Saturday, 19 September 2015 09:38

በአብነት ስሜ ላይ ለተሰነዘሩ ትችቶች የተሰጠ ምላሽ

Written by  አደዳ ኃይለሥላሴ
Rate this item
(3 votes)

 መግቢያ
አብነት ስሜ፣ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ በነሐሴ 16 እና 23 ቀን 2007 ዓ.ም የወጣ “ወሪሳ-የዓለማየሁ ገላጋይ ትንቢታዊ ድምፆች” የተሰኘ ኂሳዊ ንባብ ማቅረቡ ይታወሳል። ለዚህ ጽሁፍ ምላሽ ነው ብለው ተስፋ በላይነህ የተባሉ ጽሑፍ አቅራቢ “አብነት ስሜ ራሱ ፈራጅ ራሱ ወራጅ” የሚል መጣጥፍ አቅርበዋል። ይኸ ጽሑፍ የዚያ ምላሽ ነው። አብነት ወሪሳ በተባለው ልቦለድ ላይ ያቀረበው የአስተያየት ብእሮግ፣ አንድም እንዲህ ማለት ይሆናል፤ አንድም እንዲህ ነው በሚል አካሔድ የቀረበ አንድምታዊ ትርጓሜ ነው። አንድም ማለት ቃል በቃል ወይም ማለት ነው። አብነት ለዚህ አስረጂ ከሀገራችን የአንድምታ ትርጓሜ ባህል አንድ ምሳሌ ጠቅሷል፤ [የፈርዓን ልጅ ገላዋን ትታጠብ ዘንድ ወደ ዐባይ ወንዝ ወረደች። የፈርዖኑ ልጅ የተርሙት ወደ ዐባይ ወንዝ መውረድ አራት አንድምታዊ ትርጓሜዎች ተሰጥተውታል፤ አንድም ለህክምና ጠበል፤ አንድም ለድብቅ ፍቅር፤ አንድም ለጉማሬ አምልኮ፤ አንድም ለውሀ ዋና ትምህርት ብሎ።] ተቺው ይህንንም ጥበብ ቢተቹ መልካም ነበር። ነቢዩ ሙሴን ከባህር ያወጣች ሰው እንዴት ጉማሬ አምላኪ ትባላለች ብለው ቢሞግቱም ሸጋ ነበር።
በወሪሳ ውስጥ የተካተቱት ማኅበራዊ ጉዳዮች የገሀዱ ዓለም ነፀብራቆች ናቸው። እነዚህ ጉዳዮች ማኅበራዊ ህፀፆች፣ እንከኖች፣ ቁስሎች ወይም ህመሞች ተብለዋል። የተጻፈው ይሄ ነው። ብእሮገኛው የተሸፋፈነ ቁስል አይድንም፤ ይገለጥ ነው ያለው። ይኸ ቁስል ሲነካ ሊቆጡ የሚችሉ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ አስቀድሞ ተናግሯል። ለዚህ አንድ ሰው ተገኝተዋል። ከዚህ በመቀጠል እኒህ ሰው ባቀረቡት መጣጥፍ ላይ አስተያየት አቀርባለሁ።

      ሒስ እና ኂስ
በተለይ በፈጠራ ጽሑፍ ላይ አስተያየት ሲሰጥ ሒስ እና ኂስ የተሰኙ ቃላት በመተካካት ጥቅም ላይ ሲውሉ ይታያል። ሒስ ነቀፋ፣ ነውር፣ ክስ፣ ስድብ፣ ጸያፍ ማለት ነው። ኂስ ደግሞ ማሻሻያ፣ ማብለጫ፣ ማላቂያ ማለት ነው። ለምሳሌ ይኄይስ የተሰኘው ቃል ይሻላል፤ ይበልጣል የሚል ፍች አለው። ዝርዝር ማብራሪያውን በኪዳነወልድ ክፍሌ መዝገበቃላት (ገጽ 443 እና 477) ውስጥ ማግኘት ይቻላል። በድርሰት ላይ የሚሰጥ አስተያየት ከሒስ ይልቅ ኂስ ቢሆን የሚመረጥ ይመስለኛል። አብነት የሞከረው ኂሳዊ ንባብ ለማቅረብ ነው።
ነቢይ እና ትንቢት
