Saturday, 24 October 2015 10:02

ከክርስቶስ ሞት ጀርባ ያልተነበቡ የሄሮድስና ጲላጦስ ደብዳቤዎች

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(12 votes)

እንደ መግቢያ
አንዳንድ የፍልስፍና መጻህፍት፤ ‹‹እውነት ምንድን ናት?›› በሚለው ጥያቄው ጲላጦስን ያወሱታል፡፡ እነዚህ መጻሕፍት፤ ‹‹መጠየቅ የሚገባውን ወሳኝ የፍልስፍና ጥያቄ አነሳ›› በሚል ስሙን ያነሱታል እንጂ፤ስለ ጲላጦስ ህይወት የሚነግሩን ነገር የላቸውም፡፡ የሮማ ኤምፓየር ታሪክን የሚዳስሱ መፃሕፍት፤ከምሥራቃዊው የሮማ ግዛት እና ከኢየሱስክርስቶስ ጋር አያይዘው ስሙን ያነሱት ይሆናል፡፡ ከዚህ በቀር ስለ ጴንጤናዊው ጲላጦስ የሚሉት ነገር አልገጠመኝም፡፡ እናንተም እንደኔ ከሆናችሁ፤ ከዚህ በታች የምታነቧቸው ሁለት ደብዳቤዎች፤ ስሜት እንደሚሰጧችሁ አስባለሁ፡፡     
ጲላጦስ ኢየሩሳሌምን፤ ሄሮድስ ደግሞ ይሁዳን ያስተዳድሩ በነበረ ዘመን፤ የሮማው ኤምፓየር ገዢ ጢበርየስ ቄሳር (Tiberius Caesar) ነበር፡፡ ታዲያ ከሰሞኑ ያነበብኳት፤LETTERS OF HEROD AND PILATE፤ የምትል አንዲት  መጽሐፍ ስለ ጲላጦስ ተጨማሪ ነገረችኝ፡፡ ጲላጦስ፤ ኢየሱስ ክርስቶስን በተመለከተ ለጢበርየስ ቄሳር በተደጋጋሚ ሪፖርት መላኩን ይጠቅሳል፡፡ ብዙዎቻችንን እንደምናውቀው፤ ጲላጦስ በኢየሱስ ላለመፍረድ ብዙ ጥረት አድርጎ ነበር፡፡ ግን አልተሳካለትም፡፡ ኢየሱስን ለማዳን የሚያደርገው ጥረት፤ ሁከት ከመቀስቀስ በቀር ‹‹አንዳች እንዳይረባ ባየ ጊዜ፣ ውሃ አንስቶ፤ እኔ ከዚህ ፃድቅ ሰው ደም ንፁህ ነኝ፡፡ እናንተ ተጠንቀቁ ሲል በህዝቡ ፊት እጁን ታጠበ፡፡››
ጲላጦስ በኢየሩሳሌም ይህን ያልተሳካ ጥረት ያደርግ በነበረ ጊዜ፤ ሮም የነበረው ጢበርየስ ቄሳር ታምሞ ሐኪም ይፈልግ ነበር፡፡ ‹‹ኢየሱስ ህሙማንን በቃሉ ኃይል ይፈውሳል›› የሚል ዝና እየሰማ ለራሱ ይመኘው ነበር፡፡ ጲላጦስ ይልክለት የነበረው ሪፖርት በምን ስሜት እንደሚያነበው መገመት አያዳግትም፡፡ በአይሁዳውያን ፋታ የለሽ ጉትጎታ እና ጫና ጲላጦስ እንዲሰቀል የፈረደበት መሆኑን ያላወቀው፤ በዝና የሰማውን ኢየሱስን ወደ ሮም ይዞለት እንዲመጣ ቮሉሲያነስ  (Volusianus) የሚባል ባለሟሉን ኢየሩሳሌም ወዳለው ጲላጦስ ላከ፡፡ መልዕክተኛው የሆነውን ነገር ተረዳ፡፡
