Saturday, 10 October 2015 16:24

የሁለቱ ደራሲዎች የሁለት ሴት አባዜ

Written by  ዓለማየሁ ገላጋይ
Rate this item
(3 votes)

   ከሩሲያ ፊዮዶር ደስተየቭስኪ፤ ከኢትዮጵያ በዓሉ ግርማ አንድ አይነት የሥነ-ፅሁፍ አከዋወን ጠባይ አላቸው፡፡ በየልቦለዶቻቸው ውስጥ የሚቀርፅዋቸው ዋና ገፀባህርያት ከግራ እና ከቀኝ አጥንቶቻቸው መንታ ሴቶች የተመዘዙ ግራ አጋቢ “አዳሞችን” ነው፡፡ እነዚህ ገፀባህሪዎች ሴቶች ተራዳና ቋሚ ሆነው በመሰረቱት መስቀል ላይ ተቸንክረው “ለምን ተውኸኝ?” የሚል እሮሮ ያሰማሉ፡፡ አቀበትና ቁልቁለቶቻቸውም እነዚያው ሴቶች ናቸው፡፡ እነርሱው ላይ ይወድቃሉ፣ በእነርሱ ይነሳሉ እነርሱኑ ይጠማሉ፣ በእነርሱው ይደቃሉ…
…ደስተየቭስኪ ጥንድ ሴቴ ፀሐዮች የገነኑበት ወንዴ ዓለም የፈጠረው ደጋግሞ ነው፡፡ “The Brothers Karamazov” ውስጥ ኢቫኖቭና እና ግሩሼንካ በእኩል ጉልበት ገናን ብርሃን ይለቃሉ፡፡ “The Idiot” የተሰኘው ልቦለድ ውስጥ ደግሞ እንዲሁ አግላያ እና ናፃስያ፤ ልዑል ሚሽኪን በተሰኘው ገፀ ባህርይ ልብ ውስጥ የሚፋለሙ ፍቅር ታጣቂዎች ናቸው፡፡ “Insulted and Humiliated” የተገነባው በሁለት ግራ አጋቢ ሴት ገፀባህሪዎች መካከል የሚዋዥቅ ልብ ባለው ሰው ላይ ተመስርቶ ነው፡፡ የአስራ ሦስት አመቷ ኒሊ የማይገባትን የፍቅር ትኩረት በመሻት ከኮረዳዋ ሉቦቭ ጋር በባላንጣነት ትቆማለች፡፡ “The Crime and Punishment” ውስጥ ይሄው ጉዳይ አለ፡፡ ቫርያ እና ሶኒያ የዋናው ገፀባህርይ የራስኮሊንኮቭ “ውኃቅዳ-ውኃመልሶች” ናቸው፡፡
ወደ በዓሉ ግርማ እንመለስ፡፡ በአሉ ግርማ እንዲሁ በአብዛኞቹ ሥራዎች ውስጥ የፈጠራቸው ወንዴ ዓለሞች ባለሁለት ሴቴ ፀሐዮች ናቸው፡፡ የ”ደራሲው” ዋና ገፀባህሪ ሲራክ እንደ ሸማኔ መቂናጥ ሁለት ሴቶችን ለመዳረሻነት አበጅቶ ከወዲያ ወዲህ የሚራወጥ ነው፡፡ እወዲያ ሰብለወርቅ ታፈሰብሩ አለች፤ እወዲህ ደግሞ ፅጌ፡፡ የራሱ እና የሰው ሚስት ላይ ተንጠልጥሎ እንደ እባብ እሁለት ተቆርጦ፣ ሁለት ቦታ የሚንቀሳቀስ ልዩ ፍጡር ሆኖ ቀርቧል፡፡ “የቀይ ኮከብ ጥሪ” ውስጥም የደርቤ እጣ ፈንታ ከሲራክ የተለየ አይመስልም፡፡ ከፊቱና ከኋላው ሁለት ሴቶች ተተክለዋል፡፡ እሱ ሒሩትን ያያል፤ በፍኖት ይታያል፡፡ ፍኖት በእማዕላፍ ግፊት ደርቤን ትማትራለች፡፡ እንዲሁ ደርቤም በፍኖት ተራዳኢነት ሒሩትን ይማፀናል፡፡ እምአእላፍ ከፍኖት ፊት በሞት ይገለላል፣ ሒሩትም እንደዚያው ከቁራኛዋ ደርቤ ባልለየለት ሞት ትነጠቃለች፡፡ ዥዋዥዌው ደርቤ ፊቱን ወደ ፍኖት እስኪመልስ የሚጠብቅ ይመስላል፡፡