ነቢይ የመጪውን ብቻ ሳይሆን ያለፈውን እና የአሁኑንም የሚናገር ሰው ነው። ዝርዝሩን በደስታ ተክለወልድ መዝገበቃላት (ገጽ 832) ውስጥ ማየት ይቻላል። ትንቢት በነቢይ የሚነገር ቃል ነው። ቃሉ የመጪውን ጊዜ ብቻ ሳይሆን ያለፈውን እና የአሁኑንም ያካትታል። ነቢይ ሌላው ዝም ያለውን የሚናገር ማለት ነው። ትንቢት የታየ ብቻ ሳይሆን የተነገረ ነገር ማለት ነው። ያ የታየ ነገር ደግሞ የወደፊቱን ብቻ ሳይሆን ያሁኑንም ያለፈውንም ያካትታል።
አብነት፣ ደራሲውም እንደ ነቢይ ይታያል ያለው ደራሲው ሌላው ዝም ያለውን ይናገራል ለማለት ብቻ ነው። ስለመጪው ዘመን  ትንቢት ተናግሯል አላለም። ስለአሁኑም ዘመን ትንቢት መናገር ይቻላል። ነቢይ የሚለው ቃል አሻሚ እና አወዛጋቢ ከሆነ ነባይ የሚለውን ተለዋጭ ቃል ብንጠቀመውም ይቻላል። ነባይ ተናጋሪ በሚለው ፍችው ብቻ ተገድቦ ማለት ነው። ትንቢት የሚለውን ቃልም የተከሰተ ወይም የተገለጠ ወይም የተነገረ በሚለው መተካት ይቻላል። ትችት አቅራቢው ይህንን የተረዱት አይመስልም።
ህልም
አብነትን “ራሱ ፈራጅ ራሱ ወራጅ” በማለት የጻፉት ግለሰብ፣ “ጸሐፊው [አብነት] ስለ ህልም ምንነት፣ አስፈላጊነት እና የዕለት ተዕለት ትስስር ለመጥቀስ ይሞክራል” ብለው ጽፈዋል። አብነት በጽሑፉ ስለ ሕልም ጻፈ እንጅ ለመጻፍ አልሞከረም። የጻፈው አሉባልታ አይደለም። እሱ የጻፈው ካነበበው፣ ከመረመረው፣ ካጠናው እና ካስተዋለው ነው። ስለ ሥነህልም ከ50 በላይ መጻሕፍትን እንዳነበበ አውቃለሁ። በሀገራችን የህልም አፈታት ላይ የተጻፉ ሁለት የዲግሪ ማሟያ ጥናቶችን እንዳማከረ አውቃለሁ። በሀገራችን የህልም አፈታት ላይ በተዋበ ብእሩ ያዘጋጀው ዳጎስ ያለ መጽሐፍም እንዳለው አውቃለሁ። እንኳን የአብነት ስሜ ይቅርና የሲግመንድ ፍሮይድ የህልም እና መሰል ትወራዎችም ተፈትነዋል፣ ተፈትሸዋል፣ ተተችተዋል። የአብነትን ሐሳብ ማብጠልጠል እና መተቸት ተገቢ ሊሆን ይችላል። ስድብም እንኳን ቢሆን በሚመጥነው ሰው ቢሆን ይሻል ነበር። ለነገሩ አብነት የተለየ ሐሳብም አላራመደም፤ የህልም ትንታኔ ነባር ዕውቀት ነው።
ትወራዊ ማእቀፍ (Theoretical Framework) እና ጽንሰ-ሐሳባዊ ማእቀፍ (Conceptual Framework) አንድነት እንዳላቸው ሁሉ ልዩነትም አላቸው። አብነት የተጠቀመው ሁለተኛውን ነው። ልቦለድን-እንደ-ህልም-መፍታትን አብነት በተጠቀመበት መልኩም ባይሆን ያንግን የመሳሰሉ የሥነልቦና ሊቃውንት አራምደውታል። በሀገራችንም ሚካኤል ሺፈራው የተባሉ አስተዋይ ኀያሲ፤ “ምስጢረኛው ባለቅኔ” በተባለው ድንቅ መጽሐፋቸው ውስጥ በተግባር አውለውታል። ይህን ዘዴ አብነትም በራሱ መንገድ ተጠቅሞታል።
