Saturday, 24 October 2015 09:44

ቅዱስ ሲኖዶስ በ“ተሐድሶ ኑፋቄ” እና በሙስና ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ይሰጣል

Written by 
Rate this item
(5 votes)

• በቤተ ክርስቲያኒቷ ስም በብዙኃን መገናኛ ስለሚተላለፉ ትምህርቶች ይወስናል

   የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ የቤተ ክርስቲያኒቷን ቀጣይ ህልውና እየተፈታተኑና የምእመናኗን ፍልሰት እያባባሱ ናቸው በተባሉ፤ የ“ተሐድሶ ኑፋቄ” እና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ላይ በጥልቀት በመምከር ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ተገለጸ፡፡የቅዱስ ሲኖዶሱ የመጀመሪያ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ፣ ከትላንት በስቲያ በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በመክፈቻ ጸሎት ሥነ ሥርዐት የተጀመረ ሲሆን በምልአተ ጉባኤ የተሠየመው አጀንዳ አርቃቂ ኮሚቴ በቀረፃቸውና በምልአተ ጉባኤው በጸደቁ የመነጋገርያ ነጥቦች ለቀናት እንደሚመክር ታውቋል፡፡
የቅዱስ ሲኖዶሱን ዋና ጸሐፊ ያካተተውና ሰባት ሊቃነ ጳጳሳትን የያዘው አርቃቂ ኮሚቴ፣ ለምልአተ ጉባኤው ካቀረባቸው ከ15 ያላነሱ አጀንዳዎች መካከል፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ሰርገው በመግባት  አስተምህሮዋን፣ ሥርዐቷንና ትውፊቷን ውስጥ ለውስጥ በመበረዝ ጉዳት አስከትለዋል የተባሉ  “የተሐድሶ ኑፋቄ” አራማጆች ጉዳይ አንዱ ሲሆን የእንቅስቃሴውን ችግር የተመለከቱ ጥናቶችና መረጃዎች በጥልቀት ይፈተሹበታል፤ ተብሏል፡ከቅዱስ ሲኖዶሱ ስብሰባ ቀደም ብሎ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ደረጃ ለ34ኛ ጊዜ የተካሔደው የሰበካ አስተዳደር አጠቃላይ ጉባኤ ባወጣው መግለጫ፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ የተወገዘውን “የተሐድሶ ኑፋቄ”ን ተጽዕኖ ለመቋቋምና የምእመናንን ፍልሰት ለመግታት በቂና መጠነ ሰፊ በሆነ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ምእመናንን በእምነታቸው ለማጽናት የጋራ አቋም ይዟል፤ ለተፈጻሚነቱም በልዩ ልዩ ብሔረሰቦችና ቋንቋዎች የሚያስተምሩ መምህራንን በጥራትና በቁጥር ማሳደግ እንዲሁም አገልግሎቱን ዘመኑ በሚፈቅዳቸው ሚዲያዎች በመታገዝ ለመላው ዓለም ማዳረስ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል፡፡
ሚዲያዎቹ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ የራስዋን ድምፅ የምታሰማባቸውና ማዕከላዊነታቸውን የጠበቁ መሆን እንደሚገባቸው በመግለጫው የተጠቀሰ ሲሆን ቅዱስ ሲኖዶሱም በቤተ ክርስቲያኒቷ ስም በልዩ ልዩ ሚዲያዎች በመተላለፍ ላይ ስለሚገኙ ትምህርቶች ከምእመናን ሲቀርቡ የቆዩ አቤቱታዎችን በአጀንዳው በማካተት ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ተጠቁሟል፡፡የ“ተሐድሶ ኑፋቄ” አራማጆች፣ አስተምህሮዋን ከመፃረር ባሻገር በአንዳንድ የሀገር ውስጥና የውጭ አካባቢዎች፣ ማዕከላዊውን አስተዳደሯን የሚፈታተን “ገለልተኛ አስተዳደር” በመፍጠር ምእመናኗን እያደናገሩ እንደሚገኙ ተመልክቷል፡፡ የመልካም አስተዳደር ዕጦትና ሙስና ለችግሩ አስተዋፅኦ እንዳለው በጋራ አቋሙ የገለጸው አጠቃላይ ጉባኤው፣ ለቤተ ክርስቲያኒቱ የወደፊት ህልውና ከፍተኛ ስጋት በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶሱ መዋቅሯን የሚያጠናከርና የሕግን የበላይነት የሚያረጋግጥ አስቸኳይ መፍትሔ ሊፈለግለት ይገባል ተብሏል፡፡ለሙስናና ብክነት የተጋለጡ አሠራሮችን በወሳኝ መልኩ በመቅረፍ አደረጃጀቷና አሠራሯ ዘመኑን በሚዋጅ የግልጽነት፣ የተጠያቂነትና የአሳታፊነት መርሕ ላይ ለመመሥረት ያስችላሉ የተባሉ ዐበይት ውሳኔዎች በቅዱስ ሲኖዶሱ ሲተላለፉ ቢቆዩም ተግባራዊነታቸው የሚጠበቀውን ያህል እንዳልሆነ ተነግሯል፡፡ ያልተተገበሩ ውሳኔዎቹን በዝርዝር ይገመግማል የተባለው ምልአተ ጉባኤው፣ ተፈጻሚነታቸውን በመከታተል መዋቅራዊ ለውጡን የሚያረጋግጥ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሊያቋቋም እንደሚችልና በቀጣይነትም ከኹሉም አካላት የተውጣጣ የቤተ ክርስቲያኗን ችግር የሚያጠና ኮሚቴ እንደሚሠይም ተጠቁሟል፡፡ በተጨማሪም፤ በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ አንቀጾች የተመለከቱ ደንቦችን በተጣጣመ መልኩ የሚያወጣ አካል እንደሚሠየም የተጠቀሰ ሲሆን የፓትርያርኩ ልዩ ሀገረ ስብከት የሆነው የአዲስ አበባ ልዩ መተዳደርያ ደንብና ከባድ ቀውስ ፈጥረዋል የተባሉት የአስተዳደር ችግሮቹ በአጀንዳነት አብሮ እንደሚታይ ተገልጧል፡፡

Read 5051 times