Saturday, 14 November 2015 09:59

ብሔራዊ ቴአትር - በ60ኛ ዓመቱ ዋዜማ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  በቀዳማዊ ንጉሰ ነገስት ኃይለሥላሴ ዘመን ተሰርቶ አገልግሎት መስጠት የጀመረው አንጋፋው ብሔራዊ ቴአትር ቤት፣ የተመሰረተበትን 60ኛ ዓመት ክብረ በዓል ለማክበር ዱብ ዱብ እያለ ነው፡፡ በእርግጥ በ60 ዓመት ጉዞው ቴአትር ቤቱ ብቻውን አይደለም አንጋፋ የሆነው፡፡ በርካቶችን በጥበብ አንግሷል፡፡ ቴአትር ቤቱን በለጋ ዕድሜያቸው የተቀላቀሉ በርካታ ታዳጊዎችን፤ በጥበብ አሽቶና ሞርዶ፣ ለአንጋፋነትም  አብቅቷቸዋል፡፡  የክብር ካባ አጥልቆላቸዋል፡፡ የዝና መጎናጸፊያ ደርቦላቸዋል፡፡ አብዛኞቹ ቀደምት ተቀጣሪዎች ታዲያ ለብሔራዊ ቴአትር ያላቸው ጥልቅ ፍቅር ወደር የለሽ ነው፡፡ ፍቅር ብቻ ግን አይደለም፤ጥልቅ አክብሮትም ጭምር እንጂ፡፡ አስገራሚው ነገር፣ብዙዎቹ አርቲስቶች በቴአትር ቤቱ በትንሹ ለ30 ዓመታት ቢያገለግሉም  በገቢ ረገድ ጠብ ያለላቸው ነገር የለም፡፡ በ100 ብር ደሞዝ ተቀጥረው፣ከ30 ዓመት አገልግሎት በኋላ - 200 ብር ባልሞላች ገንዘብ ጡረታ የወጡ አሉ፡፡ ማንም ግን ብሔራዊ ቴአትርን ሲወቅስ አይሰማም፡፡ ምሬት የሚባል የለም፡፡ ፍቅር ብቻ፡፡ መወድስ ብቻ፡፡ አድናቆት ብቻ፡፡ አክብሮት ብቻ፡፡ ጥልቅ ስሜት ብቻ፡፡ ጥበባዊ መንፈስ ብቻ፡፡ ብሔራዊ ቴአትርና አርቲስቶቹ በአስማት ክር የተሰፉ ይመስላሉ፡፡ ተዓምር ነው፡፡ሰሞኑን ደግሞ ሁሉንም አርቲስቶች በቴአትር ቤቱ ውስጥ እንዲመሽጉ ያደረጋቸው አንድ ትልቅ ጉዳይ ተፈጥሯል፡፡ ብሔራዊ ቴአትር የተመሰረተበት የ60ኛ ዓመት ክብረ በዓል፡፡ እነሱም ታዲያ ልደቱን ሊያደምቁለት የጥበብ ልምምድ ላይ ናቸው፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ማህሌት ኪዳነወልድ፤የቴአትር ቤቱን  በዓል ምክንያት በማድረግ፣በብሔራዊ ቴአትር ከ30 እስከ 40 ዓመት ያገለገሉ 5 አንጋፋ አርቲስቶችን በአጭር በአጭሩ አነጋግራለች፡፡

አርቲስት አልማዝ ኃይሌ
ብሔራዊ ቴአትር መቼ ነው  የተቀጠርሽው?
የተቀጠርኩት በ1958 ዓ.ም ነው፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ጡረታ እስክወጣ ድረስ ወደ 40 ዓመታት ገደማ በብሔራዊ ቴአትር ሰርቻለሁ፡፡
ደመወዝሽ ስንት ነበር?
(ሳ….ቅ….) ስቀጠር 100 ብር ነበር፤ሲቆራረጥ 96 ብር ከ25 ሳንቲም ይደርሰኛል፡፡ ያው ጡረታ ስወጣ ግን --- 200 ብር እንኳን አልደረሰም ነበር፡፡
ብሔራዊ ቴአትርን እንዴት         ትገልጭዋለሽ?
ለኔ ትልቅ ዩኒቨርሲቲዬ ነው ዩኒቨርሲቲ እንኳን 40 ዓመት አያስተምርም፡፡ በ20 ዓመቴ ገብቼ፣ በ55 ዓመቴ ስወጣ፣ ትልቅ ልጅ ሆኜ ነው የወጣሁት፡፡ አሁንም ለበዓሉ የተለያዩ ዝግጅቶችን ለማቅረብ ልምምድ ላይ ነኝ፡፡
እስቲ የማይረሳ ገጠመኝሽን ንገሪኝ ...
ለንጉሡለጃንሆይ፣ትርኢት እያሳየን ሳለ ውስጥ ልብሴ ወደ ታች ወርዶ፣ መድረክ ላይ ስወጣ፣ ጓደኞቼ፤“አልምዬ ውስጥ ልብስሽ … ውስጥ ልብስሽ…” ያሉኝን ፈጽሞ አልረሳውም፡፡

