Saturday, 05 December 2015 09:21

ኢትዮጵያ ሰባት እጥፍ የሚታፈስባት አገር ናት

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

      የኢትዮ-ኮርያ የቢዝነስ ፎረም የተካሄደ ሲሆን ከኮርያ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኩባንያዎች ለመጡ 40 ያህል የኢንዱስትሪው ኃላፊዎች በኢትዮጵያ በዘርፉ ስላለው የኢንቨስትመንት ሁኔታ ገለጻ ተደርጓል፡፡
ከትናንት በስቲያ በካፒታል ሆቴል የተካሄደውን የቢዝነስ ገለጻ ከኮርያ የንግድ ኢንዱስትሪና ኢነርጂ፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ከኮርያ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ፌዴሬሽን፣ ከጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር፣ ከኮርያ የንግድ ም/ቤትና ከ17 የኮርያ ኩባንያዎች የተውጣጡ የቢዝነስ ልዑካን ተከታትለውታል፡፡
የፎረሙ ዓላማ በሁለቱ አገር ኩባንያዎች መካከል ያለውን ትብብር ከፍ ለማድረግ፣ አዳዲስ የቢዝነስ አማራጮችን መፍጠር፣ በሁለቱ አገሮች መካከል በስትራቴጂያዊ ትብብርና በከፍተኛ ባለስልጣናት ደረጃ የቢዝነስ ጉባኤዎች ማካሄድ መሆኑ ታውቋል፡፡
ኢትዮጵያ ለጨርቃጨርቅና  አልባሳት፣ ለቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ … ኢንቨስትመንት አመቺ መሆኗን የጠቀሱት የኢንዱስትሪ ሚ/ር ዴኤታ አቶ ታደሰ ኃይሌ፣ በቦሌ ለሚ ተሰርቶ አገልግሎት ከጀመረው የኢንዱስትሪ ፓርክ በተጨማሪ፣ በሀዋሳ፣ በመቀሌ፣ በኮምቦልቻ፣ በባህርዳርና በጅማ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እየተገነቡ መሆኑነ ገልጸዋል፡፡
6.000 ሜጋ ዋት የሚያመነጨው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ እየተጋመሰ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ታደሰ፤ ኢትዮጵያ በቅርቡ ከ10 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ ኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚኖራት፣ በአሁኑ ወቅት ለጂቡቲ የኤሌክትሪክ ኃይል መሸጧን፣ ለሱዳንና ለኬንያም ለመሸጥ መዋዋላቸውን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በርካታ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዳላት የጠቀሱት የኮርያ የልማት ስትራቴጂ ተቋም የፕሮግራም ኦፊሰርና የልማት አማካሪ ዶ/ር ሊ-ጃ-ሁን፣ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥቅም የሚታፈስባት አገር ናት፡፡ ለምሳሌ 200 ሺህ ዶላር ኢንቨስት ብታደርግ ሰባት እጥፍ ጥቅም ታገኛለህ፡፡ ይህ ትልቅ አጋጣሚ ነው፡፡ ስለዚህ በቀላል ኢንዱስትሪ ጀምሮ ወደ ትልቅ ማሳደግ ይቻላል ብለዋል፡፡
የኮርያ የጨርቃጨርቅና የአልባሳት ኢንዱስትሪዎች በአሁኑ ወቅት እየሰሩ ያሉት በባንግላዴሽ፣ በጓቲማላ፣ … እንደሆነ የጠቀሱት ዶ/ር ሉጃ-ሁን፣ ወደዚህ የመጡት በኢትዮጵያ ያሉትን የኢንቨስትመንት ሁኔታ ለማየት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በርካታ የኢንቨስትመንት መሬት፣ በቀላሉ የሚሰለጥንና በርካሽ የሚሰራ የሰው ኃይል አላት፡፡ ይህ መልካም አጋጣሚ ሲሆን ችግሮችም አሉ፡፡ ዋናው ችግር የሎጂስቲክስ ዋጋ በከፍተኛ መጠን መናር ነው። ከጅቡቲ አዲስ አበባ የተዘረጋው የባቡር መስመር ከወር በኋላ ሥራ ሲጀምር ይህ ችግር እንደሚቃለል እርግጠኛ ነኝ በማለት አስረድተዋል፡፡

Read 1488 times