Saturday, 18 July 2015 11:48

ሀሳብ ወለድ የጉዞ ቅኝት “የቡና ቤት ሥዕሎች” እና ሌሎችንም ፍለጋ

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(1 Vote)

 ማለዳ የጀመረው ካፊያ ማቆሚያ ያለው አይመስልም፡፡ ዕለቱ የታዋቂው ወግ ፀሐፊ መስፍን ሀብተማርያምን አንደኛ ሙት ዓመት መታሰቢያ ለመዘከር በ“የጠፉትን ፈላጊ ፕሮሞሽን” አስተባባሪነት ከጊዮርጊስ ተነስቶ በፒያሣ አትክልት ተራ በኩል አልፎ፣ መርካቶ በመግባት ክፍለ ሀገር አውቶብስ ተራ ጋ የሚጠናቀቅ የእግር ጉዞ የተካሄደበት ነበር። በፕሮግራሙም  ከተለያዩ ተቋማት የተጋበዙ 30 ሰዎች ተሳትፈዋል፡፡
የባለፈው ማክሰኞ ካፊያና ቅዝቃዜ ከቤት መውጣት ባያስመኝም ባልተለመደ መልኩ የተጠሩት ተጋባዦች ሁሉ ጊዮርጊስ አደባባይ ተገኝተዋል፡፡ እንደውም ከጥሪው ሰዓት ቀድሞ እንጂ ዘግይቶ የደረሰ አንድም ሰው አልነበረም፡፡ የሚበዛው ሰው ዣንጥላ ይዟል፡፡ በአንገታቸው ዙሪያ ስካርቭ የጠመጠሙም ጥቂት አይደሉም፡፡ ባለ ኮፊያ ሻማ ጃኬትና ካፖርት የደረቡም ነበሩ፡፡
“የጠፉትን ፈላጊ ፕሮሞሽን” መስራችና የዝግጅቱ አስተባባሪ ወጣት ፈለቀ ጋሻው የጠራቸው እንግዶች በሙሉ ሰዓታቸውን አክብረው በመገኘታቸው የተሰማውን ደስታ ቃላት አውጥቶ ማመስገን ከመጀመሩም አስቀድሞ ፊቱ ላይ ይነበብ ነበር፡፡
“በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ብዙዎቻችን እንተዋወቃለን ብዬ ስለምገምት እርስ በእርስ በማስተዋወቅ ጊዜያችሁን አላጠፋም፡፡ በጉዟችን  ላይ ገለፃ የሚያደርጉልን ሰዎች ተመርጠዋል፡፡ የማንተዋወቅ ካለን በዚህ አጋጣሚ እንተዋወቃለን፡፡ ይህንን ዝግጅት ለማሰናዳት ምክንያት የሆነኝ የደራሲና ወግ ፀሐፊው ጋሽ መስፍን ሀብተማርያምን መዘከሪያ ማዘጋጀት ቢሆንም የታዋቂው ደራሲያችን መዘከሪያ መድረክ ላይ ሌሎችንም ለማስታወስ ስለፈለኩ፤ ሀሳቡን ያቀረብኩላቸው አካላትም ስለተስማሙበት ነው ዛሬ በጠዋት እዚህ የተሰባሰብነው፡፡”
የዕለቱ መርሐ ግብር ከጥንታዊት ኢትዮጵያ አርበኞች ማህበር በመጡት አባት ገለፃ ነበር የጀመረው፡፡ “ታላላቅ ታሪካዊ ክንውኖች የተፈፀመበት አደባባይ ላይ ነው የምንገኘው። ሐውልታቸው በዚህ አደባባይ ስለቆመው አፄ ምኒልክ ካልነገርኳችሁ ብዬ አላደክማችሁም፡፡ አፄ ኃይለሥላሴ በአራዳ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ዘውድ መድፋታቸውን መንገርም በዚህ ማለዳ እላያችሁ ላይ የተከመረውን ብርድ አያራግፍላችሁም፡፡
“ባይሆን ልባችሁን የሚያሞቅ፣ ስሜታችሁን አነሳስቶ የሚያስገርም አንድ ሁለት ጉዳይ ልንገራችሁ። የአድዋ ጦርነት ድል 7ኛ ዓመት በ1895 ዓ.ም በዚህ አደባባይ ሲከበር በበዓሉ እንዲታደም ለተጠራው 60 ሺህ ህዝብ ማስተናገጃ 8 ሺህ በሬ ታርዶ ነበር፡፡ ዛሬም የዚህ መንደር ታዋቂ ንግድ የሉኳንዳ ቤት ነው፡፡ በከተማችን ከዓመቱ መግቢያ እስከ ማጠናቀቂያ ሥጋ ተፈልጎ የማይታጣበት ቦታ ነው፡፡
