Monday, 27 July 2015 11:12

ግብር እና ክብር

Written by  ድርሰት - ማርክ ትዌይን ትርጉም - ፈለቀ አበበ
Rate this item
(0 votes)

  ልብ የሚሰውረው ማሳሰቢያ ለመጀመሪያ ጊዜ የደረሰኝ፤ ገና ‹‹ተደላድዬ ልኖር ነው›› ባልኩበት ወቅት ፤ትርጉሙን በቅጡ ባልተረዳሁት ስያሜ ራሱን ‹‹ገማች›› ነኝ ብሎ ባስተዋወቀኝ በአንድ እንግዳ ሰው በኩል ነበር፡፡ ከዚህ ቀደም እሱ የተሰማራበትን አይነት የሙያ ዘርፍ ሰምቼ እንደማላውቅ ነገርኩት፡፡ ቢሆንም በመገናኘታችን ተደስቻለሁ፡፡ እናስ አረፍ ይል ይሆን? አዎ ተቀመጠ፡፡ ቀጥዬ ምን ብዬ ወሬ እንደምጀምር የማውቀው ነገር አልነበረም፡፡ ያው መቸም ሰዎች በህይወት ውስጥ ትልቅ ስፍራ በሚሰጠውና እንዲህ እኔ  ዛሬ እንደደረስኩበት ባለ በራሳቸው የመኖሪያ ቤት ውስጥ የመኖር ደረጃ ላይ ሲደርሱ፣ በማህበረሰቡ ውስጥ ተግባቢ፤እንግዳ ተቀባይና ሰው ወዳጅ መሆን ይጠበቅባቸዋል የሚል ስሜት አደረብኝ፡፡ ያም ሆኖ የቻልኩትን ያህል ባስብም ምንም የምለው ነገር ስላጣሁ፤ ምናልባት በዚህ ሰፈር ውስጥ ሱቅ የከፈተ ጎረቤታችን ይሆን እንደሁ ጠየቅሁት፡፡
ምላሹ አዎን ነበር፡፡ (ምንም የማላውቅ ሰው ሆኜ መታየቱን በፍፁም አልፈቀድኩም ፤ ይልቅስ በሱቁ ውስጥ ምን ምን እንደሚሸጥ እንዲያወራልኝ ፈለግሁ)
በደፈናው ‹‹እሺ ታዲያ ንግድ እንዴት ነው?›› ብዬ ስጠይቀው፤ ‹‹ደህና ነው›› ብሎ መለሰልኝ፡፡
ከዚያም ቀጠልኩና ሱቁን እንደምንጎበኝለት፣ ከሌሎች የተሻለ ሆኖ ካገኘነውም ቋሚ ደንበኞቹ እንደምንሆነው ነገርኩት፡፡
እርሱም በተራው፤የሥራ ቦታውን መውደዳችን እንደማይቀር እንደሚያስብና ሌሎች ስፍራዎችን የሚያስንቅ ብቃት ያለው መሆኑን፣ አንድ ጊዜ የእሱ አገልግሎት ተጠቃሚ ከሆነ በኋላ በተመሳሳይ ተግባር የተሰማራ የእሱ አይነት ሰው ፍለጋ ለመሄድ እግሩን ያነሳ አንድም ደንበኛ አጋጥሞት እንደማያውቅም ነገረኝ፡፡
አነጋገሩ በራስ መተማመን ይንፀባረቅበት ነበር፡፡ ምንም እንኳን ባብዛኞቻችን ላይ የሚስተዋልብን ራስን በብቃት መግለፅ ያለመቻል ተፈጥሯዊ ድክመት ቢታይበትም፤ ሰውየው ሁኔታው ሁሉ እምነት የሚጥሉበት አይነት  ነበር፡፡