አብነት በ1986 ገና የቅድመ-ምረቃ ተማሪ እያለ የልቦለድ ገፀባህርያትን በሥነልቦናዊ ማእቀፍ ውስጥ የሚተነትን የጥናት ወረቀት እንዳቀረበ አውቃለሁ። በዚህ ወረቀቱ የአበራ ለማን “እቴሜቴ” እና የስብሐት ገብረእግዚአብሔርን “አሮጊት” አኂሷል።  የጥናቱ ወረቀት የተደነቀ እንደነበረ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነጽሑፍ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑትን አቶ ዘሪሁን አስፋውን መጠየቅ ይቻላል።
አስትሮሎጂ
አብነት ልቦለድን ለማኄስ እና ለመተንተን ህልምን፣ ሥነልቦናን እና አስትሮሎጂን ያጣመረ ጽንሰሐሳባዊ ማእቀፍ ነው የተጠቀመው። ይህን በዋናነት በሀዲስ ዓለማየሁ “ፍቅር እስከ መቃብር” እና በዓለማየሁ ገላጋይ “ወሪሳ” አሳይቶታል። ይህን የሥነኂስ ስልት ጉልበቱን እና ድክመቱን በመንቀስ ጥርት አድርጎ የሚጽፍ ቢኖር እሰየው ነበር። ብእሮገኛውን ግን በድፍኑ “ግልብ” ማለት ነውር እና አላዋቂነት ነው የሚሆነው።
ልቦለድን እንደ ህልም ማየት አዲስ ነገር አይደለም። የዘመናችን ሊቃውንት “Collective Memory” እና “Collective Thought” ላይ ብዙ ተራቅቀዋል። ልቦለድን በሥነልቦናዊ ማእቀፍ ውስጥ ማየትም የተለመደ ነው። የአስትሮሎጂ ሊቃውንትም አስራሁለቱን ኮከቦች ሲያብራሩ፤ አልፎ አልፎም ቢሆን ከአፈታሪክ፣ ከልቦለድና፣ከተውኔት ገፀባህርያት ይጠቅሳሉ። ይህን ደግሞ አብነት አልደበቀንም። በየኢትዮጵያ ኮከብ እና በፍካሬ ኢትዮጵያ መጽሐፉ ውስጥ ተናግሮታል። አብነት በተለየ ያደረገው ነገር የልቦለድ ገፀባህርያትን በአስትሮሎጂ ማእቀፍ ውስጥ መተንተንን ነው። ይህንንም በድብቅ አላደረገውም። በ2001 በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተዘጋጀ ዐውደ ጥናት ላይ “የጉዱ ካሳ ኮከብ” በሚል ርእስ ጥናት አቅርቧል። ጥናቱን “ቼይር” ያደረጉት ዶ/ር ዮናስ አድማሱ ነበሩ። በወቅቱ ዶ/ር ፈቃደ አዘዘን፣ ደረጀ ገብሬን ጨምሮ ብዙ የሥነ ጽሑፍ መምህራን ነበሩ። ያኔ ሙከራው መደነቁን እንጂ አቅራቢው “ግልብ” መባሉን አልሰማሁም።
እኔ አብነት ስሜን “ወደር እና እንከን የሌለው ጸሐፊ ነው” አላልኩትም። ዕውቀት በተፈጥሮው ሁሌም እንከን ይኖረዋል። ሳይንስና ዕውቀት ፍጹም አይደሉም። ሙሉ በሙሉ ውድቅ ሊሆኑ፣ ሊሻሻሉ እና ፈርሰው ሊገነቡ ይችላሉ። አንድ የሥነጽሑፍ እና የሥነልሳን ተማሪ የሆነ ኀያሲም ከዚህ ውጭ አይሆንም። መምህራንም ሆኑ ምሁራን ፍፁም አይደሉም። ነገር ግን፣ የሚጽፈውን ነገር ጠንቅቆ የሚያውቅን ታታሪ ሰው፣“ግልብ” የሚል ጸሐፊ የአእምሮው ጤንነት ያጠራጥራል።