“ሌላው በ1950ዎቹ በእንግሊዝ አገር ግር የተሰኘሁበት ሚስጢር፤ እግዚአብሔር ዕድሜ ሰጥቶኝ፤ አራዳ ጊዮርጊስ ከርሰ ምድር ውስጥ መዘርጋት ስለቻለው ጉዳይ ነው የምነግራችሁ። በአውሮፓ የአገር መሳቂያ የሆንኩት ‹በባቡር ና› ወደ ተባልኩበት ቦታ ለመሄድ አስፋልት ላይ ቆሜ፣ በግራ ቀኜ ሐዲድ እየፈለግሁ፣ ባቡር ጣቢያው የት እንደሆነ እጠይቅ የነበረው፤ ከቆምኩበት ወለል ስር የሚርመሰመሰው ትራንስፖርት መግቢያ አንዲት ትንሽ ደረጃ ማስተዋል ባለመቻሌ ነበር፡፡ ያ የሰው ልጆች ጥበብ እዚሁ በአገሬ ተሰርቶ አየሁ፤ ድንቅ ነው፡፡”
የአርበኛው አባት ገለፃ ሲያበቃ ወደተዘጋጀልን አውቶብስ ገባን፡፡ ለአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ሥራ አጥሩ የተደፈረው አሮጌው ማዘጋጃ ቤት፣ ቀሪውን አድሶ መልክ የሚያስይዝለት ማጣቱን ከጉዟችን ተሳታፊዎች ሁለቱ ሲነጋገሩበት ሰማሁ፡፡ ማነፃፀሪያቸው አዲሱ የማዘጋጃ ቤት ህንፃ አጥርም ለልማቱ ፈርሶ የነበረ ቢሆንም፣ ስራው ካለቀ በኋላ ተመልሶ መገንባቱን እያመሳከሩ ነበር የሚወያዩት፡፡
የዝግጅቱ አስተባባሪ በጭብጨባ የአውቶብሱን ተሳፋሪዎች ቀልብ ወደራሱ ከሳበ በኋላ ከዩኒቨርሲቲ የተጋበዘውን ወጣት የታሪክ ምሁር ማንነት አስተዋወቀን፡፡ አቶ በቀለ ለማ ይባላል፡፡ አቶ በቀለ የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ለልማት የተነሳ ዕለት በቦታው እንደነበረና ሐውልቱን ወደነበረበት ለመመለስ ምን ሂደት ላይ እንዳለ ገለፃ እንዲሰጠን ተጋበዘ፡፡
“በብዙ መድረኮች ‹ታላቅ ሰው ከተናገረ በኋላ እኔ ታናሻቸው መጋበዜ ተገቢ አይደለም› እያሉ አክብሮታቸውን በትህነትና የሚገልፁ ሰዎች ያጋጥሙኛል፡፡ እኔ ግን እንኳንም ከትልቅ ሰው በኋላ የመናገር ዕድል አገኘሁ ብያለሁ፡፡ ምክንያቱም የምታውቁትን ነገር በመስበክ እንዳላሰለቻችሁ ከአባት አርበኛው ገለፃ ትምህርት አግኝቻለሁ፡፡
“ስለዚህ የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ሚያዚያ 25 ቀን 2005 ዓ.ም ከዚህ ቦታ መነሳቱን፣ ከአንድ ዓመት በኋላ ወደነበረበት ይመለሳል የሚል ቃል መገባቱን፣ ከዛሬ ነገ ወደ ቦታው ይመለሳል እየተባለ በተደጋጋሚ በመነገር ላይ መሆኑን ልንገራችሁ ብል ጆሮ አትሰጡኝም፤ ደጋግማችሁ ሰምታችሁታልና። ጆራችሁን ብቻ ሳይሆን ዓይናችሁን የሚስብ ነገር ልንገራችሁ፡፡ ፋሽስቱ በአቡነ ጴጥሮስ ላይ የሞት ፍርድ የፈረደበት ቤት የት እንደሚገኝ ስንቶቻችን እናውቃለን?” ወጣቱ የታሪክ ምሁር የብዙዎቻችንን ቀልብ መሳብ ቻለ፡፡ ከአውቶብሱ በስተግራ ጂማ ባር ያለበትን ብሎክ ቤቶች እያሳየን፣ የአቡነ ጴጥሮስ የሞት ፍርድ ከነዚያ ቤቶች በአንዱ ክፍል ውስጥ መወሰኑን አሳወቀን፡፡
