Saturday, 31 October 2015 09:33

የቱርክ ፋብሪካ ምርቱን ለውጭ ገበያ እያቀረበ ነው

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ያላቸው ፎጣ፣ የሻወር ጋዋን፣ ምንጣፍ፣--- ያመርታል
በ850 ሚሊዮን ብር የሚከናወነው የማስፋፊያ ሥራ ከግማሽ በላይ ተጠናቋል

    መሠረቱ ቱርክ ነው፡፡ እዚያ ለ25 ዓመታት ሲቆይ ታዋቂ ብራንድ ነበር፡፡ በ2011 ጓዙን ጠቅልሎ ኢትዮጵያ መጣ፡፡ በለገጣፎ ከተማ በ50ሺ ካ.ሜ ቦታ ላይ በ1.2 ቢሊዮን ብር ፋብሪካውን ገንብቶ፣ ምርቶቹን ለውጭ ገበያ እየላከ ነው - ኤምኤንኤስ (MNS) ፋብሪካ፡፡
አቶ ተስፋሁን ሳና የኤምኤንኤስ ፋብሪካ ፕሮጀክት ማናጀር ናቸው፡፡ የሚመሩት ፋብሪካ በአንድ ቱርካዊ ግለሰብና በአንድ ኩባንያ በአክሲዮን የተቋቋመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሚልካይ ቴክስታይል የተባለው እናት ኩባንያ በቱርክ ሆም ቴክስታይል የሚባሉትን የቤት ውስጥ መገልገያ ልብሶች በማምረት የ25 ዓመት ልምድ አለው፡፡
ፋብሪካው የሚያመርታቸው ፎጣዎች፣ የሻወር ጋዋን፣ ምንጣፍ፣--- የጥራት ደረጃቸው ከፍተኛ በመሆኑ ከሚያመርታቸው ፎጣዎች ከ90 በመቶ በላይ ለአውሮፓና ለመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ገበያ የሚቀርቡ ናቸው፡፡ ጀርመን፣ ኖርዌይ፣ ስዊድንና ሳዑዲ አረቢያ የፎጣዎች መዳረሻ ናቸው፡፡ “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከአሜሪካ ጋር የመገማገሚያ መድረክ አበጅተን አቅማችንንና ምርቶቻችንን እየገመገሙ ነው፡፡ በምርቱ ጥራትና በዋጋ ከተስማሙ ትዕዛዝ ይሰጡናል፡፡ ወደ አፍሪካ ገበያም ለመግባት ዕቅድ አለን፡፡ ወደ ኬንያ ኤክስፖርት ለማድረግ በሂደት ላይ ነን” ብለዋል አቶ ተስፋሁን፡፡
ፋብሪካው መጀመሪያ ላይ ትንሽ የገበያ መንገራገጭ ገጥሞት እንደነበር አቶ ተስፋሁን አልሸሸጉም፡፡ በቱርክ ለ25 ዓመት ሲሰራ ትልቅ ብራንድ (ትልቅ ስምና እውቅና) ያለው ነበር፡፡ ከዚያ ነቅሎ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲመሰረት፣ የሥራ አካባቢ (ጆግራፊካል ሎኬሽን) ለውጧል፡፡ የቀድሞ ደንበኞች እንኳ በፊት የነበረውን የጥራት ደረጃ ታሟላለህ? የቴክኖሎጂ ሽግግር በአግባቡ ተደርጓል ወይ … በማለት ያጣራሉ፡፡
በጨርቃጨርቅ ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷቸው የሚጠየቁ መስፈርቶች አሉ፡፡ አንዱ BSTI (ቢዝነስ ሶሻል ኮምፕሊያንስ ኢንሼቲቭ) ነው፡፡
 ከማኅበራዊ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ብዙ የሚነሱ ነጥቦች አሉ፡፡ የሕፃናት የጉልበት ብዝበዛ (ቻይልድ ሌበር) አለመኖሩ፣ በእስረኞች ያለማሰራትህ፣ የምትወስደው የደህንነት እርምጃ፣ … ከብዙ ነገሮች ጋር የተያያዙ መመዘኛዎች ቀርበው ትገመገማለህ፡፡ ሁለተኛው መመዘኛ ኢኮ ቴክስት የሚባለው ነው፡፡
 ይኼ ይበልጥ የአካባቢ ጥበቃን ይመለከታል፡፡ የማምረቻ መሳሪያ ወደ ከባቢው አየር ከሚለቀው የተበከለ ጋዝ ጋር … የተያያዘ ነው፡፡
ሁለቱን ሰርተፊኬቶች፤ የማኅበራዊ ቅሬታና የሶሻል ፍሬንዲሊ ኮምፕሊያንት ሰርቲፊከቶች ስላገኘን የአይኤስኦ ሰርቲፊኬት አያሳስበንም፡፡ አሁን ምርት ምርመራ (ፕሮዳክት ኦዲቲንግ) ላይ ናቸው፡፡ እየመጡ ምርቶቻችንን እያዩ ነው፡፡ ትዕዛዞችም እየመጡ ነው በማለት አቶ ተስፋሁን ስለገበያው አስረድተዋል፡፡
