Saturday, 17 October 2015 09:39

“አዝማሪ ሚዲያ አያስፈልገንም”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

መንግስት በሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ለ22 የግልና የመንግሥት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እንዲሁም ለ13 የሬድዮ ጣቢያዎች ፈቃድ ለመስጠት አቅዷል፡፡ 7 የሬድዮ ጣቢያዎችም ዘንድሮ አመት ፈቃድ አግኝተው ወደ ስራ ይገባሉ ተብሏል፡፡በዚህና ተያያዥ ጉዳዮች የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ም/ዳይሬክተር የሆኑትን አቶ ልዑል ገብሩን በፅ/ቤታቸው ተገኝቶ አነጋግሯቸዋል  

    የግል ቴሌቪዥን ጣቢያ ፈቃድ ለመስጠት ይሄን ያህል ጊዜ የዘገየው በምን ምክንያት ነው?
አጠቃላይ የፈቃድ ማእቀፎች በሬድዮ፣ በቴሌቪዥን፣ በህትመትም ሚዲያውን በማስፋፋት ለልማት፣ ለሰላም፣ ለዴሞክራሲ የሚጫወተውን ሚና ማጐልበት ነው፡፡ በዚህ ረገድ የብሮድካስት አዋጁ ከወጣ ጀምሮ የግል ሬዲዮ ጣቢያዎች ፈቃድን ስንሰጥ ቆይተናል፡፡ ወደ 30 ለሚደርሱ የማህበረሰብ ሬዲዮ ፈቃድም ስንሰጥ ነበር፡፡ የግል ጣቢያዎች ወደ 7 ደርሰዋል፡፡ በቀጣይ የትራንስፎርሜሽን እና የልማት እቅድ ቁጥሩን ወደ 20 እና ከዚያ በላይ ለማድረስ እየሰራን ነው፡፡
 የህዝብ ብሮድካስት በተለምዶ የመንግሥት የምንላቸውን በተመለከተም ሁሉም ክልሎች የየራሳቸው ብሮድካስት ጣቢያዎች አሏቸው - ከአፋር እና ከጋምቤላ በስተቀር፡፡ ሬድዮን በተመለከተ በአዲስ ፈቃድም ሆነ በማስፋፋት ሥራ በርካታ ስራ ተሰርቷል፡፡ ፕሬስ በተመለከተ ብዙ መዝግበናል፡፡
ወደ ቴሌቪዥን ስንመጣ፣ የቴሌቪዥን ፈቃድ ያልተሰጠበት ዋና ምክንያት የቴክኖሎጂ ጉዳይ ስለሆነ ነው፡፡ አለም አሁን ከአናሎግ ወደ ዲጂታል ስርጭት እየገባ ነው፡፡ አናሎጉ የምስልና የድምፅ ጥራት የለውም፡፡ በርካታ አገልግሎት የመስጠት አቅምም የለውም፡፡ አለም ወደዚህ ደረጃ ሽግግር እያደረገ ባለበት ኢትዮጵያ በኋላ ቀሩ ላይ መቆየት ስለሌለባት፣ ከአናሎግ ወደ ዲጂታል መሸጋገር ግዴታ ሆኗል፡፡ ሽግግሩ ግን የራሱን ጊዜ ይወስዳል፡፡ እስካሁን ብዙ ርቀት ብንሄድም ስራውን ከጀመርን ወደ 4 አመት ሆኗል፡፡ እናም የቴሌቪዥን ፈቃድ የዘገየው የቴክኖሎጂ ሽግግር ጉዳይ ስለሆነ ነው፡፡ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ግን ይሄ ሁሉ ሽግግር የሚጠናቀቅ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ በ2009 ዓ.ም የግል ቴሌቪዥን ባለቤት ለሚሆኑ ፈቃድ ሰጥታ፣ የግል ቴሌቪዥን በአገሪቱ ይኖራል ማለት ነው፡፡ የቴክኖሎጂው ጉዳይ ያዘገየው ለግል ብቻ ሳይሆን ለመንግሥትም ነው፡፡ የክልል ብሮድካስተሮች እንኳ ሲጠይቁ አልሰጠናቸውም፡፡ ለምሳሌ ትግራይ ጠይቆ ነበር፤ ነገር ግን በአናሎግ ቢሰራ ጣቢያውን ለማቋቋም የሚወጣው በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ስለሆነ ከጥቂት አመታት በኋላ ኪሳራ ይሆናል፡፡ ስለዚህ በሀገር ሃብት ላይ ብክነት ነው የሚከተለው፤ ትንሽ ታገሱ” ብለናቸው ፈቃዱን ሳያገኙ ቆይተዋል፡፡
ከአናሎግ ወደ ዲጂታል የሚደረገው ሽግግር ምን ደረጃ ላይ ነው ያለው? ምን ምን ቅድመ ዝግጅቶችስ ተደርገዋል?
