Monday, 31 August 2015 08:58

ፀሐፊው ያልተረዱት ነገር …......

Written by 
Rate this item
(7 votes)

ባለፈው ሐምሌ 18 ቀን 2007 ዓ.ም በወጣው  የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዕትም ላይ ዮሐንስ የተባሉ ፀሐፊ፣ በአሜሪካ መንግስት ድጋፍ የሚደረግለት ፓወር አፍሪካ ኢንሼቲቭ አካል በሆነው በኩርቤቲ የሚገነባው የጂኦተርማል ኃይል ማመንጫን አስመልክተው የፕሮጀክቱን አክሳሪነት፤ “የኦባማ ስጦታ ለኢትዮጵያ፡ የ 40 ቢሊዮን ብር ኪሳራ!!” በሚል ርዕስ ባሰፈሩት አስተያየት ለመግለጽ ሞክረዋል። በርግጥ አቶ ዮሐንስ ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ ኪሳራ ብለው የመደቡት ገንዘብ በየትኛው ስሌት እንዳስቀመጡት የሚያሳይ አሳማኝ መረጃ ባያቀርቡም፣ ስለ ፕሮጀክቱ ያላቸውን ስጋት በደፈናው ያስቀመጡበትን ሁኔታ ለመገንዘብ አዳጋች አይደለም፡፡ ነገር ግን ፀሐፊው መለስ ብለው የፓወር አፍሪካ ኢንሼቲቭ አላማን ለመረዳት ቢሞክሩ መልካም ነበረ በማለት የግል አስተያየቴን ለመሰንዘር እወዳለሁ።