በዚህ ጊዜ ጢበርየስ ቄሳር ጲላጦስን ወደ ሮም አስጠራው፡፡ ጠየቀው፡፡ ከዚያም፤ ‹‹ጥፋት እንደሌለበት እያወቅህ እንዴት ትፈርድበታለህ›› በሚል ችሎት አስችሎ፤ በጲላጦስ ላይ ሞት እንደ ፈረደበት የሚያትተው የታሪክ ሰነድ፤ ጲላጦስ የኢየሱስን ልብስ እየለበሰ ወደ ችሎት ስለሚቀርብ፤ ሰዎች ሚስጥሩን ነግረውት ካባውን እስኪያስወልቀው ድረስ እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ በቁጣ እየተንቆራጠጠ የሚጠብቀው ቄሳር፤ ጲላጦስ ሲመጣ የቁጣ ስሜቱ እየጠፋ ሁለት እና ሦስት ጊዜ ችሎቱ እንደተቋረጠ ይገልፃል፡፡
ጲላጦስ በይሁዳ ሲገዛ፤ በገሊላ የአራተኛ ክፍል ገዢ የነበረው ሄሮድስ ነበር፡፡ ጲላጦስ ምንም ጥፋት ባላገኘበት በኢየሱስ ላይ ፍርድ ማሳለፍ ስላልፈለገ፤ ኢየሱስ የመጣው ከሄሮድስ ግዛት ከገሊላ እንደሆነ ባወቀ ጊዜ፤ መልሶ ወደ ሄሮድስ ሰደደው፡፡ ቀደም ሲል መጥምቁ ዮሐንስን ያስገደለው ሄሮድስ፤ ዝናውን ሰምቶ ኢየሱስን ሊያየው ይፈልግ ስለነበር ወደ እርሱ በመምጣቱ ደስ ቢለውም ሊፈርድበት አልፈለገም፡፡ ስለዚህ እንዳሰበው ተአምር ስላላሳየው ዘበተበትና የጌጥ ልብስ አልብሶ እንደገና ወደ ጲላጦስ መለሰው፡፡ እንግዲህ ከዚህ በታች የማስነብባችሁ፤ በሁለቱ ገዢዎች ጲላጦስ እና ሄሮድስ መካከል የተደረጉ የደብዳቤ ልውውጦችን ነው፡፡
ደብዳቤዎቹ ወደዚያ ዘመን አስጉዘው የሚወስዱና የማይረሳ ልዩ ልምድ የሚሰጡ መስለው ታዩኝ፡፡ በተለየ መንገድ ክርስቶስ ወደ ነበረበት ዘመን ይመልሳሉ፡፡ ደብዳቤዎቹ፤ በእውን በዚያው ዘመን እንደመገኘት ዐውዱን፣ ድምፁን፣ ትዕይንቱን ጎትተው የሚያመጡ ናቸው፡፡ ባለታሪኮቹ የነበሩበትን ዐውድ አድምቀው በህሊና ይስላሉ፡፡ ደብዳቤዎቹ፤ የግለሰባዊ ህይወት እና የታሪክ ጉዳይ እንጂ የእምነት ግብ ሳይኖራቸው ሁነቱን የማይተርኩ በመሆናቸው፤ በዘመኑ ሰው ህሊና ምን ይመላለስ እንደነበረ ለአንባቢ ማሳየት የሚችሉ ናቸው፡፡ ደብዳቤዎቹ፤ በእምነት ሚዛን ቢታዩም ደጋፊ ናቸው፡፡
ሄሮድስ ለኢየሩሳሌም ገዢ ጲላጦስ፤
ሰላም ላንተ ይሁን
