Saturday, 24 October 2015 09:57

ህይወት እንደገና

Written by  ተሾመ ተፈራ
Rate this item
(4 votes)

    በቅርቡ፤ በሥራ አጋጣሚ በሰሜን ጎንደር ዞን፣ ደንቢያ ወረዳ ከምትገኘው ትንሽዋ ከተማ ቆላ ድባ ሄጄ ነበር። ታዲያ ቆላ ድባን ባስታወስኩ ቁጥር፤ አብራ በትዝታ የምትነግስብኝ አንዲት ጠንካራ ሴት አግኝቼ ተመልሰሻለሁ፡፡ ይህች ጠንካራ ሴት የውብነሽ (ሥሟ የተቀየረ) ትባላለች፡፡ ከቆላ ድባ ጋር የውብነሽን አስታውሳታለሁ፡፡ ቆላ ድባ ብዙ ታሪክ እና ባለታሪክ እንደሚኖራት አምናለሁ፡፡ ሆኖም ቆላ ድባ በእኔ ህሊና ከየውብነሽ ጋር ተያይዛ ተቀምጣለች፡፡ አሁን በአጋጣሚ ‹‹ቆላ ድባ›› የሚል ቃል ብሰማ፤ የውብነሽ ፈጥና በትውስታዬ መምጣቷ የማይቀር ነው፡፡
የውብነሽ ታሪኳን ስታጫውተኝ፤ ከህሊናዬ ችሎት ፊት ተገትሬ ነበር፡፡ እንደ ፀሐፊ፤ ‹‹በሴቶች ችግር ላይ አተኩሬ ለምን አልፃፍኩም?›› የሚል የህሊና ክስ ተከፈተብኝ፡፡ ህሊናዬ፤ ‹‹ያልሰጡት ተቀባይ፤ ያልጠሩት አቤት ባይ›› ሆኖ በህሊና ፍርድ ቤት ቆመ፡፡ እንግዲህ ይህ ጽሑፍ፤ ህሊናን ከእስር በማዳን ጥረት የተጻፈ እንደሆነ ቆጥሬዋለሁ፡፡
መክፈቻ
የየውብነሽ ህይወት፤ ባህላዊ እና ማህበረሰባዊ መነሻ ያላቸውን የሐገራችንን ሴቶች ችግር እንድንዘክር የሚያደርግ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ሴቶች፤ ባላደጉ ሐገራት እንደሚኖሩ ሌሎች የዓለማችን ሴቶች፤ በአንጻራዊ ሚዛን ከጠቅላላው ማህበረሰብና ከወንዶች ዝቅ ያለ ማህበራዊ ስፍራ የያዙ ሆነው ቆይተዋል፡፡ እንደ ማህበራዊ ዓውዱ ሁኔታ፤ የአንዷ ሴት ችግር፣ በደል ወይም መከራ ከሌላኛዋ የባሰ ይሆን እንደሆነ እንጂ፤ ሁሉም ሴቶች የተለያየ በደል የተሸከሙ ናቸው፡፡ በኋላ ቀር እና ድሐ ሐገራት የሚኖሩ ሴቶች ችግር፤ በሰለጠኑና በበለፀጉ ሐገራት ከሚኖሩ ሴቶች ኑሮ የከፋ እንደሆነ ሁሉ፤ በገጠር የሚኖሩት ሴቶች የኑሮ ሁኔታ በከተማ ከሚኖሩት ይከፋል፡፡
በገጠር የሚኖሩ ሴቶች በርካታ አካላዊ ሥራዎች የሚጫንባቸው ናቸው፡፡ የገጠር ሴቶች፤ ሁሉም ዓይነት አዕምሮአዊ መብት የሚነፈጋቸው ናቸው፡፡ ማይምነት እንደ ገጠር ሴት መጫወቻ ያደረገው የህብረተሰብ ክፍል የለም፡፡
የገጠር ሴቶች፤ የእናትነት ኃላፊነታቸውን ለመወጣትና ልዩ ችግሮቻቸውን ለማስወገድ የሚያስችል ጊዜ እስኪያጡ ድረስ፤ ወገብ የሚያጎብጥ ከባድ የቤትና የግብርና ሥራ ተሸክመው፣ ያለ አንዳች ማጉረምረም ህይወትን የሚገፉ ናቸው፡፡ ጧት ማልደው ተነስተው፤ ሲማስኑ ባጅተው፤ ሲማስኑ የሚከርሙ ናቸው፡
የከተማ ሴቶች የኑሮ ሁኔታ፤ ከገጠር ሴቶች ኑሮ ባይብስ አይሻልም፡፡ የከተማ ሴቶች በቂ የማህበረሰብና የህግ ጥበቃ የማያገኙ ናቸው፡፡ በሥራ አጥነት የሚቸገሩ፣ ለተለያዩ ፆታዊ ጥቃቶች የተጋለጡ፣ በኑሮ ሸክም የጎበጡ ናቸው፡፡ በብርቱ የኑሮ ሰልፍ የተሸነፈና አጉራህ ጠናኝ ብሎ የሸሸ ወይም የወሰለተ ባል፤ አስታቅፎ - አሳዝሎ ሲኮበልልባቸው፤ በብቸኝነት ልጆቻቸውን ለማሳደግ፣ ተሸክመው በመከራ የሚጠበሱ የፍቅር ግዙዎች ናቸው፡፡ የውብነሽ ከእነዚህ ሴቶች (እናቶች) አንዷ ነች፡፡