ቀድሞ የኢትዮጵያ ሬዲዮ አገልግሎት ማሰራጫ የነበረውንና አሁን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ  የጋዜጠኞች ማሰልጠኛ የሆነውን ግቢ እንዳለፍን፣ ከስፖርት ኮሚሽን የመጡት አቶ በላቸው ተካ ቀጣዩን ገለፃ እንዲደርጉልን ከሹፌሩ ጀርባና ከተሳፋሪዎች ፊት ለፊት ያለው መድረክ ተሰጣቸው፡፡
“በቀድሞ ዘመን የጊዮርጊስ ፒያሣ አንዱ መለያቸው የእግር ኳስ ጨዋታና የብስኪሌት ግልቢያ ውድድሮች በብዛት የሚካሄድባቸው መሆኑ ነው፡፡ ወደዚህ አካባቢ የሚመጡ ሰዎች ጊዜው ስንት ላይ እንደደረሰ የሚያውቁት ከአትክልት ተራ ነባር ቤቶች በአንዱ ላይ በተሰቀለው የአደባባይ ሰዓት ነበር፡፡ የአዲስ አበባ ህዝብ ከሰዓት ጋር ያለው እውቂያ ምን እንደሚመስል ታሪክ ጽፎ የሚያሳትም ካለ፣ በልማት ምክንያት ከፒያሣ አትክልት ተራ አሮጌ ህንፃዎች ጋር የተወገደውን ሰዓት ታሪክና ውለታ እንዲያካትቱ አደራ እላለሁ፡፡ ለስፖርተኞች ሰዓትና ጊዜ ምን ማለት እንደሆነ፤ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ አንዲት ሰከንድን በመጣል የሚሊዮን ዶላር ሽልማት ሊያጣና ለሽንፈት ሊዳረግ እንደሚችል የነገረንን ምክር መቼም አንረሳውም ብዬ እገምታለሁ፡፡”
ከአውቶብሱ ወርደን ፒያሣ አትክልት ተራን ዞረን እንድንጎበኝ ተደረገ፡፡ በአካባቢው ወደ ዘመናዊ ሕንፃ ለመግባት የሚታትር ንግድና የጎዳና ግብይት ተፋጥጠው አየን? ማን እንደሚያሸንፍ ለማናችንም ግልጽ ነበር፡፡ ይህ እውነታ ወደ መርካቶ ስንገባ በስፋት እንደሚገጥመን እየታሰበን ወደ አውቶብሳችን ተመለስን፡፡
ቀጣዩ ገለፃ አድራጊ ከንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የመጡት አቶ በርናባስ ሄኖክ ነበሩ። “እኔም ብዙ አልተነገረለትም ብዬ የገመትኩትን ታሪክ ነው የምነግራችሁ” ብለው ገለፃቸውን ጀመሩ፡፡ “አሁን አለ በጅምላ የመርካቶ ቅርንጫፍ የተከፈተበት የቀድሞ ጅንአድ ግቢ የመጀመሪያው ባለቤት ቤስ የሚባሉ የውጭ አገር ባለሀብት ነበሩ። ባለሀብቱ የኢትዮ-ጅቡቲ የምድር ባቡር ድርጅትን ለመግዛት ለመንግሥታቱ ጥያቄ አቅርበው ነበር ይባላል፡፡ ኩባንያው ለባለሀብቱ ተሸጦላቸው ቢሆን ኖሮ፣ የባቡር ትራንስፖርት ዕድገታችን የት ይደርስ ነበር ይሆን? ወደፊትም ዘርፉ ለግል ባለሀብት ቢሸጥ፤ ጠቀሜታና ጉዳቱ ምን እንደሆነ መነጋገሪ መድረክ ቢፈጠር ጥሩ ነው የሚል አቋም አለኝ፡፡ ይህ አቋም እራሴን እንጂ የመጣሁትን ተቋም አይወክልም፡፡”
መርካቶ ውስጥም ዘመናዊውና ባህላዊው ንግድና ነጋዴዎች ተጎራብተው፣ ተቃቅፈው፣ ተደጋግፈው … ሲያስኬዱት አየን፡፡ ፈርሶ የተገነባው፣ በመገንባት ላይ ያለው፣ የሚፈርሰውም ብዙ ነው፡፡ ከባንኮች ማህበር የመጡት አቶ ሀብታሙ ልክየለው፤ መርካቶ ውስጥ በልማት ምክንያት ከፈረሱት ቤቶች ጋር በተያያዘ የአገሪቱን ዕድገት እንዲያብራሩልን በዝግጅቱ አስተባባሪ ተጋብዘው ፊት ለፊታችን ቆሙ፡፡