አሁን አጠቃላይ የግዢ ሂደት ላይ ነው ያለው፡፡ መሳሪያዎችን… ትራንስሚተሮችን፣ የሄዲንድ መቀበያ መሳሪያዎችን ለመግዛትና ተከላውን ለማካሄድ የጨረታ አሸናፊ ድርጅቶችን የመለየት ስራ እየተሰራ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ “ሴቶፍቦክስ” የሚገጣጥሙ ድርጅቶች በጨረታ እየተለዩ ነው ያሉት፡፡ የቴክኖሎጂ መረጣው ተከናውኗል፡፡ አሁን የቀረው የግዢ ሂደቱን ማፋጠን ነው፤ በጨረታ ሂደት ላይ ነው ያለው፡፡ በ2008 አጠቃላይ የዲጂታላይዜሽኑን ስራ እንጨርሳለን፡፡ ልክ እሱ እንዳለቀ ወደ 22 የሚጠጋ የቴሌቪዥን ቻናል ነው የሚኖረን፡፡ ከዚያ ቻናል ውስጥ ለእያንዳንዱ ክልልና ለኢቢሲ ቻናል ይሰጣቸዋል፡፡ የተረፈውን ቻናል ደግሞ ለግል ድርጅቶች በጨረታ አወዳድረን የምንሰጣቸው ይሆናል፡፡
የጣቢያው ባለቤትነት የማን ነው? የግለሰቡ ነው ወይስ የመንግስት? ነፃነታቸውስ ምን ድረስ ነው?
ፈቃዱን መስጠት ስንጀምር በአጠቃላይ የፈቃድ አሰጣጡ ይቀየራል፡፡ ከዚህ ቀደም ለምሳሌ ለኦሮሚያ ቴሌቪዥን ሰጥተናል፤ ለሌሎች ክልሎችም እንደዚሁ፡፡ ፈቃድ ስንሰጣቸው ጥምር ፈቃድ ነው የሰጠናቸው፡፡ ትራንስሚተር የመሳሰሉትን በራሳቸው እንዲተክሉ የሚሰጥ የቴክኒክ ጉዳዮች ፈቃድ አለ፡፡ በሌላ በኩል የፕሮግራም ይዘት ፈቃድ አለ፡፡ ሁለቱንም በራሳቸው እንዲሰሩ ነው ፈቃድ የሰጠናቸው፡፡ ወደ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ስንመጣ ግን አንዱ ትልቁ ጥቅሙ የቴሌቪዥን ብሮድካስት አገልግሎት የሚሰጡ ጣቢያዎች ትኩረት የሚያደርጉት ይዘቱ ላይ ብቻ ነው፡፡ የቴክኒክና የትራንስሚተር ጣጣውን የሚቆጣጠርላቸው ራሱን የቻለ ትልቅ የመንግስት የልማት ድርጅት ይቋቋማል፡፡ ሄዲንግ ዲስትሪቢዩተር ይባላል፡፡ ስራው ከእያንዳንዱ የቴሌቪዥን ብሮድካስተሮች የሚመጡትን ፕሮግራሞች እየተቀበለ ያሰራጫል፤ አሰራጭ ነው የሚሆነው ማለት ነው፡፡
