Saturday, 08 August 2015 09:32

“ቅንጣት“

Written by  ሃሌታ ንባብ - አብደላ ዕዝራ
Rate this item
(4 votes)

  አበራ ለማ ሳይዘረጋጋ ሳይኮማተር የኅላዌን ፈተና መቀንበቡ
                        
     አንጋፋ ደራሲና ገጣሚ አበራ ለማ በተለይ በአጭር ልቦለድና በግጥም የፈጠራ ዉጤት ይታወቃል። አልፎ አልፎ ለትርጉምና ለሂሳዊ ንባብ ብዕሩን ደቅኗል። አብይ ታሪካዊ ልቦለድ “ጠልፎ ማለፍ” አስነብቦናል። በድምፅና በምስል የተዋበ የግጥም ስብስብ አጣጥመንለታል። የኢ-ልቦለድ መጻሕፍትም አበርክቷል። በአማርኛ ሥነ ጽሑፍ አጭርና ረጅም ልቦለድ የተለመደ ነዉ፤ እምብዛም ያልተሞከረዉ በመካከል ያለዉ ምጥን ልቦለድ -novella- ነዉ። አሁን “ቅንጣት” በሚል ርዕስ አራት የኖቬላ ስብስብ ሲያሳትም፥ በአማርኛ ሥነጽሑፍ ብቸኛ፥ በዚህ ዘዉግ የተደረሰ የመጀመሪያ መጽሐፍ ያደርገዋል። አዳም ረታ ድንቅ ኖቬላና አጭር ልቦለድ እያሰባጠረ ያሳትማል፤ “ቅንጣት”  ግን በኖቬላ ዘውግ ብቻ ነዉ የተዋቀረዉ።
በዚህ መጽሐፍ መግቢያ መንግሥቱ ወልደ ማሪያም ስለ ኖቬላ ዘዉግ ያስረዳል። “... እምቅ የአጻጻፍ ስልት ነዉ። አወቃቀሩን በውስን ገጠመኞች፥ ግጭቶችና ገጸ ባሕርያት ግንኙነቶች ይመጠናል። መቼቱም ከዚሁ አኳያ ይጠባል። እናም በዚህ አቀራረቡ ከረጅም ልቦለድ ለመለየት እንዲቻል፥ ምጥን ልቦለድ መባሉ ያስኬዳል።” [ገፅ 7]
የዴስቶቪስኪ Notes from the Underground ፋሲል ይትባረክ፤“የስርቻዉ መጣጥፍ” ብሎ ተርጉሞታል። እንዲሁም መስፍን ዓለማየሁ የሄሚንግዌይን The Old Man and the Sea “ሽማግሌዉና ባህሩ” አስንብቦናል፤ ሁለቱም ለድንቅ ኖቬላ ጥበብ አስረጅ ናቸዉ። የአበራ ስብስብ ለኖቬላ ብያኔ በተለይ የስነጽሑፍ ንድፈ ሃሳብ ቀማሪዎች well structured narrative “በሚገባ የተዋቀረ ትረካ” ለሚሉት የበለፀገበት ነዉ። ኖቬላ የገፅ መብዛት ማነስ ብቻ ሳይሆን ሣይንዛዛ ወደ እምቅነት የሚያደላ፥ ጭብጡም በአመዛኙ ከእዉነታ የፈለቀና የታከከ ነዉ። ከአብይ ልቦለድ አነስ ያሉ ግጭቶች ግን ከአጭር ልቦለድ በላቀ መወሳሰብ የሚተርክ ነዉ። የምዕራብ ደራሲያን በልቦለድ ዘዉጐች መካከል ያለውን ድንበር እስከመፋቅ ደርሰዉ አጭር-ምጥን-ረጅም ልቦለድ ብለን ለመለየት እስከሚሳነን እየከየኑ ነዉ። በአማርኛም የአዳም ረታ “ኩሳንኩስ”  መቶ አርባ ገፅ ያክል የፈጀዉ በስምንት አጭር ልቦለዶች የተዋቀረ ትረካ ነዉ። ሆኖም እያንዳንዱ ለብቻዉ ተነቦ ሊቆም ይችላል፤ ስምንቱም የሚያጠላልፋቸዉ መቼት፥ ገፀባህሪይና ሁነቶች አንድ አብይ ልቦለድ ሊያሳክሉትም ይችላል። እንደሚባለዉም a novel of short stories አይነት ነዉ። የገፆች መጥበብ መስፋት ችላ ከተባለ a novel of novellas ሊባልም ይችላል። የአበራ መጽሐፍ “ቅንጣት” ፈር የቀደደዉ ከአጭርም ከረጅምም ዘውግ ሳይቀላቅል አራት ኖቬላ ማስነበቡ ነዉ።
በአራቱም ኖቬላዎች የግለሰብ ፈተና ለቤተሰብና ለማኅበረሰብ ጦስ ይሆናል። ከአንድ የኑሮ ኩርባ ደርሰዉ ነገን እያለሙ ወይም ነገን ዘንግተዉ ሳል ባልተጤነበት ውሳኔና ድርጊት ሳቢያ ኑሮን ከማጣጣም ይልቅ በስጋትና በሥነልቦናዊ በደል መለብለብ ያመዝናል። ሰዉ ገድለሃል ተብሎ የታሰረው ነዉጤ ደስታ፣ ዳኛዉ ስሙን ከጠየቁት በኋላ ዕድሜዉን ይጠይቁታል፤ ይደናገርበታል።
እንዲቀለዉ “ዓመተ ምሕረቱን አታዉቀዉም ?” ይሉታል።
“ምን ... የምሕረት ዘመን አንዴ ይመጣል፤ አንዴ ይሄዳል፤ ምን ተይዞ ብለዉ ነዉ ጌታዉ? ሲለዉ አዝመራዉ የሰጠ ይሆናል፤ሲለዉ ዉርጩና አረሙ በቡኣያዉ ያስኧረዋል። ምኑ እጡ ብለዉ ነዉ” አለና የይቅርታ ድምፀት አሰማ። “... ባማርኛችን አልተግባባንም መሰለኝ፤ እኔ ያልኩህ ...” ሲሉ አቋረጣቸዉ ተከሳሹ ነውጤ።
“እርግ! እርግ! ... ይጫወቱ! ከከተማ ሰዉ ጋር መጨዋወትን እንድያዉ ታንጀቴ ነዉ የምወደዉ!” [ገፅ 233]  
የሰዉ ህይወት በማጥፋት ወንጀል ተከሶ ለፍርድ ሲቀርብ ጨዋታ የመሰለዉ ባላገር፣ የዋህ ሆኖ የማደግና የመኖር ዕጣ ለአደጋ ሰለባ ብቻ ሳይሆን የኅላዌ ግርምታዉ በአንድ ቋንቋ እየተናገሩ እስከ አለመግባባት የመሰለ ዘመነኛ ቀዉስም ያንስራራበታል። ልክ የ Harold Pinter ተዉኔቶች ያቆሩት ቋንቋ ከማግባባት ይልቅ ሲያራርቅ የመሰለ አንድምታ አይነት። “ሞገደኛዉ ነዉጤ” የከተሜ እና የቀበለኛ አንዳንድ ቃላት እንደ “ዓመተ ምሕረት” የቋጠረዉ የፍች መዛባት ብቻ ሳይሆን፥ አለመጠርጠር፣ ደግ ልብና ሰብዕናን እየወለወሉ ሰውንና ደባዉን ሳያጤኑ በመኖር የሚከሰት እንቅፋት ማሳመሙ ጭምር የፈጠረዉ አያዎነት ሳቅና በደል እኩል ያፈልቃል። ፍርዱ ምን ይሆን፥ የገፀባህሪዉ ታሪክ እንዴት ይቋጫል? አሰኝቶ በጉጉት ይነበባል።