እንዴት እንደ ጀመርነው ባላውቀውም ብቻ ቀስ በቀስ በጣም የመቀራረብ ሁናቴ ይታይብን ጀመር፡፡ እናም ንግግሮቻችንም የቅርብ ወዳጅነት መንፈስ ፈጠሩና ቆይታችን የምር ላፍታም የማይጎረብጥ ምቹ ጊዜ ሆኖ ነበር ያለፈው፡፡
በቃ አወራን አወራን አወራን - ቢያንስ ይህን ከማድረግ አልቦዘንኩም፡፡ እናም ሳቅን ሳቅን ሳቅን - እርሱም ቢያንስ ይህን ማድረግ ችሎ ነበር፡፡ ቢሆንም ግን በቆይታችን ጊዜ ሁሉ በጣም ጥንቁቅ ነበርኩ ፤ ከአስተዳደጌ ያካበትኩትን ‹‹በሰው ፊት ሙሉ ሆኖ የመታየት››ን ጥበብ ተጠቅሜ፡፡ የእንግዳውን ሰው ምጥን እና ቆጠብ ያሉ ምላሾቹን እየገነገንኩ፤የንግዱንና የገቢውን ምስጢር ሁሉ አብጠርጥሬ ለማወቅ ቆርጬ ነበር፡፡ ስለ ስውር ወጥመዴ አንዳችም ጥርጣሬ ሳይገባው ገመናውን አውጥቶ እንዲዘረግፍልኝ ለማድረግ ተዘጋጀሁ፡፡ በቃ በጣም ጥልቅና ረቂቅ የሆነ ሴራ ጎነጎንኩለት ማለት ይቻላል፡፡ በመጀመሪያ እኔ ስለ ራሴ የገቢ ምንጮች ዘርዝሬ እነግረዋለሁ፡፡ ያኔ በየዋህ መሳይ ተፈጥሮዬ በጣም ይመሰጥና ጥንቃቄውን ይዘነጋዋል፡፡ ከዚያም፤በቅን የጓደኝነት መንፈስ በምንቆይበት በዚያች እኔ ምን እያደረግሁ እንዳለሁ ባላወቀባት ፋታ፣ ቁጥብነቱን ወዲያ ትቶ ዘና ይልና የግል ገቢውን ምስጢር ሁሉ ይዘከዝክልኛል ማለት ነው፡፡ እናም ‹‹ጌታው፤ በአሁኑ ሰአት እያወራህ ያለኸው እንዴት ካለ ድንቅ ሰው ጋር እንደሆነ ብዙም የምታውቀው ነገር የለም!›› ልለው አሰብኩ፤ ያልኩት ግን ሌላ ነበር…
‹‹ለተሰበሰቡ ሰዎች በማቀርበው የዲስኩረኝነት ስራዬ ብቻ ምን ያህል ገቢ እንዳገኘሁ ብነግርህ በፍፁም ማመን አትችልም!››
‹‹አዎን፤ አልችልም ብል ነው የሚሻለኝ፤በኋላ ገምቼ ከማፍር ማለቴ ነው፡፡ ግን እንደው ዝም ብዬ ለመገመት እንድሞክር ከፈቀድክልኝ… ወደ ሁለት ሺህ ዶላር ገደማ ምናልባት…አይ! አይሆንም! ምክንያቱም ጌታው፤መቸም ያን ያህል ገቢ ልታገኝ እንደማትችል አውቃለሁ፡፡ እሺ አንድ ሺህ ሰባት መቶ ይደርስ ይሆናል ልበል?››
‹‹ሀ!ሀ!ሀ! ልትገምት አትችልም ብዬህ ነበር’ኮ፡፡ ባለፈው የፀደይ ወርና በዚህ ክረምት ለዲስኩሬ ብቻ የተከፈለኝ አስራ ሰባት ሺህ ሰባት መቶ ዶላር ነው! እሺ ምን ተሰማህ ?››
‹‹ኦው! ይኸ በጣም የሚደንቅ ነው! በእውነት በጣም ይገርማል! በማስታወሻዬ ላይ መያዝ አለብኝ፡፡ እናም ደግሞ ይኼም ቢሆን ሁሉም ገቢዬ አይደለም እያልከኝ ነው?››
