Saturday, 05 December 2015 09:08

የደመቀ ግጥሞች “በቡና ላይ ሀሳብ”

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(6 votes)

    የደመቀ ወልዴ “የቡና ላይ ሃሳብ” የመጀመሪያዋ ግጥም ከዓመታት በፊት ወዳነበብኩት አንድ የሥነ - ጽሑፍ መጽሐፍ ወሰደችኝ፡፡ እናም መጽሐፍት መደርደሪያዬ መዝዤ አወጣሁዋትና ቆዘምኩ፡፡ የግጥም ደግነቱ ይህ ነው። ረዥም ምላሹን አውጥቶ በነበልባል ሃሳቦቹ፣ በጥምዝምዝ ሀረጐቹ ልብን ሊከብብ ይችላል፡፡ አንዳንዴም የውስጥ ድምፃችን የገደል ማሚቶ መሆን ይከጅለዋል፡፡
ያኔ ስትነግሪኝ፣ ልብ ያልኩት ነገር፣
አይጋባም ያልሺኝ፣ መቼም የሚፋቀር፣
ሟርትሽ ደረሰልሽ፣ ምኞትሽ ተሳካ
የትዳር እንቅፋት፣ መፋቀር ነው ሳንካ
ያገባሽውን ሰው አትወጂውም ለካ፡፡
ሀሣቡ ሲጀምር ልብ ይነካል፡፡ የመጨረሻዋ ስንኝ አየር ላይ ብትንጠለጠልም፡፡ ካርል ኢ. ቤን እና ሁለቱ አጋሮቻቸው የፃፉት ጥራዝ ውስጥ ያነበብኩት ሃሳብ እንዲህ የሚል ነበር፡፡ “Poetry can be mouthpiece of our feelings even when our minds are speechless with grief or joy”
የዚህ ግጥም ተራኪ ሀዘንተኛ ነው፣ ምክንያቱም ያለመጋባታቸውን “ሟርት” ነበር ብሎታል፡፡ የሚያስፈነጥዝ ወይም ቄጠማ የሚጐዘጐዝለት፣ ዘንባባ የሚነጠፍለት አይደለም ለማለት ነው፡፡ ውስጣችን የታመቀውን፣ ቃል የለሽ ሀዘን አውጥቶ አደባባይ ላይ በዜማ የሚያፈስስ ነው - ግጥም፡፡
“የቡና ላይ ሃሳብ” በ95 ገፅዋ ረጃጅምና አጫጭር ግጥሞች ይዛለች፡፡ የጀርባ አስተያየት የፃፈው ገጣሚ ነቢይ መኮንን እንዳለው፤” እሙናዊና ምናባዊ፤ እንደ ትኩስ ቡና እንፋሎት የሚጤሱ፣ እንደሱሳችንና ልማዳችን የምናጣጥማቸው ስንኞች አያሌ ናቸው፡፡” ነቢይ በመቀጠልም “እንደ ቀና አንባቢ የቡና ስባቱ መፋጀቱ የምንላቸው ግጥሞች አሉባቸው፤ ሃሳብ ግጥም ውስጥ ብቻ አይበስልም፡፡ ቀስ በቀስ እራስም ውስጥ ይተባል።” በማለት የከአድማስ ባሻገር ተስፋውን ይጠቁመዋል፡፡ እኔም ያን ያህል ባይንተገተጉም፣ ጥሩ ፍንጭ አላቸው ያልኩትን፣ አየት አየት አደርጋለሁ፡፡ ለምሳሌ “መመሪያ” ሽሙጥና ቁዘማን ያጣመረ ነው፡፡
አመድ ካስታቀፉህ፣ ፍሙን እየጫሩ፣
ያረቀቁትን ሕግ፣ እነሱ እየሻሩ፤
ዘመን ያመጣውን፣ እሱ እስኪለው በቃ
እስክስታ መውረድ ነው፣ በወጣው ሙዚቃ!