ሶስቱ ኖቬላዎች - “ነፍስ ይማር” ፥ “ምንም አይደል” እና “ሞገደኛዉ ነውጤ” ፍቼ አካባቢ በአማራው ባህል፥ አኗኗር ዘይቤና መንፈሳዊ ተፅእኖ፥ ኩሩነት ... የተደረሱ ናቸዉ።
“የትራፊክ ፖሊስ አዛዥ” የርዕሱ ዘገባነት ቢጐረብጠም በሁለት ከተሞች - አዲስ አበባና ሰንዓ - የኖረ ገፀባህሪ አራዳነት ብልጥነትን እየቀዘፈ ከህይወት ወንዝ ለመሻገር ሲቃትት በአስተሳሰብም በቋንቋም በኑሮ ልምድም ከተሜነት የቀረፀዉ ነዉ። ከተሜነት ደግሞ የዘመኑ መንፈስ -zeitgeist- የአብዮት ዋዜማ የወቅቱ ውጥረት በገፀባህሪዩ ልቡና ባሳደረዉ ተጽእኖና ክስተቶች የማህበረሰቡን አስተሳሰብ ስለሰረስሩት ከደፈረሰ ድባብ የተቀረፀ ኖቬላ ነዉ። “አዲስ አበባ ከተማ በተማሪዎች ንቅናቄ እየተናጠች፥ ምጥ እንደያዛት ነፍሰ ጡር ሴት ከማለዳ ጀምሮ ትጨነቅ ነበር።” [ገፅ 156] መሐመድ በአባቱ የመናዊ፣ በእናቱ ኢትዮጵያዊ ቢሆንም በክልስነቱ ሳይሆን በኖረበት የዘመኑ መንፈስ ተንገላቷል። ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን “ክልስ አባ-ልበ-እግረኛ” በሚለዉ ግጥሙ “ያም ያን ሲለዉ፥ ያም ያን ሲለዉ / ከብቸኛ ልቡ ሌላ፥ ወዳጅ ያለዉ የማይመስለዉ” ብሎ እንደተቀኘለት ግለሰብ፣ከሁለት ዘር መታመሱ እምብዛም አልጐዳዉም። ለአብዮት በተቀጣጠለዉ መንፈስ ምክንያት ግን ታስሮ ወደ አባቱ ሀገር እንደ ግዞት ይወረወራል። አስማታዊ እዉነታ -magic realism- በመሰለ ህይወትና አለም ከየመን፥ በምልስትም ከአዲሳባ እየተቀነጨበ ይተረካል። በግብፃዊ ወታደርና በየመናዊ ነጋዴ መካከል የተከሰተዉ ንትርክ፣ የnovella አፃፃፍ የማይፈቅደዉ መለጠጥ፣ እንደ ነገሩ ቢሆንም በግርምት የሚከታተሉት ነዉ። አንድ ግለሰብ መጽሐፍ ሻጭ ሆኖ እያነበበ ለግራ ዘመም ርዕዮተ ዓለም ሲጋለጥ የሌሎች እንግልት ይመዘምዘዋል። “በጨፌ ዉስጥ እንደሚፈስስ ዉኃ አንዳች የሙቀት ስሜት፥ በሁለመናዉ ሲሰራጭ ተሰማዉ።”
ይህ የለውጥ አባዜ እስከ ዳርቻዉ ሲገፈታትረዉ ብቻ አይደለም የተተረከዉ፤ ግላዊ ኑሮን የማቃናት ታሪካዊ አጋጣሚም ሲጣፍጥና ሲጐመዝዝ ተወስቶበታል። ሆኖም የአባት የእናት ሀገር ጥሪ እኩል ሲጐትቱት ባይሸነፍም ለማርክሳዊ ጥሪ መቅበዝበዝ -እንደ ጥብቅ ታጋይ ባይታወክም- መታከኩ የኅላዌ አልፋ ኦሜጋ ሆኖት መሐመድ አቅጣጫዉን ይስታል። እንዴት? የት? በምን ምክንያት? ... ኖቬላዉን ማንበብ ይሻል።