‹‹ሁሉም?! ትቀልዳለህ እንዴ የተከበርከው ወዳጄ? በዛ ላይ ከጋዜጣ ጽሁፎቼ የማገኘው ክፍያዬ አለ! ከ ዴይሊ ዋርሁፕ ጋዜጣ ወደ…ወደ…አዎ! ለምሳሌ፤ እሺ እንደው ምን ትል ይሆን...በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ ወደ ስምንት ሺህ ዶላር አካባቢ አግኝቻለሁ ብልህስ?››
‹‹ኸረ በል! ማን ይከለክልሀል የፈለግከውን ብትልስ? እኔስ ብሆን እንዲህ ባለው የገቢ ውቅያኖስ ውስጥ መዋኘትን እመኛለሁ ከማለት በቀር ሌላ ምን ሊወጣኝ ይችላል ብለህ? ስምንት ሺህ፡፡ ይኼንንም በማስታወሻዬ ላይ አሰፍረዋለሁ፡፡ ወቸ ጉድ! እንዳልከውም እንዴት ያለኸው ድንቅ ሰው ኖረሀል እባክህን! እኔ እምልህ፤ አሁንም ከነዚህ ኹሉ በላይ ሌላም ተጨማሪ ገቢ እንዳለህ ገና ልትነግረኝ እንደምትችል መጠበቅ ይኖርብኝ ይሆን?››
‹‹ ሀ!ሀ!ሀ! ምን ሆነሀል? እና? ገና ጫፍ ጫፉን ብቻ’ኮ ነው የሰማኸው፡፡ መጽሐፍ ጽፌ ነበር - ‹‹ንጹኃኑ ግዞተኞች›› የሚል - ዋጋው ከሦስት ከሀምሳ እስከ አምስት ዶላር ነው - እንደ ተዳጎሰበት የጥራዝ አይነት ይለያያል፡፡ እንግዲህ በደንብ አድምጠኝ…አይን አይኔን እያየህ፤ባለፈው አራት ወራት ከአስራ አምስት ቀን ውስጥ፤ከዚያ በፊት ምንም አልተሸጠም ማለት ይቻላል፤ባለፈው አራት ወር ከግማሽ ግን ዘጠና አምስት ሺህ መጻሕፍትን ሸጥን፡፡ ዘጠና አምስት ሺህ ኮፒ! አስበው እስቲ…ዋጋውን ስታጠጋጋው በአማካይ አንዱ መጽሐፍ በአራት ብር ሂሳብ እንደ ማለትኮ ነው፡፡ እና? ምታዋ!...አራት መቶ ሺህ ዶላር አካባቢ አይመጣም የተከበርከው ወዳጄ? ከዚያ ውስጥ ግማሹ የኔ ድርሻ ሆነ እልሀለው!››
‹‹የፈጣሪ ያለህ! ይኼንንም እመዘግበዋለሁ! አስራ አራት፣ሰባት፣ ሃምሳ፣ስምንት፣ ሁለት መቶ… በድምሩ ወደ…አዎ…ወደ… ይኸን ለማመን ይከብደኛል! ድምሩ ወደ ኹለት መቶ አስራ ሶስት ወይም አስራ አራት ሺህ ዶላር! ትክክል ነኝ?››
‹‹ትክክል! ስህተት ቢኖር እንኳን ከአደማመር ችግር የመጣ ነው የሚሆነው፡፡ እንጂ ብዙ ነው፡፡ ብቻ ምናለፋህ የዚህ አመት አጠቃላይ ገቢዬ እቅጩን ሁለት መቶ አስራ አራት ሺህ ዶላር ነው፡፡ ሊያውም ባግባቡ አሳክቼ አስልቼው እንደሁ እንጃዪ…!››