     በፕሬዚደንት ኦባማ ሃሣብ አመንጪነት የተቋቋመው ፓወር አፍሪካ የተሰኘው ኢንሼቲቭ፤ አፍሪካ ለእድገቷ የሚያስፈልጋትን የኃይል ፍላጎት ለማሟላት እያደረገች ያለችውን ጥረት ለመደገፍ ያለመ ፕሮጀክት እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ። ኢንሼቲቩ ኢትዮጵያን ጨምሮ በስድስት የአፍሪካ አገራት፣ 20 ሚሊዮን ነዋሪዎችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመንደፍ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።
 ኢትዮጵያ የጀመረችውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከግብ ለማድረስ በሁሉም ዘርፍ የሚደረገው ልማት ወሳኝነት አለው። በተለይ የኃይል ልማቱ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ትኩረት የሚያሻው በመሆኑ የሃገሪቱን የኃይል ፍላጎት በበቂ ሁኔታ ለመመለስ የ25 ዓመት የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ በመንደፍ፣ የኃይል አቅርቦቱን አሁን ካለው 4000 ሜጋ ዋት ወደ 37000 ሜጋ ዋት ለማሳደግ፣ የግል አልሚዎችንም በማሳተፍ ጭምር ዓላማውን ከግብ ለማድረስ ዘርፈ ብዙ ስራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ። ከነዚህም ፕሮጀክቶች በዋነኝነት የትውልድ አሻራ ያረፈበት ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠቃሽ ሲሆን ዮሐንስ ባሰፈሩት ሃሳብ፣ “የፓወር አፍሪካ የገንዘብ ርዳታ ለምን ለህዳሴው ግድብ አይሆንም” ሲሉ ገልጸዋል፤ ነገር ግን  የህዳሴ ግድብን በተመለከተ እኛው በኛው ለኛው የምንሰራው ግድባችን መሆኑን ፀሐፊው አልሰሙ ይሆን? የውጪ እርዳታ ለማግኘት ጥረት ተደርጎ ባለመሳካቱ አልነበረም እንዴ እኛው ራሳችን ለመስራት ቃል የገባነው፡፡
እስካሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በሃገራችን 94% ያህሉ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚመነጨው ከሃይድሮ ፓወር መሆኑ ግልፅ ነው። ይህ ማለት ግን ያለን የኃይል አማራጭ በግድብ ግንባታ ላይ የተመሰረተ ብቻ ነው ማለት አለመሆኑን ፀሐፊው ሊረዱት ይገባል ባይ ነኝ። ለኢኮኖሚው ቀጣይ እድገት አስተማማኝና ዘላቂ የኃይል አቅርቦትን ለማሟላት ከተለያዩ የኃይል ምንጮች የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎችን መገንባት ግድ የሚለን ወቅት ላይ ደርሰናል። ለዚህም ሲባል ከንፋስ ኃይል 800 ሜጋ ዋት ኃይል ለማመንጨት በዕቅድ የተያዘ ሲሆን አሽንጎዳ 120 ሜጋ ዋት፣ አዳማ I የነፋስ ኃይል ማመንጫ 51 ሜጋ ዋት ኃይል ያመነጫል።  አዳማ II በቅርቡ 153 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት የጀመረ መሆኑን ሰምተናል አይተናልም። በአፍሪካ ትልቁ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በሚያሰኘው ደረጃ ላይ መገኘቱ ኢትዮጵያ በታዳሽ ኢነርጂ ልማትን በማፋጠን ላይ እንደምትገኝ ዋቢ ሆኖ ሊቆጠር ይችላል። ከእነዚህ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ባጠቃላይ በአሁኑ ወቅት 324 ሜጋ ዋት ኃይል ለማመንጨት ያስቻለ አቅምንም ፈጥረዋል።
እንደ ንፋስ ኃይልና ጂኦተርማል ያሉት የኃይል ምንጭ አማራጮች  የሃይድሮ ፓወርን በመደገፍ የዝናብ መጠን አነስተኛ በሚሆንባቸው ወቅቶች  ለክፉ ቀን ደራሾች መሆናቸው የሚያስማማን ይመስለኛል።       
ሁሉንም የታዳሽ ኃይል ምንጮች የማልማቱ ተግባር ከሚፈጥረው ሰፊ አማራጭ በተጨማሪ በተወሰኑ የኃይል ምንጮች ላይ የሚኖረውን ጥገኝነትንም ይቀንሳል። ኢትዮጵያ በስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች ከፍተኛ የጂኦተርማል ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳላት በየጊዜው የሚደረጉ ጥናቶች እያመላከቱ ነው።
ከዚህ የኃይል ምንጭ ብቻ ከ10‚000 ሜጋ ዋት በላይ ማመንጨት እንደሚቻል ታውቋል፡፡ በእስካሁኑ ሁኔታ ከጂኦተርማል ለመጠቀም የተቻለው ኃይል 7% ብቻ ነው። ይህም በዘርፉ ያለውን አቅም የመጠቀም ውስንነት እንዳለ ቢያሳይም በቅርቡ በአሜሪካ መንግስት ድጋፍ 1000 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት የሚያስችል ስምምነት ላይ ተደርሷል።
የጂኦተርማል ኢነርጂ ከአካባቢ ብክለት ነጻ የሆነ አስተማማኝ የታዳሽ ኢነርጂ ምንጭ ሲሆን ከቅሪተ አካል ኢነርጂ ምንጮች ከሚወጣው ወጪ 80% ያህል ቅናሽ እንደሚኖረውም ይነገራል።
 ከዚህ አንጻርም ለትራንስፖርትና ለማመንጫ ጣቢያዎች ጽዳት የሚወጣን ወጪ ከመቀነሱ ባሻገር ለዓለማችን ስጋት ከሆነው የግሪን ጋዝ ልቀትና የአካባቢ ብክለት ነጻ የሆነ ኃይል ለማምረት ያስችላል። በግንባታው የመጀመሪያ ወቅት ወጪው ከፍተኛ ቢሆንም በማመንጨት ሂደቱ በቀጥታ ለጥቅም መዋሉ ተመራጭና ርካሽ አማራጭ ያደርገዋል። እንግዲህ ዮሐንስ በአንድ አቅጣጫ ትኩረት ከሚያደርጉ ይልቅ የተለያዩ መረጃዎችን መመልከት ቢችሉ ፅሁፋቸውን በመረጃ የበለጸገ ለማድረግ በረዳቸው ነበር።
የጂኦተርማል ኢነርጂን ማልማት ለወደፊቱ ተመራጭና ተደራሽነቱም አስተማማኝ እንደሚሆን ተተንብይዋል።አገራት የወደፊቱን የኢነርጂ አማራጫቸውን በታዳሽ ኢነርጂ ላይ እንደሚያደርጉ የወቅቱ የዓለም አየር ንብረት ለውጥ እያስገደዳቸው እንደሆነ በግልፅ እየታየ ነው። በዓለማችን የጂኦተርማል ኢነርጂን በማልማት  በቀዳሚነት 24 አገራት ከዚህ የኃይል ምንጭ ተጠቃሚዎች ሆነዋል፡፡
በዓለም ዓቀፍ ደረጃ 12.8 ጌጋ ዋት አቅም ያለ ሲሆን ከዚህም ውስጥ 28 በመቶውን ማለትም 3‚548 ሜጋ ዋት ኃይል በማመንጨት አሜሪካ በመሪነት ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ ፊሊፒንስ 1‚904 ሜጋ ዋት፣ ኢንዶኔዥያ 1‚222 ሜጋ ዋት በማመንጨት በሁለተኛና ሦስተኝነት ይከተላሉ፡፡ በቀጣዮቹ ዓመታትም የዘርፉ አቅም ከ14.5-17.6 ጌጋ ዋት እንደሚደርስ ይገመታል።

Read 2813 times