Friday, 11 September 2015 09:24

“ተቃዋሚው አሁንም ታሪካዊ ፈተናውን አላለፈም” ዶ/ር መረራ ጉዲና (የመድረክ አመራር

Written by 
Rate this item
(4 votes)

አመቱ የምርጫ አመት ነበር፡፡ ምርጫው በአፍሪካም እንኳን ቢሆን ከደረጃ በታች የሆነ፣ በዲሞክራሲ ስም ትልቅ ቀልድ የተቀለበት ውድድር ነበር፡፡ ይሄ በዓመቱ ውስጥ በመጥፎነቱ የተመዘገበ ነው፡፡ በሌላ በኩል በአብዛኞቹ የኦሮሚያ አካባቢዎች ወጣቱ ለመብቱና ለነፃነቱ ለመታገል የነበረው ቁርጠኝነት እንዲሁም አምባገነኖችን ለመሸከም ትከሻ እንደሌለው ያሳየበት ስለነበር በዚያ ምርጫ ውስጥ መግባቴ ልዩ ደስታን ሰጥቶኛል፡፡
በነዚህ በሁለቱ መሃል ነው እንግዲህ አመቱን ያሳለፍነው፡፡ አሁንም ለዴሞክራሲ የምናደርገው ትግል ይቀጥላል፡፡ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር የለውም፡፡ ህዝቡ ተቃዋሚን ለመምረጥ ችግር አልነበረበትም፡፡ የድምፅ ሌባን ለመጠበቅ ግን አልቻለም፡፡ ትልቁ ክፍተታች እሱ ነው፡፡ እንግዲህ ድምፁንም ለማስጠበቅ የሚችል ህዝብ ማደራጀት ይገባል ማለት ነው፡፡
ተቃዋሚው ግን የታሪክ ፈተናውን አሁንም አላለፈም፡፡ የትብብር ጥያቄ ላለፉት 40 ዓመታት ምላሽ አላገኘም፡፡ ይሄ ተቃዋሚው መስራት ያለበት ትልቁ የቤት ሥራ ነው፡፡ ያንን ካላደረገ የትም መድረስ አይቻልም፡፡ ይሄ በቅጡ ሊታሰብበት የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ የተቃዋሚው ትልቁ ፈተና እሱ ነው፡፡
በመጪው አዲስ ዓመት ተቃዋሚው ራሱን እንደገና ያደራጃል፣ ወደተባበረ ትግልም ይገባል የሚል ግምት አለኝ፡፡ ተቃዋሚዎች ተባብሮ መታገልን መርጠው እንዲንቀሳቀሱ አደራዬ የጠበቀ ነው፡፡

Read 1845 times