አመድ ማስታቀፍ ተስፋን ማዳፈን ነውና፣ “እነሱ” የሚላቸው ወገኖች ለራሳቸው ፍሙን ዘግነው፣ ቤታቸውና ሕይወታቸው ሲሞቅ፣ ያንተ ሕይወት ምድጃ ደግሞ ትንኝ ሲያዜምበት፤ የፈለጉትን ቢያደርጉ ሁሉ በእጃቸውና በደጃቸው ሆኖ ሕጉን እንዳሻቸው ቢዘውሩት፣ ለዘመን ከመተው በቀር ምንም ስለማታመጣ፣ ዝም ብለህ አሸወይናዬ ማለት አለብህ የሚል ይመስላል፡፡ እንደ ቋጥኝ የሚከብድ፣ ቀዝቃዛ፣ ቋጥኝ ጫንቃ ላይ የሚጭን ግጥም ነው፡፡ “እያነቡ እስክስታ” የሚለውም ያስኬዳል፡፡
“ሞት ሆይ” የሚለው ግጥም የሰውን ልጅ የሕይወት ውጣ ውረድና ውስብስብ መዘዝ የሚያደርግ፣ የግራ አጋቢነትዋ ዕለታዊ መዝሙር ይመስላል፡፡ ባንዲራ ሰቅላ፣ ድንኳን ጥላ ባትኖርና በዓይነ ሥጋ ባትታይም በነፍስ አፍንጫ ላሸተታት፣ የዚህ ግጥም ጠረን አላት፡፡
የህይወት ትርጉሙ፣ ቅጥ አምባሩ ጠፍቶ
ሞት አንተን ስንመኝ ኑሮ መሮ፣ ከፍቶ
በእግርም በፈረስም - ታክተን ለፍለጋ
ሞት አንተ ተወደህ- ህይወት አጥቶ ዋጋ
ባንተ ተስፋ ቆርጠን - ለመኖር ስንታትር
የጭንቁ ሌት አልፎ - ተስፋችን ሲደድር፣
መኖር ስንጀምር - ያ ክፉ ቀን አልፎ
ነገን ስንዋጀው - ከዛሬያችን ተርፎ፣
ስንፈልግህ ጠፍተህ - በጨነቀን ጊዜ
ድንገት የምትነጥቅ - ነፍስ አለኑዛዜ
ብርሃን አያውቁ - የፅልመት ባለሟል
ተጠየቅ በሞቴ - ሞት ሆይ መውጊያህ የታል?   
ተራኪው ከሞት ጋር ነው ወጉ፡፡ አባይ ሚዛን ያለህ፣ የተሳሳተ ትርጓሜና ምላሽ የምትሰጥ፣ ነህ ይለዋል፡፡ ሲፈልጉህ የለህም፡፡ ነፍስ እንደቢራቢሮ አበባ ላይ ተቀምጣ ሲያምርባት ደግሞ በቅናት የምትገለጥ ምቀኛ ነገር ነህ የሚል አንደምታ አለው፡፡ ነገርህ መላቅጥ የለውም ነው የሚለው፡፡ ይህ ደግሞ የዓለም ሁሉ ቅኔ፣ የሰው ልጆች ሁሉ ሙዚቃ ነው፡፡ በየቀብሩ ሥፍራ የሚወራ፣ በየሆስፒታሉ ከንፈር የሚመጠጥበት እውነት ነው፡፡ ግን ደግሞ የሕይወት ቀዳዳ፣ የነፍስ ቁሥል ነው፡፡ አንዱ የግጥም ጉዞ ልቅሶ ድንኳን ውስጥ ጐራ ማለት ነውና! ማጉረምረሙ ግድ ነው፡፡
የሰው ልጅ ጣጣ ሞትና የሕይወት መፋጀት ብቻ አይደለም፤ ትዝታም ጅራፍ ነው፡፡ የልብን ጀርባ ገርፎ ይልጣል፡፡ ወንድዬ ዓሊ፤ “ወፌ ቆመች” በሚለው መጽሐፉ፤ “ትዝታ” በሚለው ርዕስ ሥር የፃፈው ግጥም መዝጊያ አንዳች ፉርጐ ይስባል፡፡ እንዲህ ይላል፡-
አንዳንዴ ግን ትዝታ ትንታም አለው አሉ፤
ብስባሽ ምሬት ሲታሰብ፣
የኑሮ ውጣ ውረድ…የሰቆቃ ይላሉ፡፡
ትዝታ ውስጥ የተሰነቀሩ፣ ብዙ የዘመን ጠባሳዎች፣ የእንባ ጠብታዎች ሀውልት አለ፡፡ የሰቀቀን ዜማ፣ የእንጉርጉሮ መጽሐፍ!
