Friday, 11 September 2015 09:30

የአዲስ ዓመት እንግዳ ከሰይፉ ጋር በሙሽርነት ማግስት የተደረገ ቃለ ምልልስ

Written by 
Rate this item
(13 votes)

የጫጉላ ሽርሽር የት አሰብክ?
ቤቴ ነዋ… የት አስባለሁ?! በአልም ስለሆነ ቤተሰብ ከቤት እንዳትወጡ ብሎናል፤ ስለዚህ እዚሁ ነው ልጄ … አዲስ አበባ፡፡ “ጫጉላ አብቧል ዛሬ እቴ ሸንኮሬ” ይባል የለ! ስፖንሰር ካደረግሽን ደግሞ የትም እሄዳለሁ፡፡
ለሰርግህ ያሰብከውን ወጪ ለበጎ አድራጎት ሰጥተሃል፡፡ አንዳንዶች ግን “ሰይፉ ካለው ላይ ሳይሆን ያለውን ነው የሚሰጠው” ይሄ እውነት ነው?
ለኔ ሲዘንብ ለነሱም ያካፋ ብዬ ነው (… ሳቅ …) ምን መሰለሽ ሰርግ ላይ ወዳጅ ዘመድ ጠርቶ ማስደሰቱ መልካም ነው፤ ግን አንዳንዱ ቀን የበላው ጠፍቶ ማታ ሲገባ እራት ይላል፡፡ ስለዚህ የማይጠፋውንና ለህሊና ደስታ የሚሰጠውን ነገር ለማድረግ ብዬ ነው… ለሰርጌ ወጪ ያሰብኩትን 300ሺህ ብር፤ 200ሺህ ለሙዳይ፣ 100ሺውን ደግሞ ለሜቄዶንያ የሰጠሁት፡፡
በየዓመቱ ለተመራቂ ተማሪዎች ሱፍ ትሰጣለህ የሚባለውስ እንዴት ነው?
እእእ …. ምን መሰለሽ በሰይፉ ኦን EBS ላይ በዓመት ከ30 እስከ 40 ሾዎች ይቀርባሉ፡፡ ሾው ያቀረብኩባቸውን ሱፎች ነው በዓመቱ መጨረሻ ላይ አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች የምንሰጠው፡፡ ምርቃት ለእነሱ ሰርግ ማለት ነው፡፡ በቀጣይም ከተለያዩ ሱፍ አምራቾች ጋር በመሆን በቋሚነት ሱፍ የምንሰጥበትን ፕሮግራም እናዘጋጃለን፡፡ እናም እኔ ቤት አሁን ብትመጪ ሱፍ ፍትፍት እንጂ ሱፍ አታገኚም፡፡ ለዓመታት ተምረው ሊመረቁ ሲሉ የሱፍ መግዣ የሚያጥራቸው ብዙ ተማሪዎች አሉ፡፡ እነሱ ያሳዝናሉ፡፡ እሱን በጥቂቱ ለመቀነስ ነው፡፡ እንግዲህ ከጀመርነው አንድ አራት ዓመት ሆነን፡፡
ለኮሜዲያን ደረጀ የ100ሺ ብር ስጦታ በአደባባይ መበርከቱን የሚቃወሙ ወገኖች አሉ፡፡ በሌላ መንገድ ማድረግ አይቻልም ነበር?
BGI ኢትዮጵያ የዛሬ ዓመት ለአባባ ተስፋዬ መኪና ሰጥቷቸው ነበር፡፡ ይኸኛው የዚያ ቀጣይ ክፍል ነው፡፡ አላማውም በዋናነት ለኮሜዲያኑ እውቅና መስጠት ነው፡፡ የቢጂአይ ሀሳብ፤ መሰጣጣትን ባህል ልናደርገው ይገባል የሚል ነው፡፡ የሟቹ ኮሜዲያን የሀብቴ ምትኩ እናት 50 ሺህ ብር ሲበረከትላቸው “ልጄ ሞቶም ይጦረኛል” ብለው አልቅሰዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች ለጥበብ ላደረጉት አስተዋፆፅኦ ምስጋናና ዕውቅና ስለሚገባቸው ነው፡፡
የሰይፉ ኦን ኢቢኤስ ሾው ፕሮግራሞች እየተደጋገሙ ይቀርባሉ የሚል ቅሬታ በተደጋጋሚ ይሰነዘራል፡፡ ምክንያቱ ምንድነው?
ምክንያቱ የኔ ስንፍና ነው፡፡ ያው የብዙ ጊዜ ስራይፈልጋል፡፡ በስራ ተወጥሮ አቅም የማጣቱ ነገር አለ፡፡ እንግዲህ በአዲሱ ዓመት ወጥሬ እሰራለሁ ብያለሁ፡፡፡
ሰይፉ ከሸገር ኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያ ሼር ገዝቷል እየተባለ ይወራል፡፡ እውነት ነው?
