Monday, 27 July 2015 11:10

የአረብ-አፍሪካ ፓርላማና ቢዝነስ ፎረም የዛሬ ሳምንት በአዲስ አበባ ይካሄዳል

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(2 votes)

 አፍሪካ ኢንቨስተሮች መሳቧን ቀጥላለች
                         
   በርካታ የበለፀጉ የአሜሪካና የአውሮፓ ኢንቨስተሮች ለኢኮኖሚያቸው ማደግና ለህልውናቸው መቀጠል አፍሪካን ተስፋ እያደረጉ ነው፡፡ ለምን መሰላችሁ? እንደቀድሞው በአገራቸው ብቻ ቢወሰኑ ዓመታዊ ዕድገታቸው ከ2 ወይም ከ3 በመቶ አይበልጥም፡፡ በዓለም ከፍተኛ ዕድገት እየተመዘገበ ያለው በአፍሪካና በሩቅ ምስራቅ አገሮች ነው፡፡ አንዳንድ አገሮች በሁለት አኀዝ ብዙዎቹ ደግሞ ከ5 በመቶ በላይ እያደጉ ነው፡፡ ስለዚህ በእነዚህ አገሮች ኢንቨስት ማድረግ ያዋጣል፡፡ የዓለም 10 ምርጥ ዝነኛ ባለ 5 ኮከብ ሆቴሎች በአፍሪካ ኢንቨስት ለማድረግ መወሰናቸውን ባለፉት ጥቂት ሳምንታት አስነብበናችኋል፡፡ ባለፈው ሳምንት ማርዮት፣ ሂልተን ኢንተርናሽናል፣ ራዲሰን ብሉ፣ … በሩዋንዳና በሌሎችም አገሮች አዳዲስ ሆቴሎች ለመገንባትና ያሉትንም በማስፋፋት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ነግረናችኋል፡፡ ለአብነት በአገራችን ያለውን ብናይ ማሪዮት ሆቴል በኢትዮጵያ ሦስት ሆቴሎች እየሰራ ነው፡፡
አንደኛው እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን አካባቢ የተሰራው ቢዘገይም በቅርቡ ተመርቆ አገልግሎት እንደሚጀምር ከውስጥ አዋቂዎች ሰምተናል፡፡ ሁለተኛው ቦሌ መድኀኒዓለም ቤተክርስቲያን አካባቢ፣ ሦስተኛው በሀዋሳ ከተማ እየተሰራ ነው፡፡ ሂልተን ኢንተርናሽናልም ግንባታው ዘገየ እንጂ (ኧረ ቆሟል ማለት ይሻላል) በማስፋፊያ ከኢምፔሪያል ሆቴል ፊት ለፊት ወይም ከኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ጀርባ ሁለተኛ ሆቴል እየሰራ መሆኑ ተነግሯል፡፡
አሁን ደግሞ በአፍሪካ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት የአረብ ባለሀብቶች ተራ ነው፡፡ በመጪው ሳምንት ቅዳሜና እሁድ እዚሁ በሸራተን ሆቴል የአረብ- አፍሪካ ሕግ አውጪዎችና ቢዝነስ ፎረም በአፍሪካ ኢንቨስት ማድረግ ትርጉም አለው (Investing in Africa Makes Sense) በሚል ርዕስ እንደሚወያዩ ፓን አፍሪካን ቻምበር ኦፍ ኮሜርስ ኤንድ ኢንዱስትሪ አስታውቋል፡፡
የአረብና የአፍሪካ አገሮች የቢዝነስ ትብብር ፎረም አዲስ አይደለም፡፡ የአፍሪካና የአረብ ዓለም ሴኔቶች ሹራና ተመሳሳይ ደረጃ ያላቸው ም/ቤቶች ማኅበር (ኤሴካ) ከተመሰረተ ቆይቷል፡፡ በንግድ ጉዳዮችና በሌሎም የትብብር ማዕቀፎች ተወያይተው ያውቃሉ፡፡ የአሁኑ ፎረም ያስፈለገው ሁለቱም አኅጉሮች አንዱ ከሌላው የሚፈልገው ነገር ስላለ ነው፡፡ አፍሪካ ለኢንቨስትምነት አመቺና በዕድገት ጎዳና ላይ ብትሆንም መዋለ ነዋይ በጣም ያስፈልጋታል፡፡ የአረብ አገራቱ ደግሞ ያለሥራ የተከማቸ የዘይት ዶላር አላቸው፡፡ ሁለቱን አቀናጅቶ መስራት በማስፈለጉ የፓን አፍሪካን ቻምበር ኦፍ ኮመርስና ኢንዱስትሪ (ፒፓሲ.ሲሲአይ) እና (አሴካ) በጋራ ይህን ፎረም ማዘጋጀታቸው ታውቋል፡፡
ማንም ኢንቨስተር ቢሆን ገንዘቡን አውጥቶ ኢንቨስት ሲያደርግ ከአቅም በላይ ካልሆነ በስተቀር መክሰር አይፈልግም፤ ዋስትና ይፈልጋል፡፡ ፎረም የአፍሪካና የአረብ አገሮች እንዴት መሥራት እንዳለባቸው ለህግ ጉዳዮች እልባት ያበጃል፡፡ በፎረሙ የሴኔትና የሹራ አባላት ከቢዝነስና ኢንቨስትመንት ማህበረሰቦች ማህበራት፣ የንግድ ም/ቤቶች፣ የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን ጽ/ቤት ባለሙያዎች፣ የቢዝነስ መሪዎችና ሀሳብ አፍላቂዎች፣ ዋና ዋና ኢንቨስተሮችና የመንግሥት ውሳኔ ሰጪዎች አሁን በአፍሪካና በአረብ አገራት መካከል ያለውን የንግድ መጠን ከሦስትና ከአምስት እጥፍ በላይ እንዴት ማድረስ ይቻላል በሚል የፖሊሲ ምክክር ያደርጋሉ፡፡
