Monday, 24 August 2015 10:22

የኢትዮጵያ ስኬት ከቤጂንግ በፊት

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በቤጂንግ ከተማ የወፍ ጎጆ ስታድዬም ዛሬ ይጀመራል፡፡  የመክፈቻው ውድድር የመጀመርያው የወርቅ ሜዳልያ የሚሸለምበት የወንዶች ማራቶን ነው፡፡ ኬንያ ባለፉት ሁለት ዓመታት ሁለት የማራቶን ሪከርድ የሰበሩ አትሌቶችን በማሳተፏ ከፍተኛ ግምቱን ትወስዳለች፡፡ ተቀናቃኛቸው የዓለም ሻምፒዮና የብር ሜዳልያ የወሰደው ሌሊሳ ዴሲሳ ነው፡፡ ከዚህ በታች ኢትዮጵያ ባለፉት 14 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ያስመዘገበችውን ስኬት ዳስሰናል፡፡     
               ክፍል - 2
     15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በቤጂንግ ከተማ የወፍ ጎጆ ስታድዬም ዛሬ ይጀመራል፡፡  የመክፈቻው ውድድር የመጀመርያው የወርቅ ሜዳልያ የሚሸለምበት የወንዶች ማራቶን ነው፡፡ ኬንያ ባለፉት ሁለት ዓመታት ሁለት የማራቶን ሪከርድ የሰበሩ አትሌቶችን በማሳተፏ ከፍተኛ ግምቱን ትወስዳለች፡፡ ተቀናቃኛቸው የዓለም ሻምፒዮና የብር ሜዳልያ የወሰደው ሌሊሳ ዴሲሳ ነው፡፡
ከዚህ በታች ኢትዮጵያ ባለፉት 14 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ያስመዘገበችውን ስኬት ዳስሰናል፡፡
በ1500 ሜ
1 የብር ሜዳልያ በወንዶች
1 የነሐስ ሜዳልያ በሴቶች
ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ1500 ሜትር በሁለቱም ፆታዎች የወርቅ ሜዳልያ ስኬት የላትም፡፡ በሴቶች 1500 ሜትር  በ1999 እ.ኤ.አ ሜዳልያ በቁጥሬ ዱለቻ ሲገኝ፤  በወንዶች ግን ብቸኛውን ውጤት በ2009 እኤአ በርሊን ላይ ደረሰ መኮንን በብር ሜዳልያ አስመዝግቧል፡፡
በ3ሺ መሰናክል 1 የነሐስ ሜዳልያ በሴቶች
በ3ሺ መሰናክልም በሁለቱም ፆታዎች አሁንም ለኢትዮጵያ የወርቅ የሜዳልያ ውጤት ተመዝግቦ አያውቅም፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በሞስኮው 14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በሴቶች ግን ሜዳልያዎች ተገኝተዋል፡፡ ያመዘገቧቸው የብር እና የነሐስ ሜዳልያዎች ናቸው፡፡
በ800 ሜትር 1 የወርቅ ሜዳልያ በወንዶች
በ800 ሜትር የኢትዮጵያ አትሌቶች በሁለቱም ፆታዎች ያን ያህል ተፎካካሪዎች አይደሉም፡፡ በወንዶች የመጀመርያው የወርቅ ሜዳልያ ድል የተመዘገበው ከሁለት ዓመት በፊት በመሃመድ አማን ነበር፡፡
በ5ሺ ሜትር
4 የወርቅ፣ 1 የብርና 6 የነሐስ ሜዳልያዎች በሴቶች
 1 የወርቅ፣ 2 የብርና 3 የነሐስ ሜዳልያዎች በወንዶች
