Saturday, 21 November 2015 14:27

የክዋክብት ተመራማሪው ሚስት

Written by  ደራሲ፡- ኬይ ቦይል ተርጓሚ፡- አሸናፊ አሰፋ
Rate this item
(11 votes)

 ልክ ጠዋት ከእንቅልፍ ሲነቁ ሁሉ ነገር የቆመ እንዲመስል የምታደርግ ቀፋፊ ቅፅበት አለች፡፡ ለሴቶች ብዙ
አትከብድም፤ እነሱ ያውቁበታል፡፡ ከትንሽ ማቅማማት በኋላ ብድግ ብለው መነሳት ይችሉበታል፡፡ ከራስጌው መብራት ጋር መጫወትም ወደ ንቃት ያመጣቸዋል፡፡ ወይም ከፍ ባለ ድምፅ ቤቱ ውስጥ የተኛውን ሰው ሁሉ ይቀሰቅሳሉ፡፡ የክዋክብት ተመራማሪው ሚስትም ይህችን ደባሪ ክፍተት ታውቃታለች፤ ተጫነቻት፡፡ ትሁት ድምፅዋን ከአለበት ፈልጋ በጥንቃቄ  “ቡና፡፡” ብላ ከመኝታ ቤታቸው በታች ወደአለው ክፍል ላከችው፡፡ “ቡና አምጪልኝ፡፡ ” እግሯን የእንቁላል ቅርፅ ወደ አለው ምንጣፍ ላከችው፡፡ ንጋቱን በእራቁት ክንዶቿ እቅፍ አደረገችው፡፡ የሚንቀጠቀጡ ክንዶቿን ጠበቅ አድርጋ፡-“ ወደ ግራ ወደ ግራ፣ ሰዎች በሞላ፤ ወደ ቀኝ ወደ ቀኝ፣ ተኝተን እንዳንገኝ” እያለች የመንቂያ ስፖርት ሰራች፡፡ በቃ ቀኑ ከዚህ ይጀምራል፡፡ ከዚያ ልክ እንደ ትላንቱ፣ ልክ እንደ ትላንት ወዲያው … ይቀጥላል፡፡ አንዳችም የሚለወጥ ነገር የለም፡፡ ለውጥ ስለሌለ ሀሳብ የለም፡፡ የክዋክብት ተመራማሪው ባሏ ከእንቅልፉ አልነቃም፤ ወይም አልነቃሁም እንደማለት፣ እያስመሰለ ነው፡፡ እሷ ከአልጋ ውስጥ ከወጣች በኋላ ንቃቷ ጨመረ፡፡ ባሏ ቤት እስካለ ድረስ በዝምታ ከተጀቦነው፣ ትርጉሙ ከማይታወቀው፣ ከማይመረመረው እይታው አምልጣ አታውቅም፡፡ ከእይታው ለማምለጥ
ከተለመዱት ምክንያቶቹ አንዱን ማቅረብ አለባት፡- መታጠቢያ ቤት ነኝ፡- አንድ፡፡ የቤት ውስጥ ሥራ በዝቶብኛል፡- ሁለት፡፡ ሰው ልጠይቅ ሄጃለሁ፡- ሶስት፡፡ ሰውየዋ የዚህች ምድር ሰው አይነት አይደለም፡፡ ህልመኛ ነው፡፡ ነገር አለሙ ሁሉ በህልም የተሞላ ነው፡፡ ሲለው ለሰዓታት ይተኛል፤ ሲለው ጣራ ላይ ተሰቅሎ፣ ወይ ተራራ ላይ ወጥቶ ከቴሎስኮፑ ጀርባ ሆኖ ወደ ላይ ያንጋጥጣል፡፡
ይህንን ቀን እሷ እንደ ሁሌው ነው የምትጀምረው፡፡ ቀኑ አሀዱ የሚባለው እንዲህ ነው፡- ባሏ ማታ እራት ሲበሉ
ሰደርያው ላይ ያንጠባጠበውን ምግብ ታፀዳለች፤ ከዚያ ለምሳ የሚሆን ማዮኒዝ ትበጠብጣለች፡፡ ወንድ ልጅ አንዳሻው ከላይ የሚጋልብ፣ የሚፈነጥዝ፣ ቀበጥ ማዕበል እንደሆነ፤ ሴቷ ደግሞ ወደ ነበረበት የምትመልሰው ውስጥ ለውስጥ የምትሄድ የረጋች ማዕበል እንደሆነች በተደጋጋሚ ተነግሯታል፡፡ በዝምታ ነው የተነገራት፡፡
