Saturday, 26 September 2015 09:20

እድሜና ምርጫ

Written by  ዮናቢር
Rate this item
(6 votes)

    ቆንጆ ናት... አፍላ .... 15 አመቷ ነው። ጎረምሶች ሲያዩዋት አይናቸው ይጎለጎላል። ጎልማሶች አይተው ይመኝዋታል። ወንዶች ይከጅሏታል። ሴቶች በቅናት እንደ ሽንኩርት ይልጧታል።
አንድ ቀን እንዲህ ስል ጠየቅኳት፤ “ማግባት የምትፈልጊው ባል ምን መስፈርት እንዲያሟላ ትፈልጊያለሽ?”
በፍጥነት መለሰችልኝ፤
“--- የተማረ መሆን አለበት፤ ማስተርስ ያለው ይመረጣል። ከተቻለ የግል ቢዝነስ የሚሰራ፤ ኢንቨስተር ቢሆን አሪፍ ነው፤ ካልሆነ ግን አሪፍ ደሞዝ ሊኖረው ግድ ነው ----- መኖሪያ ቤቱ G+2 ቢሆን ደስ ይለኛል፤ ከG+1 በታች ግን አልፈልግም።
--- መኪና በጣም ነው የምወደው። አሪፍ መኪኖች ቢኖሩት ሸጋ ነው ---- ካልሆነም ከተጋባን በኋላ እኔ አስገዛዋለሁ። ሙድ የገባው ቢሆን ደስ ይለኛል።
ሁሌ ግን የሚቅም፤ የሚጨብስና የሚያጨስ መሆን የለበትም። ጨዋታ የሚያውቅ፣ ሁሌ የሚያስቀኝ!
---- ቁመቱ በጣም እንዲረዝም አልፈልግም። እኔ አጠር ስለምል በጣም እንዳይበልጠኝ። ደረቱ ሰፋ ያለ ሆኖ ቦርጭ የሚባል እንዲኖረው አልፈልግም። ጸጉሩ ፍሪዝ ቢሆን ደስ ይለኛል፤ ድሬድ ቢሆን ደግሞ ነፍስ ነው። አይኑ የሚያምር፤ መልኩ ጸይም መሆን አለበት፤በጣም ቀይ ወይም በጣም ጥቁር ወንድ አልወድም። አለባበሱ ዘናጭ መሆን አለበት።
---- የሚወደኝ፤ የሚንከባከበኝ፤ ሮማንቲክ የሆነ፤ በሳምንት ቢያንስ ሁለቴ የሻማ እራት ያለበት ሆቴል የሚጋብዘኝ፤ ቢያንስ በወር ሁለቴ ጭፈራ ቤት የሚወስደኝ፤ ከበዓላት እና ከልደቴ ቀን በተጨማሪ ስጦታ እያመጣ ሰርፕራይዝ የሚያደርገኝ፤ ፍቅር የሚያውቅ፤ በተለያየ ቁልምጫ ስም የሚጠራኝና ታማኝ፣ ከእኔ ውጪ አንዲት ሴት የማያይ ...”
ይበቃል አልኳት፣ እንደማታቆም ስለገባኝ። እንዲህ አይነት ወንድ ኢትዮጵያ ውስጥ ቀርቶ አስቴር አወቀ ዘፈን ውስጥ እንኳን አይገኝም፣ አልኩ በውስጤ። ለሷ ግን አልነገርኳትም።
ከአስር አመት በኋላ ሳገኛት 25 አመቷ ነበር። አላገባችም። ዩኒቨርስቲ ጨርሳ ስራ ይዛለች። ጥቂት ቦይ ፍሬንዶች ይዛ ለቃለች። አሁንም ታምራለች፤ እንደድሮው ግን የሰው ሁሉ አይን ማረፊያ አይደለችም።
መልሼ ያንኑ ጥያቄ ጠየቅኳት።
“ማግባት የምትፈልጊው ባል ምን አይነት ነገሮች ማሟላት አለበት?”
