Saturday, 19 September 2015 09:02

“አትሌቲክሱ አማካሪ አካል ያስፈልገዋል”

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

    አቶ ደቻሳ ጅሩ ይባላሉ፡፡ ትውልዳቸው ከበቆጂ 20 ኪ.ሜ ርቃ ከምትገኘው ሽርካ ከተማ ነው፡፡ ተማሪ በነበሩ ጊዜ የማራቶን ሯጭ ለመሆን መሞከራቸውን የሚናገሩት አቶ ደቻሣ፤ ለስፖርቱ ከፍተኛ ፍቅር ቢኖራቸውም አትሌት መሆን ግን አልቻሉም፡፡ በላቀ ደረጃ የተማሩ የእርሻና ደን ጥምር ተመራማሪ ናቸው፡፡ ከጅማ ኮሌጅ የመጀመሪያ ዲፕሎማቸውን በእርሻ አግኝተዋል፡፡ ከአለማያ ዩኒቨርሲቲ በእጽዋት ሳይንስ ቢ.ኤስ.ሲ ድግሪ ሠርተዋል፡፡  በጣሊያን ከሚገኝ ዩኒቨርሲቲ በምግብ ሥርዓት  አድቫንስድ ዲፕሎም አግኝተዋል፡፡ ከአውስትራሊያው የሜልቦርን ዩኒቨርሲቲ ደግሞ የማስትሬት ዲግሪያቸውንም በ “አግሮ ፎረስተሪ” ተቀብለዋል፡፡ ከእርሻና ደን ጥምር ምርምራቸው ባሻገር አቶ ደቻሣ አትሌቲክስን በጣም ልዩ ትኩረት ይሰጡታል፡፡ በፍቅርና በፍላጐት አትሌቶችን ይከታተላሉ፡፡ የኢትዮጵያን ሯጮች የስልጠና እና የውጤት ሁኔታዎችን ባገናዘቡ ጥልቅ ምርምሮችንም እያደረጉ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ የሳይንስና የምርምር አቅጣጫዎች እንዲሁም ጥበባዊ ዕይታዎች ላይ ያተኮረ የመፅሃፍ ዝግጅታቸው ከ500 ገፆች በላይ ሆኗል፡፡ ለህትመት ለማብቃትም የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ናቸው፡፡ ከ40 ዓመታት በላይ በተቀናጀ ግብርና ምርምር (በአዝርዕትና በእንስሳት) ላይ በመስራት ከፍተኛ ልምድ ማካበታቸው ትልቅ አቅም መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ ይህን ልምዳቸውንም በስፖርቱ በተለይም በአትሌቲክስ ላይ ለመተርጐም ይፈልጋሉ፡፡  የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ወደ ሳይንስና ምርምር መጠጋት እንዳለበትም የሚመክሩት አቶ ደቻሣ፣  በሥነምህዳር እና በአየር ተስማሚነት የኢትዮጵያን አትሌቲክስ የሚያሳድግ ጥልቅ ምርምር ማድረጋቸውን ያስረዳሉ፡፡ ስፖርት አድማስ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ የለውጥ አቅጣጫ ላይ ያተኮረውን ምርምራቸውን  በመንተራስ ከአቶ ደቻሣ ጅሩ ጋር ሰፋ ያለ ቃለምልልስ አድርጓል፡፡ የቃለምልልሱን የመጀመሪያውን ክፍል እንደመግቢያ ከዚህ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

     

        የእርሻና ደን ምርምር ተመራማሪነት ሙያዎን ከስፖርቱ ጋር እንዴት ያዛምዱታል?