የደመቀ ወልዴ “የቡና ላይ ሃሳብ”ም ውስጥ “መኖር በትዝታ” የዚህ ዓይነት ቅኝት አለው፡፡ የተወሰኑ ስንኞችን እዋሳለሁ፡-
የሚደገም ቢሆን፣ አይ “ቢስ” ቢባል ፍቅር!
ደጋግሜ ባየው፣ ቅር አይለኝም ነበር፤
እንዳለመታደል በፍቅር መካከል፣ ሳንካ
ይስባል ቃታ
የመዋደዱ ጥግ፣ የፍቅር ከፍታ
መለያየት ሆኗል፣ መኖር በትዝታ፡፡
የደመቀ “ተጣጣፊ” የምትል ግጥም በዘመናችን ፖለቲካና ፖለቲከኞች ላይ የምታላግጥ ይመስላል፤ በተለይ ተቃዋሚ ነን የሚሉትን፡፡ ከንፈራቸው ላይ ቃላት እየቆሉ ልባቸው በገንዘብ ጥማት የነደደውን… የሚል ይመስላል፡፡
አንተ መንግስት ሆነህ፣ እኔ ተቃዋሚ
በሰብአዊ መብትም፣ ሳንሆን ተሸላሚ፡፡
ህዝብ አነሳስቼ፣ አንተን ሳላስቦካ
ማዕቀብ ካላስጣልኩ፣ ገብቼ አሜሪካ፡፡
እውነት ፓርቲ አትበለኝ፣ ሞቻለሁ በቁሜ
ለዓለም ሳላሳጣህ፣ አንተን ተቃውሜ
እያለ እሚፎክር ተቃዋሚ ነኝ ባይ
ሕዝብ የቀሰቀሰ፣ ቆሞ በአደባባይ፤
ባለፈው ለጉዳይ፣ ብሔድ አንድ ሥፍራ
መንግሥት ሆኖ አየሁት፣ አውራጃ ሲመራ፡፡
ጥሩ ቆመጥ ነው፡፡ ያሳምማል፡፡ ግን ደግሞ “ተቃዋሚ” ባለበት በዚህ ዘመነ መንግሥት “አውራጃ” የሚባል የመንግሥት አስተዳደር መዋቅር ስለሌለ “ወረዳ” ቢባል ሸጋ ነበር፡፡
የደመቀ ግጥሞች ብዙዎቹ ቁጭትና ያለመሳካት ናቸው፡፡ የትዕግሥት ማሞ “ቁጭት” ውስጥ ያለውን ዓይነት፣ የተንገዳገደና የወደቀ ፍቅር አሻራ አለ። የጠወለገ የሕይወት ምሥል፣ እንባ ያነደደው ጉንጭ፣ ማዲያት የቋጠረ ልብ ይነበባል፡፡ ይህ ለምን አይባልም - የሕይወት ሰንበር ነው፣ የመኖር አሻራ!
ይሁንና ብዙዎቹ ግጥሞች የዜማ ስብራት አለባቸው። ምታቸው እንደ ሀረግ ይጠመዘዛል እንጂ እንደ ጥይት አይጮህም፣ ዋናው ድከመትም እዚያ አካባቢ ነው፡፡ ነፍስ ላይ እንደ ኳስ የሚነጥሩ ገለፃዎችም የሉም፤ ጭርታው ጐልቷል፡፡ የተነሱት ትልልቅ ሃሳቦች ተጠልዘው ይቀራሉ እንጂ መረብ አይነኩም፤ ይሁንና ለክፉ አይሰጡም፡፡ ግን ያሳዝናሉ፡፡
አብዛኛዎቹ ስንኞች ከሕይወት ገጠመኙ ሥር ነክሰው የመነጩ ናቸው ብል የተሳሳትኩ አይመስለኝም፤ ቀጫጭን የሚመስሉ ወፍራም መስመሮች አሉት፡፡ እንደ አዲስ ገጣሚነቱ የአስተውሎቱ ገፅታዎች መበርከታቸው ይገርመኛል። በበኩሌ እንደ ገጣሚ ብተነብይ፤ ነገ የተሻለ ሥራ እንደሚኖረው ከወዲሁ ገብቶኛል እላለሁ፡፡

Read 5094 times