Saturday, 31 October 2015 09:42

ከ12 ዓመት በኋላ ድምጹ የተሰማው የ“ሚክሎል” ደራሲ

Written by 
Rate this item
(8 votes)

ከእንግሊዝ በተለይ ለአዲስ አድማስ)

“‘የሚያቅትህ ነገር የለም!...‘ እየተባልኩ ነው ያደግሁት...” - ደራሲ ስዩም ገ/ ህይወት


ከ12 አመታት በፊት ለንባብ የበቃው “ሚክሎል - የመቻል ሚዛን” በበርካታ አንባብያን ዘንድ ከፍተኛ አድናቆት የተቸረው የረጅም ልቦለድ
መጽሃፍ ነው፡፡ የመጽሃፉ ደራሲ ስዩም ገብረ ህይወት፣ በዚሁ መጽሃፍ ላይ ቀጣዩን “ሚክሎል - የማቃት አንጀት” ለንባብ እንደሚያበቃ ቢገልጽም፣
መጽሐፉ ለረጅም አመታት ለህትመት ሳይበቃ መቆየቱ፣ በርካታ አንባቢያን ዘንድ መልስ ያልተገኘለት ጥያቄ ሆኖ ቆይቷል፡፡ደራሲ ስዩም ገ/ ህይወት
ከአስር አመታት በላይ ድምጹን አጥፍቶ መቆየቱ ያሳሰባቸው አድናቂዎቹ፣ በቅርቡ በማህበራዊ ድረ ገጾች በኩል ደራሲውን የማፈላለግ ዘመቻ
መጀመራቸው ይታወቃል፡፡ ጋዜጠኛ አንተነህ ይግዛው፤ለደራሲ ስዩም ገብረ ህይወት በግል ህይወቱ፣ በመጀመሪያው ልብወለድ መጽሐፉና ተያያዥ
ጉዳዮች ዙሪያ፣ በኢሜይል ላቀረበለት ጥያቄዎች፣ የሰጣቸውን ምላሾች የመጀመሪያ ክፍል እንዲህ አጠናቅረነዋል፡፡

ውልደትና እድገት
ድርና ማጌ ወሎ ነው። “ሃድራው የሚደምቀው ተደራርበው ሲተኙ” እየተባለ የተዘፈነለት ባቲ ገንደድዩ፣ የአባቴ አገር ነው። “እኒህ አምባሰሎች አበላል ያውቃሉ በጤፍ እንጀራ ላይ ሳማ አርጉ ይላሉ” የተባለለት አምባሰል ደሞ የእናቴ አገር ነው። እኔ ግን ባቲ ተወልጄ፣ ያኔ የቃሉ ወረዳዋና ከተማ በነበረችው ሐርቡ ነው ያደግሁት። አስታውሳለሁ ገና የስምንት ዓመት ልጅ እያለሁ፣ ከቤታችን በር አጠገብ ባለው ወደ ሰሜን በሚሄደው ጎዳና ዳር ቆሜ፣ ወደማታ ላይ የሚያልፉትን አውቶቡሶች ማየት ደስ ይለኝ ነበር። አንዳንዶቹ አሥመራ፣ አንዳንዶቹ መቀሌ የሚል የተለጠፈባቸው ነበሩ። “እኔ ግን ሳድግ የምኖረው መቀሌ ነው” እል ነበር፤ ሁልጊዜ። ምን ታይቶኝ ነበር ማለት ነው? መቀሌን ማየት ይቅርና ስለሱ ሲወራ እንኳን ሰምቼ አላቅም።
 የትምህርት ሂደት
የአንደኛ ደረጃ ትምህርቴን ሐርቡና ቢስቲማ በምትባለው አምባሰል ባለች ትንሽ ከተማ ነው የተማርኩት። ሰባተኛ ክፍል ብቻ ባቲ ተማርኩ እንጂ የቀረው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን የጨረስኩት የቃሉ አውራጃ ዋና ከተማ በሆነችው ኮምበልቻ ነው። ከዛ እድሜዬ በኋላ ከወሎ ጋር እንደተለያየን ቀረን። መጀመሪያ አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ተመድቤ ከሄድኩበት ጊዜ አንስቶ በቋሚነት ለመኖር ተመልሼ አላውቅም። የሐርቡ ልጅነት መንፈሴ ግን የትም ልሂድ የትም፣ ቋሚ መኖሪያው እስካሁን ሐርቡ ነው። ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ላይብራሪ ሳይንስ በሚባል ሙያ በዲፕሎማ እንደተመረቅሁ፣የተመደብኩበት መስሪያ ቤት አንድ ስህተት ሰራ። አሁን ሳስበው ለካ ስህተትም ትክክል የሚሆንበት ጊዜ አለ እላለሁ። ያ መስሪያ ቤት  ስሜን ብቻ በማየት የሰሜን ተወላጅ ነው ብሎ በማመኑ፣ መቀሌ መድቦ ላከኝ። ለካ የራሴ ቃል ጥሪ ነው መስሪያ ቤቱን ያሳሳተው። ምን ይሄ ብቻ -  ያን ስህተት ትክክል የሚያደርገው ጉድ መች ታየና።