**********
አርቲስት ወይንሸት በላቸው
ብሔራዊ ቴአትር የገባሽው መቼ ነው?
በ1959 ዓ.ም ነው፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ጡረታ እስከወጣሁበት 1992 ድረስ ለ33 ዓመታት በቴአትር ቤቱ
አገልግያለሁ፡፡አሁንም ለ60ኛ ዓመት በዓሉ ልምምድ ላይ ነኝ፡፡
ደሞዝሽ ስንት ነበር …
ስትቀጠሪ?
ስቀጠርማ … በ100 ብር ነው … ብቻ
ጡረታዬ ላይ 500 ደርሻለሁ፡፡
ብሔራዊ ቴአትር ለአንቺ ምን ትርጉም አለው?
በደስታ መስራቴና የቤቱ ፍቅር ትዝታዬ ነው፡፡ እንደ ቤቴ ነው
የማየው፡፡ ሁለተኛ ቤቴ በይው፡፡ እኔ’ንጃ ምን
ልበልሽ… ፍቅሩ በጣም ይጎዳል፡፡ ደም ስር ውስጥ ስለሚገባ ከውስጥ
አይወጣም፡፡ የማይረሳሽ ገጠመኝ…
ውይ ብዙ አሉ፤ ግን አላስታውስም፡፡

****************************
አርቲስት መራዊ ስጦት
ለስንት ዓመት ነው በብሔራዊ ቴያትር ያገለገልከው?
ከ1974 ዓ.ም ጀምሮ ለ43 ዓመታት አገልግያለሁ፡፡
27ቱን ዓመት በኦርኬስትራ ኃላፊነት ነው የሰራሁት፡፡
መጀመርያ ስትቀጠር ደሞዝህ ስንት ነበር?
እኔ በ120 ብር ነው የተቀጠርኩት ያው ግን ---- ምን ታረጊበታለሽ በ8 ብር የጣሊያን ጫማ ገዝተሸ ታደርጊያለሽ፡፡ እኔ ጡረታ ስወጣ 700 ብር ደርሼ ነበር፡፡ አሁን በኔ የኃላፊነት ቦታ ላይ የሚሰራው የ6ሺ እና የ7ሺ ብር ደሞዝተኛ ነው፡፡ ጊዜው ተቀይሯል፤ መስዋእትነቱን የከፈልነው እኛ ነን፡፡ በእርግጥ ደሞዙ በማደጉ ከሁሉም በላይ ደስተኞቹ እኛ ነን፡፡ ዛሬ ዘፋኞች በሚሊዮኖች ብር የሚደራደሩበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡
ብሔራዊ ቴአትር ለአንተ ምንህ ነው ?
ብሔራዊ ቴአትር ለኔ የጥበብ መቅደሴ ነው፡፡ ከጡረታ በኋላ እንኳን ጠዋት 2፡30 ላይ ብሔራዊ ቴያትር፣ማታ ደግሞ ማርያም አታጭኝም፡፡ ብሔራዊ ቴአትር ቤትን በጣም እወደዋለሁ፡፡ በጣም አከብረዋለሁ፡፡ መጥፎ ነገር ሳይ እበሳጫለሁ፤ጥሩ ሳይ ደስ ይለኛል፡፡ ከሁሉ በላይ ግን ቲያትር ቤቱ እንደ ናይጄሪያና ሌሎች አገራት ከ4ሺህ -5ሺህ ተመልካች የሚይዝ አዳራሽ ሰርቶ ማየትን እመኛለሁ፡፡
እስቲ በሙያህ ያለህን ትውስታ ንገረኝ?
እንግዲህ ከነበርነው 13 የኦርኬስትራ አባላት የቀረነው 5 ነን፤ አሁን 80 ዓመቴን ይዣለሁ፡፡ በሙያዬ ዓለምን ዞሬያለሁ፡፡ ብዙ ትውስታዎች አሉኝ፡፡ ከሁሉም በላይ የስራ ፍቅር ነበረኝ፤ የሰራሁት ስራ ካልተወደደ እራቴን አልበላም ነበር፡፡