በወሪሳ አንድምታዊ ትርጓሜው ላይ አብነት በቁጣ ተሞልቶ (passionate ሆኖ) የጻፈው ይመስለኛል። ይኸ ለሀገሩ እና ለወገኑ ካለው ጥልቅ ፍቅርና መቆርቆር የመነጨ ስሜት ሊሆን ይችላል። እዚህ ላይ ቅሬታ ያለው አስተያየት ሰጪ ተጠየቃዊነት ያለው ጭምት ወይም አካዳሚያዊ አስተያየት ቢሰጥ እደሰታለሁ እንጂ አልከፋም። እሱ የተጠቀመውን ጽንሰሐሳባዊ ማእቀፍም በአካዳሚያዊ ባህል ፉርሽ የሚያደርግ ጽሑፍ ባነብ የምበሳጭ ሰው አይደለሁም። ከአፍላጦን ጀምሮ እስከ ሆኪንግ ድረስ ያልተሳሳተ ምሁር የለም። ፍፁምነት ቢኖር ኖሮ የዓለማችን ሳይንስና ዕውቀት እንደ ድንጋይ ቆሞ ይመለክ ነበር። ሳይንስ ዘወትር እየታረመ እና እየጠራ የሚጓዝ ትሁት መንገደኛ ነው።
ኅሊና
አስተያየት ሰጪው፣ በመጣጥፋቸው በአንቀጽ 11 ላይ ጸሐፊውን “እሱ ምን ያድርግ ንቁውና ስውሩ ኅሊናው ተምታቶበት!!” ብለውታል። ይህን ሐረግ እንደመሰለኝ አብነት “ክሱት እና ስውር ዕውቀት” ከሚለው ላይ አንሻፈው ወስደውት ነው። ይኸ ሐሳብ በሥነልቦና የጥናት ዘርፍ ውስጥ በስፋት የታወቀ ነው። ልዩነቱ አብነት የተጠቀመው አማርኛ ብቻ ነው። ክሱት የተገለጠ እና ፊት ለፊት ያለ ማለት ነው። ስውር ደግሞ ኅቡእ ወይም የተደበቀ ማለት ነው። አእምሮአችን የሚደብቃቸው ብዙ ሐሳቦች አሉ። በሀገራችን ብሂልም፣ “ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል” ይባላል።  ሆድ ያባውን ማለት ሆድ የደበቀውን ማለት ነው። ሆድ ያባው አእምሮ የደበቀው ማለት ነው። ሆድ ወይም ልብ የተሰኙ ቃላት አእምሮ ማለትም ይሆናሉ። ሰዎች በመጠጥ ሞቅታ ብቻ ሳይሆን በህልም ወይም ደግሞ በፈጠራ ጽሑፋቸው ውስጥ ሆዳቸው ያባውን የ“ስውሩን አእምሮ” ድብቅ ነገር ያወጣሉ ተብሎ ይታመናል። ይህንን በነፍሮይድ፣ በነካርል ያንግ እና ከነሱ በቀጠሉ ምርምሮች ውስጥ ማንበብ ይቻላል። ይሄ ነገር በሌላ አገላለጽ በሁለተኛ ቋንቋ ችሎታችን ፍዝ (passive) እና ንቁ (active) ቃል የምንለው ነው። አብነት ይህን ዕውቀት ነው የጠቀሰው። አንድ ሰው ፍዝ እና ንቁ ቃላቱ ተደባለቁበት ተብሎ አይወቀስም። ተስፋ የተባሉት ጸሐፊ፤ “ንቁና ሥውሩ ሕሊናው ተምታቶበት” በሚል ሐረግ ዘለፋ የመሰላቸውን ጽፈዋል። ይኸ ስድብ አይደለም፤ አሳዛኝ ስህተት ብቻ ነው።
እንስሳት ከሞላ ጎደል የሚመሩት በደመነፍስ ነው። የሰው ልጅ በደመነፍስም በኅሊናም ይመራል። ኅሊና ሐሳብ ማለት ነው። ሰውን ከእንስሳ የሚለየው ክፉና ደጉን፣ ጎጂና ጠቃሚውን ደመነፍሳዊ ባልሆነ መንገድ መለየት ስለሚችል ነው። በደመነፍስ ውስጥ ነፃ ፈቃድ የለም። ደመነፍስ “ፕሮግራምድ” የሆነ “ኦቶማቲክ” ባህሪ ነው፤ ማሰብን አይፈልግም። ከምድር ላይ ፍጡሮች በተለየ ነፃ ፍቃድ ያለው የሰው ልጅ ብቻ ነው። ነፃ ፈቃድ በሌላ ቋንቋ ኅሊና ማለት ነው።
ተስፋ የተባሉት ጸሐፊ፤ “ኅሊና” የሚለውን ቃል ምንነት አልተረዱትም። አንድን ሰው፣ “ኅሊና የለህም?” የምንለው፣ “ሰው አይደለህምን? አታመዛዝንም? ክፉና ደጉን አታውቅምን?” ለማለት ነው። መጣጥፈኛው በእርጋታ የጻፉ አይመስለኝም፤ ወይም ደግሞ ጥራዝ ነጠቅና ዕውቀት-አጠር እንዳይሆኑ እሰጋለሁ።