ከዚያም ሰውየው ለመሄድ ከተቀመጠበት ብድግ አለ፡፡ ጭራሹኑ ለማላውቀው መጤ ሚስጥሬን ሁሉ በከንቱ መዘክዝኬ ውስጤን ይጎረብጠው ጀመር፡፡ ገና ለገና እንግዳው በታላቅ መደነቅ ስለጮኸልኝ ብቻ ገቢዬን ጨማምሬ ያለመጠን እያጋነንኩ በመንገር ላሳምነው ሁሉ ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ እንደፈራሁትም በኋላ ጉዳዩ ሌላ ሆነና ተገኘአ! የተከበረው እንግዳዬ፤ልክ ሲሰናበተኝ የታሸገ ትልቅ ፖስታ እጄ ላይ አኖረልኝና፤በእሽጉ ውስጥ እስካሁን የመዘገባቸውን ማስታወሻዎች ጨምሮ የእርሱ ሙያ ምን እንደሆነም በቂ ግንዛቤ ከሚያስጨብጠኝ መረጃ ጋር በዝርዝር እንደማገኝ እናም እንደኔ አይነት የገቢ ምንጭ እንዲኖረው ያለውን ምኞት አንፀባርቆ፤ ቢያንስ ግን እንደኔ ካለ የትየለሌ ገቢ በሚያስገኙ የስራ ዘርፎች ከተሰማራ ሰው ጋር የሥራ ግንኙነት በመፍጠሩ ከፍተኛ ኩራት እንደተሰማው፤ በከተማው ውስጥ የሚኖሩና ሀብታሞች ናቸው ብሎ የሚገምታቸው በርካታ ሰዎች መኖራቸውን፤ ሆኖም  ከእነርሱ ጋር በሚያደርገው ይህን መሰሉ የሥራ ግንኙነት ቆይታው ጊዜ ግን ኑሯቸውን በመከራ የሚገፉ ምስኪኖች ሆነው እንደሚያገኛቸው፤ ከዚህ አንፃርም በእውነቱ በጣም ከረዥም ጊዜ በኋላ ገና ዛሬ እንደኔ ያለ ታማኝ ሀብታም ፊት ለፊት አግኝቶ ክብር ተሰጥቶት፣ማውራቱና እጄን በእጆቹ  መንካቱም እንዳስገረመው ገልፆልኝ፤ ስሜቱን መቆጣጠር በተሳነው አይነት ክንዶቹን ዘርግቶ ሊያቅፈኝ ቃጣና የግዱን ተወት ሲያደርገው አስተዋልኩ፡፡ በርግጥም የፈለገውን እንዲያደርግ ብፈቅድለት እንደ ትልቅ ውለታ እንደሚቆጥረው ከአኳኋኑ ያስታውቅ ነበር፡፡
ሁኔታው አንጀቴን ስለበላኝ ልከለክለው አቅም አነሰኝና፣እንስፍስፉ እንግዳዬ እጆቹን በአንገቴ ዙሪያ ጠምጥሞ ጥቂት የእንባ ዘለላዎችን በትከሻዬ ላይ እንዲያንጠባጥብ ፈቀድኩለት፡፡ ከዚያም ወጥቶ ሄደ፡፡
ገና እግሩ ከበር እንዳለፈ የሰጠኝን እሽግ ከፈትኩት፡፡ በውስጡ ያገኘኋቸውን ወረቀቶችም ለአራት ደቂቃዎች ያህል በትኩረት አጤንኳቸው፡፡ ወዲያውም ምግብ አብሳዬን ጠራሁና ምን አልኩ …
‹‹ራሴን ስቼ ስወድቅ ደግፈኝ››
ከጥቂት ሸለብታ በኋላ ስነቃ፤ከህንፃው በታች ካለው የመንገዱ ጥግ ሰው ልኬ አንድ ጠንቋይ አስጠራሁና ሥራ ቀጠርኩት - ሌሊቱን ሙሉ ቁጭ ብሎ ያንን እንግዳ ሰውዬ እንዲረግምልኝ!
