Saturday, 07 November 2015 09:52

ጠ/ሚ ኃይለማሪያም፣ በ2 ቀናት ዝነኛ የሆኑበት ሚስጥር!

Written by 
Rate this item
(12 votes)

የኢህአዴግ መልዕክቶች፡
• አሁንም ኃያል ነኝ። ከውሳኔዬ ውልፍት የለም (ሚኒስትሮችም ጭምር)።
• መሪውን የጨበጡት፣ ጠ/ሚ ኃይለማሪያም ደሳለኝ እንደሆኑ ተመልከቱ።
• በሺ የሚቆጠሩ የበታች ባለስልጣናት፣ በዘመቻ ተጠራርገው ይባረራሉ።

   በኢቢሲ የተመለከትነው የከፍተኛ ባለስልጣናት ስብሰባ፣ ትልቅ የመነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ሰንብቷል። ካሁን በፊት፣ ብዙ ስብሰባዎችን አይተናል፤ ብዙ ንግግሮችን ሰምተናል። የአሁኑ፣ እንዴት የብዙዎችን ትኩረት ሊስብ ቻለ? ኢህአዴግ፣ ‘የህዝብ የልብ ትርታ’ን ማዳመጥ ስለጀመረ ይሆን?
‘የሕዝብ የልብ ትርታ’ን ማዳመጥ ብቻውን፣ አሪፍ ነው ማለቴ አይደለም። የሕዝብን ስሜት ተከትሎ፣ የታክሲ ስምሪት ቁጥጥር መጀመሩ ወይም የሸቀጦች ዋጋ ተመን ለማወጅ መሞከሩ፤ ምን ትርፍ አስገኘ? የትራንስፖርት እጥረትን ከማባባስና ገበያን ከማቃወስ ያለፈ ውጤት አላመጣም። ዜጎችን ማዳመጥ ብቻ ሳይሆን፣ ሁነኛ መፍትሄ የማበጀት ብልህነትም ያስፈልጋል።
ለነገሩ፣ ኢህአዴግ፣ ብዙ ጊዜ፣ ዜጎችን አያዳምጥም። በሁለት በሦስት ዓመት ጉባኤ ሲያካሂድ፤ ወይም በየመንፈቁ፣ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ሲሰበሰብ፣ በርካታ እቅዶችን ያወጣል፤ ውሳኔዎችን ያስተላልፋል። በቃ፤ ከዚያ በኋላ፣ ከላይ እስከ ታች፣ ውልፍት ማለት የለም። ከዚያ ውጭ የሆኑ ጉዳዮች... (ችግሮችና አቤቱታዎች) ብዙም ሰሚ አያገኙም። በሰሞኑ ስብሰባ ላይ፣ ‘ዜጎች፣ ሰሚ አጥተዋል’ እያሉ የኢህአዴግ መሪዎች ሲናገሩ አልነበር!
በእርግጥ፣ አንዳንዶቹ ችግሮች፣ ያን ያህልም ቁምነገር የሌላቸው ጊዜያዊ ጉዳዮች ሊሆኑ ይችላሉ። በእውነተኛ መረጃ ላይ ያልተመሰረቱ አቤቱታዎችና የተጋነኑ ጩኸቶችም ይኖራሉ። ነገር ግን፣ ለተጨባጭ ችግሮችና አቤቱታዎችም ቢሆኑ፣ ኢህአዴግ ፊት አይሰጥ።
ከራሱ እቅድና ውሳኔ ውጭ የሆኑ ጉዳዮች ሲመጡ፣ “እውነት ናቸው ወይስ አይደሉም? ቁምነገር ይዘዋል ወይስ አልያዙም?” ብሎ ለመመርመርና ለመመዘን፣ ፈቃደኛ አይሆንም። እንዲያውም፣ ‘አፍራሽ’ እና ‘አደናቃፊ’ ብሎ ሊፈርጃቸው ይችላል። ጭራሽ፣ የዜጎችን አቤቱታ መስማት (‘የህዝብን የልብ ትርታ ማዳመጥ’)... እንደ ድክመትና እንደ ጥፋት የሚቆጠርበት ጊዜ አለ። “አድርባይነት” በማለት ይሰይመዋል።