“ዛሬ በዚህ ጉዞ ሁላችንም የተማርነው ነገር የሚታወቅና ተደጋግሞ የተነገረ ታሪክ ካልነገርኳችሁ ብሎ በአድማጭ ጆሮና ጊዜ ላይ መቀለድ ተገቢ አለመሆኑን ነው፡፡ የአገሪቱ ‹የፋይናንስ ተቋማት መንደር› በብሄራዊ ባንክ ዙሪያ እንዲገነቡ መጠነ ሰፊ እቅድ ተነድፎ ተግባራዊ ሥራዎች ከተጀመሩ ሰነባብቷል፡፡ የፋይናንሱ ዘርፍ ወደዚህ ደረጃ ያደገው በትናንሽ ባንክ ቤቶች ከመስራት ተነስቶ ነው፡፡ መርካቶ ውስጥ በልማት ምክንያት የፈረሰውና ለገበያዋ የመጀመሪያ የፋይናንስ ተቋም ሆኖ ያገለገለው ‹ቁጭራ ባንክ ቤት› አንዱ ማሳያ ነው፡፡”
የጉዞው ማጠናቀቂያ እንዲሆን ወደታቀደውና ለዝግጅቱ መሰናዳት ምክንያት ወደሆነው አዲስ ከተማ መሰናዶ ትምርት ቤት አካባቢ ደርሰናል፡፡ መርካቶ ውስጥ ከሰባት ፎቅ በላይ ካላቸው በጣት የሚቆጠሩ ህንፃዎች አንዱ እዚህ አካባቢ በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡ የህንፃው ባለቤት ንግድ ባንክ ሲሆን፤ ቦታው ላይ በቀድሞ ጊዜ “አምባሳደር ሆቴል” ተብሎ የሚጠራ ባለ ሁለት ፎቅ ህንፃ እንደነበረበት “የጠፉትን ፈላጊ ፕሮሞሽን” መሥራችና የዕለቱ ፕሮግራም አዘጋጅ ገለፃ አደረገልን፡፡
በልማት ምክንያት የፈረሰው የአምባሳደር ሆቴል ህንፃ በኢትዮጵያ ስነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ መቼም ቢሆን ሊረሳ የማይችል የወግ ጽሑፍ እንዲፃፍ ምክንያት የሆነ የግድግዳ ላይ ሥዕል ይገኝበት እንደነበርም አብራራልን፡፡ በሆቴሉ ቡና ቤት መጽሔትና ጋዜጦች በብዛት ይነበቡ እንደነበርና ሆቴሉ ለንባብ መዳበር ባለውለታ እንደነበረም ተወሳ፡፡
ከዚህ ሆቴልና ደንበኞች አንዱ የነበረው ደራሲና ወግ ፀሐፊ መስፍን ሀብተማርያም “የቡና ቤት ሥዕሎች” በሚል ርዕስ ስለፃፈው ወግና ለሥዕሉ መነሻ ስለሆነው ሥዕል እንዲያስረዱ በዘርፉ ሁለገብ ሐያሲ ናቸው የተባሉት ወ/ሮ አቻምየለሽ ዓለሙ ተጋበዙ፡፡
“ባህላዊው የኢትዮጵያ ሥዕል ወደ ዘመናዊ የአሳሳል ዘዴ እንዴት እንደተሻገረ ጥናትና ምርምር ቢደረግ የቡና ቤት ሥዕል ሰዓሊያን ድልድይ ሆነው ይገኛሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ የቡና ቤት ሥዕሎችን እንደሚገባው አጥንተናቸዋል ወይ? በሻይ ቤቶች፣ ጠጅ ቤቶች፣ ሆቴሎች ግድግዳ ላይ ተስለው የነበሩት ሥዕሎች የምንማርባቸው ብዙ ቁምነገር ነበራቸው። ጋሽ መስፍን ሀብተማርያም ባየበት መልኩና ትንታኔ ባቀረበበት ዘዴ በስፋት አልተጠኑም የሚል የግል እምነት አለኝ፡፡ ከነባር ቤቶቹ ጋር ሥዕሎቹም አብረው እየጠፉ ነው፡፡
በዚህ አጋጣሚ የቡና ቤት ሥዕሎችን ይዘትና ቅርጽ ከቻልን፣ እንደ ጋሽ መስፍን በጽሑፍ በመግለጽ፣ ካልቻልን ፎቶግራፍ በማንሳት ለታሪክ እንዲቀሩ ብናደርግ የሚል መልዕክት አለኝ። ደራሲው በሌለበት፣ ሥዕሉም በማይገኝበት በዚህ ቦታ ዛሬ መሰባሰብ የቻልነው በነበረ እውነታ ላይ የተሰራ ሥራና ሰሪውንም ለመዘከር ነው፡፡ ስለዚህ አዲስ ነገር ስንጨምር ነባሩ ሥራ የህዝብና የአገር ታሪክ አካል እንዲሆን አስበንና አቅደን እንስራ፡፡”

Read 1727 times