የሴቶችን መከራ ክብደት ለማየት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው፤ የሶማሊያ ተወላጇ አያን ሒርሲ ዓሊ (Ayaan Hirsi Ali) የፃፈችውን ግለ ታሪክ ማንበብ ይኖርበታል፡፡ ወይም እኔ ቆላ ድባ እንዳደረግሁት፤ እንደ የውብነሽ ላሉ ሴቶች ጆሮውን ብቻ ሳይሆን ቀልቡንም ሰጥቶ፤ የሴቶች ህይወት ሲተረክ ከልብ ማዳመጥ ይኖርበታል፡፡ ወትሮም፤ ‹‹የነገር ወጡ፣ ማዳመጡ›› እንደተባለ፤ የውብነሽን ሳዳምጥ፤ አያን ሒርሲ መጣች፡፡
አያን ሒርሲ
አያን ሒርሲ ዓሊ፤ ‹‹Infidel›› (2007) በሚል ርዕስ ያሳተመችው መፅሐፍ አለ፡፡ በዚህ መፅሐፍ ከልጅነት እስከ ዕውቀት የዘለቀ የመከራ ህይወት ጎዞዋን ተርካበታለች፡፡ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ፤ የመከራ ህይወት ያሸከሟት ወገኖች፤ በደሏን ለማስቀረት መታገሉ ቀርቶ፤ በደሉን ለምን ተናገርሽ ብለው ጮኹባት፡፡ ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሃል የሚሉት ምሳሌአዊ አነጋገር በደንብ የሚገባን በእርሷ ህይወት ነው፡፡ እርሷ ‹‹Infidel›› የተሰኘ መፅሐፏን ከማሳተሟ በፊት፤ ቲዮቫን ጎህ (Theo van Gogh) የተባለ፤ በአንድ የሆላንድ የፊልም አምራች ኩባንያ ውስጥ የሚሰራ ጀግና፤ አሳዛኙን የአያን ሒርሲ ህይወት በአጭር ዘጋቢ ፊልም አቀናብሮ ለህዝብ አቅርቦት ነበር፡፡
ቲዮ ቫን ጎህ በዚህ ሥራው ክፉና ጨካኝ ጠላት አፍርቶ ነበር፡፡ አንድ ማለዳ (ኖቬምበር፣ 2004)፤ አሮጌ ጥቁር ብስክሌቱን ጋልቦ በአምስተርዳም አውራ ጎዳና እየነዳ ወደ ፊልም ኩባንያው ቢሮ ይጓዝ ነበር፡፡ ቢሮው ከሚገኝበት ግቢ ዋና በር አካባቢ ሲደርስ፤ አድፍጦ ይጠብቅ የነበረ አንድ ሽጉጥ እና ሁለት የሉካንዳ አራጅ ካራ የያዘ ሞሮኮአዊ ካደፈጠበት ጥግ ብቅ አለ፡፡ ቲዮ ቫን ጎህ አሮጌ ብስክሌቱን እያሽከረከረ ሲመጣ ያየው መሐመድ ቦየሪ (Muhammmad Bouyeri)፤ ካደፈጠበት ሥፍራ ወጣና ሽጉጡን አከታትሎ ተኮሰ፡፡
ቲዮ ቫን ጎህን በጥይት ተመትቶ ወደቀ፡፡ ከጋለባት ሳይክል ተሽቀንጥሮ ከአስፋልቱ ተነጠፈ፡፡ በሳይክሉ ፍጥነት እየተገፋ በደረቁ አስፋልት ላይ ተንሸራቶ ወደ ጥግ ተሸጎጠ፡፡  ግዳይ እንደጣለ የተረዳው መሐመድ ቦየሪ፤ ተንደርድሮ ቲዮ ቫን ጎህን ጋ ሄደ፡፡ ቲዮ ቫን ጎህ አልሞተም፡፡ በድንጋጤ እንደተሸበበ፤ ሽጉጥ ደግኖ ወደ እርሱ የሚሮጠውን ሰው ቀና ብሎ አየው፡፡ እናም፤ ‹‹እባክህን ወንድሜ መነጋገር አንችልም›› ሲል፤ እያቀሰተ ተማፀነው፡፡
ሆኖም፤ ቦየሪ የርኅራኄ ልብ አልነበረውም፡፡ እርሱ ንግግር አያውቅም፡፡ ስለዚህ እንደገና አራት ጥይቶችን አከታትሎ ተኮሰበት፡፡ መታው፡፡ ከዚያም፤ ከያዛቸው ሁለት የሉካንዳ አራጅ ካራዎች፤ አንዱን በቲዮ ቫን ጎህ ጉሮሮ ላይ ቀበቀበበት፡፡ ሁለተኛውን ካራ ደግሞ፤ ገዳዩ ለአያን ሒርሲ ዓሊ የፃፈውን ባለአምስት ገፅ የዛቻ ደብዳቤ፤ ነፋስ እንዳይወስድበት እንደ ስፒል ከደረቱ ጋር ለማያያዝ ተጠቀመበት፡፡ አያን ሒርሲ ዓሊ፤ ‹‹Infidel›› በተሰኘ መፅሐፏ፤ ‹‹ይህ ደብዳቤ በአድራሻ የተፃፈው ለእኔ ነበር፡፡ ሁለተኛውን ካራ ለደብዳቤው ማያያዣ አድርጎ ከደረቱ ላይ ሰክቶት ሄደ›› ስትል በመፅሐፏ መግቢያ ታወሳለች፡፡     