“አብዮታዊ ፓርቲ ነኝ” የሚለው ኢህአዴግ፤ ለውጥ ለማምጣት እታገላለሁ እንጂ፤... ከህዝብ የስሜት ነፋስ ጋር አብሮ ለመንጎድ፤ መስሎ ተመሳስሎ ለማደር፣ በዚህም ተወዳጅነትንና ዝናን ለማትረፍ የምሯሯጥ፣ “አድርባይ”ፓርቲ አይደለሁም” ይላል።    
እና፣ ‘አድርባይ’ ላለመባል፣ ምን ማድረግ ይሻላል? ዜጎችን አለማዳመጥ? ችግሮችን ላለማየት አይንን መጨፈን? አቤቱታዎችን ላለመስማት ጆሮን መድፈን? “ዜጎችን የሚያዳምጥ የመንግስት አካልና ባለስልጣን ጠፍቷል” ተብሎ የለ? (በባለስልጣናቱ ስብሰባ ላይ ማለቴ ነው)።
ተመልካችና ሰሚ ሲጠፋ፤ ተጨባጭ ችግሮች ያለ መፍትሄ እየተባባሱ፣ እውነተኛ አቤቱታዎች ወደ እሮሮ ይቀየራሉ። ያኔ፣ ችግሮች ሲባባሱ ነው፣ እሮሮዎች የሚደመጡት።
ነገር ግን፣ ኢህአዴግ፤ የህዝብን ጩኸት በማዳመጥ ብቻ አይመለስም። ጩኸቱን ይወርሰዋል። “ፍትህ ጠፋ” እያለ ዋና የእሮሮ ባለቤት ይሆናል። “ሙስና አገርን ገደለ”፣ “አገር መቀመቅ ወረደች”፣ “ኢህአዴግ በሰበሰ”... እነዚህ ሁሉ፣ ካሁን በፊት ከኢህአዴግ የሰማናቸው ምሬቶች ናቸው። ሰሞኑን እንደሰማነውም፣ “መሪዎች የሚሰሩትን አያውቁም”፤ “አላግባብ የጥቅም መረብ ዘርግተው አገሪቱን ተብትበዋታል”፤ “ከማውራት ውጭ ለውጥ አላመጣንም”፤ “ለግብር ይውጣ ህዝቡን እየጠራን፣ በአሰልቺ ስብሰባ እንዲርቀን አድርገናል”፤ “ህዝቡ ሰሚ አጥቶ በኢህአዴግ ተስፋ ቆርጧል”...
እንዲህ የኢህአዴግ መሪዎች፣ ኢህአዴግ ላይ የትችትና የወቀሳ ናዳ ሲያወርዱ፤ አገሬው ምን ይበል? የሚጨመር ትችት ከየት ይመጣል?
“አላግባብ የመሞዳሞድና የሙስና መረቦች በዘመቻ መበጣጠስ አለብን”፣ “ጠራርገን በማባረር፣ ህዝቡ ተስፋ እንዲያገኝና በኢህአዴግ ላይ እምነት እንዲያድርበት ዘመቻ ማካሄድ ይኖርብናል”፤...  
ኢህአዴግ ጉባኤ ላይ ወይም በስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ላይ፣ እንዲህ አይነት ውሳኔ ከተላለፈና የዘመቻ እቅድ ከወጣ በኋላስ? ከዚያ በኋላማ... ወደ ቀድሞው “ሴቲንግ” ይመለሳል። በቃ፣ ሌላ ጉዳይ መስማት አይፈልግም።
“ኧረ፣ የኢህአዴግ መሪዎች በኢህአዴግ ላይ ያዘነቡት ውርጅብኝ ተጋኗል” ብሎ አስተያየት የሚሰጥ ሰው ቢመጣ እንኳ፣ ሰሚ አያገኝም። ምናልባትም፣ ‘አፍራሽ’፣ ‘ፅንፈኛ’፣ ‘አደናቃፊ’ ተብሎ ሊፈረጅ ይችላል። ጠራርጎ የማባረር ዘመቻው ላይ፣ ... እንደማንኛውም ፈጣን ዘመቻ፣ ንፁሁን ከነውረኛው፣ ቀናውን ከአጥፊው ጋር መጠረጉ የማይቀር ነው። ነገር ግን፣ ዘመቻውን በመደገፍ የሚያጨበጭብ እንጂ፣ ቅሬታ የሚያቀርብ ሰው ቦታ አይኖረውም።
