Saturday, 31 October 2015 09:32

አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ 151 ሚሊዮን ብር አተረፈ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

     አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ ባለፈው ዓመት ታክስና የብሔራዊ ባንክ ተቀማጭ ከተቀነሰ በኋላ 151 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ፡ ባንኩ፣ ዛሬ 11ኛ የባለአክሲዮኖች መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ በሸራተን ሆቴል እያካሄደ ሲሆን የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር ዶ/ር ጣሰው ወ/ሃና ለባለአክሲዮኖች ባቀረቡት ሪፖርት፤ የተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ለባንኩ ስኬታማ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
በዓመቱ ባደረጉት እንቅስቃሴ 151 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘታቸውን ጠቅሰው ይህም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ108 ፐርሰንት እንደሚበልጥ፣ የአንድ አክሲዮን የትርፍ ክፍያ ከአምናው በ81 ፐርሰንት ልቆ 10.63 ብር መድረሱን፣ ባንኩ የተጣራውን ትርፍ ያገኘው ለመንግሥት የትርፍ ክፍያ 74.8 ሚሊዮን ብር ከፍሎና እስከ በጀት ዓመቱ መጠናቀቂያ ከብሔራዊ ባንክ የ1.24 ቢሊዮን ብር ኩፖን ከገዛ በኋላ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ባንኩ ለስኬት የበቃው የዳይሬክተሮች ቦርድና ማናጅመንቱ፣ የባለአክሲዮኖችን እምነት ለማግኘት፣ የደንበኞችን ቀልብ ለመሳብ፣ የባንኩን መልካም ገፅታ ለመገንባትና ዝና ለመጠበቅ ባደረጉት ያላሰለሰ ጥረት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዓመቱ ባንኩ አዳዲስ አገልግሎቶችን ለገበያ ለማቅረብ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን የቀረፀ ሲሆን የአገልግሎት ብቃትን ለማሻሻል፣ የገበያውን ፉክክር መቋቋምና ሁለንተናዊ አቅም ለመገንባት የሚያስችል የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ፕላን (ዕቅድ) ነድፎ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ባንኩ እየሠራባቸው ካሉ ጉዳዮች አንዱ ተደራሽነትን ማስፋት ሲሆን በዓመቱ 29 አዳዲስ ቅርንጫፎችን በመክፈት የቅርንጫፎቹን ጠቅላላ ብዛት 89 ማድረሱን፣ የሞባይልና የወኪል ባንክ አገልግሎት ለመጀመር ከፈቃጅ አካል ይሁንታ ማግኘቱን ዶ/ር ጣሰው ወ/ሃና ተናግረዋል፡፡  

Read 2401 times