እጅግም ባይነጋም ሠራተኛዋ የእመቤቷን ድምጽና ትዕዛዝ ሰምታለች፡፡ ወደ መኝታ ቤቱ እየመጣች ነው፤ ኮቴዋ ደረጃዎቹ ላይ ይሰማል፡፡ የመኝታ ቤቱ በር ላይ ቆማ፡- “እመቤቴ፣ ቧንቧ ጠጋኙ መጥቷል፡፡” አለች፡፡
የክዋክብት ተመራማሪው ሚስት ነጭና ደማቅ ቀይ ቀለም ያለውን የቤት ውስጥ ካፖርቷን በፍጥነት ደረበች፡፡ አንገቷ ጋ ቆለፈችው፡፡ ከቧንቧው የፈሰሰው ውሃ ወደ ተኛበት ክፍል በጥንቃቄ አመራች፡፡
“እዚህ እንዲመጣ ንገሪው፡፡” አለቻት ሰራተኛዋን፡፡ ቁልቁል ወደ እንጨት ደረጃው መመልከት ያዘች፡፡
“እኔ እኮ ወይዘሮ አሜዝ ነኝ፡፡” አለች በቀስታ፣ ቧንቧ ጠጋኙ ደረጃውን መውጣት ሲጀምር አይታ፡፡
“እኔ ወይዘሮ አሜዝ ነኝ፡፡” የሚል ቀስ፣ በጣም ቀስ ያለ ድምፅዋን ቁልቁል ወደ ደረጃው ላከችው፡፡ “እኔ ወይዘሮ
አሜዝ ነኝ፡፡” አለች አንጀት በሚበላ፣ የሹክሹክታ-ለቅሶ በሚመስል ድምፅ፡፡ ይህን ስትል ቧንቧ ጠጋኙ አጠገቧ
ደርሶአል፡፡ “ፕሮፌሰሩ ተኝቷል፡፡ በዚህ በኩል ና፡፡” ቧንቧ ጠጋኙ በቀስታ የምታወራውን ወይዘሮ ደረጃው ላይ እንደሆነ ቀና ብሎ አያት፡፡ ወጣት ናት፡፡ ወጣትነቷን ግን
ረስታዋለች፡፡ የፕሮፌሰሩ ህቡእ አእምሮና የማይበገር ዝምታ የግሳፄ ጣቶቻቸውን ከናፍሯ ላይ ለጥፈውታል፤ በግልፅ ይታያል፡፡ አይኖቿ ግራጫ ሆነዋል፤ ያንቦገቡጋቸው የነበረው ብርሀን ከውስጥ “ቀጭ” ተደርጎ ጠፍቷል፡፡ ባልተበጠረውና በተንጨባረረው ወርቃማ ፀጉሯ ዙሪያ አሁንም የብርሃን አውራ (Aura) ይታያል፤ ደብዝዟል እንጂ አሁንም አለ፡፡ ቧንቧ ጠጋኙ ትልቅ ጫማ ነው ያደረገው፡፡ ኮቴው እንዳይሰማ እየተጠነቀቀ፣ ተያይዘው ከቧንቧው የፈሰሰው ውሃ እስክተኛበት የግቢው ሜዳ ሄዱ፡፡ ውሃው ለጥ ብሏል፡፡ ቧንቧ ጠጋኙ ጠንካራ፣ ከበድ፤ ገዘፍ ያለ እና ብርቱ ቢሆንም እሷን የሚያዋራት ኮፍያውን አውልቆ ነው፡፡ አይን አይኗን እያየ ነው የሚያዋራት፤ አስተያየቱ ግን ብልግና የቀላቀለ
ነው፡፡  “ከመታጠቢያ ቦታ ነው የሚፈሰው” መሬት ላይ የተኛውን ውሃ እየጠቆመ፡- “ወይስ ከሌላ …?” አላት፡፡
“ከሌላ ነው፡፡” አለች ወይዘሮ አሜዝ በእርግጠኝነት፡፡
