Saturday, 05 September 2015 10:14

የኢንቬስተሩ ችሎት!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(8 votes)

 በሽንጠ - ረጅሙና ሁለተኛው ፎቅ ለይ በተንጣለለው ቢሮዋቸው ላይ እስከ ዳር በተነጠፈው ቀይ ምንጣፋቸው ላይ ትንቡክ ትንቡክ ትንቡክ እያሉ በመሄድ ወንበራቸው ላይ ተቀመጡ፡፡ ወደ ግራ ሲያዩ አዲስ አበባ በከፊል አረንጓዴ፣ በከፊል ደግሞ ዝንጉርጉር ህንፃዎችዋን አሳየቻቸው፡፡ ሞቋቸው ስለነበር ኮታቸውን አወለቁና የፀሀፊዋን መጥሪያ ተጫኑ፡፡ ቀይ አፍንጫ ጎራዳ፣ የደም ገንቦ ወጣት መጣች፣ ሽቁጥቁጥ ናት፡፡ አይኖችዋ የተሸከሙት የውበት እሳት ግን ከሩቅ ይለበልባል፡፡ አዩዋትና አጎነበሱ፣ አለቃ እርሷ የሆነች ይመስል፡፡
ወደ ቀኝ መለስ ሲሉ በመስታወት የተለበጠው፣ የመጽሐፍት መደርደሪያ ውስጥ የተሰለፉትን መጽሐፍት አዩ፡፡ አብረሃም ሊንከን፣ ጆንኤፍ ኬኔዲ፣ ዩሊሰስ ግራንት… በተርታ ተሰልፈዋል፡፡ ቀልባቸውን ብዙ አላቆዩም፡፡
“እኔ የምልሽ ይህ ሁሉ ደብዳቤ ምንድነው?”
“እንትኖቹ ናቸዋ ያመጡት?”
ገለጥለጥ አደረጉና አዩት፡፡ የኮንዶሚኒየም ዕጣ የወጣላቸው ሰዎች ያመጡት የእርዳታ ጥየቃ ወረቀት ነው፡፡
“ሰዎቹ ራሳቸው ነው የመጡት?”
“አንዳንዶቹ ለዘበኞች ነው የሰጡት”
“ታዲያ ይህ ሁሉ ሲመጣ አንቺ መመለስ አልነበረብሽም? …. ከልክ በላይ በዝቷል አትይም ነበር?”
የእጅዋን መዳፍ እያፋተገች፤ ‹እሳቸው ደሀ አባት ናቸው፣ ለሀገራችን እግዜር የጣለልን መልዐክ ናቸው፡፡› እያሉ እምቢ አሉ፡፡ … ድሮም የደሀ ጠላት ደሀ ነው እያሉ የተናገሩ ሁሉ አሉ፡፡”
እና ቢሆንስ … የሀገር ሁሉ ደሀ እኔ ላይ መውደቅ አለበት እንዴ? … እኔ ብቻ ነኝ እንዴ ሀብታም? … መድኃኒዓለምን አደረጉኝ እንዴ? … አንድ ቤዛ አደረጉኝ እኮ!”
