Saturday, 28 November 2015 14:05

ደሞ ለሴት!?

Written by  አሰፋ ጫቦ Dallas Texas USA
Rate this item
(2 votes)

የአገር ክህደት አንድምታው!

  የዛሬው ርዕሰ ጉዳዬ እናቴ፤ማቱኬ አጆ፤ስትል የነበረውን አስታወሰኝ። “ውሃውን ማን ያናግረዋል? ድንጋይ! ድንጋዩን ማን ያናግረዋል? ውሃ!” ትል ነበር፡፡ በተፈጥሮም ሆነ በሰዎች ሕይወት ወስጥ ያለውን የመነካካት፤የመያያዝ፤የመተሳሰር አንዱ ሌላውን የመቀሰቀስ (Chain Reaction) ነገር ለመግለጽ መሆኑ ነዉ። ዛሬ በዋናነትና በብቸኝነት ለማንሳት የፈለግሁት የኢትዮጵያ የስፖርት ፌደሬሽን በቁሙ ስለቀበረው የኢትዮጵያ የሴቶች የእግር ኳስ ቡድን ነው፡፡ የመነካካቱ ነገር ያመጣውን የወደዚያ ጉዞ መንገድ ለማሳየት ስፈልግ ደግሞ ረዘመ፣ተራዘመ፡፡ መቻል ነው ደጉ!
ሸገር ራዲዮ FM 102.2 ድንገት Facebook ላይ አገኘሁትና አዳመጥኩት። ያዳመጥኩትን ደግሞ በአብዛኛው ወደድኩት። የመአዛ ብሩ ቃና፤መአዛ ነበረው። መአዛን 2001 ይሁን 2002 ኒው ዮርክ ወርጄ፣ ለ 4 ይሁን 5 ሰአት አነጋግርያት ነበር። ወርጄ ማለቴ ያኔ የነበርኩት ኬምብርጅ ፤ማሳቹሰትስ ነበርና ነው። አነጋገርኳት ከማለት ይልቅ አናዘዘችኝ (ሌሎችንም እንደምታደርገው) ማለቱ ሳይሻል አይቀርም። ለራዲዮ መሆኑ ነው። ሸገር የሚባል ራዲዮ መኖሩን ያኔ አላውቅም ነበር። የሰው አገር ሰው ነገር!!
መአዛ ብሩን ያኔ ገና ሳያት ወደድኳት። የሐረርጌ ሰው መሆንዋን ሁለንተናዋ ይናገራል። እንኳን ደህና መጣህ የሚል መልእክት (Body Language) ያለው ይመስላል።  አሁንማ በሸገር “አሻም!!” ስትልም ሰማሁ። እንደኛው እንደ ጋሞዎቹ መሆኑ ነው። አሻም!! እንኳን ደህና መጡ  መሠረታዊ ትርጉሙ ይሆንና የጋሞዉ ተጨማሪ እቅፍ የማድረግ ጠረን፤ቃና፤ቅባት ያለው ይመሰለኛል::
የመአዛ ነገር ሌላዋን የማውቃትን፤ቤትዋም ለመሔድ ዕድል የገጠመኝን ትዝታ በላቸውን አስታወሰኝ። ሌላው ተመሳሳይነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በመልክም የሚመሳሰሉ እንኳ ባልል የሚቀራረቡ መሰለኝ። ትዝታ በመጠኑ ቀጠን፤ትንሽም ረዘም ሳትል የምትቀር አይመስለኝም። ትዝታን አምና በመጋቢት ወዳጄ በነበረው ሙሉጌታ ኃይሉ መታሰቢያና መዘከሪያ ስብሰባ ላይ ዋሺንግተን ዲ.ሲ አግኝቻት በደንብ ሳንጨዋወት ተለያየን።