በ5ሺ ሜትር ሴቶች ፍፁም የበላይነት የነበራት ኢትዮጵያ የወርቅ እና የብር ሜዳልያዎች ሳታገኝ ሁለት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ካለፉ በኋላ ከ2 ዓመት በፊት ሞስኮ ላይ በሴቶች የወርቅ እና የነሐስ እንዲሁም በወንዶች ተጨማሪ ነሐስ በማግኘት ወደ ውጤት ተመልሳለች፡፡
 በ5ሺ ሜትር ሴቶች በዓለም ሻምፒዮና ከወንዶች እጅግ የላቀ ውጤት አላቸው፡፡ በ14 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ኢትዮጵያ በነበራት የተሳትፎ ታሪክ በ5ሺ ሜትር ሴቶች  4 የወርቅ ፤ 1 የብርና 6 የነሐስ ሜዳልያዎችን ሰብስባለች፡፡ በ1999 እና በ2001 እኤአ ላይ በተደረጉት ሁለት ተከታታይ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች አየለች ወርቁ ሁለት የነሐስ ሜዳልያዎችን በማግኘት ፈርቀዳጅ ነበረች፡፡ ከዚያም በ2003 እኤአ ጥሩነሽ ዲባባ የወርቅ፤ በ2005 እኤአ ጥሩነሽ ዲባባ የወርቅ፣ መሰረት ደፋር የብር እንዲሁም እጅጋየሁ ዲባባ የነሐስ፤ በ2007 እኤአ መሰረት ደፋር የወርቅ፤ በ2009 እና በ2011 እኤአ መሰረት ደፋር ሁለት የነሐስ ሜዳልያዎችን በርቀቱ አግኝተዋል፡፡  በ2013 እኤአ ላይ ደግሞ መሰረት ደፋር የወርቅ እንዲሁም አልማዝ አያና የነሐስ ሜዳልያዎችን ማግኘት ችለዋል፡፡
በወንዶች 5ሺ ሜትር በሻምፒዮናው ታሪክ ከአንድ ጊዜ በላይ የወርቅ ሜዳልያውን ለማግኘት ለኢትዮጵያ አትሌቶች ፈተና ሆኖ ቆይቷል፡፡ለኢትዮጵያ የመጀመርያው የሜዳልያ ውጤት የተመዘገበው በ1991 እኤአ ላይ በፊጣ ባይሳ በተገኘው የብር ሜዳልያ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ በ1993 እኤአ ላይ ሃይሌ ገብረስላሴ የብርና ፊጣ ባይሳ የነሐስ፤ በ2001 እኤአ ላይ ሚሊዮን ወልዴ የብር፤በ2003 እኤአ ላይ ቀነኒሳ በቀለ የነሐስ፤ በ2005 እኤአ ላይ ስለሺ ስህን የብር፤ በ2009 እኤአ ላይ ቀነኒሳ በቀለ የወርቅ እንዲሁም በ2011 እኤአ ላይ ደጀን ገብረመስቀል እንዲሁም በ2013 እኤአ ደጀን ገብረመስቀል  የነሐስ ሜዳልያዎችን ወስደዋል፡፡ በአጠቃላይ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ5ሺ ሜትር ወንዶች በኢትዮጵያ አትሌቶች የተመዘገበው ውጤት ከሴቶቹ ያነሰ ሲሆን 1 የወርቅ፤ ሁለት የብርና ሶስት የነሐስ ሜዳልያዎች ናቸው፡፡
በ10ሺ ሜትር
9 የወርቅ፣ 5 የብርና 4 የነሐስ ሜዳልያዎች  በወንዶች
 6 የወርቅ፣ 5 የብርና 4 የነሐስ  ሜዳልያዎች በሴቶች
በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ የበላይነት ካልተነቀነቀባቸው የውድድር ርቀቶች ዋንኛው 10ሺ ሜትር ነው፡፡ ከ1983 እኤአ ጀምሮ በተካሄዱ 14 የዓለም ሻምፒዮናዎች ኢትዮጵያ 9 የወርቅ ሜዳልያ በወንዶች እንዲሁም 6 የወርቅ ሜዳልያ በሴቶች በማግኘት ተሳክቶላታል፡፡ በዓለም ሻምፒዮና ላይ በ10ሺ ሜትር ወንዶች የመጀመርያው የሜዳልያ ድል የተመዘገበው በ1993 እኤአ በኃይሌ ገብረስላሴ በተገኘው የወርቅ ሜዳልያ ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ በ1995፣ በ1997 እና በ1999 እኤአ ላይ ሶስት የወርቅ ሜዳልያዎችን አከታትሎ የተጎናፀፈውም ራሱ ኃይሌ ገብረስላሴ ነበር፡፡ በ1999 እኤአ ላይ አሰፋ መዝገቡ ተጨማሪ የብር ሜዳልያ ወስዷል፡፡ በ2001 እኤአ ላይ አሰፋ መዝገቡ የብርና ኃይሌ ገብረስላሴ የነሐስ፤ በ2003 እኤአ ቀነኒሳ በቀለ የወርቅ፣ ኃይሌ ገብረስላሴ የብርና ስለሺ ስህን የነሐስ፤ በ2005 እኤአ ላይ ቀነኒሳ በቀለ የወርቅ እና ስለሺ ስህን የብር፤ በ2009 እኤአ ቀነኒሳ የወርቅ እንዲሁም በ2011 እኤአ ላይ ኢብራሂም ጄይላን የወርቅ እና ኢማና መርጋ የነሐስ ሜዳልያዎችን እንዲሁም በ2013 እኤአ ኢብራሂም ጄይላን የብርና ኢማና መርጋ የነሐስ ሜዳልያዎች በመሰብሰብ የኢትዮጵያን የበላይነት ለረጅም ጊዜ አስጠብቀዋል፡፡ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በዓለም ሻምፒዮና የተሳትፎ ታሪኳ በ10 ሺ ሜትር ወንዶች 9 የወርቅ፣ 5 የብርና 5 የነሐስ ሜዳልያዎችን ሰብስባለች ማለት ነው፡፡ በ2013 እኤአ የወርቅ ሜዳልያውን ከኢትዮጵያ የነጠቀው ሞፋራህ ነው፡፡
በሌላ በኩል በ10ሺ ሜትር ሴቶች በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ የመጀመርያው የሜዳልያ ድል የተመዘገበው በ1995 እኤአ ደራርቱ ቱሉ በተጎናፀፈችው የብር ሜዳልያ ነበር፡፡ በ1999 እኤአ ላይ ጌጤ ዋሚ የወርቅ፤ በ2001 እኤአ ደራርቱ ቱሉ የወርቅ፣ ብርሃኔ አደሬ የብር እና ጌጤ ዋሚ የነሐስ፤ በ2003 እኤአ ብርሃኔ አደሬ የወርቅ እና ወርቅነሽ ኪዳኔ የብር፤ በ2005 እኤአ ጥሩነሽ ዲባባ የወርቅ፣ ብርሃኔ አደሬ የብር እና እጅጋየሁ ዲባባ የነሐስ፤ በ2007እኤአ ጥሩነሽ ዲባባ የወርቅ፤ በ2009እኤአ መሰለች መልካሙ የብርና ዉዴ አያሌው የነሐስ ሜዳልያዎች አግኝተዋል። በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በዓለም ሻምፒዮና የተሳትፎ ታሪኳ በ10 ሺ ሜትር ከ4 አመት በፊት ምንም አይነት የሜዳልያ ውጤት ባይኖራትም በ2013 እኤአ ላይ ጥሩነሽ ዲባባ የወርቅ ሜዳልያ በመውሰድ ክብሩን መልሳለች፡፡ በላይነሽ ኦልጅራ ደግሞ የነሐስ ሜዳልያ ተጐናፅፋለች። በአጠቃላይ ባለፉት 14 የዓለም ሻምፒዮናዎች በሴቶች 10ሺ ሜትር 6 የወርቅ፣ 5 የብርና 3 የነሐስ ሜዳልያዎችን አግኝታለች፡፡
በማራቶን
1 የወርቅ፣ 2 የብር፣ 3 የነሐስ ሜዳልያዎች በወንዶች
 1 የነሐስ ሜዳልያ በሴቶች  
ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተሳትፎ ታሪኳ በማራቶን ውድድር በሁለቱም ፆታዎች ከ1 በላይ የወርቅ ሜዳልያ አግኝታ አታውቅም፡፡ በወንዶች ማራቶን ኢትዮጵያ የመጀመርያ የሜዳልያ ድሏን በመጀመርያው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ1983 እኤአ ላይ ያገኘችው ከበደ ባልቻ ባስመዘገበው የብር ሜዳልያ ነበር። ከዚያ በኋላ በ2001 እኤአ ላይ ገዛሐኝ አበራ ብቸኛውን የወርቅ ሜዳልያ ድል አስመዘገበ፡፡ በ2009 እኤአ በፀጋዬ ከበደ እንዲሁም በ2011 እኤአ በፈይሳ ሌሊሳ በ2013 እ.ኤ.አ ደግሞ በታደሰ ቶላ ሦስት የነሐስ ሜዳልያዎች ተገኝቷል፡፡ እንዲሁም በ2013 እኤአ ሌሊሳ ዴሲሳ የብር ሜዳልያ አግኝቷል፡፡
በሴቶች ማራቶን ኢትዮጵያ በዓለም ሻምፒዮናው ያስመዘገበችው ብቸኛው የሜዳልያ ድል በ2009 እኤአ ላይ አሰለፈች መርጊያ ያስመዘገበችው የነሐስ ሜዳልያ ብቻ ነው፡፡
የምንገዜም የሜዳልያ ስብስብ ደረጃ
በ14 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች የሰበሰበቻቸውን ሜዳልያዎች 300 (138 የወርቅ፤ 88 የብርና 74 የነሐስ) ያደረሰችው አሜሪካ አንደኛነቷን እንዳስጠበቀች ናት፡፡ ራሽያ 168 ሜዳልያዎች (53 የወርቅ፤ 60 የብርና 55 የነሐስ)፤ ኬንያ 112 ሜዳልያዎች (43 የወርቅ፤ 37 የብርና 32 የነሐስ)፤ ጀርመን 101 ሜዳልያዎች (35 የወርቅ፤ 28 የብርና 38 የነሐስ)፤ ጃማይካ 98 ሜዳልያዎች (24 የወርቅ፤ 42 የብርና 32 የነሐስ)፤ ሶቭዬት ህበረት 75 ሜዳልያዎች (22 የወርቅ፤ 25 የብርና 28 የነሐስ) እንዲሁም ኢትዮጵያ 64 ሜዳልያዎች (22 የወርቅ፤ 19 የብርና 23 የነሐስ) በ14 የዓለም ሻምፒዮናዎች የተሳትፎ ታሪካቸው በማስመዝገብ እስከ 7 ያለውን ደረጃ አከታትለው ይዘዋል፡፡
ባለብዙ ሜዳልያዎች ከኢትዮጵያ
በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ታሪክ የኢትዮጵያን ትልቅ ውጤት ያስመዘገበው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ሲሆን 7 ሜዳልያዎችን (4 የወርቅ፤ ሁለት የብር እና 1 የነሐስ) በመሰብሰብ ነው፡፡ ይህ የኃይሌ ወጤት በከፍተኛ የሜዳልያ ስብስብ ከዓለም 4ኛ ከኢትዮጵያ አንደኛ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ቀነነኒሳ በቀለ በ6 ሜዳልያዎች (5 የወርቅ እና 1 የነሐስ) በማስመዝገብ ከዓለም 6ኛ ከኢትዮጵያ 2ኛ ነው፡፡
በሴቶች የረጅም ርቀት ንግስቷና የአምስትና አስር ሺ ሜትር የዓለም ክብረወሰን ባለቤቷ ጥሩነሽ ዲባባ በዓለም ሻምፒዮና መድረክ አምስት የወርቅ ሜዳሊያ ያጠለቀች አትሌት ናት፡፡
ኢትዮጵያዊ የዓለም ሻምፒዮና ሪከርዶች
በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በኢትዮጵያውያን ተይዘው የሚገኙ ሶስት የዓለም ሻምፒዮና ሪከርዶች አሉ። የመጀመርያው በ2003 እኤአ ላይ በ9ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በ10ሺ ሜትር ብርሃኔ አደሬ የወርቅ ሜዳልያ ስታገኝ በ30 ደቂቃ ከ04.15 ሴኮንዶች ያስመዘገበችው ነው፡፡ ሁለተኛው በ2005 እኤአ በ10ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ5ሺ ሜትር ጥሩነሽ ዲባባ አሸንፋ የወርቅ ሜዳልያ ስትወስድ በ14 ደቂቃ ከ38.59 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ ያስመዘገበችው ነው፡፡ 3ኛው ደግሞ በ2011 እኤአ በ12ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ10ሺ ሜትር ቀነኒሳ በቀለ የወርቅ ሜዳልያ ሲጎናፀፍ 26 ደቂቃ ከ46.31 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ ያስመዘገበው ነው፡
በ14 የዓለም ሻምፒዮናዎች ኢትዮጵያ ከዓለም
ኢትዮጵያ ከ1983 እኤአ ጀምሮ በተካሄዱት 14 የዓለም ሻምፒዮናዎች በነበራት የተሳትፎ ታሪክ ሜዳልያ ሳታገኝ የቀረችው ውድድሩ 2ኛው የዓለም አትሌቲስ ሻምፒዮና በ1987 እኤአ በተካሄደበት ወቅት ብቻ ነበር፡፡ በ1983 እኤአ ላይ በ1ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሄልሲንኪ ፊንላንድ ላይ በ1 የብር ሜዳልያ ከዓለም 15ኛ፤ በ1991 እኤአ በ3ኛው ስቱትጋርት ጀርመን ላይ በ1 የብር ሜዳልያ ከዓለም 21ኛ፤ በ1993 እኤአ በ4ኛው በ1 የወርቅ፣ በ1 የብርና በ1 የነሐስ ሜዳልያ ከዓለም 12ኛ፤ በ1995 እኤአ በ5ኛው ጉተንበርግ ስዊድን ላይ በ1 የወርቅ እና በ1 የብር ሜዳልያ ከዓለም 16ኛ፤ በ1997 እኤአ በ6ኛው አቴንስ ግሪክ ላይ በ1 የወርቅ ሜዳልያ ከዓለም 22ኛ፤ በ1999 እኤአ በ7ኛው ሲቪያ ስፔን ላይ በ2 የወርቅና 3 የነሐስ ሜዳልያ ከዓለም 9ኛ፤ በ2001 እኤአ በ8ኛው ኤድመንትን ካናዳ ላይ በ2 የወርቅ፣ 3 የብርና 3 የነሐስ ሜዳልያ ከዓለም 7ኛ፤ በ2003 እኤአ በ9ኛው ሴንትዴኒስ ፈረንሳይ ላይ በ3 የወርቅ፣ 2 የብርና 2 የነሐስ ሜዳልያ ከዓለም 4ኛ፤ በ2005 እኤአ በ10ኛው ሄልሲንኪ ፊንላንድ ላይ በ3 የወርቅ፣ 4የብርና 2 የነሐስ ሜዳልያ ከዓለም 3ኛ፤ በ2007 እኤአ በ11ኛው ኦሳካ ጃፓን ላይ በ3 የወርቅና 1 የነሐስ ሜዳልያ ከዓለም 4ኛ፤ በ2009 እኤአ በ12ኛው በርሊን ጀርመን ላይ በ2 የወርቅ፣ 2 የብርና 4 የነሐስ ሜዳልያ ከዓለም 7ኛ እንዲሁም በ20011 እኤአ በ13ኛው ዴጉ ደቡብ ኮርያ ላይ በ1 የወርቅና 4 የነሐስ ሜዳልያ ከዓለም 9ኛ ደረጃ ያገኘችበትን ውጤት አስመዝግባለች፡፡ በ2013 እኤአ ላይ በሞስኮው 14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 3 የወርቅ፤ 4 የብር እና 4 የነሐስ ሜዳልያዎች በመስበሰብ ከዓለም 6ኛ ደረጃ ነበራት፡፡    

Read 2423 times