ኢቢሲም ሆነ የክልሎቹ ጣቢያዎች በራሳቸው ማሰራጫ ሳይሆን በዚህ የመንግሥት የልማት ተቋም ማሰራጫ በኩል ነው የሚሰራጭላቸው፡፡ ይሄ ለቴሌቪዥን ብሮድካስተሮች በቴክኒክ ጉዳዮች እንዳይጨነቁ ከማድረጉም በላይ ከቴክኒክ ወጪ ይገላግላቸዋል፡፡ ይህ መሆኑ በፕሮግራምና በይዘት ጥራት ላይ ብቻ ትኩረት እንዲያደርጉ ይረዳል፡፡ ሚክሰሩ ተቃጠለ፣ ትራንስሚተሩ ፈነዳ የመሳሰሉት ጉዳዮች የነሱ ጭንቀት አይሆንም ማለት ነው፡፡ ያንን የሚመለከተው የሚቋቋመው ተቋም ይሆናል፡፡ ሚዲያዎቹ የራሳቸው ነፃነት ይኖራቸዋል፡፡ ይዘታቸው ላይ ማንም ጣልቃ አይገባባቸውም፡፡ የፈለጉትን ይዘት ያሰራጫሉ፡፡ የሚያሰራጩት ግን በዚያ ሲግናል ዲስቲሪቢዩተር ወይም ሄዲንግ ዲስትሪቢዩተር በሚባለው ተቋም በኩል ይሆናል፡፡ ፈቃድ ከሰጠናቸው በኋላ የራሳቸው ጣቢያ፣ የራሳቸው ቻናል ነው የሚሆነው፡፡ “ይሄን አስተላልፉ፤ ያንን አታስተላልፉ” ብሎ ገደብ የሚጥልባቸው አይኖርም፡፡ ብሮድካስት ባለስልጣን ካሰራጩ በኋላ ያሰራጩት ፕሮግራም ህግን የሚተላለፍ፣ አመፅ የሚቀሰቅስ፣ ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጭ ከሆነና ቅሬታ ከቀረበበት፤ በህግ በተሰጠው ኃላፊነት ይሄን ለምን አደረጋችሁ ብሎ ይጠይቃል፡፡ ከስርጭት በፊት ግን ሙሉ ነፃነታቸው የተጠበቀ ነው፡፡ ጣቢያውም የግል ንብረታቸው ነው የሚሆነው፡፡ የማሰራጨት ስራውን የሚሰራው “ሲግናል ዲስትሪቢዩተር” የመንግሥት የልማት ድርጅት ግን በደንብ ወይም በአዋጅ ይቋቋማል፡፡
ብሮድካስት ባለስልጣን ሬዲዮና ቴሌቪዥኖች እየተበራከቱ ሲሄዱ ሚዲያዎቹን የመቆጣጠር (ሞኒተር የማድረግ) አቅም ይኖረዋል?