መፈጸም የነበረበት ስህተት ---  
አሁን ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት ነኝ። የመሆኔ ብርታት፣የነፍሴ ብርሃን፣ የራዕየ ምርኩዝ የሆነችው ውዷ ባለቤቴ ባትኖር ኖሮ የኔ ማንነት ባዶ ነበር። ሚክሎልን ያነበበ ሁሉ በስም ያውቃታል። ሚክሎል የተወለደው ከኔ የሁነት አብራክ ብቻ ሳይሆን ከሷምዝንታለም የማይላላ፣ የማያረገርግ የድጋፍ ምሶሶ ነው። ያለ ምሶሶ ጎጆ ሊቆም ይችላል? በብርቱ ሴት ጠጣር መንፈስያልተደገፈ የወንድ ህይውት፣ በሸንበቆ ተራዳ የቆመ ጊዜያዊ ድንኳን ነው።
ትዳር ሳልይዝ፣ሶስት ዓመት ኖሬ መቀሌን ለቅቄ ሄድኩ። ሁለት ዓመት አዲስ አበባ ከኖርኩ በኋላ እንደገና ዩንቨርስቲ ገባሁ። ከዱሮው ሞያዬ ላይ የኢንፎርሜሽንና ኮምፒውተር ሳይንስ ተጨምሮበት በዲግሪ ተመረቅሁ። በጣም የሚገርመው ነገር ግን የመቀሌ አዙሪትሊለቀኝ አልቻለም። በከፍተኛ ትምህርት ኮሚሽን ተወዳድሬ አለፍኩና አሁንም ዳግመኛ መቀሌ ተላኩ። የመቀሌ ዩንቨርስቲን ለማቋቋም ከየትምህርት ተቋሙ ተመርጠው ከተመደቡት በጣት የሚቆጠሩት የአካዳሚክ ሰራተኞች አንዱ ሆንኩ። እንግዲህ የመሆኔ መረብ ሊይዝ የሚፈልገው ዓሳ፣ እዛው መቀሌ ስለነበር ይሆናል፡፡
በመቀሌ ዩንቨርስቲ የመጀመሪያውን ላይብረሪና የኮምፒውተር ማዕከል አቋቋምኩ። የመጀመሪያውም የኮምፒዩተር ስልጠና አደራጅና አስተማሪም እኔው ነበርኩ።መቀሌ ዩንቨርስቲ ሥራ እንደጀመርን ብዙም አልቆየንም። ከሁለት ጓደኞቼ ጋር እየተጨዋወትን፣ በግቢው ውስጥ እንንጎራደዳለን። ፀሃፊዎች ለመቅጠር ማስታወቂያ ወጥቶ ነበርና ማመልከቻ ለማስገባት የሚጎርፈው ግቢውን እጥለቅልቆታል። ከፊት ለፊታችን ከሚመጡትሶስት ወጣት ሴቶች መሃለኛዋ ላይ ዓይኔ ድንገት አረፈ። በህይወቴ ተሰምቶኝ የማያውቅ ልዩ ንዝረት ሁለንተናዬን ናጠው። ልቤ አምልጦ አለት ላይ እንደወደቀ እንቁላል ጧ ብሎ የፈረጠ መሰለኝ። ልጅቷ እስከመቼውም የማይጠፋ የሚመስል እሳተጎመራ አስነስታ፣ሄደች። ደግሜ ላያትም አልቻልኩም። ተፈልጋ የምትገኝበትም መንገድ የለም።  ህመሜን ተሸክሜ ቀረሁ። እንደ ካሜራ፣ ያ ድንገት ከፊቴ ላይ ፏ ብሎ የጠፋው ብርሃን፣ አሁንም እሁንም እየተመላለሰ ይጎበኘኝ ነበር። እሸሸዋለሁ ይከተለኛል። እንዲሁ ሲያንገላታኝ አንድሁለት ሰሞን እንዳለፈ፣ አንድ ቀን ድንገት ወደ ቢሮዬ ስልክ ተደወለ። ከአስተዳደር ነበር። ከሚቀጠሩት ሶስት ፀሃፊዎች አንዷ፣ ለኔ የሥራ ክፍል መሆኑን አውቅ ነበር። አስተዳዳሪው ሦስቱ መመረጣቸውን ገልጾልኝ፣ ለኔ የተቀጠረችውን እገሌ ትባላለች ብሎ ስሟን ነገረኝ። ስሟን በልቤ እየደጋገምኩ  ወደ አስተዳደር መሄድ ጀመርኩ። ልቤ ግን ስሟን መሸከም የከበደው ይመስል ምቱ ጨመረ። “ደሞ ይሄ ምን እሚሉት በሽታ ነው ለማያውቁት ሰው። ኧረ ተው! ኧረ ተው! አንተ ልብ አበዛኸው!” አልኩት።
ሦስቱ የተመረጡት ፀሃፊዎች ያሉበት ክፍል ደርሼ፣ ዓይኔን ወደ ውስጥ ወርወር ሳደርግ፣ ልቤም ተፈትልኮ ተወረወረና በእርግጡን እንቦጭ ብሎ ፈረጠ። እንዴት አድርጎ መልሶ እቦታው እንደተመለሰ አላውቅም። ከሶስቱ አንዷ ያቺው ልጅ እራሷ ነበረች። ጉልበቴእየተብረከረከና ከንፈሮቼ እየተንቀጠቀጡ፣ “መብራት አበራ የምትባለው የትዋ ነች?” አልኩኝ፤ ዓይኖቼን ከዓይኗ ላይ ሳልነቅል። ይባስ ብሎ ይቺው ልጅ እራሷ “እኔ ነኝ” እለችኝ። እርፍ! እሞት እንደሁ ጉዱን አየዋለሁ። ለካ ያቺ ልጅ የሁነቴ አሻራ መረብ አጥምዷትየነበረችው መብራት አበራ ነበረች።