በሰፈሩ ውስጥ ያሉት ቪላዎች የተራራቁ፣ ጥቂትና ከተሰሩ የቆዩ ናቸው፡፡ ከውጪ ያምራሉ፤ ውስጥ ሲገባ ግን ውበት ይሉት ነገር የለም፡፡ ውስጥ ሁሉ ነገር የተዘባረቀ፤ የማይጣመድ ነው፡፡ ቁሶቹ ትክክለኛ ቦታቸውን ለማግኘት ከቦታው ጋር የሚያደርጉት ትግል ምቾት እንደነሳቸው በእርጋታ እየተናገሩ ነው፤ ለሚያስተውል፡፡ ቧንቧ ጠጋኙ የአካባቢው ስሜት ተጋባበት፡፡ ብርቱ ሥራ እንደያዘች ሴት ኮስተርና ሰብሰብ አለ፡፡ የከበቧቸው ተራራዎች ግን የግርማ ሞገሳቸውን ጥላ ለቁሶቹ አውሰዋቸዋል፡፡
ወይዘሮ አሜዝ፣ ለቧንቧ ሰራተኛው ቪላው ውስጥ መኖር የጀመሩት ካለፈው ክረምት ጀምሮ መሆኑን  ነገረችው፡፡ ከገቡ ቀን ጀምሮ እስከዛሬ የተከሰተውን ሁሉ ተረከችለት፡፡
“እናልህ፣ ትናንት ማታ ልክ ወደ ምኝታ ልሄድ ስል” አለች ወይዘሮ አሜዝ፡- “የሆነ የተበላሸ ነገር እንዳለ ታወቀኝ፡፡”
ቧንቧ ጠጋኙ የቆዳ ሽርጡን ለብሶ ከገንዳው የሚፈሰውን ውሃ በቅርበት አየው፡፡
“ቧንቧው ከቆጣሪው መዘጋት አለበት፡፡” አለ በመጨረሻ፡፡
“ዘግቼዋለሁ፡፡” አለች ወይዘሮ አሜዝ፡- “ትላንት ምሸት ችግሩ ምን እንደሆነ እንደ አወቅሁ ያደረግሁት ቆጣሪውን
መዝጋት ነበር፡፡ ለዚያውም ከለሊት ጋዋኔ በስተቀር አንድም ነገር አለበስኩም ነበር፡፡ ይህ አሁን የምታየው ውሃ ቆጣሪውን ከመዝጋቴ በፊት የፈሰሰ ነው፡፡”
ቧንቧ ጠጋኙ ያደረገችውን ቀይ የልጆች ነጠላ ጫማ አየት አደረገው፡፡ የተኛው ውሃ ጫፍ ጋ ቆማለች፡፡ እግሯ ስር ንፁህ፤ ሚጢጢ ማዕበል ተፈጥሯል፡፡
“ችግሩ ያለው የፍሳሽ ማስወገጃው ቧንቧ ላይ እንደሆነ ምንም አልጠራጠርም፡፡” አለ ኮስተር ብሎ፡- “የሆነ ነገር
ሳይዘጋው አይቀርም፡፡ መያያዣዎቹ ሳይላቀቁም አይቀርም የሚል ጥርጣሬ አለኝ፡፡ ተለዋጭ መቆጣጠሪያ ቢኖራችሁ ይህ ሁሉ ችግር አይፈጠርም ነበር፡፡” አለ፡፡
ወይዘሮ አሜዝ ምን እንደምትመልስለት ግራ ገባት፡፡ በቆመችበት በትንሹ እየተወዛወዘች የቧንቧ ጠጋኙ ሰማያዊ፣ አፍጣጭ አይኖች ላይ አፈጠጠች፡፡
“አዝናለሁ፡፡” አለች፡- “አዝናለሁ ባለቤቴ አሁንም እንቅልፍ ላይ ስለሆነ ሊያግዝህ የሚችል አይመስለኝም፡፡ ቢችል ደስ ይለው እንደነበር እርግጠኛ ነኝ ….”
“ምናልባትም የመታጠቢያ ቤቱን ፈሳሽ ማስወገጃ ክዳን ማሳሸግ ሳይኖርባችሁ አይቀርም፡፡” አለ ቧንቧ ጠጋኙ ፊቱን አጨፍግጎ፡፡ ወይዘሮ አሜዝ ይህንኑ ስትሰማ ጉንጮቿን በእጆቿ ደገፈች፡
አኳኋኗን ሲያይ ትንሽ አዘነላት፡፡
“ለማንኛውም ወዲያ የአትክልት ሜዳው ጥግ ሄጄ ያለውን ችግር አያለሁ፡፡”