“ምንም አይደል”  የሚለዉ ምጥን ልቦለድ አንድ ግለሰብ -ሂርጳ- እስር ቤት ከገባ በኋላ የልጆቹ እናት፥ ባለቤቱ ፋንቱ ሌላ ወንድ እያማለላት ፀንሳ ትወልዳለች። “የሚስቱን መውለድ ከሰማ በኋላ ... ነገሩ እንደ ድንጋይ መቀመጫ እያደር እየቆረቆረዉ... የእግር እሳት ሆኖ ይለበልበዉ ጀመር። ” ፋንቱ፥ጋርባ ጉራቻ በወሬ እንዳትታመስ አራሷን ለእናቷ ታስታቅፋለች። ይህ የገጠር ትዝብት፥ ያልተለመደ ድፍረትና የቋንቋ ለዛ ይስበናል። እናቷ ሆድ ይብሳቸዋል።
“ታመሽ ያስጠራሽኝ እንጂ መች ውርደት ልታሸክሚኝ መሰለኝ”
“ምንም ውርደት የለበትም! ባገር ያለ ነዉ”
“የት አገር ነዉ በባሎቻቸዉ ላይ ሲወልዱ ያየሽዉ? የሰማሽዉስ? ደሞ አለማፈርሽ!”
“ምን ያሳፍረኛል ፈቅጄ ላደረግኩት”
“አጀብ ነዉ! ‘ፈቅጄ’ የሚሉት ፈሊጥ አመጣሽ? ‘እበት ትል ይወልዳል’ አሉ እቶት ወለላ! አጀብ ነዉ!”
“እበትም የለ፥ ትልም የለ፥ ጡር አትናገሪ”
“ጡር? የምን ጡር? አንጠርጥሮ ይስደድሽና፤ ደሞ ጡር ትይኛለሽ? ጉድ ሳይሰማ አሉ”
 ብለዉ ነበር ሕፃኑን መንጭቀዋት
ወደ ሚኖሩበት ቀበሌ የበረሩት።  [ገፅ 178]
የፋንቱ የልጅነት ታሪክ፣ የአባቷ አሟሟት የዋህነት፥ ወንድ የሚያቋምጥ ገላዋ ወጥመድ ሆኖ ሳይገድባት ህሊናዋ የሚኮሰኩሳት ወቅት ይመጣ ይሆን? ሂርጳ እስር ቤት ሳለ የገጠመው ሚስቱን ገድሎ የሚማቅቀዉ የኋላሼት ዕጣ ፈንታ ለከእስር ማግስት የኑሮ ትርታ ምርኩዝ ወይስ እግረ ሙቅ ሆነዉ? እዚህ ኖቬላ ዉስጥ የተተረከዉ የጁሐር ውጣ ዉረድ ባይሰለችም አስፈላጊ ነዉ ወይ? ኖቬላ እንደ ዘውግ የማይፈቅደዉ ዝርዝርነት ይምሰል እንጂ የዘመኑን መንፈስ -zeitgeist- እንደ የአብዮት ጠባቂ ድንፋታና ደደብነት ለሌላዉም ቀዉስ የመሆን ድባብ ይታወሰናል። ሆኖም የገፀባህሪያት ሥነልቦናዊና ማኅበራዊ ቀውስ በትረካዉ እስኪቧጥጠን ድረስ ይመስጣል። ሂርጳ ዳግም ከማኅበረሰቡ ሲቀላቀል የጐረቤት ግልምጫና ንቀት አሸንፎ ዝምታን ይመርጣል ወይስ ይህ ባህላዊ ወንድነት ያስተዋል? አበራ ለማ አንድን ስዕል ለቀናት ትክ ብሎ እያስተዋለ እንደ ምንጭ ድንቅ ግጥም ፈለቀለት። የመጀመሪያ ሁለት ስንኞች የሂርጳን አንድ ጠገግ ይወክላሉ። “ያ መረቡ ልቤ ረገበ እምቢ አለ / አንድ እራሱን ማስገር አቃተዉ ዋለለ”  እራስን ማስገር ህይወትን ከመኖር የላቀ መሆኑን ይህ ኖቬላ የቋጠረዉ ሰዋዊ ጉዳይ ነዉ፤ በፍቅር፥ በነገረ ወሲብ ፥ በስጋትና በባህላዊ እርሾ የተማሰለ ጉዞ መገቻዉ ምን ይሆን?