በዓሉ ዋና ገፀባህሪዎቹን ወታደራዊ ቅጣት የበየነባቸው ያክል የሚሰማን ጊዜ ብዙ ነው፡፡ “ሀዲስ” ውስጥ ሀዲስ የተሰኘው ገፀባህርይ በሁለት “ችካል” ሴቶች መካከል ነፍሱ ማረፊያ አጥታ የሚንጠለጠል ፍጡር ነው፡፡ እንዲሁ የ”ኦሮማይ” ዋና ገፀባህርይ አዲስ አበባና አስመራ ላይ በተከለው መንታ የፍቅር ተራዳ ቀጭን የሰቀቀን ገመድ ወጥሮ የሚጓዝ ጀብደኛ ሆኖ ተስሏል፡፡
ደስተየቭስኪም ሆነ በዓሉ ባለ ሁለት አፍ የፍቅር ጐጆን ለገፀ ባህሪዎቻቸው መቀለሳቸው “ለምን?” የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ግድ ይለናል፡፡ መደጋገሙስ ምንን ያመለክታል? ደስተየቭስኪ ለአንድ ተባዕት ጥንድ እንስት የሚያቀርበው በአንዲት ሴት ላይ ማሳየት የሚከብደውን የተለያየ ገፅታ ለመከሰት ከመሻት እንደሆነ አንዳንድ የሥነ ፅሁፍ ሀያሲያን ያስረዳሉ፡፡ ራኬል ቶማስ የተሰኙ አጥኚ፤ “Ideas imbued and Exploration of Experience: The works of Fyodor Dostoevsky” በተሰኘ ምርመራቸው እንዳረጋገጡት፤ ደስተየቨስኪ የሴቶችን ጥንካሬ ከሁለት አቅጣጫ የመቃኘት ዝንባሌ ያሳያል፡፡ አንድም በሩሲያ ማህበረሰብ ጫና ውስጥ ሴቶች እንዴት ችግሩን ተቋቁመው እንደሚወጡ ሲሆን ሌላው በምዕራባውያን አስተሳሰብ ውስጥ ሊኖራቸው የሚገባውን የነፃነት ገፅታ ነው፡፡
ለምሳሌ የ091208 “The Brothers Karamazov” ካተሪና ኢቫኖቭና፡ በእጮኛዋ የሚደርስባትን ማህበረሰብ ወካይ ንቀት ለመበቀል በወንጀል ምስክርነት ስትቆም እንመለከታለን፡፡ “The Idiot” ውስጥ ደግሞ አግላያ ለጥ ሰጥ ያለ ወግ አጥባቂ ቤተሰቧን ጣጥላ፣ በወቅቱ ለሴቶች አደገኛ የሆነውን ነፃነት ለራሷ የምታጐናፅፍ ተደርጋ ተስላለች፡፡
የደስተየቭስኪ ሴቶች የመከሰቻ አላማቸው በፍቅር እቃነት የተገደበ አይደለም፡፡ ከዚያ አልፎ ለወንዶችም ትብታብ መበጣጠሻ ምክንያትነት አለው፡፡ ለምሳሌ የ “Crime and Punishment” ዋና ገፀባህርይ ከተተበተበበት የአእምሮ ወቀሳ ነፍሱ ነፃ የምትወጣው በሶኒያ ነው፡፡ በተመሳሳይ “The Brothers Karamazov” ውስጥ ግሩሼንካ እንዲሁ ለኢቫን የነፃነት መለከት ሆና ቀርባለች፡፡ “Insulted and Humiliated” ውስጥ እንዲሁ ኒሊ በይቅርታ ንፍገት የዘመነ ፍዳ ነዋሪዎች የሆኑትን አባቷን፣ እናቷንና አያቷን በእርሷ ሞት ስትፈውስና ወደ ዘመነ-ምህረት ስታሸጋግር የምትታይ ታዳጊ ገፀባህርይ ናት፡፡