ጀግና እና ጀግንነት
ዲሞክራሲ ህዝባዊ-አገዛዝ ነው፤በዲሞክራሲያዊ አገዛዝ ሥልጣን ከህዝብ ይመነጫል። ህዝብ መሪውን ወይም አስተዳዳሪውን ይመርጣል እንጂ መሪ ህዝቡን አይመርጥም። ንግሥና በዘር፣ በጉልበትና በብልጠት ካልሆነ በህዝብ ምርጫ አይደረግም። አብነት የጻፈው መሪውን የሚመርጥ ህዝብ ጀግና ነው ብሎ ነው።
አስተያየት ሰጪው ግን አብነት የጻፈበትን ዐውድ አላስተዋሉትም። እሳቸው ያደረጉት ነገር (ትህትና ቢጎድለውም) በቀቀናዊ ነው ለማለት እገደዳለሁ። ኢትዮጵያ እና ጀግና የሚሉትን ቃላት እንደሰሙ፣ “በላይ ዘለቀ፣ ዘርዓይ ድረስ፣ አብዲሳ አጋ ...” እያሉ መዘርዘር ጀመሩ። ጸሐፊው እነዚህን ብርቅዬ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች፣ ጀግኖች አይደሉም አላለም። አብነት የታሪክ ትምህርቱን ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው ነው። ተሳዳቢው ጸሐፊ ግን በአመለካከት ውዥንብር ውስጥ ገብተዋል። የሁለተኛ ክፍል መስኮት ላይ ለሦስት ሰዓት እንደተቀመጠች በቀቀን፣ ኢትዮጵያ እና ጀግና የሚሉትን ቃላት ሲሰሙ የደመነፍስ የስም ጥሪ አካሒደዋል። እኚህ ሰው አሳ ባዩ ቁጥር፣ “አሳ በጊል ይተነፍሳል” እያሉ ደጋግመው የሚጮሁ ዓይነት ናቸው። ወይም ደግሞ ፈረንጅ ባዩ ቁጥር፣ “The quick brown fox jumped over the lazy dog” እያሉ በደመነፍስ የሚዘምሩ በቀቀናዊ ሰው እንዳይሆኑ እሰጋለሁ።
አምባገነን
በወሪሳ ውስጥ የሰፈሩ ሰውና የልቦለዱ ተራኪ አምበርብር የተባሉትን ገፀባህሪ ሊገላገሉ ይፈልጋሉ።  ይህንን ነው አብነት ከአምባገነናዊ “ተውሳክ” ገዥዎች ጋር ያመሳሰለው። ለዚህ ምሳሌ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን እና መንግስቱን ጠቅሷል። ተሳዳቢው ጸሐፊ ግን፣ “[አብነት] ኢህአዴግ ከሌለ ኢትዮጵያ ብትንትኗ ይወጣል የሚለውን የአሁን ንቅዘት ሊጠቅስልን አልደፈረም።” ብለዋል።  ይኸ “በቀቀናዊ ድንጋሬ” ነው። አንደኛ ነገር የቀረ ምሳሌ አለ ተብሎ አንድ የኂስ አቅራቢ አይዘለፍም። ሁለተኛ ነገር ተሳዳቢው ያመጡት ምሳሌ አብነት ከጻፈው ሐሳብ ጋራ አይገናኝም። ይኸ ተራና “መርዘኛ” አካሔድ ይመስላል። አብነት ኢህአዴግን አልተሳደበምና አስተዋይ አይደለም ብሎ መጻፍ ምን ማለት ነው? ምን ዓይነት መዘላበድ ነው! አንባቢንስ አብዝቶ መናቅ አይሆንም? እኔ ዕድሉ ያልገጠማቸው አንባቢያን የአብነትን የኂስ ጹሑፍ እንዲያነቡት ከመጋበዝ ሌላ በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ነገር ከመጻፍ ብገታ ይሻለኛል።