ወይ ጉድ! ምን ያለው እርጉም ሰው ነበር! በፖስታው ውስጥ የነበረው የድግስ ጥሪ ካርድ አልነበረም፤ የአመት ገቢዬን ማረጋገጫ ሰነድ ነበር- በገቢዬ ልክ ግብር እንድከፍል የሚሞሉ ቅጾች፤ስለ ግል ህይወቴም አላስፈላጊና ዝርዝር መረጃዎችን እንድሰጥ የሚያባብሉ፣በጥቃቅኑ የተፃፉ መደዴ ጥያቄዎች ከታጨቁበት አራት ገፆች ጋር፡፡ “እነዚህ እንኳንስ እኔና ምናልባትም በዓለም ላይ የፈለገ ያህል እውቀት ያካበተ ዕድሜ ጠገብ አዛውንትም ቢሆን ሊረዳቸው የማይችላቸው ጥያቄዎች ናቸው!# ብዬ ምላሽ ከመስጠት የሚያግደኝ ያለ አይመስለኝም፡፡ መጠይቆቹ፤ገና ለገና እያንዳንዱ ሰው ሳይዘላብድ ትክክለኛውን የአመት ገቢውን እንዲያምን ለማድረግ ሲባል በቅፆቹ ላይ ገቢውን በአራት እጥፍ አባዝቶ እንዲሞላ የተቀናበሩ አይነቶች ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ ከዚህ ከተዘፈቅኩበት ማጥ የማመልጥበትን መንገድ ማሰላሰል ያዝኩ፡፡ ግን አንድም መሹለኪያ ቀዳዳ አልታይህ አለኝ፡፡ ጥያቄ ቁጥር 1 ብቻውን ጉዳዩን ሁሉ ጠቅልሎ አይኔ ስር ሰተረልኝ…
ባሳለፍነው የበጀት አመት አጠቃላይ ገቢዎ ምን ያህል ነበር? ከማንኛውም የንግድ ልውውጦች? ከልዩ ልዩ የግል ገቢ ማግኛ ሥራዎች? ከቅጥር ደመወዝና ከማናቸውም የሥራ ግንኙነቶች…ወዘተ፡፡ ይህ በየትም ስፍራ ያከናውኗቸውንና የተሳተፉባቸውን አጠቃላይ የገቢ ማግኛ የሥራ እንቅስቃሴዎችዎን ሁሉ ይመለከታል፡፡
ይኼ የመግቢያ ጥያቄ ብቻውን ተመሳሳይ የምርመራ ጠባይ ያላቸውን ሌሎች አስራ ሶስት ዝርዝር ጥያቄዎችን ያስከትላል፡፡ ደግሞ የጥያቄዎቹ የወዳጅነት ባህሪ ደረጃስ…! ለምሳሌ በገጠር መንገድ  የሽፍትነት፣የስርቆት ተግባር አሊያም ለእሳት አደጋ መንስኤነት ተጋልጬ እንደሁ ወይም ደግሞ በመግቢያው ንዑስ ጥያቄ ውስጥ በገቢ ማግኛነት እንድገልፃቸው ከተጠየቅኩት በተለየ መልኩ በአንዳች ልዩ የገቢ ማግኛ ምስጢራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳትፌም ሆነ በህገ ወጥ መንገድ ካልታወቀ ሦስተኛ አካል ማንኛውንም አይነት ንብረት ተረክቤ እንደሆነ ለማወቅ ተለሳልሰው ምላሽ ለማግኘት የሚያግባቡ ጥያቄዎች ናቸው፡፡
መቼም ያ እንግዳ ሰውዬ በራሴ ላይ እንዳሾፍ አድርጎ እንዳሞኘኝ በፍፁም አልክድም፤በነፍሴ እንደተጫወተብኝ ግልፅ ነው፡፡ ያገጠጠ መጃጃል! አሁንም አፈላልጌ ሌላ ሻል ያለ ጠንቋይ ቀጠርኩ፡፡ ዋ! አጉል ክብር ፍለጋ ስንጠራወዝ እንግዳው ሰው በሁለት መቶ አስራ አራት ሺህ ዶላር የአመት ገቢ የእምነት ክህደት ቃሌ ሸብቦኝ እብስ ብሏል፡፡ በህጉ መሰረት እስከ አንድ ሺህ ዶላር የአመት ገቢ ከሥራ ግብር ነፃ ነው፡፡ በቃ ይኸው ብቻ ነው እስካሁን የታየኝ፡፡ እና ይኸ ምኑ መፍትኼ ይሆናል? ከሰፊ ውቅያኖስ በእፍኝ የመጥለቅ ያክል ነው፡፡ እነሆ በህጉ መሰረት ልከፍል ከሆነ’ኮ እንግዲህ ሳልጠየቅ ከተናዘዝኩት አምስት ከመቶው ሲሰላ፣አስር ሺህ ስድስት መቶ ሀምሳ ዶላር የመንግስት ዕዳ እላዬ ላይ ያናጥርብኛል ማለት ነው!