አቅምን በተመለከተ ከጊዜው ጋር የሚሄድ አቅም በተቋማችን መገንባት ይኖርብናል፡፡ እስካሁን ይብዛም ይነስም የተለያዩ ስራዎችን ስንሰራ ቆይተናል፡፡ ግን አሁን ባለስልጣኑ ባለበት ደረጃ በቀጣይ እየተስፋፉ ያሉ ሚዲያዎችን ለመደገፍ፣ ቴክኒካል እገዛ ለመስጠትና የሞኒተሪንግ ስራ ለመስራት ያለው አቅም በቂ አይደለም፡፡ ስለዚህ እንደተቋም ይሄን አቅማችንን ማሳደግ ይኖርብናል፡፡ ይሄ አቅም ሊያድግ የሚችለው፣ አንደኛ አደረጃጀታችንን በማስተካከል ነው፡፡ አሁን እየመጣ ያለውን ዲጂታል ቴክኖሎጂ የሚመጥን ተቋም መፈጠር አለበት፡፡ ሁለተኛ የሰው ሃይል አቅም ግንባታ ላይ የምንሰራው ስራ ይኖራል፡፡ አሁን ያለን የሰው ሃይል በቂ ነው ሊባል አይችልም፡፡ በአመለካከት፣ በክህሎት፣ በእውቀት ብዙ የሚቀረን ነገር አለ፡፡ ይሄን ለማስተካከል በስልጠና፣ በስራ ላይ ልምምድ… የሰራተኞችን አቅም ማጐልበት ይኖርብናል፡፡ ሦስተኛ የሞኒተሪንግ ስራ የምንሰራበትን መሳሪያ ዘመናዊ ማድረግ፣ ሠራተኞች በአይሲቲ የተደገፈ ስራ እንዲያከናውኑ ለማድረግ መሳሪያ ማሟላትና ስራችንን በዘመናዊ መልኩ መስራት ይጠበቅብናል፡፡እነዚህን ሶስቱን ነገሮች ከሰራን አቅማችንን ወደተሻለ ደረጃ እናደርሰዋለን፡፡ አሁን ባለን አቅም ግን ወደፊት የሚመጣውን ስራ መስራት አንችልም፡፡
ሊጀመሩ ከታሰቡት አዳዲስ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች አንፃር… ሃገሪቱ በቂ የብሮድካስት ባለሙያዎች አሏት ብለው ያስባሉ?  
ይሄ በጣም ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ዲጅታሉ ላይ 24 ሰአት የሚሰሩ 22 ቻናሎች ናቸው የሚኖሩት፡፡ እነዚህን ቻናሎች ወደ ስራ ማስገባት ቀላል ነው፡፡ ትልቁ ችግር ያለው የተሰጠውን ቻናል ለ24 ሰአት የሚሞላ ይዘት አለ ወይ ነው? ኢቢሲን ብናየው 50 አመት አስቆጥሮም 24 ሰአት የሚሞላ ይዘት እንኳን ሊያዘጋጅ አሁን ላሉት ፕሮግራሞች እንኳን ጥራት ያለው ይዘት ማቅረብ አልቻለም፡፡ እኛም ከቴሌቪዥን ማስፋፋት ጋር ተያይዞ ትልቁ ችግር ይሆናል ብለን በጥናትም ያረጋገጥነው ይሄው ጉዳይ ነው፡፡ ይሄን ደግሞ ማዘጋጀት የሚችለው ባለሙያ ነው፡፡ ስለዚህ ይሄን እንደ ፈተና ተመልክተን ምን ምን መሰራት አለበት የሚለውን አይተነዋል፡፡ 1ኛ የጋዜጠኝነት ክህሎት ያላቸው በቂ ባለሙያዎች ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ተመርቀው በሚወጡበትና ስራውን ሙያዊ በሆነ መንገድ እንዲሰሩ ከወዲሁ እያነፁ የማፍራት ስራ መሰራት አለበት፡፡ 2ኛበርካታ ቻናሎች ስለሚከፈቱ የኪነጥበብ ባለሙያዎች በርካታ ድራማዎችን እንዲያዘጋጁ፤ በመዝናኛ ኢንዱስትሪው ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎችም አዝናኝ የሆኑ ፕሮግራሞችን ከወዲሁ እያሰናዱ እንዲቆዩ፣ የማስታወቂያ ባለሙያዎችም እንዲሁ ዝግጅት እንዲያደርጉ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ መሰራት አለበት፡፡በተጨማሪም እያንዳንዱ ባለጣቢያ 24 ሰዓት በሃላፊነት መስራት እንዳለበት አውቆ ባሉት ጋዜጠኞች ከወዲሁ ባክሎግ (የቅድመ ዝግጅት ስራዎች) እንዲሰራ፣ የባለሙያዎቹን አቅም በማጐልበት ዝግጅት እንዲያደርግ አቅጣጫ እንሰጣለን፡፡ እነዚህ ዝግጅቶች ከተደረጉ ብዙም ችግር የሚያጋጥም አይመስለኝም፡፡ የሌሎች ሃገሮችን ብናይ ለምሳሌ ኮርያ “ኮንተንት ፕሮዳክሽን ሃውስ” የሚባሉ የግል ድርጅቶች አሉ፡፡ የድራማ ፕሮግራም የመሳሰሉትን ሰርተውና አዘጋጅተው ያስቀምጣሉ፡፡ ብሮድካስተሩ እነዚህ የተዘጋጁትን ስራዎች እንደማንኛውም ሸቀጥ ይገዛል ማለት ነው፡፡ ትልቅ ገበያ ነው የሚሆነው፡፡ በሀገራችንም ያ መፈጠሩ አይቀርም፡፡
ፕሮዳክሽን ሃውሶች መስፋፋት አለባቸው፡፡ ይሄ መሆኑ ደግሞ ከየዩኒቨርስቲዎቹ በመስኩ ተመርቀው ለሚወጡ ሰፊ የስራ እድል ይፈጥራል፡፡
መንግሥት የጣቢያዎቹ ይዘት ላይ ጣልቃ አይገባም ብለዋል፡፡ እነዚህ ጣቢያዎች ፖለቲካዊ የሆኑ ጉዳዮች ላይ አተኩረው መንግስትን ለመተቸት ቢፈልጉ ነፃነታቸው ምን ያህል ነው? ፖለቲካ ላይ የመስራት ፍላጐት ላላቸውስ ፍቃድ ይሰጣል?
መጀመሪያ የኛ ፍቃድ አሰጣጥ የሚነሳው ከህገ መንግስቱ ነው፡፡ በህገ መንግስቱ የሃሳብ ነፃነት የተረጋገጠ ነው፡፡ ዜጐች መረጃ የማግኘት መብት አላቸው፡፡ ስለዚህ አንተ ስለ ስፖርት ብቻ ነው፣ አንተ ስለ ኢኮኖሚ ብቻ ነው መስራት ያለብህ ብሎ መንግስት ገደብ ሊጥል አይችልም፡፡ ይሄን ስሩ ያንን አትስሩ አይልም፡፡ ገደብም አይጣልባቸውም፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ራሱን ለትችት ያዘጋጀ መንግስት ነው፡፡ ጥሩ ነገር እንደሚሰራ ሁሉ የሚያጠፋቸው ነገሮች ካሉ ያንን ነገር በመተቸት መንግስት እንዲያሻሻል ለማድረግ ቁርጠኝነቱ አለው፡፡ ለመስማት ዝግጁ ነው፡፡ ስለዚህ መተቸትን የሚያበረታታና ለመተቸት ዝግጁ የሆነ መንግስት እስካለ ድረስ ሚዲያዎች በትክክለኛ ሃቅ ላይ በተመሰረተና ሚዛናዊነቱን በጠበቀ መልኩ ቢተቹ መንግሥት ደስተኛ ነው፡፡
 በቅርቡም በግልፅ አዝማሪ ሚዲያ አልፈልግም ብሏል፡፡ መንግስትን እያንቆለጳጳሰ የሚኖር ሚዲያ ብዙ አይጠቅምም፡፡ መንግስት የሰራውን በጐ ነገርም ማቅረብ አለበት፤ በዛው ልክ ደግሞ መታረም ያለባቸው የተሳሳቱ ነገሮች ካሉ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ካሉ፣ ሚዲያው በተጨባጭ እንዲያቀርብለት ፍላጐት አለው፡፡ ስለዚህ ፖለቲካ ላይ አትግቡ የሚል መንግስት አይደለም ያለው፤ ህገ መንግስቱም አይፈቅድም፡፡
ጋዜጣ ወይም ሬድዮ ጣቢያ ያለው ሰው ቴሌቪዥን ይፈቀድለታል? ለአንድ ሰው ምን ያህል ሚዲያ ይፈቀድለታል?
