Saturday, 21 November 2015 14:05

“ላምባን ባልሰራ በጣም ይቆጨኝ ነበር”

Written by 
Rate this item
(3 votes)

  ዝነኛው የፊልም ተዋናይ ግሩም ኤርምያስ፤ሰሞኑን በተጠናቀቀው 10ኛው ኢትዮ ኢንተርናሽናል የፊልም

ፌስቲቫል፣በ“ላምባ” ፊልም በምርጥ መሪ ተዋናይነት ተሸልሟል፡፡ አዲሱ ዓመት ከጠባ አርቲስቱ በዚህ ፊልም በመሪ ተዋናይነት ሽልማት ሲያሸንፍ የሰሞኑ ለሦስተኛ ጊዜ መሆኑ ነው፡፡ ግሩም በ5ኛው ኢትዮ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል በ“ትዝታህ” ፊልም፣ በ8ኛው ደግሞ በ“አራት መቶ ፍቅር” ፊልም በምርጥ መሪ ተዋናይነት መሸለሙ ይታወሳል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤አርቲስት ግሩም ኤርሚያስን ተወዳጅነትን ባተረፈው የ“ላምባ; ፊልም ትወናው፣ ባሸነፋቸው ሽልማቶችና በኩላሊት እጥበት ማዕከል አምባሳደርነቱ ዙሪያ አነጋግራዋለች፡፡       ዘንድሮ ብቻ ሦስት ሽልማቶችን አሸንፎበታል