(እንዴ! ቆይ ግን እንዲህ ብልስ በቃ…ይኼንን ያህል ገቢ አላስገባሁም፡፡)
አንድ የናጠጠ ዲታ ሰው አውቃለሁ፡፡ የመኖሪያ ቤቱ የጊቢ ስፋት ፈረስ ያስጋልባል፤እልፍኙ የቤተመንግስት፤የምግብ ጠረጴዛው ግብር የሚያበሉበት አይነት የትየለሌ፣ የቤት ወጪው እልፍ አዕላፍ፤ ሆኖም ደግሞ ምናምኒት የሌለው፤ ችግር ያቆራመደው ድሀ ነው፡፡ በግብር ከፋይ ዜጎች ሥም ዝርዝር ላይ በየአመቱ የሚከፍለውን የግብር መጠን ብዙ ጊዜ የማየት ዕድል ገጥሞኝ ያውቃል፡፡ ስለዚህም ከጠፈነገኝ ማነቆ እላቀቅ ዘንድ ምክሩን እንዲለግሰኝ ወደ እርሱ  ሄድኩ፡፡
ባለፀጋው ሰው ቅፆቹን ተቀበሎኝ፣ የንባብ መነፅሩን ሰክቶ ብዕሩን ባነሳበት ቅፅበት በድንገት መናጢ ደሀ ሆኜ ቁጭ አልኳ! መቼም እንዲህ ያለ እንከን የለሽና ፅድት ያለ የሒሳብ ቀመር ተሰርቶ አይቼም አላውቅ፡፡ በቃ በሚገርም ብልሀት ገቢዬን ጎማምዶ፣ ወጪዬን ቆልሎ ትርፌን እያቀናነሰ በቀላሉ ኮቸመልኝ፡፡ የሀገር ውስጥ ገቢ፡ የ‹ክልል›፣የከተማ መስተዳድር፡ የ‹ወረዳ›፣ወዘተ እያለ የቀረጥ አይነቶች ቀጥሎ ቀጣጥሎ እና የቻለውን ያህል የወጪዎች መአት ደርድሮ ከተበልኝ፡፡ በተለይ የሚያንገበግቡ እጦቶቼን…‹‹በመርከብ መስጠምና በእሣት ቃጠሎ አደጋዎች ያጣሁዋቸው አንጡራ ሀብቶቼ!›› ከሁሉም በላይ ደግሞ ‹‹የቤት ንብረቶቼን ስሸጥ የደረሰብኝ ታላቅ ኪሳራ›› ፤ ‹‹የቤት እንስሳቶቼንም መሸጤ!›› እናም ‹‹የተቆለለብኝን የቤት ኪራይ እዳ ተሟሙቼ መክፈሌ!›› እያለ ደርድሮ  ኮለኮላቸው፡፡ ‹‹በተረፈ ሌሎቹ ገቢዎቼ ሁሉ በደንቡ መሰረት ባግባቡ የተቀረጡ ስለመሆናቸውም፤በዩናይትድ ስቴትስ የጦር ሠራዊት አባልነቴ የሚከፈለኝ ደመወዜም ሆነ በሌሎች ማናቸውም አይነት የሥራ ግንኙነቶቼ የሚከፈሉኝ ሁሉ›› ብሎ ፃፈልኝ፡፡
በተለይ መከራና ሰቆቃዎችን በተመለከተ ሌሎችንም ብዙ ብዙ ህይወቴን ሙልጭ ያወጡ ተግዳሮቶቼን በቅፁ ላይ አስፍሮልኛል፡፡ ለእያንዳንዱ የቅፆቹ መጠይቆች አስፈላጊውን ምላሽ በበቂ ምክንያት እያስደገፈ አስደናቂ ‹‹ቅነሳ›› እና ክርከማ አድርጎ አስልቶ ሲጨርስ ወረቀቶቹን መዳፌ ላይ አኖረልኝ፡፡ ቅፆቹን ለማየት ጊዜ አላጠፋሁም፡፡ እ…ሺ…እና አሁን ከአጠቃላይ የአመት ገቢዬ የተጣራ ትርፌ ስንት ሆኖ ተገኘ ? አንድ ሺህ ኹለት መቶ ሀምሳ ዶላር ከአርባ ሳንቲም ብቻ!