ሰውየው ይህን የአረመኔ እርምጃ የወሰደው፤ ቲዮ ቫን ጎህ አዘጋጅቶ ለህዝብ ያቀረበው አጭር ዘጋቢ ፊልም፤ ሐይማኖትን የሚዳፈር ይዘት አለው በሚል ነበር፡፡ በዚህ አጭር ዘጋቢ ፊልም፤ በልጅነት ዕድሜ በአጎትዋ የተደፈረች ታዳጊ ታሪክ እናያለን፡፡  ሆኖም አባቷ ይህን የደረሰባትን ችግር እያወቀ ዝም ሲል እንመለከታለን፡፡ ፊልሙ የዚህን አባት አድራጎት የሚያሳይ ነው፡፡ አያን ሒርሲ ዓሊ፤ መፅሐፉን ለመፃፍ የቆረጠችው፤ የመጀመሪያው ዘጋቢ ፊልም ተከታይ የሆነ ሁለተኛ ክፍል ለመሥራት እየተንቀሳቀሱ ሳለ በሞተው አጋሯ የጀመሩት ፕሮጀክት በመሰናከሉ መሰለኝ፡፡ በመፅሐፏ፤ ከህፃንነት ዘመንዋ ጀምሮ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን መከራ ፍንትው አድርጋ ታሳየናለች፡፡ የሶማሌ ሴቶች፤ ያለ ፍላጎታቸው ሲዳሩና ዝሙት ሰርታችኋል በሚል ሲገረፉ ታስነብበናለች፡፡
የዘጋቢ ፊልሙ አዘጋጅ ክፍል አንድን ሰርቶ እንደ ጨረሰ፤ ‹‹ፊልሙ ቁጣን ሊቀሰቅስ ይችላል፡፡ ስለዚህ፤ አዘጋጁ አንተ መሆንህ ሳይጠቀስ ለህዝብ ቢቀርብ ይሻላል›› የሚል ምክር የለገሱት ሰዎች እንደ ነበሩ የጠቀሰችው አያን ሒርሲ ዓሊ፤ ‹‹እርሱ ግን ቱግ ብሎ ተናደደ፡፡ ቲዮ ቫን ጎህ ደንበኛ ደች ነው፡፡ ጦረኛ ባይባል ሞገደኛ ሰው ነው፡፡ እንደ ደች ህዝብ ሐሳብን ለመግለፅ ነፃነት ትልቅ ከበሬታና እጅግ የጠለቀ ትስስር ያለው ህዝብ በምድር አይገኝም፡፡ አንድ ቀን ከእኔ ጋር ስናወራ፤ ‹እዚህ ሆላንድ በሚታየው ዘጋቢ ፊልሜ ላይ ስሜን ማውጣት ካልቻልኩ፤ ሆላንድም ሆላንድ አትሆን፤ እኔም ቲዮን አይደለሁ ማለት ነው› ብሎ አለኝ›› ትላለች፡፡
በሶማሊያ እንደ ተወለደች፤ በኢትዮጵያ እና በኬንያ እንዳደገች የምትናገረው አያን ሒርሲ ዓሊ፤ ከጥቃትና ከመብት ጥሰት መጠበቅ አለመቻሏ አንሶ፤ ከህፃንነት ዘመን የሚነሳ የመከራ ህይወቷን በይፋ መናገሯ እንደ ሐጢያት ተቆጥሮባት ተሳዳጅ ሆናለች፡፡ ከብዙ መከራ በኋላ በ1992 ዓ.ም አውሮፓ ገባች፡፡ እናም በሆላንድ መኖር ጀመረች፡፡ እንዲያውም፤ በምርጫ ተወዳድራ የፖላንድ ፓርላማ አባል በመሆን ተመረጠች፡፡
አያን ሒርሲ ዓሊ፤ የህዝብ ተወካይ ስለሆነች፤ ከመንግስት በተሰጣት አንድ የጋራ መኖሪያ ህንፃ (አፓርትመንት) ትኖር ነበር፡፡ በአያን ሒርሲ ዓሊ ላይ የጥቃት ዛቻ እንደሚደርስባት ያወቁ የጋራ የህንፃው ነዋሪዎች፤ በእርሷ ዳፋ ጉዳት ይደርስብናል ብለው ሰጉ፡፡ ስለዚህ፤ ‹‹አያን ሒርሲ ዓሊ ከእኛ ጋር መኖርዋ በህይወታችን ላይ ስጋት ደቅኖብናል፡፡ እርሷ አፓርትመንቱን ትልቀቅልን›› የሚል ክስ ለፍርድ ቤት አቀረቡ፡፡ ፍርድ ቤቱም ህንፃውን እንድትለቅ ወሰነ፡፡ ደነገጠች፡፡ ከዚህ በኋላ፤ ‹‹የዜግነት ነገር ተነስቶ እጅግ ውስብስብ ችግር ውስጥ ከመውደቄ በፊት ወደ አሜሪካ ተሰደድኩ›› ትላለች፡፡
አያን ሒርሲ ዓሊ፤ ከባህል ጋር ተያይዞ በሶማሊያ ሴቶች የሚደርስባቸው የብልት መተልተል፣ ያለ ዕድሜ ጋብቻ… ሌላም መሰል መከራዎችን የተቀበለች፤ የወንድ የበላይነት በሰፈነበት ማህበረሰብ ተረግጣ የኖረች አሳዛኝ ሴት ነች፡፡ አያን ሒርሲ ዓሊ ከሌሎች ድሃ ሐገራት ሴቶች ጋር የምታጋራቸው ችግሮች አሉ፡፡ ከእርሷ ማህበረሰብ ጋር የተያያዙ ልዩ ፈተናዎች መኖራቸው ባይታበልም፤ ታሪኳ የብዙ ሴቶች ህይወት ሆኖ ሊነገር የሚችል ነው፡፡ ስለዚህ ከእኛዋ ባለታሪክ፤ ከቆላ ድባዋ የውብነሽ ጋር በተመሳስሎ የሚነሳ ነገር እንዳለ ሁሉ፤ በሁለቱ ግፉ እንስቶች ህይወት መካከል እጅግ የሰፋ ልዩነት መኖሩን እናስተውላለን፡፡