አሁን እኔ በታላቅ ጭንቀት ውስጥ እገኛለሁ፡፡ ይሄን ደብዳቤ ስፅፍልህ በከፋ ጭንቀት ውስጥ ሆኜ ነው፡፡ የደረሰብኝን ነገር ስፅፍልህና የወደቀብኝን መከራ ስትሰማ ስለኔ ማዘንህ አይቀርም፡፡ በጣም የምወዳት ልጄ ሄሮድያስ የበረዶ ግግር በሚንሳፈፍበት የመዋኛ ገንዳ ስትጫወት፤የቆመችበት ተንሳፋፊ የበረዶ ግግር ከእግሯ ስር ተሰብሮ ሲከዳት በወደቀች ጊዜ፤የበረዶው ሻፎ አንገቷን ቀንጥሶ ጣለው፡፡ ከአንገቷ በታች ያለው አካሏ ሲሰርግ፤ የተቆረጠ አንገቷ በግግሩ በረዶ ላይ ሆኖ ተንሳፈፈ፡፡
ጲላጦስ ልብ አድርግ፤ እናቷ የልጇን የተቀነጠሰ አንገት በጭኗ አድርጋ የሚደርስባትን ሐዘን ተመልከተው፡፡ ጠቅላላ ቤተሰባችንም በታላቅ ሐዘን ተውጧል፡፡ እኔ፤ ኢየሱስ ስለሚባለው ሰው ወሬ ስሰማ፤እርሱን ለብቻ አግኝቼ ላየው፤ ቃሉንም ልሰማና እርሱም እንደ ሌሎች ሰዎች ልጆች መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ፤ ወደ አንተ ዘንድ ለመምጣት ፈልጌ ነበር፡፡
ሆኖም፤ በመጥምቁ ዮሐንስ ላይ በፈፀምኩት ብዙ በደልና በክርስቶስ ላይ በመዘባበቴ የተነሳ ምኞቴ እንዳልተሳካ የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ እነሆ፤ የሌሎች ወላጆች ህፃናትን ደም በምድር እንደ ውሃ በማፍሰሴ የተቀበልኩትን የጽድቅ ፍርድ ተመልከት፡፡ የእግዚአብሄር ፍርድ የጽድቅ ፍርድ ነው፤ ሁሉም ሰው እንደ ሐሳቡ ፍርዱን ያገኛል፡፡
ሆኖም አንተ፤ በሰው አምሳል የመጣውን እግዚአብሄርን ለማየት የተገባህ ሰው ስለሆንክ፤ አንተ ለኔ ፀሎት ልታደርግልኝ የተገባ ነው፡፡ ይኸውልህ፤ ልጄ አዝቦንየስ ለሞት እንደሚያጣጥር ሰው እየተሰቃየ ይገኛል፡፡ እኔም ብዙ መከራና ፈተና ውስጥ እገኛለሁ፡፡ የጥምቀትን ነገር ለሰው ያሳወቀውን መጥምቁ ዮሐንስን በማስገደሌ የተነሣ፤  መላው ሰውነቴ አባብጦ ያዣል፤ በታላቅ ችግርም ውስጥ ወድቂያለሁ፡፡ ስለዚህ፤ ወንድሜ ሆይ፤የእግዚአብሔር ፍርድ እውነተኛ እና የጽድቅ ፍርድ ነው፡፡
እኛ የፅድቅ ዓይንን ልናወጣ የሞከርን በመሆናችን፤ ባለቤቴ በልጇ ሞት በወደቀባት ሐዘን የተነሳ፤ ከሌላ መከራዋ በተጨማሪ የግራ ዓይኗ ታውሯል፡፡ ጌታ፤ ክፉ አድራጊዎች ሰላምን አያገኟትም ብሏል፡፡ ጻድቅን ሰው ለአንተ አሳልፈው ሰጥተዋልና፤ በፀሐፍት ፈሪሳውያንና በካህናቱ ላይ እንደምታየው መከራ ወድቆባቸዋል፡፡ ይኸው የዓለም ፍፃሜ በመድረሱ፤አህዛብ የመንግስቱ ወራሾች ይሆኑ ዘንድ፤ፀሐፍት ፈሪሳውያንና ካህናቱ ተስማምተዋል፡፡ ስለጌታ እና ስለልጁ የተነገረውን ስብከት አላስተዋሉምና፤ የብርሃን ልጆች ወደ ጨለማ ይጣላሉ፡፡