*******************
አርቲስት ጌታቸው ደባልቄ

በብሔራዊ ቴያትር ለምን ያህል ጊዜ
አገለገልክ?
ከተመሰረተ ጀምሮ ጡረታ እስከወጣሁበት ጊዜ ድረስ ለ40 ዓመታት ያህል አገልግያለሁ፡፡
የደሞዝ ጉዳይ እንዴት ነበር …
መጀመሪያ ስትቀጠር?
ያው ስቀጠር በ120 ብር ነበር፤ በኋላ636 ብር ደርሼ ነው ጡረታ የወጣሁት
ብሔራዊ ቴአትርን እንዴት ትገልፀዋለህ?
እድገት ላይ ያለ ቴአትር ቤት ነው፡፡ ሌላ እድገት እንጠብቃለን፤ ሌላ ብሔራዊ
ቲያትር እንደሚሰራ ሰምተናል፡፡ እደግ ተመንደግ ነው የምለው፡፡ በኪነጥበቡ
ብዙ እድገት አይተናል፤ ማንበብ የማይችሉትን ቲያትር አስጠንተናል፤
አሁን ደግሞ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ሲሰጥ እያየን ነው፡፡
ተመስገን ነው እንግዲህ፡፡
ከመድረክ ገጠመኝ የማይረሳህ …
ከቴያትር ቤት ተወስጄ እስር ቤት
ገብቻለሁ፡፡ መድረክ ላይ ነስሮኝ፣ ነስሩ
አልቆምም ብሎ ፕሮግራም ተቋርጧል፡፡
ኧረ ብዙ ነው… ብዙ ብ….ዙ!!


*****************************

አርቲስት ሰለሞን ተካ


መቼ ነው ብሔራዊ የተቀጠርከው ?
በ1970 ነው፤ አሁንም ድረስ እየሰራሁ ነው፡፡
በስንት ብር ደሞዝ ሥራ ጀመርክ?
(ሳ…ቅ…) እንዴ --- ያኔ 100 ብር የኪስ ገንዘብ ብቻ ነበር የሚሰጠን፡፡ አሁን 2900 ብር ደርሻለሁ፡፡
ብሔራዊ ቴአትር ለአንተ ምንህ ነው?
ውይ… እኔ እንጃ፤ በቃ መንፈስ ነው ስሜት እንዴት ይገለፃል? መንፈስን ምን ብለሽ
ትገልጪዋለሽ? ለኔ ከቃል በላይ ነው፡፡
ውስጥን የማያርስ ደስታን ምን ልበልሽ?
በአፍሪካ የመጀመሪያው ቴአትር ቤት ነው፡፡ ህልሜ፤ብሔራዊ ቲአትር፣በዓለም ላይ አሉ ከተባሉ ቲያትር ቤቶች ጎን ተሰልፎ
ማየት ነው፡፡ የማይረሳህ የመድረክ ገጠመኝህ?
ሥራ እንደጀመርኩ አካባቢ፣ ያው ወጣትነትም አለ… እጩ ተዋንያን ተብዬ ተመረጥኩ፡፡ እኔ ቲያትርን ስፈልግ
ስፈልግ የምሰራው ነበር የመሰለኝ፤ በኋላም “ፍልሚያ” የሚባል ቲያትር ላይ አሽከር ሆኜ ተመረጥኩ፡፡ እኔ ሆዬ
ቤቴ ተኝቼ መጣሁና፣ ትርኢቱን ቁጭ ብዬ ማየት ጀመርኩ፡፡ በኋላ አዘጋጁ አቶተክሌ፤ “ምን ትሰራለህ እዚህ?” ሲለኝ
“መስራት ነበረብኝ እንዴ?” ብዬው፤ ደሞዝ የተቀጣሁትን አልረሳውም፡፡

Read 2976 times