Saturday, 15 August 2015 16:05

የተራራ ላይ ሩጫው ፈጣን እድገት አሳይቷል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ባለፈው ሳምንት በአቢጃታና ሻላ ሀይቅ መካከል በሚገኘው የመካከለኛው ስምጥ ሸለቆ የተካሄደው 2ኛው የተራራ ላይ ሩጫ ኢትዮ ትሬል   ፈጣን እድገት እያሳየ ነው፡፡ የተራራ ላይ ሩጫው በክልሉ ያለውን የስፖርት እንቅስቃሴ በማነቃቃት፤ የቱሪስት መሳቢያ መንገዶችን በማጠናከር እና የተፈጥሮ ሃብትን በመጠበቅ ትኩረት እንዲፈጠር ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው፡፡ በአራት የውድድር መደቦች የተካሄደው 2ኛው የተራራ ላይ ሩጫው ከ500 በላይ የሚሆኑ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ሯጮችን ያሳተፈ ነበር፡፡  የተራራ ላይ ሩጫ ለአዳዲስ አትሌቶች የውድድር  ዕድል መፍጠሩም እንደትልቅ ውጤት የሚጠቀስ ይሆናል፡፡ በተለይ 50 አትሌቶችን ሙሉ ወጪ ተሸፍኖላቸው መሳተፋቸው ውድድሩ ስፖርቱን ለማስፋፋት ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ያመለከተ ነው፡፡ የተራራ ላይ ሩጫው የውድድር እድል በመፍጠር ፤ተተኪ አትሌቶች ለማውጣት የሚያግዝ እንደሆነም ለመገንዘብ ተችሏል፡፡
በአትሌት ገብረ እግዚአብሄር ገብረ ማርያም የተመሰረተው እና በሪያ ኢትዮጵያ ቱር እና ትራቭል ድርጅት አስተባባሪነት በተካሄደው 2ኛው የተራራ ላይ ሩጫ በታዳጊዎች 1ሺ 500 ሜትር  እንዲሁም በሁለቱም ጾታዎች 12 ኪሎ ሜትር ፣21 ኪሎ ሜትር እና 42 ኪሎ ሜትር በሸፈነ ፈታኝ የሩጫ ውድድሮች ልዩ ድምቀት ነበረው፡፡ ከ80 በላይ የሚሆኑት ተወዳዳሪዎች ከ9 የተለያየ ሀገራት በመምጣት የተሳተፉበት የተራራ ላይ ሩጫው እና በተለይ የስፔን ኤምባሲአጋር ሆኖ በየተጫወተው ሚና በርካታ ስፓንያርዶችን ያሳተፈ ነበር፡፡ በአራት የውድድር መደቦች አሸናፊ ለነበሩ ተሳታፊዎች የውድድሩ አዘጋጆች ከ70ሺ ብር በላይ የሽልማት ገንዘብ ያበረከቱ ሲሆን፤ አሸናፊዎች ከሽልማት ገንዘብ ባሻገር፤ የአካባቢውን ባህል የሚያሳይ ኩርሲ የተባለ መቀመጫ  ተበርክቶላቸዋል። ለአሸናፊዎቹ ሽልማት ካበረከቱት መካከል የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር ዴኢታ አቶ እውነቱ ብላታ ፣የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሰልጣን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዳውድ ኡመር የሚገኙበት ሲሆን የኢትዮጵያ ታላላቅ አትሌቶች፣ አትሌት ወርቅነሽ ኪዳኔ፣ አትሌት ገዛኸኝ አበራ፣ አትሌት እልፍነሽ አለሙ፤ አትሌት ድሪባ መርጋ ፣ አትሌት ብርሃኔ አደሬ እና የውድድሩ ባለቤት አትሌት ገብረእግዚአብሄር ገብረማርያም ሽልማቶችን በመስጠት አሸናፊዎችን በከፍተኛ ደረጃ አበረታትዋል፡፡  
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ድጋፍ ለውድድሩ ከፍተኛ እገዛ እንዳበረከተ ለመገንዘብ የተቻለ ሲሆን በሚቀጥሉት ዓመታት ውድድሩ በከፍተኛ ደረጃ እድገት አሳይቶ የሚቀጥል እንደሚሆን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡

Read 1356 times