Saturday, 24 October 2015 09:44

ኤልኒኖን ተቋቁመው ምርታማ የሚሆኑ የሰብል ዝርያዎች ለአርሶ አደሩ ተሰራጨ

Written by  ማህሌት ኪዳነወልድ
Rate this item
(2 votes)

ኤልኒኖ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ የሚቋቋሙና ምርታማ የሚሆኑ ወደ 3ሺህ ኩንታል የሚጠጉ የሰብል ዝርያዎችን ለአርሶአደሩ ማድረሱን የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡ የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አዱኛ ዋቅጅራ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ቦሎቄ፣ ጤፍ፣ ማሽላና ሽንብራን ጨምሮ የተሰራጩት የሰብል ዝርያዎች ድርቅን የሚቋቋሙና ቶሎ የሚደርሱ ናቸው፡፡
እንደ ዶ/ር ዋቅጅራ ገለጻ፤ ዘሮቹ በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ምስራቅ ሸዋና ድሬደዋ እንዲሁም በሐረሪና ስምጥ ሸለቆ አካባቢዎችን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች ለሚገኙ አርሶአደሮች ደርሰዋል፡፡
 የዝርያዎቹ በአርሷደሩ እጅ መድረስ የድርቁን ስጋት የሚቀንስ ይሆናል ያሉት ዶክተሩ በቂ ዝናብ የሚያገኙ አካባቢዎችም ሰብሉን በደንብ እንዲንከባከቡና በቂ ምርት ማምረት እንዲችሉ መስኖን እንዲጠቀሙ እያደረግን ነው ብለዋል፡፡ አርሶአደሮቹ ከዝርያዎቹ በተጨማሪ እርጥበትን ለማቆየት የሚያስችሉ አሰራሮችን ተግባራዊ እያደረጉ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ተቋሙ ከብቶችን ከድርቁ ለመታደግ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ሳርና ድርቆሽ እያቀረበ መሆኑን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከሜትሮሎጂና ከሌሎች አካሎች ጋር በመስራት ኤሊኖ እንደሚከሰት ማወቃችን ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ ረድቶናል ነው ብለዋል፡፡
ወደፊትም መሰል ችግሮችን ቀድሞ ለማወቅና መተንተን እንዲችል በግብርና ምርምር ስር በአየር ለውጥ ላይ የሚሰራውን ዳይሬክቶሬት የአቅም ግንባታና ተሞክሮ ልውውጥ እንዲያገኝ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡  

Read 1478 times