Saturday, 17 October 2015 09:50

በ13 ዓመቱ አውሮፕላን ለመግዛት ከአጋሮ አዲስ አበባ የመጣው ታዳጊ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

     ቅልጥጥ ያሉ የሀብታም ገበሬ ልጅ ናቸው፡፡ ሐጂ አባመጫ አባደጋ፡፡ አባታቸውም ሆኑ አያታቸው በርካታ ጋሻ የቡና መሬት የነበራቸው ሀብታሞች እንደነበሩ አጫውተውናል፡፡ ሐጂ አባመጫ አሁን የሚኖሩት አጋሮ ከተማ ውስጥ ቢሆንም የተወለዱት ከከተማው ትንሽ ወጣ በምትል ኪሎሌ በተባለች የገጠር መንደር ነው፡፡
ሐጂ አባመጫ እድሜያቸውን በትክክል አያውቁትም፡፡
74 ወይም 75 ዓመቴ ነው ቢሉም ከዚያ በላይ እንደሚሆናቸው መገመት ይቻላል፡፡ አባታቸው በልጅነት ቢሞቱባቸውም አቶ ሺበሺ ገብረየስ የተባሉ ሞግዚት ተሹሞላቸው በቅምጥል ነው ያደጉት፡፡ አገር መጐብኘት የጀመሩት በልጅነታቸው ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚበርባቸውን ከተሞች ሁሉ ማየትና መጐብኘታቸውን ይናገራሉ፡፡ ከጂማ ጐሬ፣ ከጂማ አዲስ አበባ፣ ከጂማ ጋምቤላ፣ ከጂማ አስመራ፣ ከጂማ… ብዙ ቦታዎችን ጐብኝተዋል፡፡ ሐጂ ወደ ሳዑዲ የሄዱትም በልጅነታቸው እንደሆነ አውግተውናል፡፡ከቦታ ቦታ የሚዘዋወሩት በአውሮፕላን ቢሆንም፣ የዚያን ጊዜ አውሮፕላኖች አይመቹም፡፡ ቡና፣ ቆዳ፣ በርበሬ፣ ቅመማ ቅመም፣… ይጫንባቸዋል፡፡ ሰውና ዕቃ የሚጫነው አንድ ላይ ነበር፡፡ ይህ ነገር ለወጣቱ ሐጂ አባመጫ አልተመቻቸውም፡፡ “የራሴ አውሮፕላን ቢኖረኝ!” እያሉ ማሰብ ጀመሩ፡፡
በአንድ ወቅት ተከሰው አዲስ አበባ መጥተው ነበር፡፡ ከራስ አደፍርስ 20 ጋሻ የቡና መሬት ገዝተው ነበር፡፡ ሳይገብሩ ብዙ ይቆያሉ፡፡ ራስ አደፍርስ ከስሰው አዲስ አበባ አስጠሯቸው፡፡ ሞግዚታቸውን አቶ ሺበሺ፣ ቅጥረኛ ፀሐፊዎቻቸውን፣ ሌሎች አጃቢዎችንም አስከትለው መጡ፡፡ ራስ አደፍርስ “የግብር አልከፈላችሁ፣ ማር አልጫናችሁ… ምንድነው ነገሩ?” ብለው ተቆጡ፡፡
ጥፋታቸውን አምነው፣ ግብሩንም ለመክፈል ተስማምተው ተመለሱ፡፡የግል አውሮፕላን እንዲኖራቸው የመፈለግ ጉጉታቸው እየጨመረ ሄዶ ለመግዛት ወሰኑ፡፡ እንዳጫወቱን፤ አጋሮ እንደተመለሱ በ13 ዓመታቸው፤ ማርትሬዛ በስልቻ ሞልተው ብቻቸውን አዲስ አበባ መጥተው ራስ አደፍርስን “አውሮፕላን መግዛት እፈልጋለሁ” አሏቸው፡፡ ራስም ግራ በተጋባ ስሜት፤ “ለመሆኑ አውሮፕላን በስንት ብር ነው የምትገዛው?” በማለት ጠየቋቸው፡፡ ሐጂ አባመጫም፤ “ጠይቀህ ንገረኝ እንጂ!” ሲሉ መለሱላቸው፡፡ ወሬው ራስ መስፍን ስለሺ ጋ ደረሰና በንዴት ጦፉ፡፡“ብሩን አምጣ፡፡ እኔ እገዛልሃለሁ” በማለት የያዙትን ገንዘብ ተቀበሏቸው፡፡ በዚህ ብቻ አላበቁም፡፡ “ጨምር!” አሏቸው፡፡ “አውሮፕላኑን ሳላይ እንዴት እጨምራለሁ? እኔ ከዚህ በላይ የለኝም” አሉ ሐጂ አባመጫ፡፡ ራስ መስፍን፣ “እንዴት አውሮፕላን ለመግዛት ትነሳለህ? ወንጀል መሆኑን አታውቅም?” በማለት ሊያስሯቸው ፈለጉ፡፡ሐጂ “እኔ ውንጀላ መሆኑን አላወኩም” አሉ፡፡ ራስ አደፍርስና የቢትወደድ እንዳልካቸው መኮንን አባት ሽምግልና ገቡና “አሁን ይኼ ልጅ ምኑ ይታሰራል? ወጣት ነው፤ የመግዛት ፍላጐት አደረበት፣ ለመግዛት ተነሳ፡፡ ከዚህ ጥፋ ብሎ ማባረር ነው እንጂ ምኑ ይታሰራል?...” በማለት ሸመገሉ፡፡ በዚህ አይነት ሐጂ አባመጫ ከእስር ድነው፣ ሉክስ (አዲስ) ላንድሮቨር ገዝተው ወደ አገራቸው ተመለሱ፡፡ሐጂ አባመጫ ለቤተሰባቸው ሁለተኛ ልጅ ናቸው፡፡ ታላቃቸው ደግሞ ሴት ናቸው፡፡ ስለዚህ በተለያየ ቦታ ያለውን የቡና እርሻ የሚያስተዳድሩት እሳቸው ናቸው፡፡ በአንድ ወቅት ከወረሱት ሌላ በግላቸው 12 ጋሻ መሬት ቡና ነበራቸው፡፡ ታዲያ ቡና ተለቅሞ ሲሸጥ በሺዎች ኩንታል ነበር፡፡
“የቡና ዋጋ እንዳሁኑ ቢሆን ኖሮ አውሮፕላኑም ይገዛ ነበር” በማለት ቀልደዋል፡፡ ታዲያ ምን ያደርጋል? አዱኛ ብላሽ! እንደሚባለው አብዮት መጣና ሙልጫቸውን አስቀራቸው፡፡
አሁንም ግን አጋሮ ከተማ ውስጥ ቦታ ገዝተውና ቤት ሰርተው እየኖሩ ነው፡፡ ኑሮአቸው ጥሩ ነው፡፡ ቤታቸው ሰፊ ሲሆን ሁለት ግቢ አለው፡፡ አራቱ ወንዶች ልጆቻቸው አሜሪካ ይኖራሉ፡፡ ሁለት ሴቶች አዲሳባ አሉ፡፡ ሌሎቹ አጋሮ ከተማ አብረዋቸው ይኖራሉ፡፡

Read 6478 times