Saturday, 12 December 2015 11:03

የኩላሊት በጐ አድራጐት ድርጅት የባንክ ሂሳቦች እንዳይንቀሳቀሱ ታግደዋል

Written by  ማህሌት ኪዳነወልድ
Rate this item
(8 votes)

የተሰበሰበው ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ እየዋለ አይደለም የሚል ጥቆማ ደርሶናል (ኤጀንሲው)

          የኩላሊት እጥበት በጐ አድራጐት ድርጅት የዳሽንና የንግድ ባንክ ሂሳቦች እንዳይንቀሳቀሱ ማገዱን የበጐ አድራጐት ድርጅቶች ማህበራት ኤጀንሲ ጠቁሞ የባንክ ሂሳቦቹ የታገዱት የተሰበሰበው ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ እየዋለ አይደለም የሚል ጥቆማ ስለደረሰን ለማጣራት ነው ብሏል፡፡
ድርጅቱ ከሚጠቀምባቸው ሁለት የባንክ ሂሳቦች አንዱ የሆነውን የዳሽን ባንክ ሂሳብ እያንቀሳቀሰ ያለው ከድርጅቱ ከለቀቀ ቆይቷል የተባለው ዶ/ር ፉአድ ከስራ አስኪያጁ ጋር በመሆን ነው ያሉት የኤጀንሲው የክትትልና ድጋር ቡድን መሪ አቶ ታምራት ኃ/ሚካኤል፤ ከድርጅቱ የለቀቀ ሰው ሂሳብ ማንቀሳቀሱ ፍፁም ስህተት ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በሰውየው ቦታ ሌላ ግለሰብ መተካቱን የሚገልጽ ደብዳቤ ለኛ ጽፈው ለንግድ ባንክ እንድንጽፍ የተደረገ ቢሆንም የዳሽን ባንኩን ሂሳብ የሚያንቀሳቀስ ሰው መቀየሩን የሚገልጽ ደብዳቤ እንድንጽፍ ግን እስካሁን ድረስ አልተጠየቅንም ይላሉ የኤጀንሲው የቡድን መሪ፡፡
ለድርጅቱ የሚደረጉ የንብረት እርዳታዎችም ለግል ጥቅም እየዋሉ ነው የሚል ጥቆማ እንደደረሳቸው የሚናገሩት አቶ ታምራት፤ ይህንን ለማጣራት ጥረት ሲደረግም ንብረቶቹ በስርአት ተመዝግበው ባለመገኘታቸው ቦርዱ ንብረት ቆጠራ አድርጐ እስከ ህዳር 20 ቀን 2008 ዓ.ም ድረስ እንዲያሳውቅ ብንገልፅም በተባለው ጊዜ አላሳወቁም፤ ህዳር 20 ስልክ ደውለንላቸው በሚቀጥለው ቀን እንደማያሳውቁን የነገሩን ቢሆንም እስካሁን ድረስ ድርጅቱ ንብረት ቆጥሮ ሊያሳውቀን አልቻለም ብለዋል፡፡ የተጠየቁትን የማያሟሉ ከሆነ ኤጀንሲው እርምጃ ወደመውሰድ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
የበጎ አድራጎት ድርጅቱ “ጋራድ መልቲ ሚዲያ” ከተባለ ድርጅት ጋር በኮሚሽን መስራቱ ስህተት መሆኑንም አቶ ታምራት ገልፀዋል፡፡ “አንድ የበጐ አድራጐት ድርጅት በኮሚሽን መስራት አይችልም፡፡ ድርጅቱ በተለይ የSMS ብር ለመሰብሰብ ከጋራድ ጋር በኮሚሽን ሊሰሩ ተስማምተዋል፡፡ እነሱ ይህን ያደረግነው ስንጀምር ብር ስላልነበረን ለመነሻነት ነው ቢሉም ሙሉ ለሙሉ ስህተት ነው” ብለዋል፡፡  
በሌላ በኩል በበጎ አድራጎት ድርጅቱ የባንክ ሂሳብ የነበረው 7.5 ሚሊዮን ብር እንደሆነና፤ ገንዘቡ እንደተመዘበረ በአንዳንድ ሚዲያዎች የሚወራው ከእውነት የራቀ ነው ያሉት የኤጀንሲው ኃላፊ፤ በተደረገው ማጣራት ያልገቡ የSMS ብሮችን ሳይጨምር እስካሁን ያለው ወደ 4 ሚሊዮን ብር አካባቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ “የለም እኛ የምናውቀው ነገር አለ” የሚሉ ወገኖች ካሉም ማስረጃቸውን እንዲያቀርቡ አቶ ታምራት ጠይቀዋል፡፡
የኩላሊት እጥበት በጐ አድራጐት ድርጅት ቦርድ ሰብሳቢ ኢንጂነር ሳሙኤል ይርጋ የንብረት ቆጠራውን አስመልክቶ ሲመልሱ፤ “የተባሉትን ዶክመንቶች አያይዘን ለኤጀንሲው ከሰጠን ሳምንት ሆኖናል፤ ምናልባት ከመዝገብ ቤት ስላልሰጧቸው ይሆናል፡፡ ዶክመንቶቹ የዘገዩትም ስብሰባው ላይ የተገኙት ሰዎች ቀኑን አሳስተው ስለተነገሩን ነበር” ብለዋል፡፡
የዳሽን ባንኩን ያላሳወቅንበት ምክንያት በዋናነት የምንጠቀመው የንግድ ባንኩን ሂሳብ በመሆኑና የዳሽኑ ብዙም ስለማይንቀሳቀስ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡ “በኮሚሽን ይሰራሉ ስለተባለው ጉዳይ እኛ በኮሚሽን አልሰራንም፤ ወጪ በማወራረድ ነው የተዋዋልነው፡፡ ወጪዎችን ከራሳቸው አውጥተው ገንዘቡ ሲመጣ ልንከፍላቸው ነው የተነጋገርነው፡፡ እንደውም በSMS ታሪክ በጣም በአነስተኛ ወጪ ብዙ ገንዘብ የሰበሰብነው እኛ ነን” ብለዋል፤ ኢንጂነር ሳሙኤል ይርጋ፡፡

Read 4253 times