Saturday, 24 October 2015 09:17

ተንቀሳቃሽ አውሮፕላን የሰራው የበደሌ ከተማ ወጣት

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(3 votes)

    ስለአውሮፕላን ምንነት፣ አሰራር፣ … ሁነኛ እውቀት ያገኘው በአገራችን የኢንተርኔት አገልግሎት ከተጀመረ በኋላ ነው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለአውሮፕላን የሰማው ግን በጣም ህጻን ሳለ ነው፡፡ እቤታቸው ጎረቤት ተሰብስቦ ቡና ሲጠጡ “አየር (አውሮፕላን) ሰው ይዞ ይሄዳል” ሲሉ ሰማ፡፡ የ7 ዓመት ልጅ እያለ በ1986 አውሮፕላን በደሌ አርፎ ነበር፡፡ ሄዶ አየው፡፡ አንድ ወጣት ከኋላው ሲሮጥ እንጂ ሰው ይዞ ሲሄድ አላየም፡፡
ስለ አውሮፕላን እያሰላሰለ ቆየ፡፡ በትምህርቱ እየገፋ ሲሄድ በትምህርታቸው ውስጥ አውሮፕላን ሰርተው ያበረሩት ኦሊቨርና ዊልበር ራይት የተባሉ ሁለት ወንድማማቾች መሆናቸውን አወቀ፡፡ በዚህ ጊዜ እኔስ ለምን አልሰራም? የሚል ፍላጎት አደረበትና በ1993 ዓ.ም ከወዳደቁ ነገሮች ሙከራ ጀመረ፡፡ በመጽሔትና መጻሕፍትም ማገላበጥ ያዘ፡፡ የፊዚክስ መምህራንን ቢጠይቅም በቂ ምላሽ አላገኘም፡፡ “ስለ አውሮፕላን ምንነትና አሰራር በሚገባ የተረዳሁት የኢንተርኔት አገልግሎት ከተጀመረ በኋላ ነው” ይላል፤ በበደሌ ከተማ ተንቀሳቃሽ አውሮፕላን የሰራው ወጣት ፍስሐ በየነ፡፡ ወጣት ፍስሐ የመጀመሪያ ዓመት ትምህርቱን በበደሌ ከተማ በሚገኘው ዳበና ቴክኒክና ሙያ ት/ቤት፤ የ2ኛና የ3ኛ ዓመት ትምህርቱን በኢሊባቦር ዞን ተከታትሎ፣ በጀነራል ሜካኒክስ በዲፕሎማ ተመርቋል፡፡ ለብዙ ዓመት በርካታ እልህ አስጨራሽ ሙከራዎች ቢያደርግም የሚሰራው በትርፍ ሰዓቱ ስለሆነ ምኞቱን ማሳካት አልቻለም፡፡ ዓላማውን ለማሳካት የዛሬ ሶስት ዓመት ህንፃዎችና መኖሪያ ቤቶች ሲሰሩ በረዳትነት የሚሰራውን የኤሌክትሪክ መዘርጋት ትቶ፣ በሙሉ ኃይሉ በመንቀሳቀስ አውሮፕላን ሰርቶ ለመጨረስ በቅቷል፡፡ የአውሮፕላኑ አካል፣ ከአሉሚኒየም፣ ከቀላል ብረትና ቀላል እንጨት ነው የተሰራው፡፡ የብስክሌት ሞተር ተገጥሞለታል፡፡ ትክክለኛውን ሞተር ለማግኘት አንድ ዓመት እንደፈጀበት ፍስሐ ተናግሯል፡፡ ከሞተሩ ውስጥ አስፈላጊ  ያልሆኑ ዕቃዎች ወጥተው ነው የተገጠሙት፡፡ አንዱ ሞተር የ17፣ ሁለቱ የ34 ፈረስ ጉልበት አላቸው፡፡ እያንዳንዱ ክንፍ 3 ሜት. ከ20 ሴ.ሜ ርዝመት አለው፡፡ አውሮፕላኗ አንድ ሰው የምትይዝ ሲሆን ለተባይና ፀረ አረም መርጫ የምታገለግል እንደሆነች፣ አውሮፕላኗን ለመስራት ለማሽን ኪራይ፣ ለጉልበት፣ ለሞተር…. 217ሺህ ብር ወጪ መደረጉን ፍስሐ ገልጿል፡፡ ፍስሐ ወደፊት ድጋፍ የሚያደርግለት አካል ካገኘ፣ ለአገር ጠቃሚ የሆነ አዲስ የፈጠራ ውጤት ይዞ ለመቅረብ ዕቅድ አለው፡፡ አንዳንድ ወገኖች ወጣቱ የፈጠራ ሰው የትምህርት ዕድል አግኝቷል ቢሉም ከኤርፖርት አካባቢ የትምህርት ዕድል ይመቻችልሃል ከመባሉ በስተቀር ምንም
እንዳላገኘና ማንም ቀርቦ እንዳላነጋገረው ወጣቱ የፈጠራ ሰው ፍስሐ በየነ ተናግሯል፡፡

Read 2874 times