የውብነሽ ታሪክ አሳዛኝ ታሪክ ነው፡፡ ለእኔ ስታጫውተኝ አዝኛለሁ፡፡ ሆኖም ህይወቷ ከአያን ሒርሲ ዓሊ ጋር ከተነጻጸረ፤ የውብነሽ ዕድለኛ ነች ማለት ይቻላል፡፡ ቢያንስ፤ የውብነሽ የደረሰባትን መከራ ለመግለፅ እና ለመናገር አትፈራም፡፡ እኔም የእርሷን ታሪክ ፅፌ በሆነው መንገድ ለህዝብ ለማቅረብ ሳስብ ጉዳት ይደርስብኛል ብዬ አልፈራም፡፡ እርሷ በነፃነት ታሪኳን እንዳጫወተችኝ፤ እኔም በነጻነት ታሪኳን ለመናገር እችላለሁ፡፡
ከፖላንድ ወደ አሜሪካ የተሰደደችው አያን ሒርሲ ዓሊ፤ ዛሬ በምን ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ አላውቅም፡፡ የውብነሽ ግን የደረሰባትን መከራ ተቋቁማ፤ ሴቶች ልጆችዋን ከእርሷ መሰል መከራ ለመጠበቅ በፅናት ታግላ፤ ‹‹ተመስገን›› ማለት ከቻለችበት ደረጃ ደርሳለች፡፡ ከቀድሞው የመከራ ህይወት ወጥታ፣ ከባዱን የህይወት ዳገት በጥርስና በጥፍር እየቧጠጠች ዘልቃ ወጥታ፣ አሁን ከደልዳላ ጎዳና ገብታ ጉዞዋን ቀጥላለች፡፡ ዛሬ የኋላ ታሪኳን ዞር ብላ እያየች፤ የእርሷንና የልጆችዋን ዘመን እያነፃፀረች፤ የእርሷን ዘመን እወቀሰች፤ ‹‹ደግ ዘመን መጥቷል›› እያለች የልጆችዋን ማህበራዊ ዘመን ታመሰግናለች፡፡ በኑሮዋ ደስተኛ ነች፡፡ ያ የመከራ ህይወት ከእርሷ ርቆ ሄዷል፡፡ ግን ያለፈ የመከራ ህይወት ትዝታዋ ዛሬም ከእርሷ ጋር አለ፡፡ ይህ ነገር፤ አንድ ሌላ ነገር ያስታውሰኛል፡፡
የሶቭየት ሶሻሊስት ስርዓት ከፈረሰ በኋላ፤ ለምርምር ወደ አንዲት የሩሲያ የገጠር መንደር የሄደው ካሮላይን ሐምፍሬይ፤ በጥናት ሥራው መግቢያ የጠቀሰው አንድ ገጠመኝ አለ፡፡ ፀሐፊው፤ የሶሻሊስት ስርዓት ከፈረሰ ከአስር ዓመት ገደማ በኋላ ነበር፤ ባያንጉል ወደ ተባለች አንዲት የሩሲያ መንደር የሄደው፡፡
እናም እንዲህ ይላል፤ ‹‹በ1996 ዓ.ም የበጋ ወራት ወደ ባያንጎል ተመልሼ ሄድኩ፡፡ በባያንጎል የህብረት ሥራ ማህበር እርሻ የመግቢያ በር አካባቢ የነበረ የማርክስ ሐውልት ዛሬም እዛው ከድሮው ቦታ እንደ ቆመ አለ፡፡ የታላቁ ፈላስፋ የካርል ማርክስ ጭንቅላት ግዙፍ ሐውልት ሆኖ ከቆመበት ሥፍራ አጠገብ፤ በወደረኛ ግዝፈት የቆመው የመንደሪቱ የህብረት እርሻ ማህበር ስም የተፃፈበት ሰሌዳ ነው፡፡ ሁሉም ነገር ድሮ እንደ ነበረ ነው፡፡ የተለወጠ ነገር ቢኖር፤ ‹የካርል ማርክስ የህብረት ሥራ ማህበር እርሻ› የሚሉ ቃላት ይዞ ከነበረው ትልቅ ሰሌዳ አንድ ቃል ጎድላለች፡፡ ማርክስ የሚለው ቃል ተፍቆ ጠፍቷል፡፡ በምመለከተው ነገር ተገርሜ፤ ሐውልቱንና ከአጠገቡ ያለውን ሰሌዳ አትኩሬ ስመለከት፤ ወደ መንደሩ ይዞኝ የመጣው የታክሲ ሹፌር፤ ‹‹ይኸውልህ ማርክስ ከዚህ ሐገር ከሄደ ቆየ፤ ካርል ግን እዚሁ እኛ ዘንድ ቀርቷል›› ሲል ቀለደ፡፡››
ሐምፍሬይ ባያንጎል ስለተባለችው መንደር የተናገረውን፤ እኔ ስለ ቆላ ድባዋ የውብነሽ ህይወት ልጠቅሰው እችላለሁ፡፡ ‹‹ቆላ ድባ ያገኘኋት የውብነሽ መከራ የበዛበት ህይወቷ ከተቀየረ ቆየ፡፡ የመከራ ህይወት ትዝታዋ ግን ዛሬም በእርሷ ህሊና ደምቆ ይኖራል›› እላለሁ፡፡ ከእርሷም አልፎ ወደ ከእኔ የህሊና መዝገብ ታትሟል፡፡ እኔን ሰበብ አድርጎም፤ ይኸው ከእናንተ ደርሷል፡፡
የሴት እናት
የየውብነሽ ታሪክ ከህሊናዬ አልጠፋ ያለው፤ ከሐገራችን ሴቶች የተለየ ታሪክ ስላላት አይደለም፡፡ እርሷ የግል ታሪኳን ስታጫውጠኝ፤ ከአንድ ቀን የዘለለ ትውውቅ አልነበረንም፡፡ የውብነሽ ግልፅና ተግባቢ ሰው ነች፡፡ በልቤ ልዩ ስፍራ ያገኘችው በዚሁ ባህርይዋ እንደሆነ አስባለሁ፡፡
