Saturday, 24 October 2015 10:19

የሌሊት ወፍ ገብሪ፣ አይጥ ነኝ አይጥ ገብሪ፣ የሌሊት ወፍ ነኝ!

Written by 
Rate this item
(16 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ሹም ባለሥልጣን እሥር ቤት ይገባል፡፡
እንደገባ ወደተመደበለት ክፍል ሲደርስ፣ እሥረኛው ሁሉ በሱ ላይ መጠቋቆም   ጀመረ፡፡
አንደኛው - እንዴ ይሄንን‘ኮ አውቀዋለሁ፤ የናጠጠ ሀብታም ነው!
ሁለተኛው - እኔ ደግሞ አንቱ የተባለ ሹም መሆኑን ነው የማውቀው!
ሶስተኛው - ጐበዝ አትጃጃሉ! የናጠጠ ሀብታምም፣ አንቱ የተባለ  ሹምም  እንዳይሆን ምን ያግደዋል? እንዲያውም በዛሬ ጊዜ የሚበዙት    ሹሞች ሀብታሞች   ናቸው፡፡
አራተኛው - ቀስ እያለች ቢሮክራቲክ ካፒታሊዝም መጣች በለኛ!
አንደኛው - እንዴታ!
ስድስተኛው - እኔ እምለው ወንድሞቼ፣ ከዚህ ሁሉ ፍልስፍና ለምን ራሱን   አንጠይቀውም?
ሁሉም - ውነቱን ነው፣ ውነቱን ነው!
አንደኛው - ጋሼ
እንግዳው እሥረኛ - አቤት የኔ ልጅ
አንደኛው - ምን አድርገዋል ብለው ነው ወደዚህ ያመጡዎት?
እንግዳው እሥረኛ - ኮርቻ ሰርቀሃል ነው የሚሉኝ
አንደኛው - ለኮርቻ? እዚህ ከባድ እሥር ቤት ለኮርቻ ብለው አመጡዎት?
እንግዳው እሥረኛ - ምን እባክህ አንድ የማትረባ በቅሎ ከሥሩ አለች!
***
በሀገራችን ሌባው በጣም በዝቷል፡፡ ሁሉም ስለኮርቻው እንጂ ስለ በቅሎዋ አያወራም! የሚታሠረው እንጂ ስለ በቅሎዋ አያወራም! የሚታሠረው በርካታ የሀገር ገንዘብ ሰርቆ ይሁን እንጂ ምንም እንዳልነካ አድርጐ ደረቱን የሚነፋ መዓት ነው፡፡ የሀብት ዘረፋው ሳያንስ በሥልጣን የሚባልገው ሥፍር ቁጥር የለውም፡፡ ሥልጣን ወደ ኃላፊነት ሳይሆን ወደ ሀብት፣ ወደ መሬት መከፋፈል፣ ወደ ዘመድ መጠቃቀሚያ፣ ወደ ፍትሕ ማዛቢያ፣ ወደ ምዝበራ መረብ ማስፋፊያ፣ ወደ ህገ ወጥ ፎቅ መገንቢያ ካመራ፤ ወደ ልማት ሳይሆን ወደ ጥፋት እየሄድን ነው ማለት ነው፡፡ ውሎ አድሮ ሁሉም የበታች እንደ ቁንጩዎቹ የድርሻዬን ልውሰድ ማለቱ አይቀሬ ነው፡፡
ከባለሥልጣን የሚመሳጠረው አቀባባይም እኔም የድርሻዬን ማለቱም አይቀሬ ነው፡፡ በኮሚሽን የሚተዳደረው ሰው፤ ከዋናዎቹ ገዢና ሻጮች የተሻለ የሚያገኝበትን መንገድ ስለሚያሰላ ህገ-ወጥ ንግዱ እንዲፋፋም፣ የተለያዩ ወገኖች ገብተውበት የዘረፋ መረቡ እንዲሰፋ፣ ማድረጉን ይያያዘዋል፡፡ አንዱ ህገ ወጥ ተብሎ ሲታሰር ግን መረቡ አይነካም፡፡ ሀገራችን እስከወሲብ ድረስ የተወሳሰበ ሙስና እያስተናገደች መሆኑ ይነገራል፡፡
ይህንኑ ሙስና ምሁሩም መሀይሙም፣ ህገ አስፈፃሚውም አላዋቂውም አድናቆቱን እየገለፀና ወሬውን በመንዛት እየተባበረ ሀገራችን ወደ አሳዛኝ ፈተና እየገባች ነው!
የብዝበዛው መረብ ክሩ እየበዛ ሲሄድ ፖለቲካው ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ አይቀሬ ነው! ምነው ቢሉ ሌብነቱን እንዳይከላከሉ፣ በእጅ በአፍ የሚባሉ ፖለቲከኞች ይኖራሉና! ከንቲባዎች፣ የወረዳ ሊቃነ መናብርት፣ የማህበራት መሪዎች፣ ህግ አስፈፃሚዎች፣ ትላልቅ የክልል ሹማምንት ከትንሽ እስከ ትልቅ የቅሌት መዝገብ ላይ ሠፍረው ወደ ወህኒ ሲጋዙ፣ ወደ ዘብጥያ ሲወርዱ አይተናል፡፡
ገናም እናያለን፡፡ የብዝበዛው መረብ እስካልተበጣጠሰ ድረስ! በመሬት ስፋት የማይለካ፣ በፎቅ ርዝመት የማይወሰን፣ በቀረጥ ነፃ ብቻ የማይቆም የህሊና መቆሸሽና ተዛማች የሌብነት በሽታ እንደ ዘር - ደዌ መናኘቱ፤ የዲሞክራሲ፣ የመልካም አስተዳደር፣ የፍትሕ - ርትዕ፣ የዕድገት ሀገር ትሆናለች የምትባለውን ሀገራችንን፤ ህልውናዋን ጭምር የሚፈታተኑ ከተላላኪ እስከ መመሪያ አስፈፃሚ የሌብነት ባለድርሻ አካላት የሆኑባት የዘረፋ መናኸሪያ እንዳትሆን፣ ከባድ እንቅስቃሴ ትሻለች፡፡
ራሱ እየሰረቀ ሌላውን ማማት ፋሺን እየሆነ ነው፡፡ እራሱ እየገረፈ እንደ ጅራፉ የሚጮኸው እየባሰ ነው፡፡
ከሥጋ ቤት እስከ ኦፊስ ባር ሲመካከርና ሲመርብ (Weaving corruptive networks) የሚያመሸው ቁጥሩ ቀላል አይደለም፡፡
ሌብነት “ቢዝነስ” የሚል የማዕረግ ስም ከወጣላት በጣም ቆየ! አንዴ በሥልጣኑ፣ አንዴ በንግድ ውስጥ እጃቸውን እየነከሩ ያሉ በርካታ ናቸው - “የሌሊት ወፍ ገብሪ- አይጥ ነኝ፤ አይጥ ገብሪ የሌሊት ወፍ ነኝ” ማለት ይሄው ነው!   

Read 8272 times