ዓይናቸውን መለስ ሲያደርጉ በአንድ ታዋቂ ጋዜጣ ላይ የሰጡትን ቃለ ምልልስ ርዕስ አዩት፤ “የሀገሬን ህዝብ መርዳት አይታክተኝም!” ይላል፡፡
ብዙ ሰዎች በቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ አይተዋቸው ስልክ ደውለው ነበር፡፡ በተለይ እንደ ቶልስቶይ “ለድሆች ኖሬ፣ ከድሆች ጋር እሞታለሁ” ያሉትን ሲያደንቁ ነበር የዋሉት፡፡ እንደዚህ እንዲናገሩ የመከራቸው የቢሯቸው የሰው ሀብት አስተዳደር ኩራባቸው ነበር፡፡  
“ምን ዓይነት ሀገር ነው? … አንዴ ቃል ካፍ ካመለጠ….” ሲሉ ፀሐፊዋ ስርጉት “ጋሼ ይሄ ሀገር እኮ መከራ ነው፣ ልቡ የማይታወቅ ህዝብ ነው! … የሰውን ቆዳ ካልገፈፍኩ የሚል፣ ሥራ የማይወድ! በልመና ተወልዶ በልመና ያደገ! … እርሶ እግዜር የባረካትን ሀገር ትተው መጥተው በመስጠት ተወልደው በመስጠት ያደጉ … እንደጌታ ፍጥረት የሚታዩ ቱጃሮች ያሉበትን ሀገር … እዚህ ዓመዳም ሀገር … እኔ እዚያ ሄጄ ጎዳና ተዳዳሪ ብሆን ይሻለኛል፡፡”
“… ምናጣሽ እዚህ …” አሏት ድንገት … እንደቅል የሚያበራ መላጣቸውን እያደራረቁ፡፡
“… መኪና የለኝ ፣ ቤት የለኝ፣ ኑሮ መከራ ነው፡፡ …
ዓይናቸው ወደ ግራ መለሱ፤ አዲስ አበባ በራስዋ ሳቅና እንባ መሀል ተንጠልጥላለች፡፡ ስለዚህ ነገር ብዙ አያውቁም፡፡ እርሳቸው ከሥራ በኋላ ከሆነ ሸራተን አሊያም ሂልተን ነው ውሎዋቸው፡፡
“በይ የኔ ቆንጆ … ሂጂና ከመካከላቸው የባሰ ችግር ያለባቸውን… አሳማኝ የሆኑትን ለይልኝ!...”
“እሺ …” ብላ ሰነዱን ይዛ ሄደች፡፡
… አሁን የኔ ሀብትም ሀብት መሆንዋ ነው? የአሜሪካን ሀብታሞች አላዩ!... አንድ ሪል እስቴት፣ …. አንድ የስፖንጅ ፋብሪካ፣ አንድ የቀለም … ከዚያ ሌላ ሁለት ህንፃዎች… አንድ የትምህርት ተቋም … ብቻቸውን ሳቁ፡፡
ድምፁ አስደንግጧት በሩን ከፍታ “… ፈለጉኝ?” አለቻቸው፡፡ ርቀቷ ከአድማስ ብቅ ያለች ፀሐይ አስመሰላት፡፡ ችግር አለመኖሩን በምልክት ነገሯትና መልሳ ዘጋችው፡፡
“ምን አሳቃቸው?” ብላ መልሳ ደብዳቤዎቹን መክፈት ጀመረች፡፡
የመጀመሪያው… “የደሆች አባት … ጋሽዬ ቴሌቪዥን ላይ ያየሆት ቀን ስቅስቅ ብዬ አለቀስኩ፣ ከነቅላትዎ ጌታችንን ቁርጥ! … እሱን ነው ያሰብኩት … አንጀቴን በሉኝ … ፈጣሪ እኛን እንደወደደን አወቅሁ …”
ሌባ ምናቸው ነው መድኀኒዓለምን የሚመስለው?.... ዓሳማ ይመስል አብጠው፣ ማጅራታቸው ራሱ ያንድ ሰው ወገብ ያህል የለ!… እሳቸው በመስቀል ቢሰቀሉ መስቀሉ አይሰበርም!...
ይሄ ደ‘ሞ ሞላጫ ድርሰት ነው!