በእርግጥ፣ ነውረኛውና አጥፊው፣ እሪታውን መልቀቁ አይቀርም። ግን፣ ንፁሁና ቀናው ሰራተኛም፣ አላግባብ ተባረርኩ ብሎ አቤቱታ ቢያቀርብ፣ ማንም አይሰማውም። የክልል የቢሮ ሃላፊ ወይም የወረዳ አስተዳዳሪ ይቅርና፣ ሚኒስትሮችና አንጋፋ የኢህአዴግ መሪዎችም፣ ዘመቻውን ለመተቸት ቢሞክሩ፣ ለውጥ አያመጡም። እንዲያውም፣ መረር ያለ ምላሽ ይመጣባቸዋል። ይህም ብቻ አይደለም። በቪዲዮ ተቀርፆ በቲቪ ይሰራጫል፤... ሰሞኑን በኢቲቪ እንዳየነው አይነት ማለት ነው። አለምክንያት አይመስለኝም። መልእክት ለማስተላለፍ ነው። ዘመቻው ላይ ቅሬታ ለመሰንዘር ለሚሞክሩ ሰዎች፣ ማስጠንቀቂ ነው።
ከስልጣን የሚባረር የቢሮ ሃላፊ ወይም የወረዳ አስተዳዳሪ ይቅርና፣ ሚኒስትሮችና አንጋፋ መሪዎችንም ቢሆን እንደማልምር ተመልከቱ። በቃ፤ ውሳኔ ከተላለፈና እቅድ ከወጣ በኋላ፤ ወዲህ ወዲያ ውልፍት ማለት የለም - ከታች እስከ ላይ፣ አንድ አይነት ቃል ነው የሚነገረው።  እናም፣ አንደኛው ሚኒስትር ወይም ሌላኛው አንጋፋ መሪ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከባድ ተግሳፅ ሲሰነዝሩ በቲቪ ስንመለከት፤ ኢህአዴግ ለበታች ባለስልጣናት፣ ለካድሬዎችና ለአባላት እንዲሁም ለሌላውም ዜጋ፣ ማስጠንቀቂያ እያስተላለፈ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል።
ተግሳፅ የደረሰባቸው ሚኒስትሮችና መሪዎች፣ ተግሳፁን እንዴት ያስተናግዱታል? በአብዛኛው፣ በፀጋ ከመቀበል እንደ መስዋዕትነት ከመቁጠር ውጭ አማራጭ ያላቸው አይመስለኝም - “ለፓርቲዬ የምከፍለው መስዋዕትነት ነው” ሊሉም ይችላሉ። እንዲያውም፣ በኢህአዴግ መሪዎች ዘንድ በጣም የተለመደ አባባል አለ። “ፓርቲው... በሚኒስትርነት አልያም በጥበቃ ሰራተኝነት እንድሰራ ቢመድበኝ፤ ያለ ማንገራገር እሰራለሁ” ... በማለት በተደጋጋሚ ሲናገሩ ሰምተን የለ? ለፓርቲያቸው የሚያበረክቱት መስዋዕትነት ነው።
ለነገሩ፣ አይገርምም። ቢያንስ በሃሳብ ደረጃ፣ መስዋዕትነትን እንደ ቅዱስ ምግባር የማይቆጥር ኢትዮጵያዊ በጣም ጥቂት ነው። መስዋዕትነት፣ የአምልኮ ያህል በሚከበርበት አገርና ባህል ውስጥ ነው ያለነው። ለማንኛውም፣... ለአዲሱ ዘመቻ እስከጠቀመና፣ የፓርቲውን መልእክት ለማስተላለፍ እስካገለገለ ድረስ፣... በቲቪ የሚተላለፍ ስብሰባ ላይ፣ አንዱ ከፍተኛ ባለስልጣንና መሪ፣ ከባድ ተግሳፅ ቢሰነዘርበት... የመስዋዕት ተረኛ ሆኗል ማለት ነው። ያኔ፣ ከላይ እስከ ታች፣ የፓርቲ መሪና ሚኒስትር፣ የክልል ባለስልጣንና ካድሬ፣ የቀበሌ አስተዳዳሪና ተራ አባል ሁሉ፣ “መስመሩን ይይዛል፤ ሰልፉን ያሳምራል”። ይሄም አይገርምም።