ጥያቄህን የምገነዘበው ወጣና ለየት ባለ መንገድ ነው፡፡ ሃሳቤ እንደመጫኛ ረጅም ሆኖ ይያያዛል፡፡ እንደሰፌድ ላይ እህል ብትን ያለ የተቆራረጠ ሊሆን ይችላል፡፡ በአጠቃላይ አስተሳሰቤን በድር ልትመስለው ትችላለህ፡፡ በእርሻና ደን ጥምር ምርምር ባተኮረው ሙያዬ የረጅም ዓመታት ልምድ ውስጥ አግኝቻለሁ ራሴን ባይ ነኝ፡፡
ከስፖርቱ ጋር ያለው ትስስር በ60ዎቹ ተማሪ  በነበርኩ ጊዜ የተቆሰቆሰ ፍላጐት ነው፡፡ ያኔ ማናችንም ወንድ ተማሪዎች ስንዘፍን እንደ ጥላሁን ስንሮጥ እንደ አበበ ቢቂላ መመኘትና ማለም የጸና ፍላጎታችን ነበር፡፡ በወቅቱ  የሙዚቃ አርቲስቶቻችን ‹‹ጥላሁን ገሰሰ ይድርሻል፤ አበበ ቢቂላ ያገባሻል›› እያሉ በመዝፈን አትሌቱን ሙሽራ ያደርጉታል፡፡ በተለይ ይህን የመሰለው ሁኔታ ይማርከኝ ነበር፡፡ ጐበዝ ተማሪ ስለነበርኩ ያኔ ከትምህርቱ ጐን ለጐን በስፖርትም ጐበዝ የመሆን ፍላጐት ስለነበረኝ በንቃት በመሳተፍ አልፌበታለሁ፡፡
በከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ተማሪነቴ ደግሞ በተለይ በጂዮግራፊ ትምህርት በጣም ጐበዝ ነበርኩ፡፡ ስለ አየር ንብረት እና መልከዓ ምድር ሁኔታዎች ላይ በነበረኝ የምርምር ፍላጐት እታወቅ ነበር ለአስተማሪዎች ከባድ ጥያቄዎችን የማንሳት ልምዱም ነበረኝ፡፡ ኮሌጅ ስገባ ደግሞ በሜትሮሎጂ ዙሪያ ከፍተኛ ፍላጐት አሳይ ስለበር፡፡
አንዳንድ አስተማሪዎች በሜትሮሎጂም ትምህርት እንድገፋበት ይመክሩኝም ነበር፡፡ የአየር ንብረት እና የመልዕክዓ ምድር ሁኔታዎች ከስፖርቱ ጋር ከፍተኛ ተያያዥነት እንዳላቸው ማንም ይረዳዋል፡፡
በእርግጥ የእርሻና ጥምር ደን ምርምር ባለሙያ እንደመሆኔ በዚህ ዋና የግብርና ዘርፈ- ብዙ ተግባራትን አከናውናለሁ፡፡ ሞያው ቴክኖሎጂን ከማፍለቅ በዘለለ ለማህበረሰቡ ስልጠና መስጠት እና ግኝቱን ማስረጽንም ያካትታል፡፡ የሙያው ይዘትና ተግባር ከላይ እንደገለጽኩት ሆኖ፡-  እርሻና ደን ጥምር (አግሮፎርስተሪ) ምርምር  ሲገለጥ ሳይንስ አርትና ቢዝነስ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡  አካባቢን የሚያስጠብቅ፤ የኢኮኖሚ ፋይዳ ያለውና ማህበረሰቡ ተቀብሎት የሚተገበር የምርምርና የማስፋፊያ የስራ ሂደት ነው፡፡ የእርሻና ደን ጥምር ምርምር ባለሞያ የሆነ ሰው ሳይንቲስት ብቻ አይደለም አርቲስትም ነው ማለት ይቻላል፡፡ የአካባቢ ጥበቃ ተቆርቁሪ ሆኖ ደንንና ፋይዳውን በዋናነት ትኩረት በመስጠት በማስቀደም ይንቀሳቀሳል፡፡ ሰብልና እንስሳትን አካቶ በተጣመረ/በተቀናጀ/ መልኩ ማየትን መስራትንም ይችላል፡፡ ከ40 ዓመታት በላይ በሙያው ያገለገልኩት በዚህ ዓይነት ቁርጠኛ አቋም ነው፡፡ በአጠቃላይ ባለሁበት ሙያ ፈረሱን ሯጭ፣ በሬውን ጐታች፤ ላሟን ወተት ስጭ፤ ከብቱን ስጋ ስጭ፣ ዶሮዋን እንቁላል ጣይ…ወዘተ ለማድረግ ብዙ ምርምሮችን በማድረግ ሠርቻለሁ፡፡ እነዚህን የምርምር አቅጣጫዎች በሰው ልጅ ላይ ለመተግበር በስፖርቱ ለውጥ የሚፈጠርባቸውን ሁኔታዎች ለመተባበር እንደሚቻል ፍፁም እምነት አለኝ፡፡  
በሳይንሳዊ ልማት ያተኮረው ሙያዎ ተቀራራቢነት በሌለው የአትሌቲክስ ዘርፍ ላይ እንዴት ይተረጐማል? በስፖርቱ ላይ ጠለቅ ያለ ሳይንሳዊ ግምገማና አስተያየት መስጠትስ አይከብድም ወይ?