ማንበብና መጻፍ
ተሳዳቢው ጽሑፍ አቅራቢ አንብቦ መረዳትም ሆነ ጽፎ ማስረዳት የተሳናቸው ይመስሉኛል። ልቅም አድርገው ማንበብ እና ጥርት አድርገው መጻፍ አልቻሉም። ኂስ አቅራቢው  ግን ከሞላ ጎደል በቅጡ አንብቦ የተደራጀ ጽሑፍ እንደጻፈ ኅሊና ያለው አንባቢ ሁሉ መፍረድ ይችላል። አብነት የአጻጻፍ ቴክኒኮችን በቅጡ የተማረ እና ያነበበ ሰው ነው። በአማርኛም ሆነ በእንግሊዝኛ የሚጽፈው ነገር የበሳል ድርሰትን መርህ የተከተለ እንደሆነ አውቃለሁ። አብነት የበሳል ድርሰት ተማሪ እና ጸሐፊም ብቻ አይደለም። በሳል ድርሰትን (Advanced Composition) በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ደጋግሞ እንዳስተማረ አውቃለሁ። ተሳዳቢው ጸሐፊ ከዚህ መማር ሲገባቸው የድንጋሬ ጦራቸውን ሰብቀው መፎከራቸው ትዝብት ላይ እንዳይጥላቸው እፈራለሁ።
የሐሳብ ልዩነት
ትችት አቅራቢው፣ በመጣጥፋቸው መጨረሻ ላይ፣ “ዘላለማዊነት ለሐሳብ ልዩነት እያልኩ ሳምንት እቀጥላለሁ” የሚል ቃል አስፍረዋል። እሳቸው ያቀረቡት የሐሳብ ልዩነት አይደለም። ጥሩ የኂስ ሙከራ ያደረገን ጸሐፊ ጉድለቱን ነቅሶ በማውጣት  ጠንካራ ጎንም ካለው ያንን በማሳየት ወደተሻለ ጎዳና መምራት ወይም አማራጭ ሐሳብ ማራመድ እንጂ አፍ እንዳመጣ መሳደብ የሐሳብ ልዩነት አይባልም። የሐሳብ ልዩነት ካላቸው “እኔ ደግሞ ይህንን ነገር የማየው በዚህ አቅጣጫ ነው” ብለው ይጽፉ ነበር። አስቀድመው የኂስ ጽሑፉን በቅጡ አላነበቡትም፤ አልገባቸውም። ይህን አድርገው የኂስ ጽሑፉን ሙሉ በሙሉ እንኳን ፉርሽ ቢያደርጉት አደንቃቸው ነበር። ሐሳብን እያሳከሩ ዘለፋ መጻፍ የሐሳብ ልዩነት አይባልም።
ኂስ እና ስድብ ይለያያሉ። ስድብ የባለጌ ነው፤ኂስ የጨዋ ነው። አብነት የጻፈውን ጥልቅ ኂሳዊ ንባብ ብዙ አንባቢዎች እንደወደዱት ለመረዳት ችያለሁ። የአብነት ኂሳዊ ንባብ ችግር እና ድክመት ካለው በሥነጽሑፍ እና በተቀራራቢ የዕውቀት ዘርፎች ላይ በቂ ልምድ እና ዕውቀት ያላቸው ጸሐፊዎች አስተያየት እንዲሰጡበት ማድረግም የሚቻል ይመስለኛል።
ጥበብ በኢትዮጵያ
አብነት ባለፉት የጭለማ ዘመናችን ከጥበብ ርቀን ነበር ብሎ የጻፈውን ተቺው በሌላ ተርጉመውታል። ኢትዮጵያ ውስጥ የጠላ ኢንዱስትሪ ነበር፤ ስለዚህም ኢትዮጵያውያን ጥበበኞች ነበሩ ይሉናል። ጸሐፊው “አላዋቂ ሳሚ ----” ዓይነት ሆነውብኛል።
አብነት በሌሎች መጻሕፍቱና በየጊዜውም በሰጣቸው ቃለመጠይቆች ኢትዮጵያ አስትሮኖሚን ጨምሮ የብዙ ጥበባት ጀማሪ ነች እያለ በማስረጃ አስደግፎ ተናግሯል። ተቺው ያቀረቡት ሐሳብ ግን ለሰሚው ግራ ነው። “በኃላፊነት ይጠጡ” እንደሚባለው “በኃላፊነት ይጻፉ” የሚል ማስታወሻም ቢኖረን ሳይጠቅም አይቀርም።
“አማርኛ ነክ” ምንድን ነው?