ወንድሜ ሆይ፤ እንግዲህ ወገብህን ታጠቅ፤ከባለቤትህ ጋራ ሆነህ፤ በመዐልት እና በሌሊት ኢየሱስን እያሰብክ፤ እጅህን ዘርግተህ ፅድቅህን ተቀበል፡፡ እኛ የተመረጥነው ህዝቦች፤ በፃድቁ ላይ ተዘባብተናልና፤ የእግዚአብሔር መንግስት የእናንተ የአህዛብ ሆኗልና፡፡
ወንድሜ ጲላጦስ ሆይ፤ ሁለታችንም በአንድ ዘመን አብረን ገዝተናልና፤ ልመናዬን የምትቀበለኝ ቢሆን፤ እኔንና ቤተሰቦቼን የሚገባውን ሥርዓት አድርገህ ቅበረን፡፡ እኛ፤በመፅሐፉ እንደተገለጠው ክርስቶስ በሚመጣ ጊዜ የቁጣ መአት በሚደርስባቸው በካህናቱ ሳይሆን በአንተ እጅ ልንቀበር የተገባ ነውና፡፡ ከባለቤትህ ከፕሮክላ ጋር የከበረ ሰላምታዬን አቀርብልሀለሁ፡፡
በእኔ የደረሰውን በሽታ ያስታውስህ ዘንድ ከዚህ ደብዳቤ ጋር የልጄን ጉትቻና የእኔን የጣት ቀለበቴን ሰድጄልሀለሁ፡፡ ይኸው አሁን ከሰውነቴ ትል ይወጣ ጀምሯል፡፡ እነሆ እኔ ምድራዊውን ፍርድ እየተቀበልኩ ነው፡፡ የሚመጣውን ሰማያዊውን ፍርድም እያሰብኩ በፍርሃት እርዳለሁ፡፡ በሁለቱም ፍርድ በህያው እግዚአብሄር ፍጥረታት ፊት እንቆማለን፡፡ ነገር ግን ይህ ምድራዊው ፍርድ አላፊ ነው፡፡ የሚጠብቀን ሰማያዊው ፍርድ ግን ዘላለማዊ ነው፡፡
ለገዢው ጲላጦስ የተላከው ደብዳቤ መጨረሻ፤
ጲላጦስ ለሄሮድስ የፃፈው ደብዳቤ
ይድረስ ለአራተኛው ክፍል ገዢ ለሄሮድስ
ሰላም ላንተ ይሁን
እናንተ እየሱስን አሳልፋችሁ ለኔ በሰጣችሁ ጊዜ የሆነውን ነገር አይተሃል፡፡ ታውቃለህም፡፡ ለሦስት ቀን በመቃብር ቆይቶ የተነሳውንና እናንተ የፈቀዳችሁትን ነገር ያደረጋችሁበትን ሰው በተመለከተ፤ እኔን የእናንተ ሥራ ተባባሪ ልታደርጉኝ ብትወዱም እኔ ግን ለራሴ ፈርቼ ክፉ ከማድረግ ተጠበቅኩ፤ እጆቼን በመታጠብም ከበደሉ ንፁህ መሆኔን መሰከርኩ፡፡ ይኸው አሁን በመስቀል ከሰቀሉትና መቃብሩን ይጠብቁ ከነበሩት ወታደሮች አፍ ከሙታን ተለይቶ መነሳቱን ተረዳሁ፡፡
እኔም እራሴ፤ በአካል ተነስቶ በገሊላ ሲመላለስ ታየ የተባለውን ነገር አረጋገጥኩ፡፡ ያው የቀደመ ቁመናው፣ ድምፁ፣ ትምህርቱ ሳይለወጥ በአካል ከደቀ መዛሙርቱ ጋር አየሁት፡፡ ከቀድሞው አንዳች የተለወጠ ነገር የለም፡፡ ነገር ግን ስለትንሳዔው እና ስለዘላለማዊው መንግስት በኃይል እና በስልጣን ይሰብክ ነበር፡፡
