Saturday, 24 October 2015 09:06

97 ውየጪ ኩባንያዎች የሚሳተፉበት አለም አቀፍ የንግድ ትርኢት ይካሄዳል

Written by  ማህሌት ኪዳነወልድ
Rate this item
(1 Vote)

    የአገር ውስጥ ግዙፍ አምራች ድርጅቶችና 97 የውጭ ኩባንያዎች የሚሳተፉበት #ኢትዮ Sፒ” የተሰኘ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢት ከፊታችን ሐሙስ ጀምሮ ለአራት ቀናት በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ይካሄዳል፡፡ የንግድ ትርኢቱን ሻክረክስ ንግድና ኤቨንት ማኔጅመንት፣ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና ከውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ሲሆን የሻክረክስ ንግድና ኤቨንት ስራ አስኪያጅ አቶ አክሊለ
በለጠ እንደተናገሩት፤ በትርኢቱ ላይ 52 የአገር ውስጥ ግዙፍ አምራችና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች
እንዲሁም ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸው 97 የውጪ አገራት ኩባንያዎች በፕላስቲክ፣ በፔትሮ ኬሚካልስ፣ በህትመት፣ በማሸጊያና በወረቀት ምርት፣ በማሽነሪ፣ በጥሬ እቃ አቅርቦትና ቴክኖሎጂዎች ላይ የሚሳተፉ ይሆናሉ፡፡ የንግድ ትርኢቱ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍን ከማስፋፋትና ለውጪ ባለሀብቶች በአገሪቷ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጭ ከማስተዋወቅ ባሻገር የውጪ ኩባንያዎች ከአገር ውስጥ አምራችና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶችና ተቋማት ጋር በጥምረት በመስራት የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የገበያ ትስስርና የልምድ ልውውጥ የሚያደርጉበት ነው ተብሏል፡፡ ትርኢቱ በሚቆይባቸው አራት ቀናት ውስጥ በየቀኑ ከ100 በላይ ኩባንያዎች በአቻ ለአቻ የውይይት መድረክ ላይ እንዲገናኙ በቀን፣ በሰአትና በተሳታፊ ዘርፍ ተለይቶ ተጋብዘዋል ተብሏል፡፡ የውጪ ኩባንያዎቹ ከግብፅ፣ ቻይና፣ ህንድና ሱዳንን ጨምሮ ከተለያዩ አገራት የተውጣጡ መሆናቸውን የገለጹት ስራ አስኪያጁ፤ የንግድ ትርኢቱ ጥራቱን የጠበቀና የላቀ ምርት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ ረገድ የበኩሉን ድርሻ ያበረክታል ብለዋል፡፡ የንግድ ትርኢቱ ለህዝብ ክፍት የሚሆነው ከቀኑ 7 ሰዓት እስከ ምሽቱ 1 ሰዓት እንደሆነ ታውቋል፡፡  

Read 1081 times