ያቺ የነፍሴ ብርሃን መብራት አበራ (እኔ መብርህቴ እያልኩ ነው የምጠራት) ወደውጭ ለመሄድ እያደረገችው የነበረውን ዝግጅት ሰርዛ፣ መቀሌን ለቀን አዲስ አበባ በመግባት በሠርግ ተጋባን። የመሆኔ ብርታት፣ የራዕዬ ምርኩዝ ሆና፣ ሚክሎል መፅሐፍን አብረን ወለድን። ሦስት ወንድ ልጆችም ወለደችልኝ።
“የፍቅር መታሰቢያችን - ታይታኒክ” - በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ
በጣም የሚገርመው ከ22 ዓመታት በኋላ ሦስቱን ልጆቻችንን ይዘን (ሚክሎል፣ ኖባ እና ካሌብን) መቀሌ ቤተሰብ ለመጠየቅ ከእንግሊዝ አገር እንደሄድን፣ ያኔ የቅርብ ጓደኛችን የነበረው የዩንቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ክንደያ ገ/ሕይወት ዩንቨርስቲውን እንድንጎበኝጋበዘን። ያኔ ሲጀምር 42 ተማሪ ብቻ እንዳልተቀበለ ሁሉ ዛሬ ከ30 ሺ ተማሪ በላይ የሚያስተናግድበት አቅም ላይ ደርሷል። ደስ አለን። ግና በጣም ደስ የሚያሰኝም ያሳቀንም፣ ልጆቻችንንም እጅግ በጣም አድርጎ ያስገረመው ነገር የመጣው በኋላ ነበር።
ዶ/ር ክንደያ፤ ግቢውን እያስጎበኘን እያለ፣ ቀጥ አድርጎ ወደ አንድ ልዩ ቦታ ወሰደን። ያቺ ልዩ ቦታ መብርህቴን ለመጀመሪያጊዜ ያየሁባት፣ ከመጀመሪያው ያስተዳደር ህንፃ ፊት ለፊት የነበረች ነጥብ ናት። ሌላው እጅግ በጣም ጉድ የሚያሰኘውን ነገር የተናገረው ወዲያውኑ ነበር። እሱና የሥራ ባልደረቦቹ እየሳቁ፤ “ይቺን ሃውልት ያሰራነው ለናንተ ፍቅር መታሰቢያ ነው” አሉን። እኛም እጃቸው የሚጠቁመውን ስንከተል፣ በመርከብ ቅርፅ በኮንክሪት የተሰራች ትንሽ ጀልባ የምትመስል ሃውልት ዓየን። እኛም ልጆቻችንም ፍንድቅ ብለን የሳቅነውግን “ታይታኒክ” ተብላ ተሰይማለች ሲሉን ነበር። አይገርምም!
የድሮው ቢሯችን የነበረበት ህንፃም እስካሁን ድረስ አለ። “የኔ ቢሮ እዚህ፣ የናታችሁ ቢሮ ደሞ እዚህ ነበር” ብዬ ለልጆቼ ቢሮዎቹን እያሳየኋቸው ሳለ፣ ቀልደኛው ትንሹ ካሌብ ስዩም ፈገግ አለና በእንግሊዘኛ “ስለዚህ እናቴ ገና እዚህ መስራት እንደጀመረች ያለ ምክንያት ወደቢሮዋ መመላለስ ጀምረህ ነበር ማለት ነው!” ብሎ ሁላችንንም አሳቀን። ከዩንቨርስቲው ባልደረቦች አንዱ እየሳቀ፤ “ያኔ ያለምክንያት ቢሆንም አሁን ሲታይ ግን ለካ ለጥሩ ምክንያት ነበር የሚመላለሰው ያስብላል” አለ።
 ልምድ ያካበትኩበት ብሪትሽ  ካውንስል
እኔ ብዙውን የሥራ ዘመኔን ለብሪትሽ ካውንስል ኢትዮጵያ ነው የሠራሁት። አራት ዓመት ሙሉ የፕሮጄክት ማኔጀር ሆኜ ስሰራ፣ መላኢትዮጵያን ልቅም አድርጌ ለማየት ዕድል አግኝቻለሁ። ከዚያም ቀጥሎ የብሪቲሽ ካውንስል ኢትዮጵያ ቤተመጻህፍትናኢንፎርሜሽን አገልግሎት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆኜ አገልግያልሁ። በስሬ እስከ 25 ፕሮፌሽናል ሠራተኞች ነበሩ። በዚህ የሰባት ዓመት የሥራ ዘመን፣ እጅግ በርካታ የማኔጅመንትና ፕሮጄክት ማኔጅመንት ሥልጠናዎችን በአውሮፓ፣በአፍሪካና በኤስያ እየተዘዋወርኩ ወስጃለሁ፡፡ እጅግ በጣም በርካታ ፕሮጀክቶችን ነድፌአለሁም ፣ የሥራ ፕሮግራማቸውንም መርቻለሁ።