Saturday, 08 August 2015 08:13

የኢጋድ አባል አገራት የመድኃኒት ጥራትና

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

ህገ - ወጥ ዝውውርን ለመቆጣጠር ተስማሙ

የኢጋድ አባል አገራት ከጊዜ ወደ ጊዜ ጥራቱ እንዲቀንስና የመፈወስ አቅሙ እንዲደክም እያደረገ ያለውን ህገ - ወጥ የመድኃኒት ዝውውር በጋራ ለመከላከልና ለመቆጣጠር በመስማማት፤ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ፡፡ አገራቱ በዚህ ሳምንት አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የመድኃኒት ጥራት መቀነስና ህገ - ወጥ ዝውውር በጋራ ለመቆጣጠር በአዲስ አበባ - ሂልተን ሆቴል ባደረጉት የ3 ቀን ውይይት፣  ጉዳቱ እየከፋና
እየበረታ ያለውን ዓለም አቀፍ ችግር በግል መከላከልና መቆጣጠር ስለማይቻል፣ በጋራ ለመሥራት
ተስማምተዋል፡፡ በዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት መሰረት፤ ጥራታቸውን ባልጠበቀና በተጭበረበሩ መድኃኒቶች ምክንያት የብዙ ሚሊዮን ዜጎች ህይወት ይጠፋል ያሉት የጤና ጥበቃ ሚ/ሩ ዶ/ር ከሰተብርሃን
አድማሱ፤ ህገ - ወጥና ሀሰተኛ መድኃኒት ዝውውር፣ መድኃኒት የተላመዱ በሽታዎች እንዲፈጠሩ
ያደርጋል፣ በአገርና በግለሰብ ላይ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ያስከትላል ብለዋል፡፡ በጉባኤው የታደሙ የየአገሮቹ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሮችና የምግብና መድኃኒት ተቆጣጣሪ ባለሥልጣናት፤ ህገ ወጥ የመድኃኒት ዝውውር ድንበር ተሻጋሪ በመሆኑ ስብሰባው እርስ በርስ የሚሰሩበትንና በጋራ መረጃ የሚለዋወጡበትን እንዲሁም አንድ አገር የተመረተ መድኃኒት ወደ ሌላው የሚገባበትን ዘዴ፣ የመድኃኒት ፋብሪካዎችን ሲቆጣጠሩ በጋራ የሚሰሩበትን ሥርዓት፣ የተቀናጀና የተቀላጠፈ አሰራር ለመፍጠር ያግዛል፡፡ ጥራቱን የጠበቀ መድኃኒት ከቀረበ፣ በኮንትሮባንድ ወደየአገሮቹ የሚገቡ መናኛ መድኃኒቶች፣ አቅርቦት ይቀንሳል፣ …. ባለው ችግር ላይ ተወያይቶ መፍትሄ መፈለግ ዘርፈ ብዙ ጥቅም አለው በማለት አስረድተዋል፡፡ ጥራታቸውን ያልጠበቁና የተጭበረበሩ መድኃኒቶች፣ ህዝቡ በጤናው ሥርዓት ላይ እንዳይተማመን ያደርጋል ያሉት በኢትዮጵያ የምግብ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ ቁጥጥር ባለሥልጣን ም/ዳይሬክተር ሄራን ገርባ፣ አንድ ህመምተኛ ለበሽታው የተሰጠው መድኃኒት የማይፈውሰው ከሆነ የህመሙ ጊዜ ይዞራል፣ ህክምና መስጫ ተቋማት ይጣበባሉ፣ በአገር ዕድገት ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራል ሲሉ ገልፀዋል፡፡ ለ3 ቀን በቆየው ውይይት በኢጋድ አባል አገራት ያለው የመድኃኒት ቁጥጥር ሥርዓት የሚያሳዩ
ጽሑፎች መቅረባቸውን የጠቀሱት ም/ዳይሬክተሯ፣ የዓለም ሀገራት ስለደረሱበት የቁጥጥር ደረጃ፣
አባል ሀገሮች ካቀረቡት የቁጥጥር ሥርዓት  መልካም አጋጣሚና መጥፎ ተግዳሮቶች ልምድ መወሰዱን እንዲሁም የዓለም ጤና ድርጅት በመድኃኒት ጥራትና ቁጥጥር ያለውን ተሞክሮ ማካፈሉን ተናግረዋል፡፡
በኢጋድ አባል አገሮች ካሉ ችግሮች አንፃር ምን መደረግ አለበት? ክፍተቶችን እንዴት ማጥበብ
ይቻላል? በጋራ እንድንሰራ የማያደርጉን ችግሮች ምንድናቸው? … በሚሉ በርካታ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ
ውይይት መደረጉን ጠቅሰው፣ የጋራ የቁጥጥር ሥርዓት መገንባት፣ በተለያዩ አገሮች ያለውን የቁጥጥር
ሥርዓት ተመሳሳይ ማድረግ፣ ጥራታቸው፣ ደህንነትና ፈዋሽነታቸው ያልተረጋገጠ ህገ ወጥ
የመድኃኒት ግብአት በጋራ የመቆጣጠር ሥርዓት መዘርጋት፣ የመረጃ ልውውጥ ሥርዓትን ደረጃ ማጠናከር፣ የየአገራቱን የጤና ቁጥጥር ሥርዓትና ተቋም በሰው ኃይልና በግብአት ማጠናከር፣ በአንድ አገር የጤና ቁጥጥር ላቦራቶሪ፣ የማሰልጠኛ ተቋም…. ካለ አባል አገራት በጋራ የሚጠቀሙበት ሥርዓት መፍጠር፣ …. በሚሉ ነጥቦች ላይ ተወያይተው የመግባቢያ ሰነድ ማውጣታቸውንና መፈረማቸውን ም/ዳይሬክተሯ ሄራን ገርባ አብራርተዋል፡፡



Read 1345 times