ፋብሪካው ከውጭ የሚገባውን ምርት በአገር ውስጥ ለመተካት ቢቋቋምም የተሳካለት በከፊል ነው ማለት ይቻላል፡፡ በምንጣፍ ምርቱ መጠነኛ ኤክስፖርት ቢኖርም ከውጭ የሚገባውን በመተካት እየተሸጠ ነው፡፡ በሦስት ፈረቃ 24 ሰዓት የሚመረተው ፎጣ ግን ከ90 ከዓመት በላይ ለውጭ ገበያ ሲቀርብ የቆየና አሁንም በመቅረብ ላይ የሚገኝ ነው፡፡
የፋብሪካው ዋነኛ ጥሬ ዕቃ የሆነውን ክር የሚያገኙት ከውጭ አገር ነው፡፡ የኋላ ትስስር (ባክዋርድ ሊንኬጅ) በመፍጠር የጥጥ ክሩን እዚሁ ለማምረት በ850 ሚሊዮን ብር በ35ሺ ካ.ሜ ቦታ ላይ የማስፋፊያ ሥራ እያከናወኑ መሆኑን ፕሮጀክት ማናጀሩ ተናግረዋል፡፡ የፎጣ ምርታችንን በተወሰነ ደረጃ ለማሳደግ ተጨማሪ የፎጣ ማምረቻ መሳሪያዎች ጨምረን እየሰራን ነው፡፡ ማስፋፊያው ከ50-60 በመቶ በላይ ተከናውኗል፡፡ ይህ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ፣ በአሁኑ ወቅት በፋብሪካው በቋሚነት ከሚሰሩት 750 ሰራተኞች በተጨማሪ ለ400 ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር አቶ ተስፋሁን ተናግረዋል፡፡
ማንኛውም ፕሮጀክት ሲጀመር መንገዱ ሁሉ አልጋ በአልጋ አይሆንም፡፡ ኤምኤንኤስም ችግሮች እንደነበሩበት አቶ ተስፋሁን ገልጸዋል፡፡ ዋነኛው ችግር የሰለጠነ የሰው ኃይል ያለመኖር ነው፡፡ ከበቂ በላይ የሰው ኃይል ቢኖርም በቂ የሰለጠነ የሰው ኃይል ግን የለም፡፡ ይህን ችግር በፋብሪካው በማሰልጠን ለመፍታት እየጣሩ ነው፡፡
ሌላው የሎጂስቲክስ ችግር ነው፡፡ ከተለያዩ የአውሮፓና የኤስያ አገሮች ጥሬ ዕቃ ሲያስመጡ፣ ጂቡቲ ከደረሰ በኋላ የትራንስፖርት፤ ዕቃውን ለማጓጓዝ የሚፈጀው ጊዜ፣ … ችግር አለ፡፡ ይህ ችግር አዲሱ የባቡር ትራንስፖርት ሥራ ሲጀምር ይቃለላል የሚል እምነት አላቸው፡፡ መጀመሪያ አካባቢ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥና የኃይል መዋዠቅ ችግር ነበረባቸው፡፡ አሁን ግን ከገለጣፎ የኤሌክትሪክ ኃይል ጣቢያ ስለሚወስዱ ችግሩ ተወግዷል፡፡
 ይህ ሁሉ የውጭ አገር ኢንቨስተር የሚመጣው ኢትዮጵያ ሳቢና ምቹ የኢንቨስትመንት አዋጅ ቢኖራት ነው ያሉት አቶ ተስፋሁን፣ መጀመሪያ ላይ አንዳንድ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ችግሩን ተቋቁመህ ከተወጣህ በምላሹ የምታገኘው ጥቅም (ሪዋርድ) አመርቂ ነው፤ብለዋል፡፡
ጨርቃጨርቅን በተመለከተ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች አሉ፡- የሰለጠነ የሰው ኃይልና የኤልክትሪክ ኃይል፡፡ ያለውን የሰው ኃይል ካሰለጠንክ ለጉልበት የሚከፈለው ዋጋ ከሌሎች አገሮች ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ ስለሆነ ትልቅ ጥቅም አለው፡፡ የጨርቃጨርቅ ዘርፍ ትልቅ የኤሌክትሪክ ኃይል ይፈልጋል፡፡
የኃይል መቆራረጥና መዋዠቅ ከተወገደ፣ በማንኛውም አገር ሊገኝ በማይችል ዝቅተኛ ዋጋ ይገኛል፡፡ አገሪቷ አልሰራችበትም እንጂ ትልቅ የጥጥ ምርት አቅምም አላት፡፡ በእነዚህ ነጥቦች ላይ ጠንክራ ከሰራች የማታሸንፈው ገበያ አይኖርም ብለዋል አቶ ተስፋሁን ሳና፡፡


Read 2412 times