      በ“ላምባ“ ፊልም ሽልማቶችን እየሰበሰብክ ነው -----
እውነት ነው፤እስካሁን በፊልሙ ሦስት ሽልማቶችን ወስጃለሁ፡፡ አንዱ፣ በሸገር ኤፍ ኤም 102.1 የለዛ አድማጮች ምርጫ ላይ፣ በመሪ ተዋናይነት የተሸለምኩት ነው፡፡ ሌላው በዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም በዲጄ ቤቢ የአድማጮች ምርጫ ላይም፣ “ላምባ” በምርጥ ፊልም ዘርፍ ሲያሸንፍ፣ እኔ በምርጥ መሪ ተዋናይነት አሸንፌያለሁ፡፡ ሦስተኛውን ባለፈው ሰኞ ምሽት በተደረገው የኢትዮ ኢንተርናሽናል ፊልም ፌስቲቫል መዝጊያ ላይ በምርጥ መሪ ተዋናይነት አሸንፌያለሁ፡፡ ይሄ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም አድናቂዎቼ፣ ለቤተሰቦቼና ለሙያ አጋሮቼ በጣም የሚያስደስት ነው፡፡ ፊልሙ በተከታታይ አሸናፊ ለመሆን የቻለበት ምሥጢር ምንድን ነው? በጣም የሚያሳዝን በመሆኑና የወቅቱን ችግር በማንሳቱ ነው? ወይስ አጠቃላይ የፊልም አላባዊያን የሚባሉትን ያሟላ በመሆኑም ነው?ፊልሙ በሁሉም መልኩ ማኅበረሰቡ ላይ የፈጠረው ትልቅ ነገር አለ፡፡ አንደኛ የወቅቱን አንገብጋቢ ችግር የኩላሊትን ጉዳይ አንስቶ በብዙዎች ዘንድ ግንዛቤን ፈጥሯል፡፡ ፊልሙ ከፊልምም ፈቀቅ ብሎ አንዳንድ ለውጦችንም አምጥቷል፡፡ ለውጥ ስንል አንዱ ቀደም ብዬ የነገርኩሽ የግንዛቤ ጉዳይ ነው፡፡ ግንዛቤው ደግሞ ከእኔው ከራሴ ይጀምራል፡፡ ለምሳሌ
እኔ ስለ ኩላሊት ህመም የነበረኝ ግንዛቤ አሁን ካለኝ ጋር ሳነፃፅረው ምንም ነበር፡፡ ስለ ኩላሊት ሲወራ ‹ውሃ ጠጣበት፤ ውሃ ጠጪበት፣› ከማለት የዘለለ እውቀት አልነበረኝም፡፡ በተመሳሳይ ሌላውም ኅብረተሰብ የችግሩን አስከፊነት በደንብ የተገነዘበ ይመስለኛል፡፡ የዚህ ማሳያ ደግሞ ኅብረተሰቡ ለዚህ ጥሪ የሰጠው ምላሽ ነው፡፡ ለኩላሊት እጥበት ማዕከሉ በኤስኤምኤስና በሌሎች መንገዶች ምላሹን እየሰጠ ነው፡፡
ሌላ ባነሳው ሃሳብ፣ በዳይሬክቲንጉ፣ በአጠቃላይ ሥራው ---- አንድ ፊልም ሊያሟላቸው የሚገባውን ነገሮች ሁሉ
በብቃት የያዘ በመሆኑ፣ በችግሩ ዙሪያ ማንሳት የሚገባንን እንድናነሳ አስችሎናል፡፡ መቼም በዓለም ላይ መቶ በመቶ ትክክል የሆነ ነገር አይኖርም፡፡ ምንም ነገር ሲሠራ ጥቃቅን ስህተቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ሆኖም፣ “ላምባ; ባነሳው ሃሳብም በቴክኒኩም በኩል ሁሉን ያሟላ በመሆኑ ሽልማቶችን እየወሰደ ነው፡፡ ሰኞ ምሽትም አራት አዋርዶችን ሲወስድ
ተመልክተሻል፡፡ ይህን የምነግርሽ ከሙያ አኳያ ነው፡፡ ፊልሙን ዝም ብለሽ ስትመለከቺ ከጽሑፍና ከዳይሬክቲንግ ባለፈ የፊልሙ ባለሙያዎች ሁሉም ምን ያህል እንደጣሩበትና እንደለፉበት ትመለከቻለሽ፡፡ ላይት የሠሩት፣ ሜካፑን የሠሩት፣ ሲኒማቶግራፊውም አለ፡፡ ይህን ሁሉ ሲሠሩ ታዲያ ከታሪኩ ፍሰት ጋር ተዋኅዶ እንዲሄድ አመጣጥነውታል፡፡ አየሽ እነዚህ ሥራዎች ጥሩ ሲሆኑ ታሪኩን ያግዙታል፣ያጐለብቱታል፡፡ በዚህ ምክንያት ተዋንያኑ እያንዳንዱ ስሜት ገብቷቸው፣ በደንብ ወደውት ስለሠሩት ፊልሙ ተወዳጅ ሆኗል፡፡ ለረጅም ጊዜ ነበር ስንለማመድና ስናሸው የነበረው፤ ከትዕይንት ትዕይንት በደንብ አድርገን ነው የሠራነው፡፡ ለምን ብትይ ---- ከባድ ሃሳብ ነው፣ ከባድ ስሜትም ይጠይቃል፡፡ በአጠቃላይ የሁላችንም አስተዋጽኦ በደንብ የታየበት ነው፡፡ በዚህም የታለመለትን ግብ መትቷል፡፡ ብዙ ጊዜ ግሩም ሥራ ስለመጣለት ብቻ አይቀበልም፤ሥራ ይመርጣል፣ ይባላል፡፡ ይህን ፊልም ባትሠራ ይቆጭህ ነበር?
በእርግጠኝነት ይህንን ፊልም ባልሠራ ከሚቆጩኝ ፊልሞች አንዱ ይሆን ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ ከምሠራበት ዋጋም በጣም ቀንሼ የሠራሁት፣ ሃሳቡን --- የፊልሙን ዓላማ ስለወደድኩት ነው፡፡ ይህን ፕሮዲዩሰሮቹም ሊነግሩሽ ይችላሉ፡፡ እውነት ለመናገር በነፃም ብሠራው ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ነገር ግን የእኔ ህይወት ሙሉ ለሙሉ የተመሠረተው በፊልም ላይ ነው፤ሌላ ምንም ሥራ አልሠራም፤ የሕይወት ጉዳይ ሆኖ እንጂ በነፃ ብሠራው ብዬ ነበር፡፡ ያም ሆኖ ባልሠራው ግን እጅግ በጣም ይቆጨኝ ነበር፡፡ በጣም ወድጄው ነው የሠራሁት፡፡