 ብሩና ትዝታ በላቸው፤ የሴት የራዲዮ አቅራቢና ፈር-ቀዳጅ የነበረችውን ሮማነ ወርቅ ካሳሁንን ያስታውሱልኛል። ሮማነ ወርቅን መጀመሪያ ያደመጥኳት ልጅ ሆኜ ጨንቻ ነበር። የ”ገሙ” አዋራጃ ግዛት ዋና ጸሐፊ የነበሩት አቶ አሰፋ ዳዲ መኖሪያቸው ፊታውራሪ ሳጌ ሜንዴ ፎቅ ላይ ሆኖ ስምንት ሰአት ሲሆን ራዲዮናቸውን ደረጃው ላይ ያወጡትና ይከፍቱ ነበር። በከተማው ያለው ብቸኛው ራዲዮ ሳይሆን አይቀርም ብዬ እገምታለሁ። ሮማነ ወርቅ አሁን ካለችበት ወዲያ ማዶ፤ከጽራሐ አርያም ሆና መአዛንና ትዝታን፤ “አርማዬን ደህና አድርጋችሁ አንስታችኋል!! ግፉበት!!” የምትል ይመስለኛል።
ሸገር ላይ ካደመጥኩት ሦስት ጉዳዮች ውስጥ የመጀመሪያውና ለየት የሚለው አቡነ ብርሐነ እየሱስ ሱራፌልና መአዛ ያደረጉት ውይይት ነበር። መወያየት ሳይሆን መጨዋወት ብለው ይሻለኛል! የማልረሳው ዘላቂ ማሕተም ያተመብኝ ይመስለኛል። በዚያ ላይ ሁለቱም ሐረርጌዎች ናቸው። ምን ማለቴ እንደሆነ የሐረርጌን ሰው የሚያውቅ የበለጠ ይረዳኛል። ጫወታው ሳይዳልጠው እንዳለ የሚወርድ ነበር። ሊቀ ጳጳስ ብርሐነ እየሱስ አኮሩኝ! ኢትዮጵያን የካርዲናል አገር አስደረጓት! በዚህ ላይ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአካባቢ አገሮችም ጳጳስ ናቸው። ስለ ካቶሊክ ካርዲናል፤ ሊቀ ጳጳስ፣በቅጡ ለማወቅ ፤ከቤተክርስቲያኒቱ ፓትሪያርክ፤ (ፖፕ Pope) ለጥቆ ያለው መንበር ነው። ካርዲናሎቹ ፖፑን መራጮችም በተራቸው ለዚያ መንበር ተመራጮችም ናቸው። ካርዲናል ብርሐነ እየሱስ ነገ ተመርጠው በቅዱስ ጴጥሮስ መንበር ላይ ሲቀመጡ ይታየኛል! እንዲያውም የፈረንጅ፤በተለይም የጣሊያን ተወላጅ ፖፕ ዝንተ ዓለም ነገሠበት የሚል እሮሮ ስለነበር ነው የአሁኑን አርጀንቲና ወርደው የመረጡት የሚል በሰፊው ተጽፎ ሳነብ ሰንብቻለሁ። የሚቀጥለው ዙር የአፍሪቃ ከሆነም፣ የኢትዮጵያ እንደሚሆን እምነትም፤ተስፋም፤ምኞትም አለኝ። “ቸር ተመኝ! ቸር እንድታገኝ!” ነውና።
እኝህ ካርዲናል ብርሐነ እየሱስ ተዘውትሮ የምናውቀው ጳጳስ አይነትም አይደሉም። ውጣ ውረዳቸው፤ የኔው ትውልድ የተጓዘበት ወጣ-ገባ አቀበት፤ ቁልቁለትና ገደላ ገደል አቆራርጦታል። ዩኒቨርስቲውም አንድ ዘመን፤ የተማሪ ንቅናቄውንም፣ ደርግንም ከነመራራውና ኮምጣጣው ጎኑ ተጎንጭተዋል። በዚያ ጎራ አልፈው ለወሬ ነጋሪ ከተርፍነው ውስጥ ናቸው። ሸገር FM 102.2 ጎራ ብሎ ማዳመጥ ነው። አሜሪካ ያላችሁ በስልክ ቁጥር 712 432 6885 ደውሎ ማዳመጥ ይቻላል። ካልተገኘ አርካይቭ (የትላንትን ማሕደር) የት እንደሚገኝ መአዛን መጠየቅ ነው። እኔማ ሲለኝ አንድ ቀን ስለ እኝህ ጳጳስ መጻፌ የማይቀር ይመስለኛል። ስለ ጳጳሳት የመጻፍ ልምዱም አለኝ። ስለ አቡነ ጳውሎስም ስለ አሁኑም ፓትሪያርክ አቡነ ማቲያስ ጽፌያለሁና!
ሁለተኛ ያደመጥኩት የዘፋኟን የጸደንያን ቃለምልልስ ነበር። በየትኛው እንደሆነ እንጃ እንጂ አንዴ በቴሌቪዥን ቃል ምልልስ ስታደርግ አድምጭያት ነበር። ስምዋ ያልተመደ እሷ ደግሞ አውቄ የኖርኳት አይነት ሆነችብኝ። እንደ ዘፋኝ፤እንደ ታዋቂ ዘፋኝ ሳይሆን አነጋገርዋ ልክ እንደኛው እንደ ተራና ተርታ ሰዎች ነበር። ለአደባባይ ያዘጋችው ገጸ ባሕርይ (Public Persona) አልነበራትም። የማእከላዊ ወዳጄ የነበረውን ጥላሁን ገሠሠን አስታወሰችኝ። ጥላሁን በአካል በዝና ሰማየ ሰማየት፤አጽናፈ አጽናፋት የነካ፤የነገሰ ፍጹም አይመስልም። መምስል ሳይሆን መሆንም ስለነበር ትንሽ ለማመን የሚያስቸግር ነበር። “እርግጥ አንተ ያ ጥላሁን ነህ!?” በል የሚያሰኝ ነገር ነበረው፡፡
ጸደንያ በአፍሪቃ የዘፈን ውድድር ናይጄሪያ ወርዳ፤ዘፍና፤አምራ- ሠምራ ፤የለበሰችው ጥበብ፤ (እድሜ ኑሯቸው “ያው በገሌ!” ለሆነ ጋሞ፤ዶርዜ ዘመዶቻችን ይስጣቸውና)፤የጉድ- ጉድ ተደንቆ ፤በዚያም ላይ አሸንፋ ጥዋት አዲሳባ ስትደርስ ከእንቅልፏ ቀድሞ ሸገር አግኝቷት፣ የሰጠችውን ቃለ ምልልስ ነበር ያደመጥኩት። ባቡር ዉስጥ በጆሮ ማድመጫ እያደመጥኩ ነበርና ስትጨርስ “እሰይ አበጀሽ የኛ ሸጋ! ባሳር ተገኘሽ በፍለጋ !” አልኩኝ ጎላ ባለ ድምጽ። “What did you say now?” አለችኝ ከጎኔ  
የተቀመጠችው ፈረንጅ። (ምን አልከኝ አሁን? ማለቷ ነው) “Thinking out Loud!” አልኳት። (ብቻዬን እያውጠነጠንኩ ነኝ! ማለቴ ነው፡፡) እዚህ ለብቻ መናገር እንደ ልብ ነውና አልገረማትም።
ይህ ሁሉ ወደተነሳሁበት ለመድረስ መግቢያ መሆኑ ነው!
ሦስተኛ ያደመጥኩት የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን የሰጠውን መግለጫ ወይም በዚያ መግለጫ ላይ የተሰጠውን ፍሬ ሐሳብና ግምገማ ነበር። የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን፤ አውቆ በድፍረትና በንቀት፤ ያለበለዚያም በንሕዝላልነት፤በማን አለብኝነት፤ደሞ ለሴት የኳስ ቡድን ያን ያህል ቦታ መስጠት !! በሚል በቁሙ የቀበረበትን ታሪክ ነበር። ታሪክ ሳይሆን ደረቅ አይን ያወጣ ወንጀል ማለቱ ይቀል መሰለኝ። ለኔ!
ገረመኝ! ደነቀኝ! የሰማሁትን ማመን አቃተኝ! ደግሞም የተወሳሰበ ነገር፤ነጥብ (Issues) አልነበረውም! የኢትዮጵያ የሴቶች የእግር ኳስ ቡድን፤በአፍሪቃ የሚያሸንፈውን ሁሉ አሸንፎ ለሚቀጥለው ለመጨረሻው ውድድር ሊሔድ ተዘጋጅቷል። አዘጋጆቹ ፤የአፍሪቃ ስፖርት የበላይ አካላት፤ “ጎበዝ! እንግዲህ መቼ ነው የምትመጡት?” የሚል ደብዳቤ ለኢትዮጵያ ፌዴሬሽን ይልካሉ። መልስ የለም!! ትንሽ ቆየት ብለው ሁለተኛ ደብዳቤ ይልካሉ። አሁንም መልስ የለም! “ጎበዝ! አገር ደህና !?” በሚል ሶስተኛም ደብዳቤ! ጭጭ! አራተኛም ደብዳቤ ይላካል! ፍንክች ያባ ቢለዋ ልጅ!! እንደገናም ዝም! ጭጭ ! ምጭጭ! ሆነ:: አካሉ የማታ የማታ የብረት መዝጊያውን ቀርቅሮ፤መክፈቻውን ቁልፍ ወረወረው!! የኢትዮጵያ ሴቶች ልጆች፤እንደ ጸደንያ ፤አደባባይ ውለው ፤አምረው ሠምረው፣ ዋንጫ አንግተው፤ጉሮ ወሸባዬ፤ “አለምሽ ዛሬ ነው ዛሬ! ኢትዮጵያ አገሬ!” ብለው እየዘመሩ፤ እየፎከሩ፤ እያቅራሩ የሚመጡበትን የተስፋ ምድር፣ የስፖርት ፌዴሬሽን በቁሙ ቀበረው። ማቅም አለበሰው! ጥላሸትም ቀባው!!