‹‹እንግዲህ…›› አለ ‹‹እንደሚታወቀው በሥራ ግብር አፈፃፀም ህጉ መሰረት አንድ ሺህ ዶላሩ ከሥራ ግብር ነፃ ነው፡፡ አሁን ካንተ የሚጠበቅ ነገር ቢኖር፤ ቅፆቹን ይዘህ ሄደህ መሀላህን ትፈፅምና ከሁለት መቶ አምሳ ዶላር ገቢህ ላይ የሚጣልብህን የሥራ ግብር መክፈል ብቻ ነው›› አለኝ(እሱ ለኔ ይሄንን እያለኝ፤ ትንሹ ልጁ ዊሊ ከአባቱ ኪስ ሁለት ዶላሮችን መዝዞ አውጥቶ ሹልክ አለ፡፡ እንዲህ ስል አሰብኩ…  መቼም ያ የተረገመ እንግዳ ነገ ዊሊንም አግኝቶ ጥያቄ ቢያቀርብለት፤ ዊሊ ስለ ገቢው ጉዳይ ሽምጥጥ! አድርጎ እንደሚክደው እርግጠኛ ነኝ፡፡)
‹‹እንደው ለመሆኑ ጌታው›› አልኩት  ‹‹ሌላም ጊዜ የየትኛውንም ስራዎችህን ገቢዎች ሁሉ እንዲህ ባለ መልኩ አራቁተህ ማለቴ ቀናንሰህ ነው የምታሳውቀው ማለት ነው?››
‹‹እንክት! ‹ወጪዎች› በሚል አርዕስት ስር እነዚህ አስራ አንድ ጥያቄዎች በቅፁ ላይ ያልተካተቱ ቢሆኑ ኖሮኮ፤ በየአመቱ ሀብቴ እየቆረቆዘ እመነመነ ወርዶ ወርዶ ነጫጭባ ድኃ ሆኜ ቀርቼ ነበር፡፡ ህእ! ምን በወጣኝ ነው ለዚህ ጨካኝ! ግፈኛ! አረመኔ! አምባገነን መንግስት በግብር ስም ገንዘቤን የማስታቅፈው?!›› አለኝ ባለፀጋው፡፡
ይህ ባለፀጋ ሰው፤በከተማችን ውስጥ አሉ ከሚባሉት ስመ ገናና ሀብታሞች መካከል በዋነኝነት የሚጠቀስ ነው፡፡ በሰው ልጅ የበጎ ሥነ-ምግባር መለኪያም በንግድ ሞያቸው በኩል በተዓማኒነት ከሚወደሱት፤በማህበራዊ ህይወት ተሳትፏቸውም እንከን የማይወጣላቸው ከሚባሉት ተርታ የሚመደብ፡፡ ታዲያ እኔስ ምኔ ሞኝ---የዚህን የተከበረ ዲታ ምክርና ብልሃት የማልመራበት?
ወደ ግብር መክፈያው ቢሮ ሄድኩ፡፡ እናም በትዝብት አፍጥጠው በሚያዩኝ የዚያ የእንግዳዬ ሰው አይኖች ፊት ‹‹አይኔን በጨው አጥቤ›› ቆሜ፤ በሀሰት ላይ ሀሰት እያነባበርኩ ሽምጥጥ አድርጌ ክጄ መሀላ ፈፀምኩ፡፡ የውሸት መአት! የቅጥፈት መአት! የክህደት መአት! የማስመሰል መአት! ግብሬ እየቀነሰ … እየቀነሰ … እየቀነሰ በሔደ መጠን፤እኔም ቁልቁል እየወረድኩ…በመንፈስ ልዕልናዬ እየጎደፍኩ… እየዘቀጥኩ… እየዘቀጥኩ እሄድ ጀመር፤ከራሴ ህሊና ጋር መልሼ ወደማልታረቅበት የክብረ-ቢስነት አዘቅት፡፡

Read 1389 times