በብሪትሽ ካውንስል ቆይታዬ ከሠራኋቸው ብዙ ነገሮች አንድ ሁለቱን ልጥቀስ። በኢትዮጵያ የመጀመሪያዎቹን ቴሌሴንተሮች (ኢንተርኔት ካፌና ኮምፒውተር ማዕከል) ያቋቋመው ፕሮጄክት ሃሳብ፣ንድፍና ትግበራም የኔው የአእምሮ ውጤት ነው። እኒህ የመጀመሪያዎቹማዕከሎች የተቋቋሙት በወሊሶ፣ በደብረብርሃን፣በጎንደርና በአክሱም ከተሞች ነበር። በኢትዮጵያ ውስጥ ያኔ የነበሩትን ሁሉንም ዩንቨርስቲዎች፣ ኮሌጆች፣ መምህራን ማሰልጠኛ ተቋማት፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎችን በኢንፎርሜሽን ቁሳቁስ፣መጽሐፍትና ሥልጠና ይረዳ የነበረውን እጅግ በጣም ሰፊ ፕሮጀክት በሃላፊነት መርቻለሁ። የኢንፎርሜሽን ማኔጅመንትና ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኮርሶችን በማዘጋጀትና በማስተማርም አገልግያለሁ።
የሥራ ልምዴ በእንግሊዝ -----
በፊት የነበረኝን የማኔጅመንትና የፕሮጄክት ማኔጅመንት ዕውቀትና ልምድ በመጠቀም፣ እዚህ እንግሊዝ አገር ባለሁበት ክፍለ ሀገር (ዮርክሻየር) ለክፍለ ሃገሩ ስደተኞች ጉዳይ አስተዳደር መ/ቤት የፖሊሲና ሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ በመሆን አገልግያለሁ።  ዋና ስራዬ ግን፣ በእንግሊዝኛ የሚታተም ወርሃዊ ጋዜጣ ማዘጋጀት፣ የማኔጅመንት ኮርሶችን ማዘጋጀትና መምራት፣ ዌብ ሳይት ማኔጅ ማድረግ፣ ኢንፎርሜሽን ማሰራጨት፣ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ጥናትና ምርምር ማካሄድን ይጨምር ነበር።
ጉግሳና ስዩም ምንና ምን ናቸው?
የሚክሎልጉግሳ ሙሉ በሙሉ ሃሳብ ወለድ ገጸባህሪይ ነው። እኔንም ሆነ ሌላ ማንንም ሰው አይወክልም። መጀመሪያ ስዩም ና ጉግሳ የማይመሳሰሉበትን ብናነሳ አይሻልም? አንባቢዎቼም ይሄንን ልብ ብለው እንዲረዱልኝ እፈልጋለሁ። ካልሆነማ እኔም በየአእምሮአቸው ጓዳሲንጀላጀል የሚኖር ዘባተሎው ጉግሳ ቀዌ ሆኜ መቅረቴ ነው።
ጉግሳኮ በየስብሰባው “ያዝ እንግዲህ” እያለ ታዳሚን ሲያሰለች ነው የሚውለው። እኔ ግን እሱ በተገኘበት ስብሰባ ሁሉ እግሬ የረገጠ ቢሆንም አንድ ቀን እንኳን ትንፍሽ ብዬ አላውቅም። ሲነሳ ሲወድቅ የነበረውን የዩኒቨርስቲ ተማሪ ስሜት ማዕበል ልብ ዬ መታዘብነበር ስራዬ። በልቤ ጓዳ ውስጥ ግን ልብ ያላልኩት የጉግሳ ሽል እየተፈራገጠ ሊሆን ይችላል። የማቀው ነገር የለኝም።ጉግሳ ሁሌ አለባበሱ የተንጀላጀለ፣ ያን ድንኳን የሚያህል ጃኬቱን እያንጓፈፈ ባለፈ ቁጥር በአካባቢው የነበረ ሁሉ “ይሄ ጅልአንፎ ቀውስ መጣ እንግዲህ” እያለ እሚጠቋቆምበት ነበር። ስዩም ግን ከረባት ከአንገቱ፣ ሱፍ ከትከሻው ወርዶ የማያውቅ፣ ዘወትር ሽክ እንዳለየሚታይ የዘመናዊ (አውሮፓዊ) ቢሮ ፕሮፌሽናል ማኔጀር ነበር።ጉግሳኮ ሴቶች ሲፈልጉት አይገባውም። መቼስ ጉዳዩ ነበረና ለሴት። እነ ፀደኒያና እነ ሶስና እንዴት ነበር በድንዝዝነቱ ልባቸው እርር ይል የነበረው። ስዩምም ለሴቶች እንደጉግሳ ነበር ብል እውነት አሁን የሚያውቁኝ ሁሉ ልባቸው ፍርስ እስኪል አይስቁም ትላላችሁ።