በፊልሙ ታሪክ እህትህ የምትሞትበት ትዕይንት ላይ ራስህን መቆጣጠር እንዳቃተህ ሰምቻለሁ፡፡ እስኪ የነበረውን ስሜት ንገረኝ ----
እንግዲህ የዚህ ፊልም የመጨረሻው ትዕይንት ለብዙ ጊዜ የታመምኩበት ነው ማለት እችላለሁ፡፡ ትዕይንቱ ከመቀረፁ በፊትም ሆነ ከተቀረፀ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ ታምሜ ነበር፤ልክም አልነበርኩም፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ከመጀመሪያው አንስቶ ተዋናይ ሊዲያ ሞገስ ታናሽ እህቴ፣ የእውነት እህቴ ነበር የምትመስለኝ፤ በጣም ጥሩ፣ ትሁት ልጅ ናት፤
ወደፊትም ተስፋ የሚጣልባት ናት፡፡ ስንሠራ እንደ ታላቅ ወንድምና እንደ ታናሽ እህት ነበር የተያየነው፡፡ ከሥራው በፊት ያንን ስሜት የሚፈጥረውን መቀራረብ ነበር ያዳበርነው፡፡ ይህ ቅርርብ ከፊልሙም ውጭ ነበር፡፡ እንደ ታላቅና እንደ ታናሽ ነበር የምናወራው፡፡ ከቀረፃው በፊት በማንኛውም ጊዜ ለታላቅ ወንድም የሚጠየቀውን ትጠይቀኛለች፡፡ ይህ ነገር ከፊልሙም ባሻገር ሆነና ያቺ የመጨረሻ ትዕይንት (እሷ የምትሞትባት) ስትሠራ የእውነት እንዳጣኋት ነበር የተሰማኝ፡፡ ከመቀረፁ በፊት ራሱ ስሜቴን መቆጣጠር አቅቶኝ ሰውነቴ ይንቀጠቀጥ ነበር፡፡ በጣም ከባድ ጊዜና ከባድ ትዕይንት ነበር፡፡ እስከዛሬ ብዙ ከባድ ከባድ ትዕይንቶች ገጥመውኛል፤ እንደዚህ ግን አልከበደኝም፡፡ ያም ሆኖ የተወጣሁት ይመስለኛል፡፡
ፊልሙን ከምትሠራበት ዋጋ በጣም ቀንሰህ እንደሠራህ ነግረኸኛል፡፡ ስንት ተከፈለህ?
ይሄ ብዙ ቁምነገር የለውም፤ዋናው ነገር ሃሳቡና የሃሳቡ መሳካት ነው፡፡ በቃ ሌላ ጊዜ ከምጠይቀው በጣም መቀነሴንና አስተዋጽኦ ማድረጌን ከነገርኩሽ ይበቃል፡፡
የኩላሊት ዕጥበት ማዕከሉ አምባሳደር እንደመሆንህ በአሁኑ ሰዓት ምን አይነት እንቅስቃሴዎችን እያደረግህ ነው? ሰሞኑን በማዕከሉ ላይ ስለሚባለውስ ምን አስተያየት አለህ?
እኔ በማዕከሉ ትልቁ ድርሻዬ፣ ያለኝን እውቅና በመጠቀም ሕዝቡን ከማዕከሉ ጋር ማገናኘት ነው፡፡ ሰሞኑን በሚወራው ጉዳይ ላይ ማኅበሩ የራሱ የቦርድ አባላትና አመራሮች አሉት፤ በዝርዝር ጉዳዩን የሚያውቁት እነሱ ናቸው፡፡ ምንም እንዲህ ነው የምልሽ ነገር የለም፡፡
እንደው የገንዘብ ምዝበራ ምናምን የሚለውን ስትሰማ አልደነገጥክም?
በፍፁም አልደነገጥኩም፡፡ ዋናው ነገር የእኔ ድርሻ ምን እንደሆነ ነግሬሻለሁ፡፡ ከሚገባው ገንዘብ ጋር ግንኙነት የለኝም፤ አንድም ሽራፊ ሳንቲም በእኔ በኩል አያልፍም፡፡ የማውቀውም ነገር የለም፡፡ ነገር ግን እንደማንኛውም ሰው ስሰማው
አላስደነገጠኝም፤ ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች ይህን ያደርጋሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡ ይሄ የግል ስሜቴ ነው፡፡ ማዕከሉ የሚመራው በበላይ ጠባቂ ነው፡፡ ጤና ጥበቃ ራሱ አለበት፤ ዘውዲቱ ሆስፒታልም አለበት፤በሶስትዮሽ ወገን በጥብቅ የሚንቀሳቀስ ማዕከል ነው፡፡ ስለዚህ በነዚህ ዋና ዋና ምክንያቶች ክፍተቱ ይፈጠራል ብዬ አላምንም፡፡ እንግዲህ ሁሉንም ወደፊት የምናየው ይሆናል፡፡
“ላምባ” በፌስቲቫሉ መዝጊያ ላይ በአራት የውድድር ዘርፎች አሸንፏል፤ ይገባዋል ትላለህ?
ምናለ መሰለሽ ---- የሠራ ሁሉ ይገባዋል ባይ ነኝ፡፡ በዕለቱ ውድድር ሆነና የመምረጥ ጉዳይ ሆነ እንጂ ለእኔ እዛ ቦታ በዕጩነት የቀረቡት ፊልሞችም፣ ባለሙያዎችም አሪፎችና ምርጦች ናቸው፡፡ የምርጫው ጉዳይ ደግሞ የዳኞች ነው፡፡ ቀደም ሲል በነገርኩሽ አሪፍ አሪፍ ምክንያቶች “ላምባ” ይገባዋል፡፡ ያ ማለት ሌሎቹ አይገባቸውም ማለቴ አይደለም፡፡ እኔ ሙያውን አክብሮ፣ ህብረተሰቡን አክብሮ፣ ከልቡ በአግባቡ የሚሠራ ባለሙያ ተሸላሚ ነው ባይ ነኝ፡፡ ሽልማት የግድ በዝግጅቶችና በውድድሮች መድረክ ላይ ወጥቶ መሸለም ብቻ አይደለም፡፡ ለሙያውና ለህብረተሰቡ ታማኝ ሆኖ፣ ክብር ሰጥቶ፣ መሥራትም ራሱን የቻለ ትልቅ ሽልማት ነው ባይ ነኝ፡፡

Read 2808 times