“ሰልፍን ማሳመር”፣ በአገራችን ጎልቶ የሚታይ ጥንታዊ ባህል ነው። ቅንጣት የሚያፈነግጥ ሃሳብ፣ እንዳይኖር እንፈልጋለን። ለምሳሌ፣ በሃይማኖት ዙሪያ፣ “ከተለመደው ነባር ሃሳብ” ውጭ፣ ምንም አዲስ ነገር ከመጣ፣ ብዙዎችን ያስቆጣል። አንዱ ሌላውን ለማጥፋት፣ ዘመቻ ይከፈታል።
በፖለቲካም ተመሳሳይ ነው። “እኔ የምደግፈው ፓርቲ ላይ፣ አንዳች ትችት ትንፍሽ እንዳትል። አንተ የምትደግፈው ፓርቲ ላይ፣ የእውነትም ይሁን የሃሰት ውንጀላ ሳዥጎደጉድበትም፣ አፍህን ያዝ”... የሚል ስሜት የገነነበት ባህል አለብን። ሁሉንም፣ በመስመር ማሰለፍ ያምረናል። ሌላውም እንዲሁ፣ በራሱ መስመር ውስጥ ካላስገባሁ ሞቼ እገኛለሁ ይላል። እናም፣ ከመጠፋፋት ውጭ ሌላ መፍትሄ አይታየንም።
በእርግጥም፣ ለጭፍን እምነት ሳይሆን ለሳይንስ፣ ለጭፍን ስሜት ሳይሆን ለእውነታ፣ ለጭፍን ጉልበትና ለቡድን ሳይሆን፣ ለማስረጃና ለአእምሮ ዋጋ የሚሰጥ ስልጡን ባህል ብናዳብር ኖሮ፤ ችግር አይኖርም ነበር። ነፃነትንና ለእውነታ በፅናት የመቆም ስነምግባርን፤ መከራከርንና መከባበርን ያዋሃደ መፍትሄ እናገኝ ነበር። ያንን ስልጡን ባህል እስካላዳበርን ድረስ ግን፤ ብዙም አማራጭ አይኖረንም።
በየፊናው አዛዥ ናዛዥ ለመሆን የሚፈልጉ ሰዎችና ቡድኖች፣ ገናና ለመሆን ሲሻኮቱና ሲጋጩ፣ አገሬው በስርዓት አልበኝነት ይታመሳል። ወይም ደግሞ፣ ከፋም ለማም፣ አንዱ ሰው፣ አንዱ ቡድን፣ አንዱ ውሳኔና እቅድ፣ ሌሎችን ሁሉ አንበርክኮ ገናና ይሆንና፣ ከላይ እስከ ታች፣ ከጫፍ እስከ ጫፍ፣ “ስርዓት” ይሰፍናል። “የፓርቲ መመሪያ ከላይ ወደ ታች የማውረድ አሰራር”፣ “የማዕከላዊነት አሰራር” ብለው ይጠሩታል። ከማዕከል፣ አንዳች ውሳኔና እቅድ ሲወጣ፣ በዙሪያው የተዘረጋ ቅርንጫፍ በሙሉ፣ አቅጣጫውን ያስተካክላል።
ታዲያ፣ “መስመር የሚያስይዝ የማዕከላዊነት አሰራር”፣ ለውሳኔና ለእቅድ ብቻ አይደለም። መሪነትንም ይጨምራል። ጭፍን እምነትና ስሜት በበዛበት የኋላቀርነት ባህል ውስጥ፣... ያው፣... በርካታ ፊታውራሪዎችና አበጋዞች፣ ቡድኖችና ድርጅቶች፣ በየፊናቸው ገናና ለመሆን ሲሻኮቱና ሲጋጩ፣ አገር ይቀወጣል። ጥንታዊው የጎሳ አስተዳደር፣ ከእንዲህ አይነት መቋጫ የሌለው የግጭት ስርዓት አልበኝነት ያልተላቀቀ አስተዳደር ነው።
ኢትዮጵያ፣ ለሺ ዓመታት፣ በየጣልቃው ወደ ስርዓት አልበኝነት ብትንሸራተትም፣ በተወሰነ ደረጃ አገራዊ ስርዓት እስከመመስረት የደረሰ፣ ትልቅ የስልጣኔ ታሪክ የተሰራባት አገርም ናት። እናም፣ አብዛኛው ሰው፣ በርካታ አበጋዞችና ቡድኖች የሚሻኮቱበት ስርዓት አልበኝነትን አይፈልግም። እና ምን ይሻላል?