ጉግሳ የሐርቡ ልጅ ሆኖ ሲያድግ እንጂ አዲስ አበባ ከገባ በኋላ የነበረው ሁሉ ትምህርቱም፣ ድርጊቱም፣ ውሎውም የራሱ ብቻ ነው፡፡ ከስዩምጋር ምንም ግንኙነት የለውም። ስዩምኮ ሥነ-ጽሁፍ የሚባል ነገር ተምሮ አያውቅም።እሺ አሁን ደሞ ጉግሳና ስዩምን የሚያመሳስላቸው ምንድነው የሚለውን እንይ። የጉግሳ አስተዳደግና የጉግሳ አባት ባህሪና ታሪክ የራሱ የስዩም አባት ባህሪና ታሪክ ቀጥተኛ ነፀብራቅ ነው። ጉግሳ  የስዩምን ማንነት ኮርጆ ተወለደ እንጂ ስዩም የጉግሳን ማንነት ኮርጆ አልተወለደም። ለካ መኮረጅ የምጠላው ገና ከመወለዴ በፊት ነበር።
እንግዲህ ልብወለድ ያልሆነውን ፤ እውነቱን (ያልተኮረጀውን) ስዩም፣ የሐርቡን ልጅ አስተዳደግ እንዲህ እንዲህ አድርገን ዳሰስ ልናደርገው እንችላለን።
አባቴ “ትንሽ ነገር አታስብ” እያሉ ነው ያሳደጉኝ  
በአብዛኛው የባላንባራስ ልጅ እየተባልኩ ነበር የምታወቀው፤ በዛችው በሐርቡ ከተማ ሳድግ። አባቴ ባላንባራስ ገ/ሕይወት ሽማግሌ ከሆኑ በኋላ ነበር የወለዱኝ። ባላንባራስ ገ/ሕይወት ገና በጉርምስናቸው ነበር ከወላጆቻቸው ጋር ከሚኖሩበት ባቲ አካባቢ ካለ ገጠርመንደር በመጥፋት ወደ አስመራ የተሰደዱት። ከጣሊያን ወረራ በፊት ገና ዱሮ ነው ይባላል ይሄ የሆነው። ባላንባራስ ገብረሕይወት በጉርምስናቸው አገር ቤት እያሉ  ሰፈር ከሰፈር በሚደረገው ውጊያ የወንድ አውራ ነበሩ። በዛም የተነሳ ዑመር አባስበር የሚል ስምወጥቶላቸው ነበር። ይህን ያልወደዱላቸውና ስሞታው ያሰለቻቸው አባታቸው ሸህ አሊ ያሲን፤ እረግምሃለሁ እያሉ ስላስቸገሯቸው ነው ጥሎ ለመጥፋት ወስነው የተሰደዱት።
አስመራ ከተማ የትሪቦሊ (ትሪፖሊ) ዘማች ወታደር ሲመለምል ለነበረው ጣሊያንም ያን መለሎ፣ዠርጋዳ፣ወጠምሻ ዑመር አሊ ማግኘት ትልቅ ሲሳይ ነበር። ወጣቱ ዑመር አባስበር ዘወትር የሚናፍቀውን የወንድ ቦታ አግኝቶ፣ “ሸጋው ትርቡሊ” እየተባለ የሚዘፈንለትንሠራዊት ተቀላቀለ። ቦርድ ወጥቶ ወደ ጣሊያን እስኪመለስም ድረስ ወደ ስምንት አመት በየአረብ በረሃው ሲዋጋ ቆየ። ከዛም በኋላ ለዚያኑ ያህልጊዜ በጣሊያን አገር የዘመናዊ እርሻና አትክልት አዘማመር ሙያ ሲማርና ሲሰራ ቆይቷል። ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ፣ በአሥመራናመቀሌ ከተሞች ለብዙ ጊዜ እንደኖረ ይናገራል።
ገና ወዲያው መቀሌ እንደደረሰም ነው ያኔ የትግራይ ንጉስ ከነበሩት ከራስ ስዩም መንገሻ (የአፄ ዮሐንስ የልጅ ልጅ) ጋር የተዋወቀው። አብሮአቸው እንዲሰራም ሲጋብዙት ተስማምቶ በአስተርጉዋሚነት ከቤተመንግስታቸው መስራት ገና ከመጀመሩ ነበር ክርስትና ያነሱት።ዑመር አሊ ቀረና ገ/ሕይወት ካሳ የሚል አዲስ ስም አወጡለት። ‘ባላንባራስ’ የሚል ማዕረግም ሰጡት።
ባላንባራስ ገ/ሕይወት እድሜያቸው ገፋ ካለ በኋላ ነበር ወደ ትውልድ አገራቸው ባቲ ተመልሰው ሚስት አግብተው ልጅ መውለድ የጀመሩት። እስከዛ ድረስ መሃን ነኝ ብለው ይገምቱ የነበሩት ሰውዬ፣ አከታትለው ሦስት ልጅ ወለዱ። ሶስተኛ የተወለደውን ወንድ ልጅ በራስ ስዩም ስም ጠሩት። የስዩም ገ/ሕይወት ነፍስ፣ የህልውና ፊደሏን መቁጠር ጀመረች። አድጋም ከመብራት ህልውና ጋር ተሳሰረች። መብራት የማን ልጅ እንደሆነች ታቃላችሁ? የመብራት አባት አስር አለቃ አበራ ወልዱ የራሳቸው የራስ ስዩም ልጅ የሆኑት የራስ መንገሻ ስዩም ዋና አጃቢ ነበሩ። ታዲያ ይሄን ምን ትሉታላችሁ? ባላንባራስና ስዩምን ወደ መቀሌ ምን ጎተታቸው? አጋጣሚ ወይስ የህልውና አብሮነት አሻራ አዙሪት?
