Monday, 27 July 2015 11:08

የተሻሻለ የግል የአቪየሽን ፖሊሲ ሊወጣ ነው

Written by  ማህሌት ኪዳነወልድ
Rate this item
(1 Vote)

 - በዘርፉ የሚነሱ ችግሮችን ይፈታል ተብሏል
                        

    የመጓጓዣ አውሮፕላኖችን የወንበር ገደብ ጨምሮ በግሉ የአቪየሽን ዘርፍ ላይ የሚታዩ አጠቃላይ ችግሮችን ይፈታል ተብሎ የሚጠበቅ ፖሊሲ፣ በያዝነው ዓመት መጨረሻ ተጠናቅቆ ተግባራዊ እንደሚሆን የትራንስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ የሚኒስቴሩ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ አሳልፈው አመዲን ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ በተሻሻለው የግል የአቪየሽን ፖሊሲ ላይ የፍትህ አካላት አስተያየት እንዲሰጡበት እየተደረገ ነው፡፡ የግል የአቪየሽን ዘርፍ አንቀሳቃሾች፤ የወንበር ገደብና ከ22 ዓመት በላይ የሰራ አውሮፕላን ወደ አገር ውስጥ እንዳይገባ የተቀመጠው ገደብ እንዲሁም በዘርፉ የሚታዩ መሰል ችግሮች ለስራቸው እንቅፋት እንደሆኑባቸው በተለያዩ ጊዜያት  ለሚኒስትሩ መስሪያ ቤት መግለፃቸውን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ የአቪየሽን ፖሊሲው በዘርፉ የሚነሱ ችግሮችን በመፍታት፣ውጤታማ ስራዎችን ሊያሰራ በሚችል መልኩ እየተዘጋጀ እንደሆነ የገለጹት ኃላፊው፤የባለሀብቱን እንዲሁም የአገሪቱን ጥቅምና ደህንነት የሚያስጠብቅ ይሆናል ተብሏል፡፡
 “ከዚህ ቀደም የወንበር ገደቡ ሲቀመጥ የግል አንቀሳቃሾች አቅምም አነስተኛ ነበር” ያሉት አቶ አሳልፈው፤አሁን የተነሳው ጥያቄ የዘርፉ ማደግና የአገሪቱ ልማት እድገት ውጤት ነው ብለዋል፡፡ የዘርፉ ተዋናዮች የሚያነሱት የጋራዥ ችግርም የአዲሱን ኤርፖርት መገንባት ተከትሎ የሚፈታ እንደሚሆን ሃላፊው ተናግረዋል፡፡  
የግል የአቪየሽን ኢንዱስትሪ አንቀሳቃሾች፣ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ የራሳቸውን ሚና እንዲወጡ ለማድረግ ፖሊሲው ጥያቄያቸውን መመለስ በሚያስችል መልኩ እየተሻሻለ እንደሚገኝ የጠቆሙት ኃላፊው፤ በአመቱ መጨረሻ የአፈፃፀም መመሪያ ተዘጋጅቶለት ወደ ስራ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡  

Read 1351 times