የቆላ ድባ የከተማ ነዋሪዋ የውብነሽ ያወጋችኝ ‹‹ግለ ታሪክ››፤ የብዙ ሴቶች ታሪክ በመሆኑ፤ አዲስ ነገር የለውም፡፡ አዲስ ስላልሆነ ቀልብ የሚስብ አይደለም፡፡ አደጋውም ይኸው ነው፡፡ የየውብነሽ ታሪክ የተለመደ የብዙ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ችግር በመሆኑ፤ እንደ ልዩ ክስተት አይታይም፡፡ ስለዚህ አይነገርም፡፡ ታዲያ አሁን፤ እኔ የእርሷን ታሪክ የማነሳው፤ ልማድ የሚያመጣውን መደንዘዝ ተሻግሬ ለመሄድ በማሰብ ጭምር ነው፡፡   
አሁን - አሁን፤ በአገራችን ዘመናዊ  የፋብሪካ ውጤት የሆነው ቢራ በየገጠሩ እንደ ልብ የሚገኝ ቢሆንም፤  በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ባህላዊው መጠጣችን ጠላ፤ አሁንም ተወዳጅና ተመራጭ መጠጥ ሆኖ የቀጠለ ይመስለኛል። ጓደኞቼ  ዘመናዊውን መጠጥ ሊጋብዙኝ ቢፈልጉም፤ የእኔ ምርጫ ባህላዊው መጠጥ ጠላ ሆነ፡፡ በመሆኑም  ወደ አንድ ጠላ ቤት ጎራ አልን። ጠላ ቤቱ ሞቅ ደመቅ ያለና ከዚህ ቀደም ከማውቃቸው ሌሎች ጠላ ቤቶች በተለየ መልኩ እጅግ ጽድት ያለ ነው፡፡ ጽዳቱን በጣም ወደድኩት።
ጠላ ሻጯ የውብነሽ በመካከለኛ ዕድሜ ላይ የምትገኝ ሴት ናት። ያም - ያም ይጠራታል። እርሷም ያለመሰልቸት ሁሉንም እንደ ፀባዩ ለማስተናገድ ጥረት ታደርጋለች።  ሳቂታ እና ተጫዋች ባህርይዋ ከሰው ጋር በቀላሉ ለመግባባት አግዟታል። ሰዉ ከጠላ ባሻገር ለጨዋታ የሚሰበሰብበት ቤት ይመስላል፡፡ አንዳንዶች ጠላ ሳይዙ፤ እንዲሁ ከጓደኞቻቸው ጋር ተቀምጠው ሲጫወቱ አይቻለሁ፡፡ በአጭር ጊዜ የእኔም የባይተዋርነት ስሜት ጠፍቶ፤ ከበርካታ ሰዎች ጋር መግባባት ችያለሁ።
በተለይ ከጎኔ ተቀምጦ ከነበረው ወጣት ጋር የረጅም ጊዜ ትውውቅ እንዳለን ሁሉ የልብ ወሬ ማውራት ጀምረናል፡፡ ሌላው ቀርቶ በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ጭምር በነጻነት ተጫውተናል። መቼም ወጣቱ  ጨዋታውን ያውቅበታል። በሚያወራው ነገር የሰውን ቀልብ በቀላሉ የመግዛት አቅም ያለው ወጣት ነው። ከጨዋታ አዋቂነቱ ባሻገር፤ ሰው አክባሪና ትሁትም ነው።
እኔና ጓደኞቼ ሒሳብ ከፍለን ልንወጣ ስንነሳ፤ ሒሳቡ እንደ ተከፈለ ተነገረን። ስለግብዣው እና ስለጫወታው ወጣቱን አመስግነን ልንለያይ ስንል፤ የልጁ ጨዋታ አዋቂነት ስለማረከኝ ደግሜ ላገኘው ፈለግኩ፡፡ እናም በማግስቱ እንድንገናኝ  ቀጠርኩት። ግብዣዬን ተቀብለ፡፡ በዚሁ ተለያየን።
በማግስቱ፤ የወጣቱን ጨዋታ በመናፈቅ ብቻ ሣይሆን የግብዣ ብድሬን ለመመለስ በማሰብ ቀድሜ ተገኘሁ። አንድ ሁለት እያልኩ ጠበቅኩት፡፡ ወጣቱ አልመጣም። ጠላ የምትቀዳውን ሴት (ኮማሪቷን) ስለ ልጁ ጠየቅኳት፡፡ በነገርኳት ምልክት ወጣቱን በቀላሉ አወቀችው። ከእኔ ቀድሞ እንዳልመጣ፤ ነገር ግን ደንበኛዋ በመሆኑ መምጣቱ እንደማይቀር ነግራኝ ‹‹ጠብቀው›› አለችኝ። ጠበቅኩት፡፡ ግን ባለውለታዬ አልመጣም፡፡ በጥበቃ መቆየቴን እና ብቸኝነቴን የተረዳችው ኮማሪ፤ ሄድ መጣ እያለች ታጫውተኝ ጀመር።