አፍሪካ፣ ከዓለም የነዳጅ ድፍድፍ ያላት 12 በመቶ ያላት ሲሆን፣ የወርቅ ክምችቷ ደግሞ 42 በመቶ ነው፡፡ በምስራቅ የአኅጉሪቷ ክፍል የተገኘው በርከት ያለ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት የአህጉሩ የኢኮኖሚ አቅም እንዲጨምር አድርጓል፡፡ አፍሪካ፣ አዲስ የዕድገት ዋልታ ስለሆነች በማንኛውም ዘርፍ፣ የመሰረተ ልማት፣ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ፣ የችርቻሮ ንግድ፣ በጤና ዘርፍ በማኑፋክቸሪንግ፤ … ኢንቨስት ቢያደርጉባት ከማንኛውም የዓለም ክፍል የተሻለ ከፍተኛ ጥቅም እንደሚገኝባት የፎረሙ አዘጋጆች ያምናሉ፡፡
በሌላ በኩል ደግም በነዳጅ ኃይል ምንጭነት የበለፀጉ የገልፍ አገሮች የትብብር ምክር ቤት ከፍተኛው የነዳጅ ሽያጭ (አሁን ቢቀንስም) ያከማቸለት የተትረፈረፈ ካፒታል አለው፡፡ ከአፍሪካ አገራት ጋር ዋነኛ የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር ያላቸው አገሮች ዱባይና የተባበሩት የአረብ ኢመሬትስ ብቻ እንደሆኑ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው በቅርቡ በዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካና በዱባይ ኢንቨስትመንት ኮርፖሬሽን ጋር የተደረገው የ300 ሚሊዮን ዶላር ትብብር ስምምነት ነው፡፡
በተመሳሳይ ወር፣ የኳታር ብሄራዊ ባንክ ከትራንስናሽናል ኢኮ ባንክ ድርሻ መግዛቱ ነው፡፡ የዱባዩ ኢንቨስትመንት ኮርፖሬሽን በዚህ ዓመት መጀመሪያ ከደቡብ አፍሪካ ሆቴል ማናጀር Kerzner International የአክሲዮን ድርሻ ገዝቷል፡፡ ሌሎች በርካቶችም በግል ሀብትና በልማት ብድር በአፍሪካ አህጉር ኢንቨስት ማድረጋቸው ታውቋል፡፡
በምግብ ሰብል ራስን ለመቻል በእርሻው ዘርፍ የሚደረገውን ጥረት ወደ ላቀ ደረጃ ማሳደግ የሚቻልበት መንገድ ሰፊ ነው፡፡ ሌላስ በአፍሪካና በአረብ አገሮች መካከል የሚደረገው ትብብር ማሳደግ የሚቻልበት መንገድ ይኖር ይሆን? አዘጋጆቹ በአፍሪካና በአረብ አገሮች መካከል ሊኖር የሚገባው አዲስ የረዥም ጊዜ ትብብር በፎረሙ ውይይት ወቅት ይነሳል የሚል እምነት አላቸው፡፡
የአፍሪካን የውጭ ኢንቨስትመንት ዕድገት መጠን (ኤፍዲአይ) ለማሳደግ ምን መደረግ አለበት? የሚለው ሌላው የፎረሙ መወያያ ርዕስ ነው፡፡ በ2013 ዓ.ም 1.9 ትሪሊዮን ዶላር የነበረው የአህጉሩ አጠቃላይ ጂዲፒ አሁን ከብራዚል ወይም ከሩሲያ እኩል ስለሆነ አፍሪካ ከዓለም አገራት በፍጥነት እያደገ ያለ ኢኮኖሚ ባለቤት ሆናለች፡፡
የቢዝነስ ፍላጎት ከአመቺ የቢዝነስ ሁኔታ ጋር የተቆራኘ ስለሆነ ቀደም ሲል በአፍሪካ ኢንቨስት ለማድረግ ይፈሩ የነበሩትን ኩባንያዎች ሁሉ በአፍሪካ ኢንቨስት እንዲያደርጉ እየገፋፋቸው ነው፡፡ የአፍሪካ ገበያዎች እንደ አሜሪካ፣ ቻይናና ምዕራብ አውሮፓ አገሮች ካሉ አስቸጋሪ ግዙፍ ገበያዎች የተሻለ ቢሆንም አሁንም እጅግ በርካታ ስጋቶች አሉበት፡፡
ለአፍሪካ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መቀጨጭ ብዙ ምክንያቶች ቢጠቀሱም ዋነኞቹ እርግጠኛ ያለመሆን ወይም የፖለቲካና የማክሮ ኢኮኖሚ ያለመረጋጋት፣ ግልጽ ፖሊሲ ያለመኖር፣ የጂዲፒ ዕድገትና የገበያ መጠን ማነስ፣ የመሰረተ ልማት እጥረት፣ ለአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች የሚደረግ ከፍተኛ ከለላ፣ ከፍተኛ የሸቀጣ ሸቀጥ ጥገኝነት፣ የፉክክር ክፍተትና ሙስና፣ ደካማ አስተዳደር እንዲሁም ደካማ የገበያ ስትራቴጂ…. መሆናቸውን አዘጋጆቹ ጠቅሰው፣ በእነዚህ ነጥቦች ላይ በማተኮር ውይይት እንደሚካሄድ አመልክተዋል፡፡

Read 1741 times