ስዩም ገ/ሕይወት ከእናቱ ተለይቶ ማደግ የጀመረው ገና የስምንት ወር ልጅ እያለ ነበር (በህመም ምክንያት) ። ባላንባራስም በአንቀልባ እያዘሉ፣ ወደ ስራቸው ቦታ ይዘውት ይሄዱና የፍየል ወተት የተሞላ ጡጦውን እያስታቀፉ ከዛፍ ጥላ ስር ደልድለው ያስተኙት ነበር። እዛበርሃ መሃል። ባላንባራስ ያኔ  ዱብቲ ተንድሆ አዋሽ ወንዝ ዳር የጥጥ እርሻ መሬት በማልማት ሥራ ላይ ተሰማርተው ነበር።
አባትም እናትም ሆነው ያሳደጉኝ ባላንባራስ ገ/ሕይወት፤ ገና ሦስት ዓመት ሳልሞላ የፍየል ሃሞት ያጠጡኝ እንደነበረ በደንብ አስታውሳለሁ። ፍየል ባረዱ ቁጥር የሃሞቱን ከረጢት ከሆድቃው መዝው ያወጡና “ናልኝ እስቲ ወዲህ የኔ አንበሳ... አንተነህ የወንዶች ወንድጀግና.... በል ያዝና ግጥም አድርጋት” እያሉ ይሰጡኝ ነበር። ታላቄ የነበሩት ወንድሜና እህቴ ከጎን ቆመው ያዩኛል። “እዩት እዩት የኔን ልጅ ፊቱ ትንሽ እንኳን ጨምደድ አይልም” ይላሉ ባላንባራስ። እኔም አንድ ጊዜ ጀግና የወንዶች ወንድ ተብሎ የተሰጠኝን ስም ላለመነጠቅ፣ ፊቴ ዘና እንዳለ ጭልጥ አደርጋታለሁ። በወንድነት ኩራትም እህትና ወንድሜን ጀነን ፈጠጥ ብዬ አያቸዋለሁ።
“ትንሽ ነገር አታስቡ” እያሉ ነው ያሳደጉኝ ባላንባራስ። “ትንሽ ነገር ማሰብ ትንሽ ያደርጋል። የኔልጅ ትልቅ ነህ። የሚያቅትህ ነገር የለም!!” ይሉኝ ነበር በየአጋጣሚው።ባላንባራስ የሚዝረከረክ ሰው አይወዱም። “ሰው ማለት ሁሉ ነገሩ ስትር ያለ ነው። ይሄ ልብሱን እንኳን በአግባቡ መሰተር ያቃተው ሰው፣ ምን የተሰተረ ህይወት ሊኖረው ይችላል።” ሲሉ እየሰማሁ ነው ያደግኩት።
ገና የአስራ ስድስት ዓመት ልጅ ሳለሁ ነው የሐርቡ ከተማ ወጣቶች ሊቀመንበር ሆኜ የተመረጥኩት። እንዴት እሳት የላሰ ምላስ እንደነበረኝ አስታውሳለሁ። ያኔ ነበር ሸዋየ እብዲቱ ‘የልጅ ሹም’ ትለኝ የነበረው። “አይ የልጅ ሹም..... የልጅ ሹምና የህዳር ጉም አንድ ነው”ትለኝ ነበር ባየችኝ ቁጥር። አስታውሳለሁ-- ጓደኞቼ ሁሉ የመንግስት ሠራተኞች ነበሩ፤ ካድሬ፣የግብርና ሚ/ር ሠራተኞች፣ አስተማሪዎች።
ከጥበብ ጋር ትውውቅ
በዛው እድሜዬ በወረዳው የታውቅሁ ሰዓሊ ነበርኩ። የመስከረም ሁለት ዓመታዊ በዓል ሲመጣ፣ አንደኛ ሆኖ የሚመረጠው አብዮታዊ ግጥም የኔ ነበር። ሰው ጢም አለበት አደባባይ ወደ መድረክ ወጥቼ አሸናፊ ግጥሜን ሳነብ ኩራቴ ወደር የለውም ነበር። የባላንባራስማ ኩራት ምኑ ተወርቶ። “ እንዴት ያለ ልጅ ነው ያለዎት አቦ አላህ ያሳድግልዎት” እያለ ሰው አድናቆቱን ሲገልፅላቸው፣ “ድሮስ የኔ ልጅ ምን ያቅተውና” ይሉ ነበር በኩራት ጀነን ብለው። በተመሳሳይ ጊዜ ነው በሐርቡ ከተማ የመጀመሪያውን ቤተመጽሐፍት ያቋቋምኩትና እዛው የመጀመሪያው አስነባቢ ላይብረሪያን ሆኜ መስራት የጀመርኩት። ትዝ ይለኛል እነዚያን ትርጉም የሩስያ ልብወለድ መጻሕፍት እንዴት አድርጌ እየተንሰፈሰፍኩ አነባቸው እንደነበረ።
እሚገርም እኮ ነው።  በጣም ከመጓጓቴ የተነሳ የነቻርልስ ዲክንስና ዶስቶይቪስኪ ትልልቅ የእንግሊዘኛ ልብወለድ መፃሕፍት ለመረዳት እታገል ነበር። ከእንግሊዘኛ ጋር የነበረን ፍጥጫ ትዝ ይለኛል። “እኔ ደግሞ ትሞታታለህ እንጂ አልገባህ” ይለኝ ነበር አያ እንግሊዘኛ።
እረስቼው....... ለካ በኪነትም ሃርሞኒካ ተጫዋቹ እኔው ነበርኩ።