ዋናው የኛ ስርአት የሚያስቀምጠው የሃሳብ ሞኖፖሊ መኖር እንደሌለበት ነው፡፡ አንድ ኩባንያ የራሱን ሃሳብ ብቻ በሬዲዮም በጋዜጣም በቴሌቪዥንም እያስተላለፈ፣ የሱ ሃሳብ ብቻ ዜጐች ላይ መጫን የለበትም፡፡ የሌሎች ሃሳብም መስተጋባት አለበት፡፡ ሚዲያዎችን ስናስፋፋም የሃሳብ ብዝሃነትን ማረጋገጥ ይኖርብናል፡፡ ከሚረጋገጥባቸው መንገዶች አንዱ ለተለያዩ ድርጅቶች ፈቃድ መስጠት ነው፡፡ አንድ ድርጅት ብቻ ሁሉንም ጠቅልሎ የሚወስድ ከሆነ የሃሳብ ሞኖፖሊ መፈጠሩ አይቀርም፡፡
ቴሌቪዥን ያለው ጋዜጣ፣ ጋዜጣ ያለው ሬድዮ፣ ሬድዮ ያለው ቴሌቪዥን ወይም ጋዜጣ ይሰጠዋል ወይ የሚለውን በተመለከተ መመሪያ እያዘጋጀን ስለሆነ መመሪያው ሲጠናቀቅ ምላሽ የሚያገኝ ይሆናል፡፡
ሬድዮ ጣቢያዎቹስ እንዴት ነው የሚስተናገዱት? በራሳቸው አቅም ነው ማሰራጫቸውን የሚተክሉት ወይስ እንደ ቴሌቪዥኑ በአንድ ማዕከል እንዲሰራጩ ይደረጋል?
ዲጂታል ሽግግሩ ለጊዜው በዋናነት የሚመለከተው ቴሌቪዥኑን ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ኤፍ ኤም እና ሌሎቹ የሬድዮ ጣቢያዎች ማሰራጫውንም ጭምር በራሳቸው ይዘው ይሄዳሉ፡፡ የሬድዮ ዲጂታላይዜሽን በሚመጣ ጊዜ በይዘት ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ሊደረግ ይችላል፡፡ ይሄ እንግዲህ የረጅም ጊዜ እቅድ ነው የሚሆነው፡፡ ቴክኖሎጂው መስፋፋት ሲጀምር ማለት ነው፡፡ አሁን ግን ማሰራጫ ጣቢያ የመገንባቱንም ሆነ በራሳቸው ሙሉ አቅም የመንቀሳቀሱን ጉዳይ ይዘው ይቀጥላሉ ማለት ነው፡፡
መቼ ነው የሬድዮ ጣቢያዎቹ ስራ የሚጀምሩት?
