት ጊዜ ነው የታተመው፣ “ጎበዝ ተማሪ የመሆን ሚስጥር” ሶስት ጊዜ ታትሟል፤ “መለስ እና ግብፅ” ሁለት ጊዜ ታትሟል፤ ነገር ግን ከዚህ ሁሉ ያገኘሁት ነገር በጣም ትንሽ ነው። የእለት ጉርስ ከመሸፈን ውጪ የተረፈኝ ነገር የለም፤ ከዚህ መረዳት የሚቻለው የመሀመድ ሀሰን መፅሐፍ ከጀርባ አሉበት እየተባሉ ያሉት ሰዎች ለገንዘብ ብለው ነው የሚለው
አነጋገር አሳማኝ አይደለም፤ እውነት እንዲመስል ሴራውን ከፍ ማድረግ ነበረበት፤ አለበዚያ ውንጀላው ውሀ የሚያነሳ አይሆንም። እኔ መፅሐፉን ማከፋፈሌ ዳኛቸው ከሚለው ነገር ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም፤ መፅሐፉ ችግር ካለው ከፀሐፊው ጋር ነው መጨረስ ያለበት፡፡ እርሱ አልፈልገውም፤ እኔ እምፈልገው ሌሎች ነው ካለ ደግሞ ይሄ ከመፅሐፉ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም። በአጠቃላይ የሚለው ሁሉ ከምክንያት የወጣ ነገር ነው፤ በዚህ አካሄድ ከሆነ መፅሐፉን የሚሸጡት መፃህፍት መደብሮችና አዟሪዎችም፣ ገዝተው ያነበቡትም ሁሉ መጠየቅ ሊኖርባቸው ነው ማለት ነው። እንግዲህ እንዲህ ዓይነቱ ህግ እስካሁን በዓለም ላይ የለም።ከዩኒቨርሲቲው ጋር ያለውን ፀብ ወደ እኛ ወደ ተማሪዎቹ ለማዞር የሄደበት መንገድ ስህተት ያለበት ነው፤ አህያውን ፈርቶ ዳውላውን ይላል ሀበሻ ሲተርት፤ ይሄም እንደዚያ ዓይነት ነው። ተማሪዎቼ አማካሪ ለምን ተቀየረላቸው ብሎ ከሆነ የተናደደው፤ እሱ ሌላ ነገር ነው፤ የሚያማክራቸው
ተማሪዎች ተመርቀው ስራ መያዝና ቤተሰባቸው መርዳት ስላለባቸው በእርሱ ምክንያት ቢጉላሉ
ተገቢ አይሆንም፤ ሲሆን ሲሆን የተሰጠውን ሀላፊነት መከታተል የነበረበት ራሱ ነው፡፡ ከስራ ሲታገድ ከእኔ ጋር ያሉት ተማሪዎች እንዴት ነው የሚሆኑት ብሎ ዲፓርትመንቱን መጠየቅ ነበረበት፤ እኔም በጊዜ ሊያሰናብተኝ ይገባ ነበር፤ በአስራ አንደኛው ሰዓት ስልክ ደውሎ አማካሪው አልሆንም ካለ በኋላ፤ መልሶ እኔኑ አልነገረኝም ብሎ ይወነጅለኛል፤ እኔ መረጃው ቢኖረኝማ ጨርሼ እመረቅ አልነበር! “ስለመፅሐፉ አልነገረኝም፤ መታገዱንም አልነገረኝም” ሲል ወሬ እንዳመላልስለት የቀጠረኝ እኮ ነው የሚመስለው።
 