በዚህ መሐል የኮማሪቷ ስልክ ጠራና መልዕክት ተቀበለች። ደዋዩ ቀጠሮ ያስያዘኝ ወጣት ነበር። ወጣቱ ያልጠበቀው ነገር እንደገጠመውና መምጣት እንዳልቻለ፤ ይቅርታ እንድትጠይቅለትና በደንብ እንድታስተናግደኝ ጭምር አደራ ማለቱን ነገረችኝ። በቅርብ እንደማውቀው ሰው በመቅረቱ ቅሬታ ተሰማኝ። ቅሬታዬን የተረዳችው አስተናጋጅም በቅርበት ሆና ታጫውተኝ ጀመር። በቆይታ ጠላው በማለቁ ጠጪው ቀስ በቀስ እየወጣ ሄደ።
የያዝኩትን ዋንጫ ጠላ እያጣጣምኩ፤ ከአስተናጋጇ ጋር መጨዋወታችንን ቀጠልን። የወጣቱን አደራ የተቀበለችው የውብነሽ፤ ጠጪው ከወጣ በኋላ ቡና ማፍላት ጀመረች። ቡናው ለተጨማሪ ጨዋታ በር ከፈተልን።  ስለከተማዋ ሁኔታ፣ ስለጠላ ንግድ አዋጭነት፣ ስለቆላ ድባ ኑሮ፤ በአጠቃላይ ስለበርካታ ነገሮች ልቧን ከፍታ አጫወተችኝ።
የውብነሽ በመካከለኛ ዕድሜ ላይ የምትገኝና ደልዳላ ሰውነት ያላት የስድስት ልጆች እናት ነች፡፡ ስድስቱም ልጆቿ ሴቶች ናቸው። ሁሉም ልጆቿ ሴቶች በመሆናቸው ምክንያት ብቻ ትዳሯ እንደፈረሰና ስድስት ልጆቿን፤ ብቻዋን እንዳሳደገች ወይም እንደምታሳድግ ነገረችኝ።
በልጅነቷ የተዳረችው የውብነሽ፤ ቤተሰቦቿ ወይም ዘመዶቿ ከሚነግሯት ነገር በቀር፤ የሰርግና የሙሽርነት ጊዜዋን በደንብ አታስታውሰውም። ‹‹የእኛ ባህል ለሴቶች መጥፎ እና ከባድ ነው›› ትላለች የወብነሽ፤ ‹‹በእኛ ጊዜ፤ ሴቶች ምርጫ የለንም። ምርጫህ በቤተሰቦች፤ በተለይም በአባት ፍላጎት የሚወሰን ነው፡፡ አባቴ ሊወዳጅ ከፈለገው ሰው ጋር ጋብቻ እንድፈጽም ያደረገኝ ገና ጡት እየጠባሁና በእናቴ እቅፍ ላይ ሳለሁ ነው›› አለችኝ፡፡
‹‹በእኛ ጊዜ ሴትን ልጅ ወደ ትምህርት መላክ አይታሰብም። ትምህርት ቤትም እንዳሁኑ በየቀበሌው አልነበረም። ሴት ልጅን ማስተማር ለብልግና በር ይከፍታል ይባል ነበር፡፡ ብዙ ሰው ሴትን ልጅ ወደ ትምህርት ቤት አይልክም›› የምትለው የውብነሽ፤ እስከ አስራ ሁለት ዓመቷ ድረስ፤ ቤተሰቦችዋን በጉልበት ሥራ ስትረዳ ከቆየች በኋላ፤ ‹‹ትንሽ ጠንከር ስል ደግሞ ደርሳለች በማለት ባል ለተባለ ሰው ሰጡኝ። የሚገርመው ወደ ባለቤቴ ስላክ በደረቴ ላይ ጡት አልነበረም። ገና ክፉና ደጉን አለየሁም። እንኳን ቤተሰብ መምራት፤ ራሴንም በቅጡ መምራት የምችል አልነበርኩም። ትዳር ተጀመረ፡፡ በቤት እሰራለሁ፤ በአዝመራ ወቅት ደግሞ ከባለቤቴ ጋር እርሻ ሥራ እወርዳለሁ›› ትላለች የውብነሽ፡፡
‹‹አሁን - አሁን ሳስበው በቀድሞ ጊዜ እኮ የገጠር ሴት እንደ ዕቃ እንጂ እንደ ሰው አትታይም። ታዲያ ይኸውልህ ወንዱ እስከ እኩለ ለሊት ይህን ጠላ ሲግፍ  ይቆይልህና ወደ ቤት ሲመጣ ሚስቱ ተኝታ ያገኛት እንደሆን በያዘው ሽመል ነው የሚያንቆራጥጣት። ስለዚህ ሴቶች እያንቀላፋንም ቢሆን ቁጭ ብለን ባሎቻችንን የመጠበቅ ግዴታ ነበረብን። ድንገት እንቅልፍ ወስዶን በር ሲያንኳኳ ያቆየነው እንደሆነ አይ ያለብን አበሳ። የአሁኑ መንግስት ለገጠሯ ሴት የመጣ ይመስለኛል›› ያለችኝ የውብነሽ፤ ‹‹ዛሬ ሚስቱን የሚመታ ወንድ እኮ ከስንት አንድ ነው።  ሴቷም መብቷን ጠንቅቃ አውቃለች፡፡ ወንዱም ህግ ይፈራል። ህጉም ከተበዳይ ጎን ነው። ዛሬ የማን ሴት ናት እንደ ዱሮው ስትነረትና ስትሰደብ ዝም ብላ የምትመለከት›› አለችኝ፡፡
ሰራቂያን