“እባክህ እንዲያ አድርግ፡፡” አለች፡፡ ይህ ሰው ስለ ተግባርና ስለ ነገሮች ነው የሚያወራው፤ ሴቶች ደግሞ ሁኔታዎችን የሚረዱት እንዲህ ሲወራላቸው ነው፡፡ “እባክህ እንዲያ አድርግ፡፡” ብላ የተናገረችው በለስላሳ ድምጽ ቢሆንም ብቻውን ተኝቶ፣ የቀን ህልም ያልም የነበረው ባሏ ጋ ደርሷል፡፡ እሷ እና ቧንቧ ጠጋኙ  ውሃው የተኛበትን ክፍል ለቀው ሲመጡ፣ ቆም ሲሉ፣ የውሃውን ኩሬ ሲሻገሩ ኮቴአቸውን እየሰማ ነበር፡፡
“ካትሪን!” አለ የክዋክብት ተመራማሪው በሚያስተጋባ ድምጽ፡- “ያንቺን ጥንካሬ የሚፈልግ ስራ አግኝተሻል፡፡”  ወይዘሮ አሜዝ አልዞረችም፤ ቧንቧ ጠጋኙን እየመራችው ደረጃውን ወረዱ፡፡ ከቤት ውስጥ ወደ አትክልት ስፍራው ወጥተው፣ ፀሀይ ፊቷ ላይ ሲያርፍ የፊቷ ቀለም ሲርገበገብ አየ፤ ምክንያቱ ምንም ሊሆን ይችላል ግን አፍራ እንዳይደለ ታውቆታል፡፡ “እንዴት እንደሆነ ታውቂያለሽ” አለ የወይዘሮዋን ትኩረት ለማስለወጥ፡- “ከእነዚህ ቤቶች የሚወጣው ውሃ የሚፈሰው ወደ ኮረብታው አናት ነው፡፡ ጉልበቱን ደግሞ አትጠይቂኝ፤ ውሃው ከኮረብታው ላይ ሲወርድ
በሀይለኛ ጉልበት ከመገፋቱ የተነሳ ኮረብታው ስር የቱንም ያህል ረዥም የሆነ ሰው አንድም የውሃ ጠብታ ሳይነካው መቆም ይችላል፡፡”
 ይህን የሚላት የአትክልት ሜዳው ላይ ቆመው ነው፡፡ አበቦቹ የበቀሉት ወይ የተተከሉት ተዘባርቀው ነው፡፡ ቧንቧ ጠጋኙ ወይዘሮዋን በደንብ እያያት ወሬውን ቀጠለ፡- “እናልሽ በስተመጨረሻ በውሃ መፍሰሻው አድርጎ፣ ጫካውን ተሻግሮ ይፈሳል፡፡”
ወይዘሮዋ ባሏ የተናገረው ነገር አሁንም ጆሮዋ ውስጥ ያስተጋባል፤ አስጨንቋታል፡፡ ‘የወንዶች አእምሮ ሁሉን ነገር መጠርጠር ልማዱ ነው፤ ሲለው ዘሎ ተራራ ላይ መሰቀል ነው፤ ሲለው በሆነው ባልሆነው መቦረቅ ነው፤ ሲለው በህልም አለም መንቦጫረቅ ነው፤ ሲለው የማይጨበጠውን ነገር ማሳደድ ነው’- ብላ አሰበች፡፡ ይህ ግን ባሏ ዘንድ አይሰራም፡፡ ረዥም ዝምታውን ጥሶ የሚናገረው ነገር አጥንት ይበሳል፡፡ ማለቂያ የሌለውን ዝምታውን የምታመሰግነው
ያኔ ነው፡፡ በዝምታው በረሃ መሀል የሚበቅሉት ንግግሮች እንደ በረሃ እባብ መርዛማ ናቸው፡፡
ህይወት? ህይወት ሴቶችን ለማስጠም አፉን ከፍቶ የሚጠብቅ ባህር ነው ብላ አሰበች፤በሀዘን፡፡ ሴቶቹ ደግሞ
ላለመስጠም ባህሩ ላይ የሚንሳፈፈው ውድቅዳቂ ላይ ሁሉ ይንጠለጠላሉ፡፡ እሷ ይህን እያሰበች ቧንቧ ጠጋኙ ሳሩ ላይ በእግሮቹ ተንበርክኮ፤ ጣቶቹን ቆልምሞ ክፍት ወደ አገኘው የቧንቧው መጋጠሚያ ውስጥ ላካቸው፡፡ ወይዘሮዋ ቁልቁል አየች፡፡ እንደ ወርቅ የሚያብረቀርቅ ፀጉር ታያት፡፡ “ ምንአልባት ባለቤትሽ” አለ ቧንቧ ጠጋኙ በምሬት፡- “መጥቶ ጉድጓዱ ውስጥ አብሮኝ ወደታች ወርዶ ምን እንደተበላሸ ማየት ይፈልግ ይሆን?”