ደራሲዉ ከፈጠረዉ አራት ምጥን ልቦለዶች ለኔ እጅጉን የመሰጠኝ “ነፍስ ይማር” ነዉ። መሳይ የሴትን ቀልብ የሚያሸፍት ቁመና ቢኖረዉም እንደ ሀገሩ ደንብ ልጃገረድ አግብቶ ጐጆ ለመቀለስ አይተጋም። “ድፍን የጋርባ ጉራቻ ሕዝብ መሳይን የሚያውቀዉ ‘ነፍስ ይማር’ በሚል ቅፅል ስም ነዉ። በሕይወቱ ሙሉ እንደ አካባቢዉ ወግና ልማድ ተድሮ ሶስት ጉልቻ የሠራበት ጊዜ የለም። ባሎቻቸዉ የሞቱባቸዉን ሴቶች በከተማይቱ ዉስጥ እያሰሰ ሱሪዉን መጣል ግን መለያዉ ነዉ።” [ገፅ 16] ገፀባህሪዩ በልጅነቱ ከአእምሮዉ ፈሶ ለዛሬ አኗኗሩ መመሪያ የሆነዉን ሥነልቦናዊ ሸክም፣ ማኅበረሰቡ ስለማያጤን እንደ እኩይ ያፌዝበታል እንጂ ይህን ዉስጣዊ ቀዉስ ለመገንዘብ ንቃተ ህሊናዉ አይፈቅድለትም። “አባቱ በልጅነቱ ሲሞቱበት አንድ የአካባቢያቸዉ ታዋቂ ባላባት እናቱን ሊጠይቅና ሊያጽናና ጐራ የሚል እየመሰለ፥ እናቱን እየተመላለሰ ያማግጥ እንደነበር በቁጨት እያስታወሰ አድጓል። ሁሌም ይዝት የነበረዉ ሲያድግ የአባቱን አልጋ የደፈሩትን ባላባት አልጋ ደፍሮ ሊበቀላቸዉ ነበር። ... ልክ እንደ ባላባቱ በሙት ሚስቶች ጐጆ ዉስጥ እየተሟሟቀ፥ የአባቱን አልጋ በቀል ሥራዬ ብሎ ተያያዘዉ።”  ይህ ሥነልቦናዊ ቀዉስ እየገዛዉ እንስት ሰለባዎቹን ለማደን መረቡን እንደ ዘረጋ፣ ወቅቱ የአብዮት ስለነበር የሸፈተን ጀግና -ፊታዉራሪ ሙላቱ- ከነጭፍሮቹ ለማደን ከብዙ ወንዶች ጋር እሱም ይመረጣል። በቅድመ አብዮት “ደግና አዛኝ ሰዉ” የነበሩትን ባለዉለታዉ ፊታዉራሪን ለማስገበር ያቅማማል፤ ለግሉ ጉዳይ ሳይሆን ለበደለዉ ማኅበረሰብ ለመሰዋትም ልቡ በጭንቀት ማዕበል ተናወጠ።
ይህ ኖቬላ የግለሰብ ዕጣ ፈንታ ብቻ ሳይሆን የማኅበረሰብ ጭካኔና እርጉምነት የሆነ ሰበብ እየፈለገ ሲፈነዳ፣ ሰላባዎቹ ምራቁን የዋጠ አዋቂ ብቻ ሳይሆን ህፃናትም ሥነልቦናዊ እንግልት ሲዳሽቃቸዉ ተተርኮበታል። ፍቅር፥ ፍትወት፥ ከኢ-ንቁ አእምሮ የዘቀጠ ቀዉስ፥ ጀማዉ ጋጋታን ተከትሎ  ሌላዉን ሲደፈጥጥ፥ የአብዮት ውጤት በገጠር ትናንሽ ከተሞች መመሰቃቀሉ ... እየመሰጠን ይተረካል? የአብይ ገፀባህሪያት መነሻ መድረሻቸዉ ምን ይመስላል? ልብ ተንጠልጥሎ የሚጓጉለት ብቻ ሳይሆን የዘመን ስሜት ያከሰለዉ ድባብ እና ለዚህ አጭር ህይወት እድሜን መገበር ማስበርገጉን እኩል ያውኩናል።