በሁለተኛው እቅዳችን እንደመነሻ ለ13 ሬድዮ ጣቢያዎች ነው ፈቃድ ለመስጠት የታሰበው፡፡ ከዚያም በላይ ጥያቄ ከመጣም እናስተናግዳለን፡፡ በዚህ አመት 7 ለመስጠት አቅደናል፡፡ ጨረታውን በዚህ ወር እናወጣለን፡፡ ሬድዮ ጣቢያ አቋቁመው ለመስራት ለሚፈልጉ የግል ብሮድካስተሮች በጋዜጣና በሬድዮ እንዲሁም በቴሌቪዥን የጨረታ መወዳደሪያ ማስታወቂያ በቅርብ ቀናት ውስጥ እናወጣለን፡፡
የተሻለ አቅምና ብቃት ላላቸው ፈቃድ እንሰጣለን፡፡ ከሰባት ድርጅቶች በላይ አቅም ያላቸው ከተገኙም በዚሁ አመት ለመስጠት አይቸግረንም እንሰጣለን፡፡ ፈቃዱ የሚሰጠው በተለያዩ ክልሎች ነው፡፡ አዲስ አበባ፣ ባህርዳር፣ ደሴ፣ መቀሌ፣ ኮምቦልቻ፣ ድሬደዋና በሌሎች ከተሞች እንሰጣለን፡፡ ከቋንቋ አንፃርም በአማርኛ፣ በኦሮሚኛ፣ በትግርኛ፣ በእንግሊዝኛ በመሳሰሉት በመስጠት የሃሳብ ብዝሃነት እንዲሰፍን የማድረግ ስራችንን እንሰራለን፡፡ ጨረታው ግን በዚህ ጥቅምት ወር ይወጣል፡፡ ፍላጐቱ ያላቸው ተዘጋጅተው ይጠብቁ፡፡
ከዚህ በፊት የግል ኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያ አቋቁመው እየሰሩ ያሉ ብሮድካስተሮች ውጤታማነትና ተደራሽነት ምን ያህል ነው? የናንተ ግምገማ ምን ያመለክታል?
ይሄን በሁለት ደረጃ ማየት እንችላለን፡፡ በመሰረታዊነት የሃሳብ ነፃነት ለመረጋገጡ ማሳያ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ የግል ሬድዮ ጣቢያ በዚህ ስርአት ነው ለመጀመሪያ ጊዜ የተቋቋመው፡፡ ሁለተኛ ታዳጊ ሚዲያ ነው ያለን፡፡ ገና በእድገት ጐዳና ላይ ነው ያሉት፡፡ የሰው ሃይል እጥረቱም የአቅምም ጉዳይ ይኖራል፤ ግን እስካሁን እየሰሩ ያሉት በተለይ በልማት ላይ ዜጐች የጋራ መግባባት እንዲኖራቸው በማድረግና ንቅናቄ በመፍጠር ረገድ የማይተካ ሚና አላቸው፡፡ ለምሳሌ ታላቁ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ ጣቢያዎቹ በእኩል ድምፅ ነው እየሰሩ ያሉት፡፡ ለምሳሌ 8100 A ማስታወቂያን በነፃ ነው ሁሉም የሚያስተላልፉት፡፡ ይሄ መልካም ስራ ነው፡፡ በሌላ በኩል በምርጫ ጉዳይ ህብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲያገኝ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምፅ እንዲሰማ በማድረግ እየሰሩ ያሉት ስራ በጥሩ ጐን የሚጠቀስ ነው፡፡በሌላ መልኩ ግን ማስተካከል ወይም ሊታረም ይገባዋል የምንለው ጉዳይም አለ፡፡ አብዛኞቹ ጣቢያዎች ለስለስ ያሉ ጉዳዮች ላይ ያተኩራሉ፡፡ ስፖርትና ሙዚቃ ላይ የማተኮር ዝንባሌ አለ፡፡ ይሄ በራሱ ሃጢያት አይደለም ግን እንደ ታዳጊና ከድህነት ለመውጣት እንደምትፍጨረጨር ሃገር ትልቁ አጀንዳ ስፖርት ሊሆን አይችልም፤ ትልቁ አጀንዳ የልማት ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ በኩል ጠንከር ብለው በዲሞክራሲ፣ በልማት፣ በሴቶችና ወጣቶች ተሳትፎ ላይ በርካታ ስራ መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ አሁን ግን በዚያ ደረጃ ላይ አይደሉም፡፡ በመልካም አስተዳደር ጉዳይ እንደ ሃገር ችግር አለብን ተብሏል፡፡ ጣቢያዎች እነዚህን ክፍተቶች መርምረው እንዲስተካከሉ ከመስራት አንፃር የሚቀራቸው ነገር አለ፡፡ ወደፊት የሚያድግ የሚዲያ ዘርፍ እንደመሆኑ በይዘታቸው ጠንካራ ሃገራዊ ጉዳይ ላይ አተኩረው መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
የመንግስት ማስታወቂያዎች ፍትሃዊ በሆነ መንገድ የግል የሚዲያ ተቋማትን ለማጠናከር ይከፋፈላሉ የሚለው የመንግስት እቅድ መቼ ነው ተግባራዊ የሚሆነው?