(…… ሳቅ …..) ሼር እኮ ነው የምንሰራው፤ ከምናገኘው እንካፈላለን፡፡ ያ ማለት ሼር ነው (… ሳቅ ….) ሸገር ውስጥ እራሴን እንደኮሚሽን ሰራተኛ አላይም፤ እንደ ቤተሰብ እንጂ፡፡ ከአበበም ከመዓዚም ጋር ያለን ቅርበት የቤተሰብ ነው፡፡ ያንን ቅርበት ያዩ ሰዎች ናቸው “ይኼማ በቃ ሼር አለው ማለት ነው” ብለው ያሰቡት፡፡ ያው እኔ በሰራሁበት ይከፈለኛል፤ በሸገር በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ እውነቱ ግን ከሚገኘው ገቢ በስምምነታችን መሰረት ከምንካፈለው ውጭ ጣቢያው ላይ ምንም አ…ይ..ነ..ት.. (ሳቅ) ሼ…ር.. የለኝም፡፡
አንዳንድ ሰዎች “ሰይፉ ኢንተርቴይነር እንጂ ጋዜጠኛ አይደለም” ይላሉ፡፡ አንተ ራስህን የምታስቀምጠው የቱ ጋ ነው?
ጋዜጠኛ ባልባል ደስ ይለኛል፡፡ ውጪ አገር ጋዜጠኝነት በራሱ የተለያዩ መመዘኛዎች አሉት፡፡ ዘርፉ ይለያያል፡፡ እኔ TV Host ነኝ፡፡ እውነቱን ለመናገር ጠንከር ያለ ነገር ብዙም አልወድም፡፡ እኔ የምወደው የሚያዝናኑ ነገሮችን ነው፡፡ ሰው እንደየራሱ ስሜት ስያሜ ይስጠኝ፡፡ ለራሴ ግን “ስያሜ አጣሁላት” የሚለውን ዘፈን ጋብዣለሁ፡፡
አንዳንዴ በአርቲስቶች ላይ ክብረ ነክ ቀልዶችን ትቀልዳለህ ይባላል፡፡ እንደውም በአንድ ወቅት አንድ አርቲስትን “ይሄን ፊት ደገምከው” ብለሃል ተብሎ ይወራል፡፡ እውነት ነው?
አንዳንድ ጊዜ የሚባሉ ነገሮች ማስረጃ የላቸውም፡፡ ይኼንን እኔ በጭራሽ አላልኩም፡፡ ዘውዱ እራሱ ሰይፉ ኦን ኢቢኤስ ሾው ላይ ቀርቦ ተናግሯል፡፡ እኔ እንደውም ብዙ ግዜ የምታወቀው እራሴ ላይ በመቀለድ ነው፡፡ ኢትዮጵያ  በመሆኑ ነው እንጂ ሌላ አገር ፕሬዚዳንቱ ላይ ሳይቀር ይቀለዳል፡፡ የኛ አገር ኮሜዲያን ትልቅ ደረጃ የማይደርሱት በተለያየ ምክንያት ስለሚገደቡ ነው፡፡ እንደ ልብ መቀለድ የለም፡፡
ያለፉትን የሥራ ዓመታት እንዴት ትገልፀዋለህ?
እንግዲህ መጀመሪያ አካባቢ “ሆሊውድ” ጋዜጣ ላይ ነበር የምሰራው፤ የኔ መሰረት ጋዜጣ ነው፡፡ ያኔ የአገር ውስጥና የባህር ማዶ የመዝናኛ ዜናዎችን ጋዜጣ ላይ እሰራ ነበር፡፡ ለጋዜጣ አሁንም ድረስ ልዩ ፍቅር አለኝ፡፡ ከጋዜጣ ሥራ በጣም የሚገርመኝ ምኑ እንደሆነ ታውቂያለሽ    ?  ስትሰሪው አድረሽ ጠዋት ታትሞ ሲወጣ ሁሌ ስህተት አይጠፋውም፡፡ (ሳቅ …) በመቀጠል “አዲስ ዜማ” ኤፍኤም 97.1 ላይ ነው የሰራሁት … ከዚያ በኋላ “ኢቲቪ ሚዩዚክ” …እያለ እያለ አሁን “ታዲያስ አዲስ”፣ “ሰይፉ ኦን ኢቢኤስ” በቃ… ይኸው ነው፡፡
ምነው ፊልሙን እርም አልክ?