“የደሀ አባት መሆንዎን ሰምቼ ነው፡፡ በቀበሌ ቤት ስኖር ለልማት ተብዬ ተነሳሁ፣ በዚያ መሀል አንድ የቆርቆሮ መጠለያ በመከራ ተሰጠኝና ስኖር፣ ከሁለቱ ልጆቼ አንዱ በብርድ ታምሞ ሞተብኝ፡፡ ያለ አባት ያሳደኩት ልጅ ነበር፡፡ … ቀን ቀን እንጀራ ጋግሬ ስሸጥ እውላለሁ፣ ማምሻም ከሞት የተረፈ ልጄን እህል አቅምሼ እንጀራ ለመሸጥ ብርድ ሲመታኝ ያመሻል፤ ኑሮዬ የመከራ ነው … ዕጣው እንደ ጥሩ ነገር ደረሰኝ … ይኸው እንቅልፍ አልወስድ ብሎኝ ልሞት ነው፡፡ … በየወሩ የሚከፈለውን ከየት አምጥቼ ነው የምሰጠው?”
የኔን እናት ህይወት ይመስላል፤ ከዚህ የተሻለ ህይወት አልነበራትም፡፡ አባቴ ጨካኝ ባይሆን ይሄኔ ያለ እናት አልቀርም ነበር፡፡ የሰው ቤት ገረድ ሆና አስተምራኝ ሞተች፡፡…
ወደ ወረቀቶቹ ተመለሰች፡፡
“ለአብዮታዊት ኢትዮጵያ በቆራጥነት ተሰልፌ፣ ሀገሬን ከመገንጠል አደጋ ለመታደግ ስታገል አንድ አይኔንና እግሬን ያጣሁ ነኝ፡፡ የደርግ ወታደር ሳልሆን የኢትዮጵያ ወታደር ነኝ፡፡ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የጦር አካዳሚ ምሩቅ ነኝ፡፡ ዛሬ መኖሪያ ቤት እንኳ የለኝም፡፡ ይኸው ኮንዶሚኒየም ተመዝግቤ ዕጣ ቢወጣልኝ የምከፍለው አጥቻለሁ፡፡
ሻለቃ፡፡”
ለእኒህማ ጨምረው ነው የሚሰጧቸው፡፡ አባታቸው የጃንሆይ ክብር ዘበኛ ስለነበሩ ወታደር ሲያዩ ይባባሉ… አለችና ሳቀች፡፡
ሌላው የኢትዮጵያ አባት፤
“እኔ የልጆች አባት ነኝ፤ ድንገት በተፈጠረ የመኪና አደጋ ወህኒ ቤት እገኛለሁ፡፡ ልጆቼን የማስተዳድርበት አንድ አይሱዙ መኪና አደጋ ደርሶበት፣ የብዙ ሰዎች ሕይወት ጠፍቶ የማልወጣው ዕዳ ውስጥ ገብቻለሁ፡፡ እባክዎ ከዚህ አደጋ ውስጥ ልጆቼን ይታደጉልኝ! ልጆቼም ከትምህርታቸው ተደናቅፈው ቤት ሊውሉ ነው፡፡”
ሳቀች፡፡ አባትዋ የሞቱት በመኪና አደጋ እንደሆነ ሰምታለች፡፡ ብዙም ነፍስ አታውቅም ነበር፡፡ እናትዋን አባርረው ሌላ ሚስት አግብተው እንደነበር ሁሌ የምትሰማው ነገር ነው፡፡ ግን ሆድዋ ባባ፡፡
ሌላኛውን ገለጠች፡፡
“…ለሀገሬ ልማት ሌትና ቀን አልተኛም፤ እጄን ኪራይ ሰብሳቢነት ውስጥ ስላላስገባሁ ደሀ ነኝ፡፡ የምኖረው በቀበሌ ቤት ነው፡፡ ከኔ ጋር የሚሠሩ ዛሬ ሕንፃ አላቸው፤ መኪና ያሽከራክራሉ፡፡ ሠፈራቸው ቦሌ ነው፡፡ እኔ ግን ይኸው ዛሬም ሕዝብን በእውነት ለማገልገል በሕዝቡ መሀል እዳክራለሁ፡፡
ከሁሉ ይልቅ ሕዝቡ ራሱ “ለነፍስህ ነው ለሥጋህ” እያለ መግቢያ መውጫ ያሳጣኛል፡፡ እውነት ዋጋ ታስከፍላለች፡፡ ልማታችን ይቀጥላል! እርስዎ እንደልማታዊ ባለሀብት ጉዳዬን ይዩልኝ”
ከት ብላ ሳቀች፡፡ ረጅም ሣቅ፡፡ ድንቅ ድርሰት!