“ወደታች ወርዶ?!” አለች ወይዘሮ አሜዝ በአግራሞት፡፡
“ወደ ውሃ መውረጃው” ብሎ መለሰ፡- “ነገሮች እንዴት እንደሚሰሩ ማወቅ ለሚፈልግ ሰው ምርጥ አጋጣሚ ነው፡፡”  
“እ፣ ባለቤቴ አቶ አሜዝ” አለች ወይዘሮ አሜዝ ግራ በመጋባት፡- “አሁንም፣ እስከ አሁንም ድረስ እንደተኛ ነው፡፡ ይገባሀል መቼም፡፡”
ጠንካራ የአየር ሁኔታዎች የተፈራረቁበትን ጠንካራ ፊቱን ቀና አድርጎ በመገረም አያት፡፡ ወንድ ልጅ እስከዚህ ረፋድ ድረስ፣ ለዚያውም ይህችን የመሰለች ፀሀይ ወጥታ እያለ እንዴት አልጋ ውስጥ ሊንከባለል እንደሚችል መቼም አይገባውም፡፡ የክዋክብት ተመራማሪው ሚስት ቧንቧ ጠጋኙ ላይ አፍጥጣለች፡፡
ቀጥ ያሉ ጉንጮቹን፣ ረዣዥምና ጠንካራ አጥንቶቹን፣ ግንባሩ ላይ በጥልቀት የተቆፈሩ የሚመስሉ መስመሮችን በእጅጉ አየቻቸው፡፡ የሰውነቱ ስጋ ጠንካራና በመላጊያ ቅርፅ የወጣለት ይመስላል፡፡
ቆዳው በፀሐይ ሙቀት የጠየመ ነው፡፡ ጣቶቹ በስራ ብዛት ጉልጥምታሞች ሆነዋል፡፡ እጆቹ ላይ ወፋፍራም፣
የተጠማዘዙ፣ የተጠላለፉ፣ በደም የተሞሉ የደም ስሮች ጎልተው ይታያሉ፡፡
“ለማንኛውም” አለች ልትናገር ያለችው ነገር ከንፈሮቿን በፈገግታ በትንሹ ገርበብ አድርጎት፡- “ምንም ቢሆን ምንም ባለቤቴ አቶ አሜዝ በህይወት እያለ ጉድጓድ ውስጥ አይገባም፤ ወደ ታች አይወርድም፡፡
 እሱ የሚወደው ወደ ላይ መውጣትን ነው፡፡” አለች በማላገጥ ወደ ሰማይ እየጠቆመች፡- “ወደ ላይ መውጣት
ያስደስተዋል፡፡ ጣራ ላይ፣ ተራራ ላይ መውጣት ይወዳል፤ ሁለቱም ላይ ብዙ ጊዜ ወጥቷል፡፡”
“የሰው ምርጫ ይለያያል፡፡ ” አለ ቧንቧ ጠጋኙ፤ ይህን ብሎ ድንገት ወደ ጉድጓዱ መውረድ ጀመረ፡፡ ቀስ በቀስ ሰውነቱ
ሁሉ ገብቶ አለቀ፡፡ ወይዘሮ አሜዝ በስተመጨረሻ ያየችው የምታብረቀርቅ፣ ኮከብ የምትመስል የፀጉር ጫፍ ነበረች፡፡ ከጥልቁ ጉድጓድ ውስጥ፣ ጥልቀት የሌለው በጥርጣሬ የተሞላ ድምፅ ሰማች፡፡
 “የቧንቧዎቹ ጉልበት ላይ አንዳች ነገር ገብቶ ሳይዘጋው አልቀረም፡፡ ጉልበቱ ላይ ተዘግቷል፡፡ ”
ንግግሩ ውርር አደረጋት፡፡ ጀሮዋ ውስጥ ብቻ አይደለም፣ ስጋዋ ውስጥም ገብቷል፡፡ አጥንቷንም አግኝቶታል፡፡
አግራሞት ሁለመናዋን ሞላት፡፡ በቃ እንዲህ አይነት ንግግር ነዋ የሚገባት፡፡ ባሏ ስለ ርቀት ሲያወራት አይገባትም፡፡
ምኑም አይገባትም፡፡
ጥልቀት፣ ምጥቀት፣ አስማት ይሏቸው ነገሮች ምናቸውም አይገባትም፡፡ የሆነ ሌላ ስም፣ የአለም ስም ሊኖራቸው