እባክሽ ጊዜ ጠፋ፡፡ “ይፈለጋል” የተሰኘው ፊልሜ አድካሚ ነበር፡፡ ፊልም ድካሙና ገቢው አይመጣጠንም፡፡ በርግጥ ወጪውን መልሷል፡፡ ለአምለሰት ሙጬም (የቴዲ አፍሮ ባለቤት) የመጀመሪያ ስራዋ ነበር፡፡ አሁን ግን “ታዲያስ አዲስ” አለ፤ “ሰይፉ ኦን ኢቢኤስ” አለ… አጉል መወጣጠር ነው የሚሆነው፡፡
ከድምፃዊ ሚካኤል በላይነህ ጋር ተዛመድክ አሉ?
(ሳቅ ….) አንዱ እንደውም ባለቤቴ የሚካኤል የሚስቱ እህት ናት ስለው፤ “ለዛ ነዋ ታዲያስ አዲስ ላይ ጠዋት ማታ ሚካኤል በላይነህን የምትጋብዘን” አለኝ፡፡ አዎ … አማች ሆነናል፡፡
አሁን እንግዲህ የቀረህ ልጅ መውለድ ነው …
እንግዲህ እንደ እግዚአብሔር ፍቃድ ነው፡፡ ግን እኛ ቤት 3 ወንድና 1 ሴት ነው ያለው፡፡ እኔ የመጀመሪያ ልጅ ነኝ፡፡ በኔ ህይወትም ይህ ቢደገም ደስ ይለኛል፡፡ ዋናው ግን ጤነኛ ልጅ መሆኑ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ሴት ፀጋ ናት፤ ወንድም በረከት ነው፡፡
ባለቤትህ ሙያዋ ምንድነው?
ባለቤቴ …. ሆስተስ ነበረች፡፡ ነርስም ነበረች፡፡ አየሽ ከዚህ በኋላ የህክምና ወጪ አያሰጋኝም፡፡ የማርኬቲንግም ምሩቅ ናት፡፡ በቃ (…. ሳቅ ….) የማስታወቂያ ነገር እንግዲህ አያሳስበኝም … አሁን በማርኬቲንጉ እየሰራች ነው ያለችው፡፡ ምን አለፋሽ 3 ሚስት ነው ያገባሁት፡፡ ሆስተስ … ነርስ … የማርኬቲንግ ባለሙያ ማለት ነው፡፡
2007 እንዴት አለፈ?
ለ2007 ዘፈን ጋብዘው ብትይኝ… “እያነቡ እስክስታ” የሆነበት ዓመት ነው፡፡ ጥሩም መጥፎም ተከስተዋል፡፡ የኦባማ መምጣት ትልቅ ነገር ነው፡፡ በአገራችን ላይ የተከሰተው የድርቅ አደጋ ደግሞ በጣም የሚያሳዝን ነገር ነው፡፡ ሁለቱ ለየቅል ነው፡፡ እኔ ደግሞ መቼ ነው ያገባኸው ስባል “በ2007” የምልበት ነው፡፡
የሚገርመው ነገር ያገባሁት ልክ በልደቴ ቀን ነው፡፡ ያው እድሜ እንደሆነ አይገለፅም፡፡ 2008 ሳይገባብኝ ነው የሸወድኩት፤ በአንድ ሳምንት ልዩነት 2008ን መቀላቀሉ አስደስቶኛል፡፡ እንዳልኩሽ ያለፈው ዓመት አሪፍም ነገር አለው ደስ የማይልም ነገር አለው፡፡
በአዲሱ ዓመት ምን …
በ2008 … ወጥሬ አድማጭና ተመልካችን ለማስደሰት እሰራለሁ፡፡ ሰይፉ ኦን ኢቢኤስም የማይደጋገምበት ዓመት ይሆናል፡፡ የቅድሙን ቃል ልጠቀመውና (ሳ…ቅ…) በአዲሱ ዓመት እንደ እግዚአብሔር ፍቃድ ይሄንን ፊት እደግመዋለሁ፡፡ እስቲ እናንተንም ልመርቅ …
 “አዲስ አድማስ”ን እንደ “ዋሽንግተን ፖስት” በሚሊየን ቅጂዎች የሚሰራጭ ያድርግላችሁ!
አንቺም ከጠያቂነት ወደ ተጠያቂነት የምታድጊበት ያርግልሽ!
መጣ የተባለውንም ርሃብ እግዚአብሔር በአጭሩ ያስቀረው!! የጥጋብ ዘመን ይሁንልን!!
የምንዋደድበትና የምንረዳዳበት የሰላም ዓመት እንዲሆን እመኛለሁ፡፡
ለኢትዮጵያ ህዝብም እንኳን አደረሳችሁ ብያለሁ!!

Read 6447 times