እያንዳንዱን አገላብጣና መርጣ፣ ለአለቃዋ ይዛላቸው ሄደች፡፡ ስልካቸው ላይ አቀርቅረዋል፡፡ መላጣቸው ቦግ ብሎ ጥቁር ሰማያዊ ሸሚዛቸው ላይ ያለው ነጭ ሸንተረር ደመቀባት፡፡
“ይቅርታ!”
“ግቢ ግቢ … ለየሻቸው?”
“አዎ!”
“የሚያሳምኑ አሉ?”
“እርስዎ ይዩት”
ወረቀቱን አስቀምጣላቸው ወጣች፡፡
ሁሉንም ተራ በተራ እያዩ ሳቁ፡፡ አንዳንዱም አሳዘናቸው፡፡ የተወሰኑት ላይ ፈረሙ፡፡
ከዚያ ስርጉት ተቀብላቸው እያገላበጠች እያየች ሳለ፤ ጥቁሩ፣ ፈገግተኛውና ወፍራሙ የሰው ሀብት አስተዳደር ኃላፊ ኩራባቸው ብቅ አለ፡፡
“እሺ የኔ ቅመም!”
“አለሁልህ”
አንገትዋን አቅፏት፤ “እንዴት ሆነ?”
“ካቀረብካቸው ውስጥ ሦስቱን ለዓመል አሥቀርቼ ሁሉንም ሰጠኋቸው”
“ከዚያ ፈረሙበት በይኛ!”
ቀዝቀዝ ያለች መስላ “የ…ስ” አለችው፤ “አደገኛ ልቦለድ ፀሐፊ ነህ፤ አስለቀስከኝኮ!”
“አንቺን ካስለቀሰሽ፣ ጌቶችን ይታይሽ!”
“የተወሰኑ ሰዎች ግቢ አስገብቻለሁ”
“ምን የሚያደርጉ?”
“ዘበኞች እንዲሰሙዋቸው …ጌቶች ጋ ውሰዱን የሚሉ… የኮንዶሚኒየም ዕጣ የወጣላቸው … ቂቂቂ!”
“አንተ ግን የቴአትር ደራሲ መሆን ነበረብህ!”
“ሆንኩ‘ኮ አስለቀስኩሽ አይደል… ምን ትፈልጊያለሽ! አሁን ለሰዎቹ ትንሽ ሣንቲም ሰጥቼ ላባራቸው፤ የሂሳብ ክፍሉ አቤ ገንዘቡን ሲያወጣ እየመጡ እንዲቀበሉ ሰዎች አዘጋጅቻለሁ፡፡ ያንቺ ሰላሣ ፐርሰንትም ይሰጥሻል!”
“የምን አሜሪካ ነው ታዲያ!” አለችና ሳቀች፡፡
“አሜሪካ መሄድ ቂልነት ነው! እሳቸውም አሜሪካ ሄደው የቀናቸው፣ ትላልቅ ዘመዶች ስለነበሯቸውና ትልቅ ዩኒቨርሲቲ ስለተማሩ ነው፡፡ ሊንከን … ግራንት … ኬኒዲ … የሚሉት ወድደው መሠለሽ፡፡”
“ወንድ ነህ… ግጭ!”
እጅ ለእጅ ተገጫጩ፡፡
“ሕልማችን ተሳካ! ልማቱ ሠመረ!”
ተሣሣቁ፡፡           

Read 3605 times