 “--- የማፈቅረው ሰው መሆን አለበት፤ ፍቅር ከሌለ ላገባው አልችልም። ከማልወደው ሰው ጋር አንድ ቀን አላድርም፡፡  
 --- ታማኝ እንዲሆን እፈልጋለሁ። እንዲያከብረኝ እፈልጋለሁ።
ጥሩ ስራ ቢኖረው፤ ማንበብ የሚወድና በሃሳብ የምንግባባ ቢሆን ደስ ይለኛል።
---- ቆንጆና ሃብታም ከሆነ ጥሩ ነው፤ ካልሆነም ግን አብረን ሰርተን መለወጥ እንችላለን። ዋናው መግባባት ነው።
---- በተረፈ ቤተሰቡን የሚወድና የማይዋሽ መሆን አለበት። ወንዱ ሁሉ የማይታመን ሆነብን እኮ። ዋናው የሚታመን ከሆነ ሌላው ችግር የለውም”
ጊዜው ይሮጣል!!! ከአስር አመት በኋላ ስንገናኝ አላገባችም። 35 አመት እያለፋት ነበር። ደግሜ ያንኑ ጥያቄ ጠይቅኳት።
“ማግባት የምትፈልጊው ባል ምን አይነት ነገሮች ማሟላት አለበት?”
ትንሽ አሰብ አደረገችና፤
“--- የምግባባው ሰው ከሆነ ሌላው ችግር የለውም” አለችኝ
“መልኩ፤ ጸጉሩ፤ ሃብቱ፤ እውቀቱስ?” አልኳት።
#----ወንድ ልጅ ደግሞ መልክ ምን ያደርግለታል? ከቺምፕ (ቺምፓንዚ) መለስ ካለ ሌላው ችግር የለውም” አለች እየሳቀች።
ከአስር አመት በኋላ ሳገኛት አግብታø ሁለት ልጆች ወልዳ ነበር።
ባሏ አጭር፤ ጥቁር፤ መላጣ፤ የከባድ መኪና ሾፌር አይነት ቦርጭ ያለው፤ ሱሪውን ቦርጩ መሃከል ላይ የሚታጠቅ፤ ሁልጊዜ መላጣውን የሚያልበው፣ ዝጋታም ነገር ነው፡፡
“እንዴት ነው ትወጂዋለሽ?” አልኳት
“ምን ማለትህ ነው ትዳር አይደል?”
“ማለቴ ድሮ የነገርሽኝ አይነት ሰው አይደለም ብዬ ነው?”
#ያኔማ አየር ላይ ነበርኩ፤ እድሜ መስታወት ነው፤ ብዙ ያስተምራል፤ አሁን ተምረን ልብ ገዝተን ነው” አለች ተከዝ ብላ።
“ሁሌ የማይቀያየር አንድ መስፈርት ነበረሽ፤ ታማኝ መሆን አለበት ትይኝ ነበር። ባልሽ ታማኝ ነው?”
“ታማኝ እግዜር ብቻ ነው፤ በቃ ግን ... ትዳር ስለሆነ ከማይታመን ሰው ጋር መኖር ትለምዳለህ፤ አየህ አሁን የገባኝ ነገር ትዳር ማለት እንደ ፖለቲካ ነው። ፖለቲከኞች ውሸት እየነገሩን አብረን እንደምንኖር፣ ትዳር ውስጥም ይሄ ያጋጥማል” አለች
“በትዳርሽ ደስተኛ ነሽ?” አልኳት እያዘንኩ
“ደስታ አንጻራዊ ነው፤ በልጆቼ ደስ ይለኛል፤ ትዳሬን አከብራለሁ። በተረፈ ግን እየኖርኩ ነው” አለች ፈገግ ብላ። በዛች ቅጽበታዊ ፈገግታ ውስጥ የጊዜን ኃይለኝነት አየሁ።
ጊዜ ነው እንጂ ቁምነገራም
ባላባትነት አያኮራም ---- እንዲሉ እመው፡፡

Read 4004 times