የደስተየቭስኪ ሴት ገፀ ባህርይዎች በሙሉ ከወንዶቹ የላቀ ቦታና አላማ ተሰጥቷቸዋል ማለት ይቻላል፡፡ በሚታይና በማይታይ ኃይል የተሞሉ ናቸው፡፡ ናሙናው ደግሞ ናታሊያ ፎንቪዚና የተባለች ሴት እንደሆነች ተደጋግሞ ይነገራል፡፡ ይቺ ሴት ደስተየቭስኪ መንግሥት ላይ ደባ በመስራት ሲወነጀል፣ አብሮት ሞት የተፈረደበትና በኋላም በምህረት ወደ ሳይቤሪያ የተጋዘ ጓዱ ሚስት ነበረች፡፡ ባላቸውን ተከትለው ወደ ሳይቤሪያ በፈቃድ ከተጋዙት ጠንካራ ሴቶች አንዷም ናት፡፡ ከደስተየቭስኪ ጋር የተዋወቁት በሳይቤሪያ ጉዞ ላይ ሳሉ ሲሆን በወቅቱ የአዲስ ኪዳን መፅሐፍ አስር ሩብል ጨምራ ሰጥታው ነበር፡፡
 በሳይቤሪያ ቆይታው በተዳባይ አፍቃሪነት ይቺን ሴት ልቡ ውስጥ ሲያጉላላት መቆየቱ በሥራዎቹ ውስጥ “የስርቆሽ በር” ያላቸው የፍቅር ጐጆዎችን ለመመስረቱ እንደ ዋነኛ ምክንያት ይጠቀሳል፡፡ በዓሉስ?...
…በግልፅ እንደሚታወቀው የእኛ ሥነ-ፅሁፍ ሆነ የደራሲዎች ህይወት በጥልቅ የሚመረመርበት አግባብ የለም፡፡ በዓሉ ግርማ በአብዛኛዎቹ ሥራዎቹ ውስጥ ባለመንታ አፎት ፍቅር እንዲሽሟጠጥ የማድረጉ ምንጭ በውል አልተመረመረም፡፡ ከህይወቱም ጋር አልተገናዘበም፡፡ ይሁንና አንዳንድ ጥቁምታዎችን ከመዘዝን ወደ አንድ መዳረሻ ማምራታችን ግድ ነው፡፡ ለምሳሌ የቀድሞው ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለማሪያም ከጋዜጠኛ ገነት አንበሴ ጋር ተወያይተው ወደ መፅሐፍ በተለወጠው ሥራ ውስጥ በዓሉ ግርማ የድምፃዊቷ ብዙነሽ በቀለ ወዳጅ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ በ”ደራሲው” ዋና ገፀ ባህርይ በሲራክ፣ በ”ሀዲሱ” ሀዲስ፣ በ”ቀይ ኮከቡ” ደርቤ፣ በ”ኦሮማይ” ፀጋዬ ኃይለማሪያም ላይ የታየው የሁለት ቤት ስቅለት በደራሲው የተጠና ወይም የተኖረ ነበር ለማለት የምንችልበት ቀዳዳ እዚህ ላይ ይፈጠራል፡፡ ታዲያስ? ደስተየቨስኪ “He retreated to the confines of his novels for exploration of his experiences.” እንደተባለው መሆኑም አይደል?

Read 3791 times