እነሆ ሰማይና ምድር ሐሴትን አደረጉ፡፡ የእስራኤል ህዝብ በመጥፎ ሐሳባቸው ተነሳስተው ክርስቶስን አሳልፌ እንድሰጣቸው በጠየቁኝ ጊዜ፤ ባለቤቴ ፕሮክላ በራዕይ የተገለጠላትን መልዕክት በእምነት ተቀብላ ነበር፡፡ አንተ ግን ኢየሱስን ለእስራኤል ህዝብ አሳልፌ እንድሰጥ መልዕክት ላክህብኝ፡፡
ባለቤቴ ፕሮክላ ኢየሱስ ከሞት መነሳቱንና በገሊላ መታየቱን በሰማች ጊዜ፤መቃብሩን ሲጠብቅ የነበረውን የመቶ አለቃ ሎንጊንየስን እና ሌሎች አስራ ሁለት ወታደሮችን አስከትላ ለክርስቶስ ለመስገድ ወደ ገሊላ ሄደች፡፡ ማየት ያልቻልነው እኛ እናየው ዘንድ በገሊላ የተገለጠውን ኢየሱስን ከደቀመዛሙርቱ ጋር ሆኖ አየችው፡፡
ከዚያም ክርስቶስ ባለበት ሥፍራ ቆመው ሲያደንቁና እርሱን ሲመለከቱ ባያቸው ጊዜ ምን ትፈልጋላችሁ? በኔስ ታምናላችሁን? ሲል ጠየቃቸው፡፡ ፕሮክላ፤ እግዚአብሄር አምላክ ለአባቶች በሰጠው ቃል ኪዳን፤ ወደ መቃብር የወረደና የሞተ ሁሉ በእኔ ሞት የተነሳ ህይወትን ያገኛል የሚል ቃል ተፅፏል፡፡ ይሄንንም በዓይንሽ አይተሻል፡፡ ይኸው እናንተ የሰቀላችሁኝ እኔ በህይወት እንዳለሁ አይታችኋል፡፡ በመቃብር እስክገባ ብዙ መከራን ተቀብያለሁ፡፡ ነገር ግን አሁን ቃሌን አስተውሉ፡፡ በእኔ ባለው በአባቴም እመኑ፡፡
እኔ የሞትን ቀንበር ሰብሬዋለሁ፡፡ የሞትን ገመድ ፈትቻለሁ፡፡ የሲኦልንም በር ሰባብሬአለሁ፤ መምጣቴም ከዚህ በኋላ ይሆናል አላቸው፡፡ባለቤቴ ፕሮክላ እና ሮማውያን ወታደሮች ይህንን ቃል በሰሙ ጊዜ፤ በእርሱ ላይ ተነሳስተው ክፉ ነገር እንዲሆንበት ሁኔታዎችን አመቻችተዋልና እያለቀሱ ስለሆነው ነገር መጥተው ነገሩኝ፡፡ እኔም እነርሱ በመጡ ጊዜ በበሽታ ተይዤ ከአልጋ የወደቅሁ ቢሆንም የእነርሱን ነገር ስሰማ፤ የሐዘን ካባ ደርቤ፤ ሃምሳ የሚሆኑ የሮማ ወታደሮችንና ባለቤቴን አስከትዬ ወደገሊላ ሄድኩ፡፡
በመንገዴም ሳለሁ ሄሮድስ ይህን ክፉ ነገር በኔ እንዳስደረገ፤ ከኔ ጋር መጥቶ እንደተማከረና በእርሱ ላይ እጄን እንዳነሳ እንዳደረገኝ፤ ሁሉን በሚፈርደው ላይ እንድፈርድና እውነተኛውን ፃድቅ እና የእውነትን ጌታ በአለንጋ እንድገርፍ እንዳደረገኝ አሰብኩ፡፡ ወንድሜ ሄሮድስ ሆይ!  ወደእርሱ በቀረብንም ጊዜ ታላቅ ድምፅ ከሰማይ ተሰማ፤አስፈሪ ነጎድጓድ ተፈጠረ፡፡