የገረመኝ ደግሞ በዚህ መፅሐፍ ላይ እጃቸው ያለበት ሰዎች አማካሪያቸው ብሆን ኖሮ አሳያቸው ነበር ዓይነት ንግግሩ ነው፤ ሲኮንነው የኖረው አንድ ሰው ያለውን ስልጣን ተጠቅሞ ሰው ላይ ጉዳት የማድረስ ወንጀል ራሱም እንደሚፈፅመው የሚያሳይ ነው፡፡ በአጠቃላይ እያነሳው ያለው ሀሳብ አሉሽ አሉሽ ላይ የተመሰረተ፤ የሰፈር ባልቴቶች ፀብ ነው የሚመስለው፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ ከምክንያታዊነትና ከምሁራዊነት አውጥቶ ተራ ወደ ሆነ አሉባልታ ስላወረደው ነው። በመሰረቱ የዶ/ር ዳኛቸው ፅሁፍ “እንዲህ እንትና ነገረኝ፤ እንትና እንዲህ አለኝ” ከሚል ውጪ አንድም የረባ የመከራከሪያ ነጥብ አላየሁበትም። የፈረንሳዩ ፈላስፋ ሬኔ ዴካርት እኮ የምናደንቀው የራሱን ሀሳብ ሳይቀር ትክክል ላይሆን ይችላል ብሎ ሀሳቦቹን ሁሉ ለመመርመር የተነሳ ሰው በመሆኑ ነው። እንዴት ይህን ፍልስፍና ሲያስተምርን የኖረን ሰው፣ ሰዎች የሚነግሩትን ሁሉ ሳይጠራጠር እንዳለ ተቀብሎ ያስተጋባል። አሁን ሆኜ ሳየው ይሄ መፅሐፍ ለዶ/ር ዳኛቸው ጥሩ ነገር ይዞለት የመጣ አይመስለኝም፤ ራሱን እንዲያዋርድ፤ ውስጣዊ ማንነቱ እንዲታይ በር የከፈተለት ይመስላል፡፡ ይሄ የሆነው ደግሞ ገንዘብ ስላጓጓው ይመስለኛል። መሀመድ ሀሰን እኮ ከእሱ ተሽሎ ተገኘ፤ ከመፅሐፉ ምንም አልፈልግም፤ ተሽጦ የሚገኘውን ትርፍ ሁሉ ላንተ ልስጥህ ብሎታል፤ እንግዲህ ይሄ ልጅ ምን እንዲያደርግለት ነው የሚፈልገው።ዶ/ር ዳኛቸው ለበድሉ የሰጠሁትን ተገቢ መልስ ሲተች፤ “አስራትና ጓደኞቹ ዶ/ር በድሉን የመሰለ ራሱን በምሁራዊ ግብር ያስመስከረ ሰው እንደ እኩያቸው በመቁጠር መዘባበቻ አደረጉት በማለት ኮንኗል። እኔ የምለው ራሱን በምሁራዊ ግብር ያስመሰከረ ሰው ስህተት ሲፈፅም፣ የሰው ስም አንስቶ ሲዘረጥጥ ዝም መባል አለበት ወይ?! እንዲህ ያለን ሀሰታዊ የስም ማጥፋት ዘመቻ ሲፈፅምብህ፣ ራስህን ለመከላከልና እውነታውን ለማስረዳት የግድ በእርሱ ደረጃ መገኘት ያስፈልጋል ወይ?! ቁም ነገሩ ራስን በምሁራዊ ደረጃ ማስመስከርና አለማስመስከር አይደለም፤ ቁም ነገሩ የአቋም፤ የመርህ፣ የሞራልና የእምነት ነው። አንድ ሰው የሚለካው ከዚህ አንፃር ነው እንጂ ካለበት የትምህርት እርከን አይደለም፤ የተማረ ሆኖ አድርባይነት የሚያጠቃው ከሆነ፤ ውሸታም ከሆነ በምንም መንገድ የሚከበር የሚታፈር ሰው ሊሆን አይችልም። ሌላው “ከዶ/ር በድሉ ጋር በእኩልነት ደረጃ መነጋገራችን በዩኒቨርሲቲው የእውቀት ዕርከን እየተደፈጠጠ የመጣበትን ኹኔታ ማሳያ ነው” ይላል፤ ይህ የእውቀት እርከን የተባለው ሀሳብ በራሱ ስሑት አገላለፅ ይመስለኛል፤ የትምህርት ደረጃ እርከን ነው ሊኖር የሚችለው፤ ጠቅላላ እውቀትን በሚመለከት አንድ ወጥ የሆነ የሆነ፣ ሁሉንም ሰው በአንድ የሚያቅፍ የእውቀት ደረጃና እርከን ያለ አይመስለኝም፡፡ ዶ/ር በድሉ በተማረው ትምህርት ከእኔ የተሻለ እውቀት ሊኖረው ይችል ይሆናል፤ እኔ በተማርኩት ትምህርት ደግሞ ከእርሱ የተሻለ እውቀት ሊኖረኝ ይችላል። በፍፁም ሁለት ሰዎች እኩል ሊሆኑ አይችሉም፤ የተለያየ እውቀትና ችሎታ ነው የሚኖራቸው። በመሰረቱ ዶ/ር ዳኛቸው አስራትና ጓደኞቹ የሚለው ዶ/ር በድሉ በእኔ ላይ ለሰነዘረው ሀሰተኛ ውንጀላ መልስ የሰጡ ሰዎችን ነው፤ የበድሉ እኩዮች አይደላችሁም የሚላቸው እንግዲህ በበድሉ ፅሁፍ ላይ አስተያየት የሰጠነው እኔ፣ ሰለሞን ስዩም እና ይባቤ ነን። ከበድሉ ጋር የማይተናነስ ወይም የተሻለ ስራና ስም ያለን ሰዎች ነን። እንዲያውም እኔ ራሴን ከበድሉ ጋር እኩል አድርጌ  አላይም፤ እንደዚያ ቢሆንማ ባንድ ኮሌጅ ውስጥ ተራ ሌክቸረር ሆኜ እቀር ነበር። ሌላው የገረመኝ የእሱን ውንጀላ ደግፈው የጻፉትን እንደፍትሃዊያንና ለእውነት ጥብቅና እንደቆሙ አድርጎ ሲያቀርባቸው፤ ተገቢ ካልሆነ ውንጀላ ራሳቸውን የተከላከሉና በሚመስላቸው መንገድ በጉዳዩ ላይ ሀሳብ የሰጡትን ደግሞ እንደ ጥራዝ ነጠቅ አድርጎ ሲያቀርባቸው ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ የእኔ ጓደኞች እንደሆኑ አድርጎ አቅርቧቸዋል። እንዲህ ዓይነቱ በአንድ ጉዳይ ላይ የተለያየ መለኪያ
(Double Standard) መያዝ መቼም ከአንድ የፍልስፍና እውቀት አለው ተብሎ ከሚታሰብ ሰው
የሚጠበቅ አይደለም። ለምሳሌ ሰለሞን ስዩም በአንድ ወቅት ከዶ/ር በድሉ ጋር በጋዜጣ ስለተመላለሱበት ጉዳይ የጋዜጣውን ስምና የወጣበትን ቀን ጠቅሶ፤ የበድሉ አቋም ምን እንደነበረ ለማሳየት በአባሪ መልክ በመፅሐፉ ውስጥ በማከታቱ ነው ዶ/ር በድሉ ከእኔ ጋር አያይዞ የፃፈበት፤ “የእኔን ፅሁፍ ከራሱ ጋር ጠርዞ አሳተመ” ብሎ የወነጀለው። ለዚህ ተራ ውንጀላ ተገቢ መልስ ሰጥቶታል፤ “የሚኮረጅ ነገር የለህም” ነገሩን ጠቅለል አድርጌ ሳየው ዘመቻው በመፅሐፉም ሆነ በአማካሪነቱ ጉዳይ አይመስለኝም፤ ይሄ ሁሉ ሽፋን ነው፤ የሌላ የሶስተኛ አካል ረጅም እጅ ያለበት መስሎ ነው የሚሰማኝ። በዚህ ሀገር ምንም ተደብቆ የሚቀር ነገር ስለሌለ ጊዜው ሲደርስ እውነታው ፍርጥርጥ ብሎ ይወጣል፤ ይሄ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ዛሬ ወዳጅ መስለው እያሳሳቱት ያሉት ሰዎች ነገ አጠገቡ እንደማይቆሙ የታወቀ ነው። እንግዲህ “ሰላም አስኗል፤ በዚህም ሊኮሩ ይገባል” ያላቸው ሰዎች (መቼም እሱ በሰላምና በፀጥታ መሀል ያለው ልዩነት ይጠፋዋል ብዬ አላስብም) አሁን ደግሞ ፍትህ አስፍኗል፤ እያለ ነውና ፍትህ ይስጡት፡፡ መሀመድ ሀሰንም ፍትህ ሲያጣ ያኔ እናያለን፡፡ መቼም ፍርድ ቤቱ የሁላችንም ነው፡፡




Read 2287 times