ጥያቄህን በጥያቄ ልመልሰው? ‹‹አትሌቲክስን ኢ-ሳይንሳዊና ጸረ-ልማት ያደረገው ማነው›› አላግባብ? ስለምንለያየው እንጂ አትሌቲክሱም ሳይንሳዊ ልማት ነው፡፡ በእርግጥ ሳይንሳዊ ግምገማ እና አስተያየት መስጠት ይከብዳል ማለትህ ልክ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ማንኛውም የምርምር መስክ ከባድ ነው፡፡ የባለሙያው ኃላፊነት ከባድንቱንና ውስብስብነቱን ማቅለል እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ የወደፊት አቅጣጫዎች ስርነቀል ለውጥ እንደሚያስፈልግ አስተያየቶች ይሰጣሉ፡፡ በዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቅረብና ውጤታማ ለመሆን ስፖርቱ ያለበት ደረጃ አስተማማኝ አይደለም፡፡ ከፌዴሬሽኑ እና ከአትሌቶች ባሻገር የለውጥና የዕድገት አቅጣጫዎችን በመቀመር ወሳኝ ሚና መጫወት ያለባቸው ባለድርሻ አካላት እነማን መሆን አለባቸው?
በርግጥ ስር ነቀል ለውጥ የሚለው አካሄድ ትንሽ የሚከብድ ይመስለናል፡፡ የባሰ ችግር ሊፈጥር ስለሚችል ነው፡፡ የዛፍ ሰው ስለሆንኩ መሰለኝ፣ ከስሩ መንቀል መጣል የሚያዋጣ አይመስለኝም፡፡ ማን ማንን ይተካል፣ የቱን ግንዛቤ ብናዳብረው የተሻለ ይሰራል በሚለው መንገድ ለውጥን ማሰብ ይሻላል፡፡ ስለስፖርቱ የወደፊት አቅጣጫዎች ምላሽ ሰጪዎቹ ከሞያው ጋር ይበልጥ አግባብነት ያላቸው የፌዴሬሽን ባለሙያዎች እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ ከፌዴሬሽኑ፣ ከስፖርት ኮሚሽኑ እና ከአትሌቶች ባሻገር ግን የላቀ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችሉ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ብዙ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል አትሌቲክሱ ሳይንሳዊ በሆኑ አቅጣጫዎች መመራት አለበት፡፡ እንደሰማሁት የአትሌቶች የሙያ ማህበር መቋቋሙ አንድ ትልቅ እምረታ ነው፡፡  በማንኛውም የሙያ ማህበር እንደምናየው ግን መሆን የለበትም፡፡ ከመዋጮ ክፍያ እና መብትና ግዴታ ከማስጠበቅ ባሻገር በስፖርቱ ዕድገት ማህበሩን ውጤታማ ተግባር እንዲወጣ ማስቻል ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም ከተለመደው የፌዴሬሽኑ መዋቅር ውጭ ለስፖርቱ ለውጥና ዕድገት ወሳኝ ግብአቶችን የሚሰጡትን ሌሎች ባለድርሻ አካላት አስተባባሮ መንቀሳቀስ ግድ ነው፡፡ ባለሙያዎቹ በየመስኩ ያላቸውን እውቀትና ልምድ በማገናዘብ ጠቃሚን መረጃዎች የሚያቀርቡበት ሂደት መፈጠር አለበት፡፡ ለአሰልጣኞችና ለአትሌቶች ድጋፎችን በመስጠት እንዲሳተፉ ማድረግ ነው፡፡  ከዓለም ጋር ተፎካካሪ ሆኖ ለመቅረብ፣ በየጊዜው ተተኪ አትሌቶችን በተሟላ ብቃት ለማውጣት የሚቻለው በዚህ ዓይነቱ አቅጣጫ ብቻ ነው፡፡ በከፍተኛ ምርምር እና ቅንጅታዊ ስራዎች  ላይ ሁሉም ወሳኝ ባለድርሻ አካላት አስተዋጽኦ እንዲኖራቸው ያስፈልጋል፡፡ የግብርና፤ የጤና፣ የስነምግብ፣ የስነልቦና፣ የአየር ሃይል፣ የአየር መንገድን፣ የሜትሮሎጂ ባለሞያዎች የሚያካትት መዋቅርን ፌዴሬሽኑ ማመቻቸት ይጠበቅበታል፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች ከባለሞያዎቹ ጋር በዚህ ጉዳይ ስንወያይ ሁሉም የበኩላቸውን  ማድረግ እንደሚፈልጉ ይገልጻሉ፡፡ ፌዴሬሽኑ ለፍላጐታቸው ትኩረት ሰጥቶ አቅማቸውን መጠቀም አለበት፡፡
እርስዎን ጨምሮ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ ያሏቸውን ባለሙያዎች ወደ ስፖርቱ ማቅረብ የሚቻለው እንዴት ነው?
የመጀመሪያው ርምጃ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ፣ የአትሌቶች ማህበርና የስፖርት ኮሚሽኑ ሌሎቹን ባለድርሻ አካላት አሰባስበው ለውጥ ሊፈጥሩ የሚችሉበትን መድረክ መፍጠር ነው ይህን አስመልክቶ በአገር አቀፍ ደረጃ ምክክር የሚደረግበትን የስብሰባ መድረክ ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡   
ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ውጤት ማሽቆልቆል ፌዴሬሽኑ ብቻ ሳይሆን ሁላችንም ተጠያቂ ነን፡፡ ይህ ስል የአስተዳደሩንና የአመራሩን ድክመት ወደ ጐን በመተው አይደለም፡፡ እንደዜጋ ያገባናል የምንል የሁሉም ዘርፍ ባለሙያዎች ግን ተጠያቂ ከመሆናችን በፊት አብረን የምንሠራበት ዕድል አልነበሩንም፡፡ እንደሚባለው አብረን መብላት እንጂ አብረን መስራት የማንችል ሆነናል፤- ለስራ ያለን ትኩረት ግለሰባዊ ነው፡፡ የቡድን ስራ ውጤታማ እንደሚያደርግ ፍልስፍናው በስኬት ላይ መንጸባረቁ እንደማይቀር የምንገነዘብ ይመስለኛል፡፡ የምክክር መድረኩ ተዘጋጅቶ ከዚያም ሁሉም ባለሙያ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዴት ማቅረብ እንደሚችል ከሌሎች ጋር ተማክሮ መወሰን ይጠበቅበታል፡፡ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ በተናጠል ድጋፍ የሚያደርግለት አማካሪ አካል ያስፈልገዋል፡፡
የአትሌቶችን ውጤታማነት በመፈታተን ለከፍተኛ ውጣውረድ የሚዳርጓቸው በርካታ ሁኔታዎች አሉ፡፡ የጤና በስነልቦና ያለመረጋጋትን ጨምሮ፤ የግል ብቃት፤ ከአሰለጣጠንና አቀባብል ጉድለትና ከመሳሰሉት የሚመነጩ ክፍተቶች ብዙ ናቸው፡፡….(ይቀጥላል)

Read 3252 times