Saturday, 24 October 2015 09:47

የ“ሎሚ” መፅሄት ባለቤት የ18 ዓመት ፅኑ እስራት ተፈረደበት

Written by 
Rate this item
(4 votes)

የ300 ሺ ብር የገንዘብ ቅጣትም ተበይኖበታል

የ“ሎሚ” መፅሄት አሳታሚ የነበረው ዳዲሞስ ኢንተርቴይንመንትና የፕሬስ ስራዎች ኃላ/የተ/የግል ማህበር እና ስራ አስኪያጁ አቶ ግዛው ታዬ፤ ከ800 ሺህ ብር በላይ ታክስ በማጭበርበርና በሌሎች ተያያዥ 14 ክሶች፣ ፍ/ቤት የጥፋተኝነት ውሳኔ በይኖበት፣ የ18 ዓመት ፅኑ እስራትና የገንዘብ ቅጣት ተላልፎበታል፡፡
ድርጅቱም ሆነ ስራ አስኪያጁ ግዛው ታዬ፤ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ክሱ እስከተመሰረተበት ጊዜ ድረስ ለ5 ዓመታት ሂሳቡ ኦዲት አልተደረገም የሚለው የአቃቤ ህግ የክስ መዝገብ፤ ሁለቱም ተከሳሾች የተለያዩ የታክስ ማጭበርበሮችን ሲያከናውኑ ቆይተዋል ይላል፡፡
 የገቢ ግብርና የተጨማሪ እሴት ታክስ በመሰወርም ድርጅቱም ሆነ ስራ አስኪያጁ መንግስትን ከ800 ሺህ ብር በላይ ማሳጣታቸውን የክስ መዝገቡ ይገልፃል፡፡
ተከሳሽ በሚያሳትመው “ሎሚ” መፅሄት፤ ህዝብን ለአመፅ በማነሳሳትና ሃሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት ወንጀል ተከሶ በ50 ሺህ ብር ዋስ ከተለቀቀ በኋላ መሰወሩ የተጠቀሰ ሲሆን ይሄኛውም የፍርድ ሂደት ተከሳሹ በሌለበት እንደታየ ታውቋል፡፡
ተከሳሽ በአቃቤ ህግ የቀረበበትን ክስ በአካል ቀርቦ መከላከል ባለመቻሉም፣ ፍ/ቤቱ በሌለበት የ18 ዓመት እስርና የ100ሺህ ብር ቅጣት እንዲሁም ያስተዳድረው በነበረው ድርጅት ላይ የ200 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

Read 2828 times