Saturday, 15 August 2015 15:42

መድረክ አንድ ውህድ ፓርቲ ለመሆን አቅዷል

Written by 
Rate this item
(8 votes)

    ያለፈውን የትግል ሂደቱን ሲገመግም የሰነበተው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ፤ አዲስ የትግል ስልት መቀየሱን ጠቁሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከግንባር ወደ አንድ ውህድ ፓርቲ ለመሸጋገር ማቀዱን አስታወቀ፡፡
የአራት ብሄር ተኮር ፓርቲዎች ግንባር የሆነው መድረክ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ እያንዳንዱን የፓርቲ አባላት በማሳመን በውህደት አንድ ፓርቲ እንደሚፈጥር የጠቆሙት አቶ ጥላሁን፤ በቀጣዩ ምርጫም አንድ ፓርቲ ሆኖ ለውድድር ይቀርባል ብለዋል፡፡
መድረኩ በሁለት ቀን ጉባኤው፣ አባል ድርጅቶች በውህደት ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥተው በመወያየት የውህደቱን ሂደት እንዲያፋጥኑ ከስምምነት ላይ የተደረሰ ሲሆን በየ6 ወሩ በሚካሄደው ስብሰባም የውህደቱ አጀንዳ እንደሚገመገም ኃላፊው ገልፀዋል።
ግንባሩ ባለፈው የግንቦት ወር ምርጫ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን መገምገሙን የጠቆሙት አቶ ጥላሁን፤ ገዥው ፓርቲ ምርጫውን ለማሸነፍ ማስፈራራትን፣ ጉልበትንና የገንዘብ አቅምን መጠቀሙን፣ እንዲሁም ምርጫው ህግና ስርዓትን በተከተለ መንገድ አለመከናወኑን ገምግሟል ብለዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት ቅዳሜና እሁድ መድረኩ ባካሄደው ጉባኤ፣ እስካሁን ያከናወናቸው ፖለቲካዊ ትግሎች ያስገኙትን ውጤትና በቀጣይ ሊወሠዱ የሚገቡ አዋጭ የትግል ስልቶችን መገምገሙን የጠቆሙት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ጥላሁን እንደሻው፤ ግንባሩ የነበሩበትን ድክመቶች ለይቶ ማስመቀጡንና ከአሁን በኋላ የመንግሥትን ጫና ተጋፍጦ ወደ ህዝቡ በመውረድ፣ የተለያዩ አደረጃጀቶች ፈጥሮ ለመታገል መወሰኑን ተናግረዋል።
ባለፉት ምርጫዎች መድረኩ ጫናዎችን ተቋቁሞ ህዝቡን ለትግል በማደራጀትና በማንቀሳቀስ ረገድ የራሱ ድክመቶች እንደነበሩበት የገመገመ ሲሆን፤ ግንባሩ በምርጫው ሙሉ ኢትዮጵያን መወከል አለመቻሉም ተጠቅሷል፡፡ በአማራ ክልልና በአዲስ አበባ የመድረኩ እንቅስቃሴ በደካማነት ተገምግሟል ያሉት አቶ ጥላሁን፤ በትግራይና በኦሮሚያ በአንፃራዊነት ተሳትፎው እንደጨመረ ገልፀዋል። በጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል፣ አፋርና ሌሎች ክልሎች የመድረክ መዋቅር እንዳልተዘረጋ ሃላፊው ጠቁመው በቀጣይ በነዚህ ክልሎች መዋቅር ለማበጀት ግንባሩ እንደሚተጋ አስታውቀዋል፡፡
በሁለቱ ቀናት ጉባኤው ግንባሩ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ሊኖረው ስለሚገባ ግንኙነት መምከሩ የተገለፀ  ሲሆን ከመድረኩ አላማና ፕሮግራም ጋር የሚቀራረቡ ፓርቲዎችን ለመሳብ በሩን ከፍቶ መጠበቅ ብቻ ሳይሆን የተወሰነ ርቀት ሄዶ ለመጋበዝም እንዳቀደ ታውቋል፡፡

Read 1810 times