የውብነሽ፤ ‹‹ስርቂያን ታውቃለህ?›› አለችኝ፤ ‹‹አላውቅም›› አልኳት። ሳቅ አለች፡፡ በአስራ አምስት ዓመቷ የመጀመሪያ ልጇን እንደ ወለደች የነገረችኝ የውብነሽ፤ ‹‹ያ ጊዜ የመከራ ወቅት ነበር›› ብላ ጨዋታዋን ቀጠለች። ‹‹የመጀመሪያ ልጄን ስወልድ፤ በወሊድ ወቅት ደም መታኝ። በእኛ አገር ሰራቂያን ይባላል። ሰራቂያን ማለት በወሊድ ወቅት ከመጠን ያለፈ የደም መፍሰስ ነው። ብዙ እናቶች በዚህ ይሞቱ ነበር፡፡ በዕድል ካልሆነ ደም የመታት ሴት አትተረፍም፡፡ እኔ ዕድለኛ ሆኜ ከሞት ተረፍኩ፡፡ የመጀመሪያ ልጄን፤ ሁለት ቀን አምጬ ስወልድ፤ ደም ክፉኛ መታኝ። ሦስት ቀን ራሴን አላውቅም ነበር።
‹‹…..በኋላ ልጄን ማጥባት እና መንከባከብ ከብዶኝ ነበር፡፡ ልጄንም ሆነ እኔን ተንከባክባ በደንብ ያረሰችኝ እናቴ ነበረች። ግን ከእናቴ ዘንድ ብዙ ሳልቆይ ወደ ባለቤቴ ተመለስኩ። ከተመለስኩ በኋላ በብዙ ነገር ታግዘኝ የነበረች አንድ ጎረቤቴ ነበረች። ማታ ማታ ልጄን ታጥብልኝ ነበር፡፡ ኧረ ስንቱን መከራ ላጫውትህ።  የመከራ ጊዜ  ነበር። 
‹‹እንዳልኩህ፤ ስድስት ልጆች ወለድኩ፡፡ ግን ባለቤቴ ወንድ ልጅ ባለመውለዴ ደስተኛ አልነበረም። እንግዲህ ልጅ የሚሰጥ እግዚአብሄር ነው። እኔ አልጠፈጥፍ፡፡ የተሰጠኝን መቀበል እንጂ። እናም ከባለቤቴ ጋር ለፍቺ ያበቃን ወንድ ልጅ አለመውለዴ ነበር፡፡ ባለቤቴ እየጠላኝና እየራቀኝ ሲሄድ ምናልባት ወንድ ልጅ ብወልድ ወደ ቤቱ እመልሰዋለሁ በሚል ጉጉት ሁለት ልጆች አከታትዬ ወለድኩ፡፡ ግን ዕድሌ አልቀናልኝም፡፡ ሁለቱም ሴቶች ሆኑ። ከዚያ ወዲያማ እኔን ብቻ ሳይሆን ልጆቼንም ጭምር ለዓይኑ ጠላን። ምን ብዬ ልንገርህ ለየለት። በወጣ በገባ ቁጥር ያለ ምንም ምክንያት፤ የእኔንም የልጆቼንም ቅስም የሚሰብር ስድብ ያወርድብናል፡፡ አለፍ ሲል ዱላም አለልኝ። እየዋለ እያደረ ባለቤቴ ቤቱ አስጠላው፣ በሰበብ አስባቡ ከተማ መሄድ፣ አምሽቶ መምጣት፣ መጠጣት ጀመረ። እንዲያውም ውሽማ ያዘ። ከዚያ ወዲያማ ህይወት እጅግ እየከፋች ሄደች። የምናገኘውንም አዝመራ ለሁለት ቤት እየከፈለ፤ እኔንም ሆነ ልጆቼን መርሳት ጀመረ።
‹‹ቀድሞ ወደ ውሽማው በድብቅ ይወጣና ይገባ የነበረ ሰውዬ፤ እያደር በግልጽ ያደርገው ጀመር። በመጨረሻ ውሽማ ተብዬዋ ሚስት፤ እኔ  ደግሞ ውሽማ ሆኜ አረፍኩት። በቃ እየሰነባበተ ይመጣ ጀመር። በመጨረሻ የማይቀረው ነገር መጣ። እኔንም ልጆቼንም ትቶን ኮበለለ። ችግሩ ይገርፈኝ ጀመር። ልጆቼ ትምህርታቸወን ሊያቋርጡብኝ ሆነ። በዘመድ አዝማድ ለመንኩት፤ አስመከርኩት፡፡ ግን ልመልሰው አልቻልኩም። የእኔና የእሱ እህል ውሃ እንዳለቀ ገባኝ። ጥሎን ሲሄድ፤ እኔና ልጆቼ ዓለም የተደፋብን፤የቀን ጅብ የሚበላን መሰለን፡፡ ከዚያ ወዲያ ህይወት የማይኖር መሰለን፡፡ ስናለቅስ አደርን። እኔም እንዲያ የምጠላውን እና የምፈራውን ፍቺ በግድ ገባሁበት።
በመጨረሻ፤ ለ17 ዓመት በውጣ ውረድ የዘለቀው የትዳር ህይወቷ ፈረሰ። የውብነሽ እንዲህ ትላለች፤ ‹‹ሽማግሌዎች የማውቀውን ንብረታችንን እንኳን አብዛኛውን ለእርሱ ሲፈርዱ፤ እኔ ልጆች ይዤ የተፈረደልኝ የእርሱን ግማሽ እንኳን አያክልም ነበር። ይህ ቤት (አሁን ጠላ የምትሸጥበት ማለቷ ነው) ለእኔ ስለተፈረደልኝ ልጆቼን ሰብስቤ ገጠሩን ትቼ ከተማ ገባሁ። ባለቤቴ ደግሞ ገጠር ያለውን ቤት እንዲወስድ ተደረገ። የከተማን ኑሮ እንደጀመርኩት እጅግ ከባድ ሆነብኝ። ከመጀመሪያዋ እና ከእርሷ ተከታይ በስተቀር፤ አራቱ ልጆቼ ምንም መስራት የሚችሉ አልነበሩም። የከተማው ኑሮ ከበደኝ፡፡ ከባለቤቴ ጋር የተካፈልኳቸውን ከብቶች፤ አንድ በአንድ ሼጬ ጨረስኳቸው። ጥሪቶቼን በሙሉ ለመሽጥ ተገደድኩ።