የስፖርት ፌዴሬሽን ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት የግዱን የተስማማው ይህ ፤ብሔራዊ የቀበር ሥነ ስርዓት እንዴት እንደተፈጸመ፤ማን ጉድጓድ ቆፋሪ፤ማን አፈር አልባሽ፤እንዴት?ለምን? መቸ? የሚለውን ለማስረዳት ነበር፡፡ የመጀመሪያው ደብዳቤ የመጣው በሰኔ ወይም ከዚያ በፊት ሆኖ የመጨረሻው የመጣው በነሐሴ ወር ነበር። አምና ማለት ነው። የጋዜጣ መግለጫው ደግሞ ዘንድሮ በሕዳር ወር ነበር:: ጋዜጣዊ መግለጫው ወይም ፍሬ ነገሩንና (ፍሬ ነገር ቢኖረው) ትንተናውን ሳዳምጠው የበለጠ ገረመኝ።
እንደምናውቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 90 ሚሊዮን ነው። ሴት- ወንድ ስብጥሩ መሳ- ለመሳ (50%) ነው። ማለትም ኢትዮጵያ 45 ሚሊዮን ሴቶች አሏት ማለት ነው። የኢትዮጵያ ስፖርት ቦርድ ውስጥ አንዲት ሴት እንኳን የለበትም። በፌዴሬሽኑ ውስጥ የሴቶች ጉዳይ ሐላፊ ደግሞ አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ ናቸው። አቶ ወንድ መሆናቸውን አንጠራጠርም። ወይም ሴት አለመሆናቸውን እርግጠኞች ነን። ይህም ማለት ከዚህ 45 ሚሊዮን ሴት ውስጥ ለዚህ ለቦርድ የሚበቃ፤ሌላው ቢቀር የሴቶችን ጉዳይ የሚከታተል አንዲት ሴት ማግኘት አልተቻለም ማለት ነው። ወይም፤ ለመሆኑ ይህ የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን በየትኛው ምዕተ አመት ውስጥ ነው የሚገኘው? ማለትም ተገቢ ጥያቄ ይመስለኛል። ተራ፤የታወቀውና የተለመደው የወንድ ትምክህተኝነት ብሎ ለማለፍ ትንሽ የሚከብድ ይመስለኞል። እኔ ይከብደኛል!! ዘመነ መሳፍንት የሚባለው መቼ ነበር? 200 መቶ አመት አለፈው? ያም ዘመን ቢሆን እንደነ ዕቴጌ ጣይቱን መሳይ አፍርቶ ነበር። ይህ አገር ዛሬም የነጣይቱ አገር ነው!! እነዚህ የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ዘመናቸው የፈቀደውን ጀግንነት ለማሳየት አድዋ መዝመታቸው ነበር።  
ይህን የተሰራውን ደባ፤ኩነኔ ለማካካስ ተወሰደ የተባለው እርምጃ የበለጠ ደነቀኝ። አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ፤የሴቶቹ ተጠሪ፤ከስራቸው ታገዱ። ዮሴፍ፤የሴቶች ኃላፊው ታገዱ! ኃላፊ ያልነበሩ፤ወረድ ብለው ያሉ፣ ግና ሴት የሆኑ፣ከስራቸው ተባረሩ! ለማመን የሚያስቸግር ቢመስልም የነገሩን ይህንኑ ነበርና እውነቱ መሆኑ ነው! ተባለ! “እሰየው! የምናላክክባት ሴት ተገኘች!” መሆኑ መሰለኝ:: ነውም!
“ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም!” ይባል የለ? እንዴ እስቲ ቆይ! Just a Minute! “…ከንፈረ ሞንሟና ከዚሁ ተስሞ ምን ይተርፋትና” ም ይባል ይለ? እኝህ ፥ከስራቸው ታገዱ የተባሉት፣አቶ ዮሴፍ፤ተናገሩ የተባለውን Facebook ላይ አገኘሁትና እንደወረደ እዚሁ ለጠፍኩት። እንዲህም አሉ፡- “ህዝቡንም...ሚዲያውንም ለማብረድ አንተ ጥፋተኛ ነኝ ብለህ ይቅርታ ጠይቅ.፤.እኛ ከሁለት ሳምንት በኋላ እንመልስሃለን ብለውኛል።” .... (ከእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ታግደዋል የተባሉት አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ፣ ሂልተን ሆቴል በግል በሰጡት መግለጫ የተናገሩት)
የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን፤በዚህ የሴቶች የእግር ኳስ ዙሪያ ያደረገውን ትልቁን ምስል ስመለከት ፤እንደ “የአካባቢ ማስረጃ (Circumstantial Evidence) ወስጄ ካለማመን ወደማመኑ አዘነብላለሁ። ካልሆነ ደግሞ አላልኩም ብለው ማስተባበሉ የአቶ ዮሴፍ ፋንታ ነው።
እናም፤ይኸ፤የወንዶች የኢትዮጵያ የስፖርት ፌዴሬሽን ስራ፣ የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩ፤ በኋላም የአለም የጤና ጥበቃ (WHO) ዲሬክተር የሆኑት Gro Hartlem Brutland ተናገሩ የተባለውን አስታወሰኝ። አንዴ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑ ጊዜ ካቢኔያቸውን፤ሚኒስትሮቻቸውን በሙሉ ሴቶች ብቻ ሾሙ። “ምነው ምነው ወንድ በአገሩ የለም ወይ?” የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው፣ “የወንዶችን ስራ እስከዛሬ አየነው’ኮ!” አሉ። “አለምን እዚህ ማጥ ውስጥ ለዘመናት የዘፈቁ ወንዶች አይደሉም ወይ?” ሲሉም አከሉ። መልሳቸው አጉል አባባል አስታወሰኝ። “ለማያውቅሽ ታ…” የሚለውን። ታዲያ፤ይኸ የስፖርት ፌዴሬሽን ስራ፣ Bruntland ያሉትን ሸተተኝ።
እኔ የማቱኬ አጆ ልጅ ነኝ። ከለስላሳውና ልዝቡ አባቴ ይልቅ ሁለንተናዬ በናቴ የወጣ ይመስለኛል። አንዴ፤እዚህ አሜሪካ የመሐል ስም (Middle Name) የሚሉትን ጨምሬ፣ አሰፋ ማቱኬ ጫቦ መባል አለብኝ የሚል ሃሳብ መጣብኝና ህጋዊ ለማድረግ ፈልጌ ፍርድ ቤት ሄድኩ። “ችግር የለም!” ብላ የሚሞላ ቅጽ (form) ሰጠችኝ። ቅጹን ሞልቼ ስመልስላት ደረሰኝ ለመቁረጥ ተዘጋጅታ፣ “$200 አምጣ!” አለችኝ። እናቴንስ በ$200 አልለውጥም ብዬ ተውኩት።
ማቱኬ ሰውን ሁሉ፤ወዳጅ፤ወዳጅ ያልሆነ፤ዘመድ አዝማድ፣ወንድ ሴት፣ልጆቿን ጨምሮ የምትከፍለው በሁለት ብቻ ነበር። ሥነ ስርአት ያለውና ሥነ ስርአት የሌለው። ሥነ ስርአት የለውም ለምትላቸው የምትጠቀመውን ቃላት እዚህ መድገም አልፈልግም። ከበድ ይላል።
ደርግ ሁለት ልጆቿን አስሮ ነበር። የኔ መታሰር ተደብቆ ኖሮ ሲሰለቻት፣ “አዲሳባ ሄጄ ማየት አለብኝ!” ብላ ተነሳች። ምርጫ ሲታጣ “ታስሯል!” ሲሏት “የኔን ልጆች እያሳደደ የሚያስር አሳዳጊ የበደለው ባለጌ ማነው!?” ስትል መንግስቱ ኃይለማርያም መሆኑን ነገሯት። መንግስቱን ለማነጋገር በነጋታው ተነስታ አዲሳባ መጣች። አነጋገረችውም! እንዴት አድርጋ እዚያ እንደደረሰች ይገርመኛል። ዝርዝሩን አልነገሩኝምና ነው። የሆነ ሆኖ የመንግስቱ ጠባቂዎች ትንሽ አጉላልተዋት ስለነበር፣ለነሱ፣ለራሳቸዉ፣ ስለነሱ የምታስበውንም እዚያው ነገረቻቸው አሉኝ። ይህንን ማምጣቴ መሆን የሚገባው ሳይሆን ቀርቶ ፤ መሆን የማይገባው ሲሆን ፤ ማለትም ሥነ ስርአት የጎደለው ሆኖ ሲገኝ፣እኔንም እንደ እናቴ ያደርገኛል ለማለት ነው። የዚህ የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን ድርጊት እንደዚያ አደረገኝ!!