ይህ ንባቤ የተደራሲያንን ጉጉት ላለመሻማት ሃሌታ ነዉ፤ ቆይቶ በጥሞና ይገመገማል። አራቱም ኖቬላዎች ኮስታራ ሂሳዊ ንባብ ያደፋፍራሉ። ከደራሲዉ ግጥሞቹ እና ከአጭር ልቦለዶቹ እየተነፃፀሩ መነበብ አለባቸዉ። ዛሬ ዛሬ ልቦለድ እየተስለመለመ፣ ሰንደቁ በመጣጥፍ -essays- ይነጠቃል ብለዉ ምእራባዊያን ይሰጋሉ፤ ልቦለድ ከዕውነታዉ እየሸሸ እንዲሁ ተንሳፋፊ ቅዠት መሰል አልም መምረጡ በአንባቢ ችላ ለመባሉ አንድ ምክንያት ነዉ። የአበራ ኖቬላዎች በሚጥም አተራረክ፥ በተለይም የገጠር ግለሰብ ለአመታት ሰቅዞ ባፈነዉ ባህል ለበጐም ለደግም እየኖረ ከለውጡ ዳርቻ ሲቃረብ ምላሹን ያውጠነጥንበታል። ምን ይሆን? የጋራ ዕጣ ፈንታ ብቻ ሳይሆን የግለሰብ ከጐህ እስከ ጐህ እርምጃም ብዙ ብዙ የተፈተነበት ነዉ። እየዘነጋነዉ የመጣነዉን ቀበልኛ ቋንቋና አስተሳሰብ ለኛነት ያባንነናል።
አበራ የኖርዌይ ምቾት፥ ብርቅ ፀሐይና የሚደመሙበት በረዶ እንደ የሺጥላ ኮከብ ብዕሩን ሳያዘናጉት ወደ ፈጠራ ድርሰት መመለሱ ለአማርኛ ሥነጽሑፍ እልልታ ነዉ።
ዝነኛዉ ደራሲ Paul Auster “The Music of Chance” ፥ “The Book of Illusion” በመሳሰሉ ልቦለዶች አንባቢን አስደምሟል። ስለ ፈጠራ ድርሰት ያጠኔዉ ሀቅ አለ። “… think of your own childhood, how important the bedtime story was. How important these imaginary  experiences were for you. They helped shape reality, and I think human beings wouldn’t be human without narrative fiction” እስቲ ሰለ ልጅነትህ አስብ፥ በዚያን ወቀት የተነገረህ ተረት፥ የተተረክልህ ምናባዊ ገጠመኝ ዕውነታን ለመቅረፅ ረድተውሃል። የሰዉ ልጅ ያለ ተራኪ ፈጠራ ሰብአዊ ይሆናል ብዬ አላስብም እንደ ማለት። የአበራ ለማ አይነት ብዕር ህይወት ልሙጥ፥ ጠፍጣፋና ገለልተኛ ከመሆን ይልቅ ዥንጉርጉር፥ ተናዳፊና አጓጊ ኅላዌ እንድ ታጐነቁል ያበቃታል።  

Read 5245 times