Saturday, 26 September 2015 09:39

ኤርፖርቶች ድርጅት በ18ሚ. ብር የእሳት አደጋ መኪኖችን ገዛ

Written by  ማህሌት ኪዳነወልድ
Rate this item
(0 votes)

    የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት፣ ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ስድስት ዘመናዊ የእሳት አደጋ መኪኖችን መግዛቱን አስታወቀ፡፡ መኪኖቹ እያንዳንዳቸው ዘጠኝ ሺህ ሊትር ውሃና አንድ ሺ ሁለት መቶ ፎም የመያዝ አቅም አላቸው ተብሏል፡፡ ከእሳት አደጋ መኪኖቹ ውስጥ አንዱን ለአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በማስቀረት፣ ቀሪዎቹ በይበልጥ የቱሪስት መዳረሻ ወደሆኑ የክልል አለም አቀፍ ኤርፖርቶች
እንደሚላኩ ታውቋል፡፡ የመኪኖቹ መገዛት ኤርፖርቱ አለም አቀፍ የደህንነት ህግ እንዲያከብርና ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ያስችለዋል ያሉት አቶ ወንድሙ፤ በቀጣይም 25 ተጨማሪ ተሽከርካሪዎችን
ለመግዛት መታቀዱን ተናግረዋል፡፡ኤርፖርቱ እስካሁን አራት የ2008 ሞዴል የእሳት አደጋ መኪኖችን በመጠቀም በአደጋ መከላከል ዘርፍ አለም አቀፍ መስፈርት፣ ዘጠነኛ ደረጃን የያዘ ሲሆን የአሁኖቹ ዘመናዊ
የእሳት አደጋ መኪኖች የ2014 ሞዴል እንደሆኑ ተጠቁሟል፡፡ በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ማስፋፊያ ፕሮጀክት 15 በመቶ የደረሰ ሲሆን ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅም የማስተናገድ አቅሙን በ150 በመቶ ያሳድገዋል ተብሏል፡፡ ሁለቱን የመንገደኞች ማስተናገጃ ህንፃዎች ለማስፋትና ተጨማሪ የVIP ህንፃ ለመገንባት ታቅዶ በመከናወን ላይ ያለው የማስፋፊያ ሥራ፤ በአጠቃላይ 345 ሚሊዮን ዶላር
እንደሚፈጅ ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 1902 times