ማስታወቂያ ለአንድ ሚዲያ የፋይናንስ አቅም ምንጩ ነው፡፡ ስለዚህ እንደ መንግስት በሚዲያው አካባቢ ከተለዩ ችግሮች አንዱ የማስታወቂያ ጉዳይ ነው፡፡ አንዳንዱ በርካታ ማስታወቂያ ይገኛል፡፡ አንዳንዱ ደግሞ አንድም ማስታወቂያ የለውም፡፡ የሌለው እየከሰመ ይሄዳል፡፡ ይሄ መስተካከል አለበት፡፡ ለዚህ አንዱ መፍትሄ የመንግስት የሆኑ ማስታወቂያዎችን ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ለሁሉም ማከፋፈል ነው፡፡ የግለሰብ የሆኑትን አይመለከትም፡፡ማስታወቂያ የማከፋፈሉ ስራ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ከብሮድካስት ባለስልጣን ጋር በመተባበር የሚከናወን ስራ ነው፡፡ በዚህ አመትና ከዚህ አመት በኋላ ባሉት ጊዜያት ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ ታስቧል፡፡ ምክንያቱም ቀኑን ለመቁረጥ ብቻችንን የምንሰራው አይደለም፡፡ የመንግስት ባለድርሻ አካላት በጋራ የሚወስኑት ነው የሚሆነው፡፡ በዚህ ጊዜ ነው ብሎ ለማስቀመጥ ከዚህ አንፃር ይከብዳል፡፡ ግን ተግባራዊ ለማድረግ መንግስት ቁርጠኝነቱ አለው፡፡
ከዚህ ቀደም የኢንተርኔት ሚዲያዎችን የሚመለከት ህግ እንደሚወጣ ተገልፆ ነበር.. ምን ላይ ደረሰ?
ኦንላይን ሚዲያዎችን በተመለከተ አሁን ያለው የብሮድካስት አዋጅ ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ስልጣን አይሰጠውም፡፡ ህጉ ላይ የለም፡፡ በዚህ አመት 2008 ላይ የሚፀድቅ አዲስ የሚዲያ አዋጅ አለ፡፡ በረቂቅ ደረጃ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ም/ቤት ቀርቧል፡፡ እዚያ ላይ ኦንላይን አገልግሎቶች እንዴት ነው የሚስተናገዱት? እንዴት ነው ፍቃድ የሚሰጣቸው? እንዴት ነው ክትትሉ የሚደረግባቸው? የሚለውን የሚመልስ ረቂቅ ህግ ፓርላማው ካፀደቀው ባለስልጣን መ/ቤቱ በህግ የሚሰጠውን ሃላፊነት ተቀብሎ፣ እነሱንም ማስተናገድ ይጀምራል፡፡ ነገር ግን ይሄን መስራት የምንችለው ሃገር ውስጥ ባሉት ላይ ብቻ ነው፡፡
 በውጭ ሆነው የሚያሰራጩትን አይመለከትም፡፡ በሀገር ውስጥ ሆነው መረጃ የሚያስተላልፉትን በተመለከተ ግን አዋጁ ከፀደቀ በኋላ ፍቃድ የመስጠቱ፣ የመከታተሉና የመቆጣጠሩ ስራ ይጀመራል፡፡
 


Read 3684 times