በመሠረቱ የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን መባሉም ትክክለኛ ስሙ አይመስለኝም። የወንዶች ፌዴሬሽን ቢባል እርግጠኛና እውነተኛ ስሙ ይሆናልና። የሚወክለው ከኢትዮጵያ ሕዝብም ውስጥ ከፊሉን 50% ነውና። ደግሞም ይህ በሴቶች የእግር ኳስ ቡድን ላይ የተፈጸመው ደባ፤ የአሰራር ቸልተኝነት፤ መሪ የማጣት ችግር ብቻ አይመስለኝም። መሠረታዊ የሰው ልጆች የመብት ገፈፋ ጥያቄ ነው። አገላብጬ አላየሁትም እንጂ፤ ሌላ ቦታ እንዳልኩት የደረቅ ወንጀልነትም ባሕርይ አያጣም። በኔ አስተያየት የዚህ አይነት ድርጊት እንዳይደገም ፤መቀጣጫም ፤መማማሪያም እንዲሆን ከስር መሠረቱ መስተካከል ያለበት ይመስለኛል።
ይህ እንዴት ነው የሚቻለው? ለዚህ ዛሬ ምን ችግር አለው! ትላንትና የኢትዮጵያ መንግስት፤ ኢሕአዴግ፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰብሳቢነት፤ “እዚህ ቤት ጉድ ፈልቷል!” ብሎ ያለ የሌለ ጉዱን በአደባባይ ነግሮን የለ! ስለዚህ በመላው ኢትዮጵያ ያሉት የሴቶች ማህበራት፤ የሰብአዊ መብት ተቋማት፤ የፌዴሬሽን አባላትና አካላት የሆኑ ቡድኖች በሙሉ በሚመቻቸው መንገድ ሁሉ (By all Means Necessary) ተነስተው ፌዴሬሽኑን ካለበት ጽኑ ሕመም አጽድተው፣ እውነተኛውንና የሚወክለንን ፌዴሬሽን ማቋቋም ማለት ነው። በሌላ አነጋገር የጽዳት ዘመቻ ማካሄድ ማለት ነው። መመንጠር ሳይሆን ማጽዳት ማለት ነው። እድሜ ለዘመኑ፣ ማሕበራዊ ድረገጾች (Social Media) አሉልን፡፡
ሆይ ብዬ መጣሁ ሆ ብዬ !
የአፍሪቃ ዋንጫ ይዤ!
ሆይ ብዬ መጣሁ ብዬ ሆ ብዬ! እያሉ --- የሴት ቡድናችን ሲገባ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶች፤በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተስፈኛ ፤ታዳጊ ወጣት ሴቶች ሲቻል በአደባባይ፤ሳይሆንም በህሊናቸው፤ በየመንፈሳቸው እ-ል-ል-ል-ል-ል-ል-ል! እያሉ የሚቀበሉበትን ቀን ለመፍጠር ነው።
አገር ሲከዳ ለማየት የግድ በአደባባይ፣ጃን ሜዳን ለፈረንጅ የሚያስማማ እጅ ከፍንጅ መያዝ ያለብን አይመስለኝም። አገር መክዳት ብዙ መልክና አንድምታም አለው ብዬ አምናለሁ፡፡ የጸዳ ቤት ለማየት ያብቃን!! የከርሞ ሰው ይበለን!!

Read 2761 times