እና ይሄውላችሁ ጉግሳ እንዳለ የኮረጀው  የሐርቡው ልጅ ስዩም፣ ልብወለድ ያልሆነው ታሪክ ይህን ይመስላል።
 “የቃሉ ሰው ቃል ማንጠር ይወዳል”
የቃሉ ሰው ከሆንክ ከቃሉ ጋር የሚኖርህ ፍቅር በእንዶድ ቢያጥቡት የሚለቅ አይደለም።የቃሉ ሰው ቃል ማንጠር ይወዳል። ተራው ሰው እንደ ዋዛ ጣል እሚያደርገው ነገር አባባል ሆኖ ይቀራል። ስነፅሁፍ ተፃፈም አልተፃፈም ያው ቃል ማንጠር ከሆነ ስነጽሁፍ የጀመረኝ ገና እኔ አድጌ ሳልጀምረው ነበር። ገና ብዕር ይዤ ልጻፍህ ሳልለው በፊት ነበር፣በልጅነቴ ቃል በገፍ የሚነጠርበትን ገበያ ሁሉ ማዘውተር የጀመርኩት። ከነ ሰይድዋ ሙሄ መች መለየት እወድ ነበር፡፡ እኔም ጅና የጠገበ ሸመሌን ይዤ በየለፍጀሌው (የሠርግ ዋዜማ ዘፈን ምሽት)፣ በየሠርጉ ሆታ፣ በአረፋው ጭፈራ እየታደምኩ፣ ያን የቃሉ ቃል እሸትእየዠመገግኩ ስቅመው፣ ያቺ ትንሽ ነፍሴ እንዴት ውስጧ ጥግብ እያለ ትመለስ እንደነበር ትዝ ይለኛል። የነ ሸህ ሁሴን ማሃዲ፣ የነሸህ ሙሃመድ አወልን መንዙማ ስሰማማ እንኳን ያኔ አሁንም ቢሆን ቀልቤን ይዞት ጥፍት ይላል። የነፍሴን ክሮች ልብን በሰመመን ጣቶችደበስበስ እያደረገ በሚያስተኛ የንዝረት ቅኝት ያርገበግባቸዋል። የእናቶቻችን ቡና እየጠጡ የሚፈለፍሉት የወግ እሸትስ የት ይረሳል።ቃልን በጽሁፍ የማንጠሩንም ስራ የጀመርኩት በዛውን ዘመን ነው። ለአብዮት በዓሉ፣ ለኪነቱ ማድመቂያ የሚሆኑ ግጥሞች እሞነጫጭር ነበር። አዎ እንዲያውም አንድ ነገር ትዝ አለኝ። እሱ ተጣፈው የሴትን ልጅ ልብ በአንድ ጊዜ ትኩስ ምጣድ ላይ እንዳረፈ ቅቤ ቅልጥነው የሚያደርገው ይባልለት የነበረ የፍቅር ደብዳቤም እፅፍ ነበር፤ለራሴ ሳይሆን ለሌሎች ጓደኞቼ። እኔማ አይናፋር ነበርኩ። አስታውሳለሁ አንድ ቀን ለጓደኛዬ የፃፍኩለት የፍቅር ደብዳቤ አምጥቶብኝ የነበረው መዘዝ። ደብዳቤው የተፃፈላት ልጅ ልክደብዳቤውን እንዳነበበች፣ እሱን ትታ ለምን እኔኑ ወዳ እርፍ አትልም መሰላችሁ። ጓደኛዬ መቼም ምን ቢማር ቢራቀቅ እንዲህ ያለ ደብዳቤ በህልሙም ሆነ በእውኑ ሊጥፍ እንደማይችል ለካ ልቧ ነግሯት ነበር።ሕይወት’ኮ ቅኔ ነች፤ ወርቁን ሳይሆን ሰሙን ብቻ እየኖርነው ሆኖ እንጂ።
 ቃሉና ቃሉ (አገሩ) እንዲህ በማይላቀቅ የፍቅር ቃልኪዳን ተሳስረው መኖራቸውን ሳስበው ግርም ይለኛል!
ሚክሎል -  ከጽንሱ እስከ ውልደቱ
ሚክሎል የተፀነሰው የሁነቴ አሻራ አካል ሆኖ ነው፣ እኔ ልብ ባልለውም።
መጀመሪያውኑ ከዘሩ ውስጥ ያልነበረ ነገር በኋላ የዛፍ ቅጠል፣ አበባና ፍሬ ሆኖ ሊታይ አይችልም። ቃለሚክሎል ከልቤ ውስጥ ሆኖ ኩኩሉሉ ሲል መሰማት የጀመረው ግን በኋላ ጊዜ የዩንቨርስቲ ተማሪ እያለሁ ተነስቶ የነበረውን የፖለቲካ ነውጥ ካሸተተ በኋላ ነበር።የዛን ጊዜ የዩኒቨርስቲ ተማሪ ትርምስን አባዜ በልቤ ውስጥ፣  የብላቴ ወታደር ማሠልጠኛ ጣቢያ ህይወቱን በፅሁፍ ልቅም እያደረግኩ እዘግብ ነበር - አንድ ቀን ወደ መፅሐፍ እቀይረዋለሁ በሚል ምኞት።