ምድርም ተንቀጠቀጠች፤በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ እንኳን ታይቶ የማያውቅ ግሩም መዓዛ አፈለቀች፡፡ አሁን በመንገዴ እንደቆምኩ፡፡ ጌታችን ከደቀመዛሙርቱ ጋር እየተነጋገረ ሳለ ተመለከተኝ፡፡ አንተ አሳልፈህ ለኔ የሰጠኸኝ ይህ የማየው ሰው፣ የፍጥረት ሁሉ ገዢ፣ የምድረ ዓለም አስገኚ መሆኑን ስላወኩ በልቤ ፀሎት አደረስኩ፡፡ እኛም እንዳየነው ሁላችንም በፊታችን ከእግሩ ላይ ወደቅን፡፡ እኔም ድምፄን ከፍ አድርጌ፤አቤቱ ጌታዬ ሆይ ሃጥያት ሰርቻለሁ፤ ሁሉን በእውነት የምትበቀለውን አንተን ለመዳኘት በፍርድ ወንበር በመቀመጤ በደል አድርጌያለሁ አልኩ፡፡
እነሆ አንተ አምላክ፤ ወልደ አምላክ መሆንህን አውቄአለሁ፤ ያንተን ሰውነት እንጂ መለኮትነትህን አላወኩም ነበር፡፡ ነገር ግን ሄሮድስ ከእስራኤል ልጆች ጋር ሆኖ በአንተ ላይ ክፉ እንዳደርግ አነሳሳኝ፡፡ አቤቱ የእስራኤል አምላክ ሆይ፤ ስለዚህ ለኔ ምህረት አድርግልኝ፡፡ በምህረትህ ዳኘኝ! አልኩ፡፡
ባለቤቴም በታላቅ ሐዘን ተውጣ፤ አቤቱ የሰማይ እና የምድር አምላክ ሆይ! አቤቱ የእስራኤል አምላክ ሆይ! እንደ ባለቤቴ እንደ ጴንጤናዊው  ጲላጦስ አድራጎት ወይም እንደእስራኤል ልጆች ምኞት ወይም እንደ እስራኤል ካህናት ልጆች ሐሳብ አትፍረድብኝ፡፡ ነገር ግን ባለቤቴን በክብርህ አስበው! አለች፡፡
ከዚያም ጌታችን ወደኛ ቀረበና ባለቤቴን እና እኔን እንዲሁም የሮማን ወታደሮች ከወደቅንበት አነሳን፡፡ ከዚያም ፊቴን አቅንቼ ተመለከትኩት፡፡ በመስቀል ችንካር የተወጋ እጁን አየሁት፡፡ ፃድቃን አባቶች ሊያገኙት ይመኙት የነበረውን በአንተ በዘመናት ጌታ፣ በሰው ልጅ፣ ዘላለማዊ የሆነው የልዑል እግዚአብሄር ልጅ ከሙታን ተነስቷል፤ በፈጠረው ፍጥረት ሁሉ ክብርን ተቀዳጅቷል፤ ከዘላለም እስከዘላለም ፀንቶ ይኖራል፤ ተብሎ ለዓለም ሁሉ ይነገር፡፡እነሆ አንተን እንደሰው እንፈራህ ነበር፤ ከእንግዲህ በኋላ አንተ ከሟች ፍጡራን እጅግ የላቅህ ሆነህ ትታያለህ፡፡ ከዚያም እርሱ ከበላዩ የቆመ አንድ መላዐክ አየ፤ ሞት እንደሚመታ አድርጎ መታው፡፡ጲላጦስ ለሄሮድስ የላከው ደብዳቤ መጨረሻ

Read 7304 times