ይገባል፡፡ አሁን ስለ ቧንቧ እያወሩ ጉልበቱ ተዘግቷል የሚል ቋንቋ በግልጽና በደንብ ይገባታል፡፡ ምንም አይነት እብደት
በእለት ተእለት ቋንቋ ሲነገር ግልፅ ይሆናል፡፡
 ሳሩ ላይ ተቀመጠች፡፡ አሁን የሰማሁት ድምጽ የወንድ ነው የሴት? ተወዛገበች፡፡ ሴቶች ናቸው እንዲህ አይነት ቀላል
ቋንቋ መናገር የሚችሉታ፡፡
ሳሩ ላይ እንደ ተቀመጠች ቅጠሎቻቸውን ሲዘረጉ አየች፡፡ ልትነቅላቸው፣ ከህይወት ልትነጥላቸው አልፈለገችም፡፡

አቅም አልባ ሆነች፡፡
የስሜት ህዋሳቶቿ ከአካባቢዋ ጋር መናበብ አቆሙ፡፡ እጆቿ ተልፈሰፈሱ፡፡ ወንዶች እንዲህ ሆነው ለረዥም ሰዓታት

መቀመጥ እንደሚችሉ ታውቃለች፡፡ ወንዶች የሀሳባቸውን መነሻ ነቁጥ እስኪያገኙ ድረስ እንዲህ ሆነው መቀመጥ

ይችሉበታል፡፡ የወንዶች አእምሮ የመመጠን፣ የማካፈል፣ አረም የማረም፣ ሲለው ያለውን የማውደም ተክህኖ አለው፡፡

የሚመቸው ሳር ላይ ተዝናንታ ተቀምጣ፣ የቧንቧ ጠጋኙን መምጣት ፈዝዛ መጠበቅ ያዘች፡፡
ሁለት አይነት ሰዎች አሉ ብላ አሰበች፡፡ የመጀመሪያዎቹ የባሌ አይነት ናቸው፡፡ ልክ እንደ ሙታን ነፍስ ወደ ላይ፣ ወደ

ሰማይ መሄድ የሚፈልጉ፡፡ ሁለተኞቹ ደግሞ፡- እንደ እዚህ እንደ ቧንቧ ጠጋኙ አይነት ናቸው፡- ወደ ታች፣ ወደ ምድር

ከርስ፣ ወደ በድናቸው ማረፊያ መውረድ የሚወዱ፡፡ ሰዎች በሁለት ወገን የተከፈሉ መሆናቸውን ማወቁ ነገሮችን

አቀለለላት፡፡
ሀሳቧን አጠራላት፡፡ በውዝግብ ወዲያ ወዲህ ይወዛወዙ የነበሩ እግሮቿ ረግተው ተቀመጡ፡፡ ካለችበት

አልተንቀሳቀሰችም፡፡ የተራሮቹን ድምፅ እየሰማች፣ ጥርት ያለውን ሀሳቧን አዳመጠች፡፡ ባሌ የዚህች አለም አእምሮ ነው

ብንል  አለች ለራሷ፣ ቧንቧ ጠጋኙ ደግሞ የዚህች አለም ስጋና ደም ነው፡፡ ከትንሽ ቆይታ በኋላ ቧንቧ ጠጋኙ

ከነበረበት ጉድጓድ ወጣ፡፡
“ፍሳሽ ማስወገጃው መስመር ነው፡፡” አለ በደስታ፡፡
“ምን አባታችን እናድርግ ታዲያ?” ብላ በቀስታ ጠየቀች፡፡ ስለማያውቁት ነገር፣ መልስ ላለው ሰው ጥያቄ ማቅረብ