የመጣጥፉ አቅራቢ ገና ሲጀምሩ፤ “ስለ አማርኛ ነክ ጉዳዮች እና ስለ ኢትዮጵያ ኮከብ የሚል ሁለቱን መጻህፍቶቹን አይቼለታለሁ።” በማለት ጽፈዋል። ዐረፍተ ነገሩ በመዋቅሩም ሆነ በይዘቱ የተጣረሰ ነው። “ስለ አማርኛ ነክ ጉዳዮች” ምን ማለት ነው? ያሳዝናል።  አብነት የጻፋቸው መጻሕፍት የኢትዮጵያ ኮከብ፣ ፍካሬ ኢትዮጵያ፣ የቋንቋ መሠረታዊያን፣ ሳይኪ እና ኪዩፒድ እና አሁን በቅርቡ ደግሞ ጠቢባን ምን አሉ የተባሉ ናቸው። “ስለ አማርኛ ነክ ጉዳዮች” የጻፈው መጽሐፍ የለም። ባለመጣጥፉ ሊሉ የፈለጉት ምናልባት የቋንቋ መሠረታዊያን የሚለውን ከሆነ ይኸም መጽሐፍ “አማርኛ ነክ” አይደለም። መጽሐፉ የቋንቋን ሳይንስ መሠረታዊ እሳቤዎች የሚያብራራ እንጂ “አማርኛ ነክ” መጽሐፍ አይደለም። የመጣጥፉ አቅራቢ ዐረፍተ ነገር ሳያጠሩ ለትችት ባይቸኩሉ ደግ ነበር።
አላዋቂ ሐኪም ታማሚን የመግደል መብት የለውም። አላዋቂ መሀንዲስም “ዲሞክራሲያዊ መብቴ ነው” በሚል ህዝብን አደጋ ላይ የሚጥል ድልድይ ሲገነባ ዝም መባል የለበትም። ተረቱም ከመጠምጠም መማር ይቅደም ይላል። ተቺው “አይቼለታለሁ” የሚል ቋንቋም ተጠቅመዋል። ይኸ የጠራ ሐሳብ አይደለም። ይዩልኝ ብሎ የለመናቸው ያስመስላል።
የሁለት ሺህ ዘመን ታሪክ
መጣጥፈኛው ተስፋ፤ ኂሳዊ ንባብ ያቀረበውን ጸሐፊ፣ የሁለት ሺህ ዘመንን ታሪክ በአንድ ዐረፍተ ነገር የሚጨፈልቅ “ፈራጅ” ብለውታል። ይኸም ማስተዋል የጎደለው ግርድፍ አስተያየት ነው። ጸሐፊው የኢትዮጵያ ኮከብ በተባለው መጽሐፉ የዓለምን ታሪክ በየሁለት ሺህ ዘመን ከፍሎ አቅርቦልናል። በኂሳዊ ብእሮጉ ያመለከተው የኢትዮጵያ የሁለት ሺህ ዓመት ታሪክ ከዚያ ጋር የተገናኘ ነው። እሱ የጭለማ ዘመን ብሎታል። ከዚያ በፊት ባለው ዘመን ኢትዮጵያ ታላቅ እንደነበረች የታሪክ ጸሐፍትን እየጠቀሰ ተናግሯል። እንዲያውም በቅርቡ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ በወጣ “ምጽአተ ኢትዮጵያ” በተባለው ብእሮጉ፤የኢትዮጵያን ሥልጣኔ ከገናናው የአትላንቲስ ዘመን ጋር አገናኝቶታል። አብነት የኢትዮጵያን የ26 ሺህ ዓመት ታሪክ የዳሰሰበት “ውዳሴ ኢትዮጵያ” የተባለ መጽሐፍ እንዳለውም አውቃለሁ።
ማጠቃለያ
አብነት ስሜ የጻፈው የብእርወግ ነው። ተስፋ በላይነህ የጻፉት ግን የብእርወሬ ይመስላል። ተስፋ የተከበሩ እና አስተዋይ ሰው ሊሆኑ ይችላሉ፤ ይሄ መጣጥፋቸው ግን በቅጡ የተደራጀ አይደለም፤ የችኮላ ሥራ ሳይሆን አይቀርም። ሊናገሩ የፈለጉትን ጥርት ባለ ቋንቋ አልገልጹትም። በመጣጥፋቸው ውስጥ የሚያስከፋ ስድብ እንዳይኖር አልተጠነቀቁም። ይሄ ነገር ደግሞ ምላሽ ያስፈልገዋል ብዬ ስላመንኩ ይህን ጽፌአለሁ።

Read 2015 times