ከዚህ ሁሉ በጣም ጠንካራ የሚመስሉኝ ግን እነዚህ ሁለት ምክንያቶች ናቸው። አንደኛው ከእውነት ስሪት ምንነት ጥያቄ ጋር ሁልጊዜ እንደተፋጠጠ የሚኖረው አእምሮዬ ነው። ገና ከልጅነቴ ጀምሮ እውነት እንደቡና ቁርስ ቂጣ ተቆራርሳ ልትኖር አይገባትም ይልየነበረው ልቤ ቂም አግቷል። “አንድ ፈጣሪ ከሆነ ያለው ለምን ብዙ እውነት ይኖራል። ብዙ እምነት ማለት’ኮ ብዙ እውነት ማለት ነው። እውነትማ አንድ ብቻ ትንፋሽ ነው እንጂ መሆን ያለበት። ፖለቲካ እንጂ እውነት እንዴት በጎራ ተከፋፍሎ ያዙኝ ልቀቁኝ እያለ፣በበላይነት ነግሶ ለመውጣት ይፋለማል። እውነትማ ገለልተኛ ገላጋይ ዳኛ እንጂ ጎራ የለየ አዋጊ ሊሆን አይገባውም። እውነት የጥያቄና መልስ አንድነቱን ጨርሶ፣ ሙሉነቱን ያለ የነበረ አንድ ትንፋሽ ካልሆነማ፣ መጀመሪያውኑስ እንዴት ሊፈጥረን ቻለ። የጥያቄና መልስእድሜውን ጨርሶ እንደ አለቀ እውነት ያልተቋጠረ፣ እስቲ የትኛው ትንተና፣ የትኛው ንድፈ-ሃሳብ ነው ወደ ድርጊት ተቀይሮ መፍጠር የቻለ።” ከዚህ ጥያቄጋ ግብግብ የሚገጥም መጽሐፍ የመጻፍ ህልሜ፣ ዘወር በል ብለውም ዘወር የማይል የመንፈሴ አውራጅና ማገር ሆኖይኖር ነበር።እውነቴን አይደለምን’ዴ? እውነት ያልሆነችውን ስንሆን እንከፋፈላለን፣ እርስ-በርስ እንገዳደላለን፣እውነት የሆነችውን ስንሆን ግን አንድ እንሆናለን፣እንፋቀራለን፤
ከራስም ከማህበረሰብም ጋር። ታዲያ መሆን ማለት ሌላ ምን ትርጉም አለው? የእራስን እውነትእንደ አንድ ያለቀ የህልውና ትርጉም ፈልጎ ከማግኘት ውጭ!ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የሚገርም ነው። አንድም ቀን ባነበብኩት መጽሐፍ  እርካታ የማታውቀው ውስጠ ነፍሴ፣ ‘አንተ ልታነብ የምትፈልገውን ዓይነት መጽሐፍ መጻፍ አለብህ’ እያለች ሁልጊዜ ትሞግተኝ ነበር። አሁንም አልረካችም። ‘ሚክሎል፤የመቻል ሚዛን’ መጀመሪያህ፣እንጂ መጨረሻህ አይደለም ትለኛለች፤ እስካሁን።
ሚክሎል እና አንባቢው
ሚክሎል የመቻል ሚዛን በመጀመሪያ ህትመቱ አንባቢዎችን የመድረስ ችግር ነበረበት። የታተመው ቅጂ ብዛት ውስን፣ የስርጭቱ አያያዝ በአግባቡ ያልተደረገ ነበር። ምንም የማስተዋወቅም ሥራ አልተሰራለትም ነበር። እንደምንም ከብዙ ጊዜ በኋላም ቢሆን እጃቸውከገባው አንባቢዎችውስጥ፤ ‘ይሄ ሁልጊዜ ላነበው እፈልገው የነበረ፣ ሁሉን ነገር በአንድ ላይ አሰናድቶ የያዘ፣ መቼም ተሰርቶ የማያውቅ ሥራ ነው’ እያሉ እስካሁን አድናቆትና ከበሬታቸውን የሚገልፁልኝ ብዙ ናቸው። “ይሄ በጣም ከባድ መጽሐፍ ስለሆነ እኔ የምወደው ዓይነትአይደለም” የሚሉም አይብዙ እንጂ አሉ።
 ሚክሎል ላይ ያበቃል --?
ሚክሎል የመቻል ሚዛንን ያሳተምኩት በራሴ ገንዘብ ነበር። ከላይ እንደገለፅኩት፣ ስርጭቱ በጣም ብዙ ችግር ስለነበረበት የወጣውን ወጪ እንኳን መመለስ አልቻለም። ‘የማቃት አንጀት’ አብዛኛው ሥራው አልቆ የነበረ ቢሆንም እንደገና መጽሐፍ ማሳተም፣የሚታሰብ አልነበረም። ምንም እንኳን ምናቤ እጅግ በጣም ከፍ ያለ ቢሆንም በአጠቃላይ በሃገራችን ከነበረው ተጨባጭ እውነታ አንፃር፣ መጽሐፍ ተጽፎ ሊኖር እንደማይቻል ስረዳ፣ ብዕሬ፤”ምነው ገና ብዙ ለመውለድ ዱብ ዱብ ከማለቴ ወደ ኪስህ ከተትከኝ”  ስትለኝ  ሰምቼ፣እንዳልሰማሁ ዘጋኋት፤ ተውኳት። ‘ምናልባት አንድ ቀን ይሆናል..... አሁን ግን አልሆነም’ እያልኩ በልቤ የማቃት አንጀትን ረቂቅ ይዤ፣ ከነቤተሰቤ አገር ለቅቄ ወጣሁ። አሁን አስራ አራት ዓመት አልፎ፣ ከስንት ፍለጋ በኋላ አድነው የያዙኝ አድናቂዎቼ ጩኸት ቀሰቀሰኝ።ጠፍቷል ተብሎ ተስፋ የተቆረጠበት፣ሁለተኛውክፍል ‘የማቃት አንጀት’ ረቂቅም ከጓሮ አሮጌ ዕቃ ማጠራቀሚያ ጋራዥ ውስጥ አቧራ ለብሶ ተገኘ።


Read 6577 times