እጅጉን ደስ ይላል፡፡ የክዋክብት ተመራማሪው ማለቂያና መልስ በሌላቸው ጥያቄዎች ሲያደርቃት፣ ልቧን ሲያወልቀው

ነው የኖረው፡፡
“እስኪ ወዲህ ነይ” አለ ቧንቧ ጠጋኙ ፈገግ ብሎ፣ ቁልቁል እያያት፡- “ለእያንዳንዱ ችግር መፍትሔ አለ፡፡ ለእያንዳንዱ

ደዌ መድሃኒት አለ፡፡ አንዳንዴ መፍትሔው ይህ እና እዚሁ ያለ ይሆናል፡፡” አላት፡፡
 ለህፃን ልጅ የሚያወራ ነው የሚመስለው፡- “አንዳንዴ ደግሞ መፍትሔው ያ እና እዚያ ያለ ይሆናል፡፡ እያንዳንዱ

የተዝረከረከንም ሆነ የተዘባረቀ ነገር ማስተካከል እንደሚቻል ግን አትጠራጠሪ፡፡”
አሁን ምንም ቢላት ታምነዋለች፡፡ ስትበይው ወጣትነትሽን የሚመልስ እፅ አለ ቢላት ታምነዋለች፡፡ ከአሁን ጀምሮ

በማንኛውም ሰዓት የሚዘንበው ዝናብ የነፍስሽን ጥማት ያረካዋል ቢላት ታምነዋለች፡፡ ሀያሉ፣ አይበገሬው ጊዜ

አይደለም ጊዜያዊ ቁስልን የተሰበረ አጥንትን ይጠግናል ቢላት ታምነዋለች፡፡
“የተዘረጋውን መስመር ተከትዬ እስከ እጣቢ መውረጃው ድረስ እሄዳለሁ፡፡ ብልሽቱ ያለው ከዚህ እስከ እዚያ ባለው

መስመር ላይ እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ፡፡ በጥንቃቄ ከፈለግሁት አገኘዋለሁ፡፡ የተበላሸ ነገር ለመጠገን ደግሞ የማይደረግ

ነገር የለም፡፡”
አስተያየቱ ውስጥ ምን ነበር? ብልግና አለ፡፡ ደግነት፣ ገራምነት ነበር፡፡ ፍቅርም ነበር፡፡ የክዋክብት ተመራማሪው ሚስት

ካለችበት ተነሳች፡፡ የፀጉር ማስያዣዋን አስተካከለች፡፡ ፊቷን ወደ ማብሰያ ቤቷ አዙራ ሰራተኛዋን መጣራት ያዘች፡፡

ይሄኔም ቧንቧ ጠጋኙ ወሬውን አላቋረጠም፡፡
ሠራተኛዋ መጣች፡፡ ወይዘሮ አሜዝ በፈገግታ ጠበቀቻት፡፡
“ይሄውልሽ ችግሩ በጣም የተወሳሰበ ነው፤ እጅግ በጣም፡፡” አለች፡- “አቶ አሜዝ ሲነሳ ወደ ጉድጓድ፣ ወደ ታች

እንደወረድኩ ንገሪው፡፡”  
ቧንቧ ጠጋኙ ቦርሳውን አነገተ፡፡ ወደ ታች እንድትከተለው ሊረዳት፣ እጁን አቀበላት፡፡ እጁን ይዛ ቁልቁል

ተከተለችው፡፡ ምነው ያለው ነገር ሁሉ እውነት በሆነ እያለች ነበር፡፡
 (የዚህ አጭር ልብ-ወለድ የእንግሊዝኛው ርዕስ፡- Astromer’s Wife ነው፡፡)
ስለ ደራሲዋ፡-
ኬይ ቦይል ከ1903 እስከ 1992 ዓ.ም የኖረች አሜሪካዊት ደራሲ ናት፡፡ ከአህዮ ሚካኒክስ ኢንስቲትዩት በአርክቴክቸር

ተመርቃለች፤ ሲንሲናቲ ኮንስርቫቶሪ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ገብታም  ቫዮሊን ተምራለች፡፡
 በርከት ያሉ ረዣዥም ልብ - ወለዶች ብትፅፍም ይበልጥ የምትታወቀው በአጫጭር ልብ - ወለዶቿ ነው፡፡ ይህ

Astromer’s Wife የተሰኘ አጭር ልብ - ወለዷ በሀያሲዎች እኩል ተጨብጭቦለታል፡፡

Read 4186 times