‹‹ከተማ እንደገባሁ የምሰራው ነገር ግራ ገባኝ፡፡ ከዚያ በኋላ ያገኘሁትን ስራ ሁሉ መስራት ጀመርኩ፡፡ አረቄ ማውጣት፣ በየሰዉ ቤት እየዞርኩ ልብስ ማጠብ፣ እንጀራ መጋገር፤ ብቻ ምን ልበልህ የልጆቼን ጉሮሮ ለመድፈን ሌት ተቀን እሰራ ጀመር። የመጀመሪያዋም ልጄ ትምህርቷን አቋርጣ ሰው ቤት ተቀጠረች። በጣም ያዘንኩት ልጄ ትምህርቷን በማቋረጧ ነበር። ምክንያቱም፤ ልጄ ትምህርቷን ለማቋረጥ የተገደደችው ለእኔ ብላ ነው።››
የውብነሽ በአንድ ወቅት ራሷን ለማጥፋት አስባ እንደነበር ነገረችኝ። ‹‹እንደኔ ስድስት ነፍስ የያዘች፤ ምንም ትምህርትና ሃብት ወይም ወገን የሌላት ሴት ተስፋ ብታጣ ይገርማል? አዎ፤ የደረሰበት ብቻ ነው የሚያውቀው›› አለችና አቀረቀረች። አያይዛ፤ ‹‹ኑሮው እጅግ ቢፈትነኝም፤ ከትዳሬ ውጭ ሌላ ህይወት ተመኝቼ አላውቅም ነበር። የማስበው ልጆቼን ነበር፡፡
እኔ ኑሮ እጅግ ቢከብደኝም፤ ለትምህርት የደረሱ ልጆቼን ሁሉ ተማሪ ቤት እልክ ነበር። ሁሉም ልጆቼ ሴቶች በመሆናቸው፤ የእኔ እጣ ፈንታ እንዳይገጥማቸው የባለቤቴን ነገር ታግሼ መኖርን እመርጥ ነበር። ሴት ልጅ ካልተማረች፤ በተለይ በገጠር፤ የባል መጫወቻ ሆና ነው የምትቀረው፡፡ ልጆቼ እንደኔ የመከራና የስቃይ ህይወት እንዳይገጥማቸው በትምህርታቸው እንዲጠነክሩ፣ ከትምህርት ቤት እንዳይቀሩ እመክራቸው ነበር። ዛሬ ትምህርት ቤቱ በደጅ ነው። ሴት ልጁን ወደ ትምህርት የማይልክ ሰው አታገኝም።››
የውብነሽ በሐሳብ የመከራ ጉዞዋን ጨርሳ፤ ተስፋዋን መናገር ጀመረች፡፡
በመጀመሪያ ሽማግሌዎቹ ባይወስኑላትም፤ በኋላ በሴቶች ጉዳይ ድጋፍ ከባለቤቷ ጋር የእርሻ መሬት እኩል እንደተካፈለች ያጫወተችኝ የውብነሽ፤ ‹‹ዛሬ ስምንት ቃዳ የእርሻ መሬት ለእኩል ሰጥቼ አርሳለሁ፡፡ ለቀለብ እህል ሸምቼ አላውቅም። እነዚህን ሰርቪስ ቤቶችም ሰራሁ፡፡ ቀበሌ በአነስተኛና ጥቃቅን አደራጄኝ፡፡ ስልጠናም ሰጡኝ፡፡ ብርም አበድርውኝ ግንባር ቦታ ላይ  የባልትና ውጤቶችን የምሸጥበት ሱቅ ከፈትኩ።
‹‹ይኸው ዛሬ በየገጠሩ ውሃ ገባ፣ መንገዱ ተስፋፋ፣ ስልክ መጣ፣ መብራቱ ተዘረጋ፣ ትምህርት ተስፋፋ፣ ሃኪም መጣ፡፡ ይህን ሁሉ በእኛ ዕድሜ ተቀይሮ አየነው። ….አይ ጊዜ ደጉ። የተማረ ሰው ወድቆ አይወድቅም። በአሁን ጊዜ ሴቱ ደሞዝተኛ ሆኗል። እኔ ሳልማር በመቅረቴ ስረገጥ ኖሬለሁ። ይሁንና ከመሸም ቢሆን ዕድለኛ ሆኛለሁ፡፡ የኋላ ኋላ ኑሮ ተሳካልኝ። አሁን የመጀመሪያ ልጄ፤ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ገብታ ሦስተኛ ዓመት ደርሳለች፡፡ የእርሷን ተከታይ እየከፈልኩ ጎንደር በግል ኮሌጅ ነርሲንግ አስተምራታለሁ። የቀሩት እዚሁ እየተማሩ ናቸው። ዛሬ ህይወቴ ተቀይሯል። በፊት፤ የሰው ቤት እንጀራ የምጋግር ነበርኩ፡፡ ዛሬ የሁለት ሠራተኞች አስተዳዳሪ ሆኛለሁ፡፡ ይኸው  ከራሴ አልፌ ለሰው በቅቻለሁ›› አለችኝ የውብነሽ፡፡
በየውብነሽ ዓይኖች ተስፋ ሲፈንጥቅ አየሁ። ህይወት እንደገና!!! እኔም በየውብነሽ ተስፋና በጽዋው ጢም ብዬ ከመቀመጫዬ ተነሳሁ፡፡ ለስንብት እጄን ዘረጋሁ። ጠንካራዋን እናት አመስግኜአት ወጣሁ፡፡ ቸሩን ሁሉ ተመኘሁላት፡፡ አያን ሒርሲ ዓሊስ የት ትሆን?








Read 3157 times