ሁለት አማራጮች አሉ። በአንድ በኩል፣ የትኛውም አበጋዝና ቡድን፣ አዛዥ ናዛዥ የማይሆንበት፣ ገናና እንዲሆንም የማይፈቀድበት፣ የእያንዳንዱ ሰው የሃሳብ ነፃነትና የምርት ባለቤትነት መብት የሚከበርበት፤ እያንዳንዱ የመንግስት ባለስልጣን በሕግ የተገደበ ሃላፊነትን ብቻ የሚያገኝበት ስልጡን ስርዓት መፍጠር ይቻላል - የሕግ የበላይነት የሰፈነበት የነፃነት ስርዓት ልንለው እንችላለን።
ለምሳሌ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን፣ እንዲሁም የሌሎች ሚኒስትሮች ሃላፊነት፣ ምን እንደሆነ ለማወቅ፣ የግድ የሚስጥር ተካፋይ የውስጥ አዋቂ መሆን አያስፈልግም። የሕገመንግስት አንቀፆችን ማንበብና መገንዘብ በቂ ይሆናል። ከዚያ ውጭ ውልፍት ማለት፣ አይቻልማ - የህግ የበላይነት በሰፈነበት ስልጡን ስርዓት። ይሄ አንዱ አማራጭ ነው። ነገር ግን፣ ለአእምሮና ለሳይንስ ክብር የሚሰጥ ስልጡን ባህል ካልዳበረ፣ የሕግ የበላይነት ስርዓትን መፍጠር አይቻልም።
ሌላኛው አማራጭ? ብዙ አበጋዞችና ቡድኖች፣ በየፊናቸው ገናና ለመሆን እየተጋጩ አገር በስርዓት አልበኝነት ጨለማ ከምትታመስ፣... አንዱ መሪ፣ ገናና ሆኖ ቢወጣ ይሻላል። ግን፣ ወደ ግጭት የሚያመራ ሽኩቻ እንደጠፋና አንድ መሪ ገናና ሆኖ እንደወጣ፣ እንዴት ማረጋገጥ ይቻላል? ውስጥ ለውስጥ እየተሻኮቱ ሊሆን ይችላል። “ሕገመንግስት ላይኮ፣ የእያንዳንዳቸው የሥልጣን ልክ በዝርዝር ተፅፏል” ብንል ዋጋ የለውም። በሕገመንግስት አንቀፆች ላይ መተማመን የሚቻለው፣ ስልጡን ባህልና የሕግ የበላይነት ሲስፋፋ ነው።
ካልተስፋፋስ? ያው፣ ስርዓት አልበኝነትን በመጥላት ብቻ፤... አንድ መሪ፣ ከሌሎች ሁሉ ጎልቶ እንዲወጣ እንጠብቃለን። አለበለዚያ፣ ነገሮች ሁሉ ‘አይጥሙንም’። እናም፣ ገናናነትን የሚጠቁም አጋጣሚንና ንግግርን የማየት ፍላጎት ያድርብናል። አለበለዚያ፣ በመሪነት የተቀመጠውን ሰው፣ እንደ ደካማ እንቆጥረዋለን። ለዚህም ይመስለኛል፤ ባለፉት አመታት ጠ/ሚ ኃይለማሪያም ደሳለኝ፣ አብዛኛውን ጊዜ፣ ከአነጋገራቸው ቁጥብ እና ሰከን ያሉ በመሆናቸው፣ በብዙዎች ዘንድ እንደ ደካማ የተቆጠሩት። የሚናገሩትን ሃሳብ በማገናዘብና በመመዘን፣ ጥንካሬንና ድክመትን ከመለካት ይልቅ፣ ቁጥብነትን እንደድክመት የሚቆጥር ባህል ውስጥ መሆናችን ያሳዝናል።
ከሦስት የስልጣን ዓመታት በኋላ፣ ሰሞኑን፣ ቆጣ እና ረገጥ ያለ ንግግራቸውን በቲቪ ስንመለከትስ? ወዲያውኑ ነው፣  የጠንካራ መሪ ዝና ያገኙት። በቲቪ የተሰራጨው ስብሰባ፣ የጠ/ሚ ኃይለማሪያምን ስልጣን በጉልህ የሚያሳይ መልእክት የያዘ ነው የምለውም በዚህ ምክንያት ነው።    

Read 10114 times